Saturday, 05 March 2022 12:39

...በጊዜ ይድረስላቸው!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)


                "--ደግሞላችሁ...ሌላ ምን አለ መሰላችሁ...ይቺ “የዘር ማጥፋት” የምትለዋን ክስ በመጠቀም ስንት ነገር ሊያደርጉን ሲያሰፈስፉ አልነበረም እንዴ! እንደውም እኮ የተዘጋጀው ሰነድ በተፈለገ ጊዜ ሊመዘዝ  አሁንም ጠረዼዛው ላይ ነው ይባላል፡፡ ታዲያላችሁ... አሁን ሩስያ “በዩክሬይን ባሉ ዜጎቼ ላይ የዘር ማጥፋት እየተፈጸመ ነው...” ስትል ምዕራባውያኑ በተራቸው "ወረራውን እውነተኛ ለማስመሰል የተፈጠረች ክስ፣" እያሉ ነው፡፡--"
          

              እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ሊጀመር ነው!”
“ዓለማችን በኑክሌር ልትጠፋ ነው!”
“የተፈራው ደረሰ!”
የዩቲዩብ ሰዎቻችን ከግራ ቀኝ እያጣደፉን ነው፡፡ ለነገሩ በየቀኑ በፍጥነት እየተለዋወጡ ያሉትን ሁኔታዎች ስናይና በተለይ ፑቲን የኑክሌር መከላከያቸውን በተጠንቀቅ እንዲቆም ትእዛዝ ሰጡ መባልን ስንሰማ የሦስተኛው የዓለም ጦርነት፣ የኒክሌር እልቂት ነገሮች ቢመጡብን አይገርምም፡፡ (ዛሬ መረር ወዳለው ወሬ ልንገባ መሰለኝ፡፡ ዝም ከማለት ወርወር አድርጎ ለማለፍ ያህል ነው፡፡)
ስሙኝማ...የእኛ ሰው “አይመጣምን ትተሽ፣ ይመጣልን ያዢ፣” ሲል የኖረው እኮ ዝም ብሎ አይደለም፡፡ ልክ ነዋ... ዘንድሮ እኮ “በምንም አይነት ሊሆን አይችልም...” ብላችሁ ስታስቡ የቆያችሁት ነገር፤ ሊሆን ይችላል ብላችሁ በመጨረሻው ቀሽም ህልማችሁ እንኳን መጥቶባችሁ የማያውቅ ነገር  እየሆነ ነው ግራ እየተጋባን ያለነው። እዛ ላይ አውሮፓ ውስጥ እየሆነ ያለውን ነገር እዩትማ! አሁን በአውሮፓ ምድር እንዲህ አይነት ነገር ይፈጠራል ብሎ ያሰበ ነበር?! “ያው እንደለመዱት ተዛዝተው፣ ተዛዝተው ሲበቃቸው አደብ ይገዛሉ፣” ይባላል እንጂ ይሄ ሁሉ ተኩስ! የአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኛ “የመንገድ ላይ ውጊያዎች በአውሮፓ ከተማ መሀል!” ብሎ ሲገረም ነበር፡፡ እንደዛ አይነት ‘እብደት’ ለእኛ ብቻ የተሰጠ ነዋ!
የምር ግን...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ምን መሰላችሁ፣ በአንዳንድ ወገኖቻችን የምናየው አንዱን ‘ጥፋተኛ፣’ ሌላውን ‘ንጹህ’ የማድረግ አይነት ችኮላ አሪፍ አይደለም፡፡ አሁን ትርክቱን የተቆጣጠረው አንድ ወገን ብቻ ነዋ! ዓለም እንዲሰማ ‘እየተገደደ’ የሚመስለው አንዱን ወገን ብቻ ነዋ! እናላችሁ...ነገሩን ማን መጀመሪያ ተኮሰ፣ እነማን ተታኮሱ ብቻ ሳይሆን ወደ ኋላ ሄዶ በርካታ የሚመዘዙ ነገሮች ያሉበትን ነው፡፡ ለዚህም ነው ታሪክን ገልበጠበጥ ማድረጉ አሪፍ የሚሆነው፡፡ ለነገሩማ... አለ አይደል... ማንን ደገፍን፣ ማንን አልደገፍን ምን ለውጥ ልናመጣ ነው! በራሳችን ጉዳይ “እህ...” ተብሎ ጆሮ ያልተሰጠን ሰዎች አሁን ምናቸውንም፣ ምናምናቸውንም ጠልቀን ስለማናውቃቸው ‘ፈረንጆች’ የፈለግነውን ብንል ማን ግድ ይሰጠዋልና ነው፡፡ “ሁ ኬርስ!” እንደሚል ፈረንጅ ራሱ! እናማ ስጋትና ጭንቀት ‘ካማረን’ ከራሳችን አልፈን ለሌሎች ልንሰጣቸው የምንችላቸው መአት አጄንዳዎች አሉ፡፡ ግን በመወገንና ባለመወገን ሳይሆን ለመረጃ ያህል ነገርየውን መከታተሉ ክፋት አይኖረውም፡፡ (ዛሬ ‘መረር’ ልንል ነው ተባብለን የለ!)
በምዕራባውያኑ ፖለቲከኞችና የሚዲያ ሰዎች እኛ ላይ ሲደረግ የነበረውን ዘመቻ አሁን ደግሞ በሌላ በኩል፣ በሌላ ወገን ላይ ሲደረግ እያየነው ነው፡፡ በጦርነቱ ማን እውነትን ይዟል የሚለው በመጀመሪያ ደረጃ የእነሱ ጉዳይ ነው፡፡ ነገሬ ብላችሁ ማህበራዊ ሚዲያንና ሌሎችን የመረጃ ምንጮች ብታዩ... አለ አይደል...አሁንም እዛ አካባቢ ማርቲን ፕላውቶች አሉ፤ አሁንም ኒማ ኤልባጊሮች አሉ፣ አሁንም ሳማንታ ፓወሮች አሉ፣ አሁንም ዊሊያም ዴኒሰኖች አሉ...ምን አለፋችሁ፣ እኛ የቀመስናትን ሁሉ የፑቲን ሀገርም ‘እየቀመሰች’ ነው...ምክንያቶቹና ግቦቹ የተለያዩ ቢሆኑም፡፡ እናላችሁ... ስለ ምዕራባውያኑ ሚዲያዎች የደረሰንበት ድምዳሜ ምን ያህል ትክክል እንደሆነ ኤ-ፕላስ የሚያሰጠን ነው፡፡
ኮሚክ እኮ ነው...እኛ ስናደርገው መአት ውግዘት ሲያደርሰብን የነበረው ነገር ሁሉ አሁን የፈረንጅና የፈረንጅ ጉዳይ ሆነና የሚያስጨበጭብ ሆኖላችኋል። ለምሳሌ መከራ የበዛባቸው የዩክሬይኑ መሪ ዜሌንስኪ ማንኛውም የሀገሩ እጣ ፈንታ የሚያሳስበው መሪ ሊያደርግ እንደሚገባው ህዝቡን ሀገሩን እንዲከላከል ጥሪ አድርገውለታል። ለመዋጋት ፈቃደኛ ለሆነ ከአስራ ስምንት ዓመት እስከ ስድሳ ዓመት ለሆነ ዜጋ ሁሉ መሳሪያ እየታደለ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ መዋጋት የሚችሉ እስረኞችም እንዲፈቱ ዜሌንስኪ ወስነዋል... ሀገርን ለማዳን የትኛውን ያህል እርቀት ይኬዳልና!) ምዕራባውያኑ ሚዲያዎችም ስለ ዩክሬይን ህዝብ ሀገሬን አላስነካ ማለት እየዘገቡ ነው። እሰየው!
ግን የእኛ ጊዜ ምን ነበር ሲሉ የነበረው! የህልውና ዘመቻ ጥሪ ሲደረግ “ህዝቡን ሊያጫርሱት” ምናምን እያሉ ቀን ከሌሊት ሲረባረቡብን አልነበረም እንዴ! ህዝቡን “ሀገርህ ተከላከል...” ማለት ፈረንጅ ሲያደርገው ትክክል፤ ጥቁር ሲያደርገው ስህተት ብሎ የበየነው ማን ነው! (እንደውም እኮ ምዕራባውያኑ ሚዲያዎችና ፖለቲከኞች፣ ሌሎች አውሮፓውያን ለዩክሬይን ሄደው እንዲዋጉ እየቀሰቀሱ ነው። የኛ ጊዜ የኤርትራ ወታደሮች ገብተዋል ተብሎ የነበረውን ጩኸት ልብ በሉልኝማ!)
ደግሞላችሁ... ሌላ ምን አለ መሰላችሁ...ይቺ “የዘር ማጥፋት” የምትለዋን ክስ በመጠቀም ስንት ነገር ሊያደርጉን ሲያሰፈስፉ አልነበረም እንዴ! እንደውም እኮ የተዘጋጀው ሰነድ በተፈለገ ጊዜ ሊመዘዝ  አሁንም ጠረዼዛው ላይ ነው ይባላል፡፡ ታዲያላችሁ... አሁን ሩስያ “በዩክሬይን ባሉ ዜጎቼ ላይ የዘር ማጥፋት እየተፈጸመ ነው...” ስትል ምዕራባውያኑ በተራቸው "ወረራውን እውነተኛ ለማስመሰል የተፈጠረች ክስ፣ እያሉ ነው። በነገራችን ላይ ከዩክሬይን ህዝብ 30% የሚሆኑት ሩስያውያን ናቸው፡፡
ይሄ ጦርነት ገና ብዙ ነገር እያወጣ ነው... በፊት ከማንም የማይወግኑ፣ ማንም ዘንድ የማይደርሱ ገለልተኞች እየተባሉ ስማቸው ሲደጋገም የነበሩ ሀገራት አሉ አይደል... በተለይ የስካንዲኔቪያን ሀገራት የምንላቸው... አሁን ክንብንቡ ሲገለጥ፣ ነገርዬው ፍጥጥ አለላችኋ! አይደለም ለሌላ ሊተርፉ የራሳቸው ጦር ሀይል እንዳላቸው እንኳን በቅጡ የማናውቅላቸው ሀገራት፣ ዋነኛ የጦር መሳሪያ አቅራቢዎች ሆነው አረፉላችሁ፡፡ በነገራችን ላይ...ከእነኛ ሀገራት አብዛኞቹ እኛ ላይ ዞረውብን እንደነበርም አይረሳም፡፡ እናማ ምን ለማለት ነው...ብዙ ስንሰማቸው የነበሩ ነገሮች መሸፋፈኛዎች ናቸው፤ እናም ጊዜ እንደዚህ ግልጽልጽ ያደርጋቸዋል፡፡
የአንድ ወዳጅ ስልክ ጥሪ..
“ስማ እየተከታተልከው ነው?”
“ምኑን?”
“የዩክሬይንን ጦርነት፡፡”
“መከታታል ባይሆንም አልፎ፣ አልፎ እያየሁ ነው፡፡”
“ፑቲን ቀጠቀጠልን እኮ! ዋጋዋን ነው ያገኘችው!” ኸረ ግዴለም... እዚህ ደረጃ መድረስ አያስፈልግም፡፡
“አይ እንደዛ ማለት ትክክል አይደለም። የሚጎዳው እኮ ምንም የማውቀው ሰላማዊው ሰው...” ምናምን ብላችሁ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አይነት ሊያደርጋችሁ ሲሞክር ነገርዬው ያን ያህል ቀላል አይሆንም፡፡
“የጸጥታው ምክር ቤት ያንን ሁሉ ጊዜ ሲሰበሰብ፣ እኛ ላይ ማእቀብ እንዲጣል ደጋግማ እጇን ስታወጣ የነበረች አይደለች እንዴ!”
እዚህ ቦታ ላይ መከራከር፣ “እስቲ ነገሩን ከየአቅጣጫው እንየው፣” ማለት ብልህነት አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ሲደረግብን በኖረው፣ ሲዶለትብን በኖረው፣ ሲጎነጎንብን በኖረው የህዝብ ስሜት ቆስሏልና! የሚገርማችሁ (ለነገሩ መግረምም የለበትም) ነገር እንዲህ አይነት ስሜት የብዙዎች መሆኑ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሚለቀቁ አስተያየቶች እያየነው ነው፡፡ እናማ...ሀገራችንን ላይ ከደረሰው (በተለያያ ደረጃ እየደረሰ ካለው) መከራ አንጻር ሰዋችን ቂም ቢይዝ አይገርምም፡፡ በውጭ ሀይሎች ሲሞከርብንና ሲደረግብን በኖረውና ምናልባትም አሁን ውስጥ ለውስጥ እየደረሰብን ካለው ጫና ሰከን ብሎ ለማሰብ ያስቸግራል፡፡
ድፍን አውሮፓ ክተት ያለ በሚመስልበት በዚህ ጦርነት በተለይ ለዩክሬይን ንጹሃን እንዲሁም በጦርነቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጠቂ ለሚሆኑ ምስኪኖች ሁሉ ፈጣሪ በጊዜ ይድረስላቸው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1623 times