Print this page
Tuesday, 08 March 2022 00:00

አንዳንድ ነገሮች ስለ “አድዋስ” ቴአትር

Written by  ቴዎድሮስ ይደግ (በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሲኒማና ቴአትር ጥበባት መምህር)
Rate this item
(0 votes)

      [ወፍ በረራዊ ቅኝት]
                          
                “አድዋስ” የተሰኘውን ቴአትር በአካል መታደም ባልችልም በቴሌቪዥን ተከታተልኩት፡፡ እናም የተሰማኝን እንደወረደ ይኸው ….
አድዋ ድል ነው፡፡ “አድዋስ” ደግሞ የዚህን ድል ታሪክ የሚያስታውስ ቴአትር ነው፡፡ አድዋ በአንድ ወቅት (ከ126 ዓመታት በፊት) በተደረገ ጦርነት የተገኘ ድል ብቻ አይደለም፡፡ ትዕምርቱ ከፍ ያለ ባለቅኔው እንዳለው “የአለት ምሰሶ” “ሰማይ ጠቀስ” ነው ምልክትነቱ፡፡ ለእኛ ብቻ አይደለም፡፡ ለመላው ጥቁር ህዝብ እንጅ፡፡ ይህ ትዕምርት ቀላል አይደለም፡፡ የዓለምን ስርዓተ-ማህበር ያናወጠና የለወጠ ነው፡፡ ነጭና ጥቁርነትን ያመጣጠነ ነው፡፡ የሠውን ልጅ እኩልነት በተግባር ያስመሰከረ ነው፡፡ ድምፃዊቷ “የሰው ልጅ ክቡር ሰው መሆን ክቡር” እንዳለችው፣ የሰውን ልጅ ክቡርነት በሰው በተከፈለ የደም ዋጋ ያስገነዘበ ትዕምርት ነው፡፡ አድዋ ጦርነትን ከማሸነፍ፣ በጦርነት ድል ከማድረግ በላይ የሆነ፣ ሰውን ከሰው ያስተሳሰረ መንፈስም ነው፡፡ ሰውን ከአገሩ ጋር ያስተሳሰረ መንፈስ ነው፡፡ ሰውን ከነገው ያስተሳሰረው መንፈስ ነው፡፡
አገር ብቻውን አይሰላም፡፡ ቢያንስ ሶስት ጉዳዮችን ያቅፋል፡፡ (1) አገር የሚኖሩበት ቀዬ ነው፡፡ (2) አገር በቀየው የሚኖረው ሰው ነው፡፡ (3) አገር ከሁሉም በላይ መንፈሱ ነው፡፡ ሰውን ከሚኖርበት ቀዬ፣ ሰውን እርስ በእርሱ ያያዘው መንፈስ ነው፡፡ ይህ መንፈስ ነው አድዋ፡፡ አድዋስ የተሰኘው ቴአትር የገለጠው ይህንን መንፈስ ነው፡፡ “አድዋስ” ያሳየን የአድዋን “ሰማይ ጠቀስ” ምልክትነት ነው፡፡
በ”አድዋስ” ውስጥ የተለመደው አቀራረብ አይገኝም፡፡ ጎራዴ ይዞ፣ ጠመንጃ አንግቦ፣ ጋሻ ወድሮ ሽለላና ፉከራ ብቻ አያሳይም፡፡ እንደ ጥበብ ጠለቅ ያለ አቀራረብ ያሳየ ነው፡፡ የአድዋን መንፈስ፣ የአድዋን ትዕምርት አጉልቶ ያሳየ ነው፡፡ የነበረውን ሁነት ከመተረክ ይልቅ መንፈሱን ለማሳየት የተጨነቀ ጥበብ ነው፡፡ ለዚያም ነው “አፅና አገርህን፣ አግራ ልብህን፣ ጠብቅ አቆይ አድዋ አርማህን” ማጠንጠኛ ሆኖ የተዜመው፡፡ ይበልጥ ነገሩን ለመረዳት አንድ ጥያቄ እንጠይቅ፡፡ “ጠብቅ አቆይ - አድዋ አርማህን” ሲል ምን ማለቱ ነው እንበል፡፡ አድዋ ጦርነቱን ነው? አድዋ ቦታውን ነው? አድዋ የሚለውን በየዓመቱ የምናከብረውን የድል ቀን ነው? ወይስ መንፈሱን ነው? መልሱ አጭር ነው፡፡ መንፈሱን ነው። መንፈሱ ከሌለብን አድዋን በየዓመቱ ማክበር ከንቱ ድካም ነው፡፡ ለዚያም ነው “አድዋ አርማህን” የሚለው፡፡ አርማ መለያ ነው፡፡ አድዋ ሲያሻን የምንቀይረው አርማ ግን አይደለም፡፡ ባለቅኔው ያለውን ልብ ይሏል፡፡ የአለት ምሰሶ ነው - የማይናወጥ የማይለወጥ፡፡ “ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን ሰውን ሊያስከብር” እንዳለችው የምንወዳት፣ እኛም ይህንን ምሰሶ በሞታቸው ለክብራችን ያቆዩልን አያቶቻችን ልጆች ነንና ይህን አርማ ከነትርጉሙ መኖር ይፈለግብናል፡፡ አድዋስ ቴአትር ጉዳዩ ይህ ነው፡፡ ትናንትን እያስታወሰ፣ ከዛሬው ጋር እያሰናኘ ነገን ያበጃል እንጅ የነበረውን ብቻ ሲተርክ አይቆይም፡፡ ዘጋቢ ብቻ አይደለም፡፡ ነገንም ያመላክታል፡፡
አድዋ በብዙ እንደተባለው መገኛው ኢትዮጵያችን  ትሁን እንጅ መዳረሻው ግን የትም ነው፡፡ ድንቅነሽ ከአፋር ተመዛ በዓለም ውስጥ ላለ የሠው ልጅ ሁሉ መነሻ ሆና እንደተገኘችው ሁሉ የአድዋ መንፈስም መላውን የአለም ህዝብ የደረሰ ነው፡፡ ለጥቁር ህዝብና ለተገፉ የሰው ልጆች ሁሉ የይቻላል ድልድያቸው፣ ሲጋፉ ለኖሩና ለነጭ ህዝብ ደግሞ የአመለካከት ሚዛንን ያስተካከለ መንፈስ ነው፡፡ “አድዋስ” ቴአትር ይህንንም አልሳተም፡፡ በተለይ በአቀራረብ ቴክኒኩ ውስጥ የታዩ አላባውያን ይህንን አግዝፈው ያስረዳሉ፡፡ ጥቂቶችን በጥቂቱ እንቃኝ፡-
ታሪክ ነገራ (Story telling)
ታሪክ ነገራ አንዱ የአፍሪካውያን የቴአትር ምንጭ ተደርጎ የሚወሰድ አላባ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በድህረ-ቅኝ ግዛት ውስጥ የመጡ ምሁራንና የኪነጥበብ ሃሳባውያን፣ አፍሪካውያን ለማንነታቸው የሚበጀውን የአተራረክ ስልት በቴአትር ስራዎቻቸው፣ በፊልሞቻውና በስነ-ፅሁፋቸው እንዲያንጸባርቁ ይወተውታሉ፡፡ የተለመደውና ማንነታቸውን  የሚገልፀው የአፍሪካውያን ታሪክ መንገሪያ ስልታችን እንደ ተረት ተጀምሮ እስኪያልቅ ያለውን ጊዜ በ “ከዚያስ…” እያያዙ የሚያስቀጥል ነው፡፡ ይህ ስልት አብሮ የኖረ ትውፊታችን ነው፡፡ ይህንን ትውፊት በኪነጥበብ ስራዎቻቸው ለማስቀጠል የሞከሩና የተሳካላቸው አፍሪካውያን ከያኒያን ጥቂት አይደሉም፡፡ በተለይ አፍሪካ-አሜሪካውያን ወደ ቀደመ ማንነታቸው እየተመለሱ አቀራረባቸውን ተረታዊ አድርገው ስራዎቻቸውን ይሰራሉ። በዚህም የአቀራረብ አዲስነት ለአለም የማበርከት ብቻ ሳይሆን ከቅኝ ግዛት በኋላ ለተነሳው የአዲሱ ቅኝ ግዛት አስተሳሰብ እጅ ያለመስጠት ትግል ማስኬጃም ሆኗል። የአለም አስተሳሰብ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚነሳ ሳይሆን ከሁሉም አቅጣጫ በሚመጣ አስተሳሰብ እንዲቃኝ ቴአትሩ ትልቅ ሚና እንዲጫወት ጥረታቸው ብዙ ነው፡፡ “አድዋስ” ቴአትርን ከዚህ አንፃርም የምንመለከተው ነው፡፡
የቀረበበት ስልት በታሪክ ነገራ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ፊታውራሪ ተ/ሃዋሪያት ተ/ማሪያም በሚያወጉት ትዝታ እየተመራ የሚፈስ ታሪክ ነው፡፡ ተረታዊ ነው። ምን ሆነ? ከዚያስ? እያለ የሚቀጥል፡፡ ይህ አፍሪካዊ አተራረክ ስልቱ ተገቢነት አለው፡፡ የአድዋን አፍሪካዊነት በአተራረክ ስልቱም አምጥቶታልና ስልቱ የመመረጡን ምክንያትም በቀላሉ እንረዳዋለን፡፡  ተራኪው ፊታውራሪ ተ/ሃዋሪያት በቴአትሩ ውስጥ በትውስታ ነው የተጠሩት፡፡ ዛሬ የሉም፡፡ ትውስታችን ውስጥ ግን አሉ - በሰሯቸው ስራዎች፣ በአሳተሙት “አውቶባዮግራፊ” መፅሃፋቸው፡፡ በትውስታ የተጠሩት ተራኪ መድረኩ ላይ ደግሞ የራሳቸውን ትዝታ ይጠራሉ፡፡ ልጅነታቸውን፡፡ ወደ ትናንት እንድንሄድ የበለጠ ብርታት የሰጠው ቴክኒክ ነው፡፡ ልጅነታቸውን እያዩ፣ እኛም እያየን፣ እሳቸውንም በሽምግልና ዘመናቸው እያየን …. በሽማግሌው ፊታውራሪ ተ/ሃዋሪያት ትዝታ ጉብሉን ተ/ሃዋሪያት እየተመለከትን ደረጃ በደረጃ ወደ ነበረው ሁነት ርቀን እንሄዳለን። ግሩም ነው። በነገራችን ላይ ፊታውራሪ ተ/ሃዋሪያት ተ/ማሪያም የመጀመሪያው የኢትዮጵያ “ዘመናዊ” ቴአትር አስፈንጣሪ ተደርገውም ይወሰዳሉ - የአውሬዎች ኮሜዲያ መሳለቂያ ተውኔታቸውን ዋቢ በማድረግ፡፡ ጸሐፌ-ተውኔቱ ፊታውራሪ ተ/ሃዋሪያት ናቸው እንግዲህ በተውኔት ውስጥ የተገለጡት፡፡  (ይህ ብቻውን ብዙ  መወያያ ይሆናል፡፡ የዚህ ፅሁፍ ጉዳይ ግን ከዚህ በላይ በዚህ ርዕስ ላይ እንድንሄድ አይፈቅድምና ለሌላ ጊዜ እናቆየው)
ሙዚቃና ዳንስ
ሌለው አፍሪካ ቴአትር ልምምድ ውስጥ ጉልህ ቦታ የሚሰጠው ሙዚቃውና ዳንሱ ነው፡፡ የአፍሪካ ቴአትር (የአውሮጳውም ቢሆን) መነሻው ስርዓተ-ከበራው እንደመሆኑ ሙዚቃውና ዳንሱ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡ ሙዚቃውም ዳንሱም አመጣጡ ተነጥሎ አይደለም። ከታሪኩ ጋር ተሰፍቶ ነው፡፡ ሙዚቃው ታሪኩን ያስተሳስራል፡፡ ቀደም ሲል እንዳልነው አድዋ መንፈስ ነው ብለናል፡፡ ሌላም ብለናል - “አድዋስ” ቴአትር የአድዋን መንፈስ ከትናንት እያነሳ ከዛሬ እያዋሃደ፣ ነገን በልኩ የማበጀት ጥረት ነው ብለናል። ሙዚቃው ሲያደርግ የነበረውም ይህንን ነው፡፡ መንፈሱን ያጋባብናል፡፡ ትናንትን ብቻ ሳይሆን ነገ የሚኖርብን ድርሻም ያስገነዘብናል፡፡ መንፈሳችን በአድዋ መንፈስ ይሞላዋል፡፡ ለጆሮ የሚጥም ነው፡፡ ለመንፈስ ያለስስት የሚደርስ ነው፡፡ ከጀርባ የተሰደሩት ህብረ-ዘማሪያን የጥንቱን የግሪክ ቴአትር ህብረ-ዘማሪያንን አይነት ሚና ነበራቸው፡፡ ታሪኩን ጉልበት ይሰጡታል። በክዋኔው የጎደለውን ይሞላሉ፡፡ በታሪኩ ያልተዳሰሰውን በዜማና ግጥሙ ምልዐት ይሰጡታል፡፡ አዚያዚያማቸው ከታሪኩ፣ ከድርጊቱ ጋር የሚሰምር ነው፡፡ ለዚያ ነው ተነጥለው የማይታዩን፡፡
በዚህ ቴአትር ላይ ከተደመምኩበት ሌላው ጉዳይ ዳንሱና ሰርከሱ ነው፡፡ ንጥል አይደለም፡፡ ትርጉም አልባ አይደለም። ዳንሱ የተውኔቱን ታሪክ ስነ-ውበታዊ ግዝፈት በመስጠት፣ በተውኔቱ መደበኛ ትረካ ውስጥ መድረስ የማንችላቸውን የታሪክ ሁነቶች ለማሻገር የሚያስችል ድንቅ ድልድይ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ፊታውራሪ በትረካቸው ያልነገሩንን ታሪክና ሁነት ሁሉ በዳንሱና በሰርከሱ ተገንብቶ እናገኘዋለን። እያንዳንዱን ስሜት በማግዘፍ ረገድም ሚናው ከፍ ያለ ነው፡፡
መውጫ
ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው “አድዋስ” ሁሉም አላባውያን ያለመነጣጠል የቀረቡበት፣ አንዱ አላባ ያለሌላው እንዳይቆም ሆኖ የተገነባ ነው (አድዋ የጋራና የአብሮነት ድል መሆኑም ልብ ይሏል)። ይህ ደግሞ ትልቁ ጥንካሬው ነው። ምንም ነገር ያለምንም ምክንያት ቴአትር ውስጥ ከመጣ አቅርቦቱን ያደበዘዝዋል። የቴአትር ጥበብ ዋና መለያው መምረጥና የተመረጠውም አላባ ተገቢ መሆኑን ማሳየቱ ነው፡፡ “አድዋስ” በዚህ ረገድ ተዋጥቶለታል ብለን ብንደመድም አንሳሳትም፡፡ ያሳተፈው የባለሙያና የከዋኝ ብዛት፣ ይህንን ሁሉ ሙያተኛ በማስተባበር እንዲህ አይነት ብቁ ስራ ለማቅረብ የተደረገው ጥረት፣ የቴአትር ስራ እንዲወደድ የሚያደርገው ስራው መሆኑን በማሳየት ረገድ የተጫወተው ሚና (ዝቅተኛው መግቢያ 350 ብር መሆኑን ልብ ይሏል) የተለየ ያደርገዋል፡፡ ለብዙ ባለሙያዎች ንቃትን የፈጠረ ስራ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡



Read 8277 times