Print this page
Saturday, 05 March 2022 12:49

ሦስቱ የዓድዋ ድል በዓላት

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

   126ኛው የአድዋ የድል በዓል “አድዋ ለኢትዮጵያውያን በረከት፤ለአፍሪካውያን የነጻነት ጮራ” በሚል መሪ ቃል፣ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሐውልት ከሚገኝበት አድዋ አደባባይና ሲግናል ተብሎ በሚታወቀው  አድዋ ድልድይ ላይ ተከብሯል፡፡ የአንድነትና የመተባበር ምልክት የሆነው የአድዋ በዓል በተከፋፈለ መንፈስ በተለያዩ ቦታዎች ሲከበር የአሁኑ  የመጀመሪያው አይደለም፡፡
1998 ዓ.ም የአድዋ ድል  አንድ መቶኛ ዓመት ነበር፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያን መንግስት እንደ ፈለገ የሚያሽከረክረው ትሕነግ፤ በዓሉ የሚከበረው አድዋ ላይ ነው  ብሎ ተነሳ፡፡  በዓሉን ለማሰብ የተዘጋጁ ጥናቶች አድዋ ላይ በሚደረግ ስብሰባ እንደሚቀርቡ ተገለጠ፡፡ እንቅስቃሴው  ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው። ተቃውሞው እየጠነከረ በመሄዱና ትህነግ አሸናፊ ሊሆን ባለመቻሉ፣ በዓሉ ሁለት ቦታ ተከፍሎ እንዲከበር  ተወሰነ፡፡ ጠዋት አድዋ ላይ፣ የጦርነቱን ታሪክ  የሚዘክር ሙዚየም  እንደሚሰራ፣ ጦርነቱ በተካሄደባቸው የአድዋ ዙሪያ ተራራዎች  ለጎብኚ በሚያመች መንገድ  የመሰረተ ልማት ተሟልቶላቸው ለጎብኚ ክፍት እንደሚሆኑ፤ አዲስ አበባ ላይ አሁን ሕዝብ መገናኛ እያለ የሚጠራው አደባባይ “አድዋ አደባባይ” በማለት ሲሰየም፣ “አፍሪካ የአድዋ ፓርክ; ተብሎ በአዲስ አበባ የሚገኙ የአፍሪካ አገራት አምባሳደሮች፣  የየአገራቸው ስም የተጻፈበት ሰሌዳ እንዲተክሉ በማድረግ ተጠናቀቀ፡፡ እጅግ  የሚያሳዝነው አድዋም ሆነ አዲስ  አበባ ላይ የታሰቡት ነገሮች በሙሉ የውሃ ሽታ ሆነው መቅረታቸው ነው፡፡
ሁለተኛው በመስቀል አደባባይ የተከበረው 125ኛው የአድዋ ድል በዓል ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተገኙበት የተከበረው ይህ በዓል፣ የደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶን እንዲሁም  የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ፎቶግራፍ ግራና ቀኝ አቁሞ እንደ ነበር አስታውሳለሁ፡፡ ከመላው ኢትዮጵያ ወደ አድዋ የዘመተውን ጦር  የመሩት ዳግማዊ አጼ ሚኒልክ፣ የውጫሌ ውል  እንዲሰረዝ አጥብቀው የተከራከሩት፣ በጦርነቱም ጊዜ  የመቀሌ ምሽግን ለማስለቀቅ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያደረጉት እቴጌ ጣይቱ  አለመነሳት፤ ያንን የመስቀል አደባባይ ክብረ በዓል ለነቀፋ ከዳረጉት  ምክንያቶች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸው አይዘነጋም፡፡
ወደ ሶስተኛው የአድዋ በዓል አከባበር ከመግባቴ በፊት ግን አንድ ነገር ማስታወስ ይኖርብኛል፡፡ ይኸውም የአድዋ በዓልን የሕዝብ በዓል  ስላደረጉት  ወጣቶች ነው። የአድዋ ድል በዓል የኢትዮጵያ መንግስት ፖለቲካዊ ዋጋ ሰጥቶ ብሔራዊ በዓል ካደረጋቸው  ሶስቱ ብሔራዊ በዓላት አንዱ ነው፡፡ ለዚህም  ነው ለበዓሉ 12 ጊዜ መድፍ የሚተኮሰው፡፡ በደርግ ዘመን ፕሬዚዳንቱ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም፣ አድዋ አደባባይ ተገኝተው የመታሰቢያ አበባ ያስቀምጡ  ነበር፡፡  በአሁኑ መስቀል አደባባይ (አብዮት አደባባይ)  ህዝባዊ ሰልፍም ይደረግ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ግን ለድሉ የሚሰጠው መንግስታዊ አክብሮትና ትኩረት በእጅጉ አሽቆለቆለ፡፡
ይህን የታዘቡ  ወጣቶች፡- መሐመድ ካሳ፣ ያሬድ ሹመቴና ሌሎችም በራሳቸው አነሳሽነት “ጉዞ አድዋ” የሚል ቡድን አደራጅተው፣ ከአዲስ አበባ እስከ አድዋ ድረስ በእግር እየተጓዙ፣ በዓሉን አድዋ ላይ ማክበር ጀመሩ፡፡  ይህ ጉዞ እየተወደደ ሄዶ በሐረር፣በትግራይና በሌሎችም አካባቢዎች ተከታይና ደጋፊ እያገኘ መጣ፡፡  የአድዋ ጦርነት  ያስገኘው የድል ፍሬም ወደ ሕዝብ ጆሮ መድረስ  ቻለ፡፡
የዚህ እንቅስቃሴ ደጋፊ በሆነው ተዋናይ ሚካኤል ሰለሞንና ተባባሪዎቹ አዲስ ሃሳብ ተፈጠረ፡፡ ይኸ ደግሞ ዓመታዊውን የአድዋ ድል በዓልን  አድዋ አደባባይ ላይ ካከበሩ  በኋላ በእግር  እስከ አድዋ ድልድይ መጓዝ ነው፡፡ ለአካባቢው ታዋቂነት  ያስገኘው ኢሳያስ ማስታወቂያ ድርጅትም፣ የተጫወተው ሚና ሳይጠቀስ  አይታለፍም። የድልድዩን አካባቢ በምኒልክ፣ በእቴጌ ጣይቱና በሌሎችም የአድዋ ዘማቾች ፎቶ በነጻ ማስዋቡን አለመመስከር ንፉግነት ነው።
የአድዋ የድል ቀንን በማግነንና ህዝባዊ  በማድረግ ረገድ የራሱን ድርሻ የተወጣም ሌላ ሰው አለ፡፡ እሱም ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ነው፡፡ ነፍሱን ይማረውና በአንድ ቃለ መጠየቁ ላይ፣  ከዘመዶቹ ውስጥ አድዋ የዘመተ ሰው እንዳለ መናገሩ አይዘነጋም። አድዋን ያወደሰበት ዘፈንም እንዳለው ሰምቻለሁ፡፡ ከ1998  ጀምሮ የክልሉን ዋና ከተማ ወደ አዲስ አበባ ያዘዋወረው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የአድዋን ድል በአደባባይ  እንዲያከብር ያነሳሳው ሃጫሉ ሁንዴሳ ነው የሚል ጥኑ እምነት አለኝ፡፡
የካቲት 23 ቀን 2014 ዓ.ም የተከበረው 126ኛው የአድዋ ድል በዓል ቀደም ሲል እንደጠቀስኳቸው ሁለት በዓላት ሁሉ  በመንግስትና በሕዝብ መካከል መቃቃር የፈጠረ ሆኖ አልፏል፡፡ ይሄ ደግሞ የፖለቲከኞችና የካድሬዎች ፍላጎት እንጂ የህዝብ ፍላጎት እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡
የዘንድሮውን የአድዋ ድል በዓል ያዘጋጁት ባህል ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና የጥንታዊ ኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር መሆናቸው ተገልጧል፡፡
 ሁሉም በጉዳዩ ላይ እርስ በእርስ በስልክም ሆነ በደብዳቤ ሃሳብ መለዋወጣቸው አይቀርም፡፡ በዚህ የመረጃ ዘመን ነገራቸው በሙሉ በሚስጥር ተይዞ ይዘልቃል ብለው ማሰባቸው የዋህነት ነው። እዚህ ላይ የመንግስት ሃላፊዎቻችን በሳል አለመሆን በግልጽ ተስተውሏል፡፡ እኔ እነሱን ብሆን ኖሮ፤ “126ኛው የአድዋ ድል በዓል ጠዋት በአድዋ አደባባይ በአፄ ምኒልክ ሀውልት ስር የመንግሥት ባለሥልጣናት አበባ ያስቀምጣሉ። አድዋ ድልድይ ላይ ደግሞ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሚገኙበት ፕሮግራም ይቀጥላል” በማለት ግልፅ አድርጌ እናገር ነበር፡፡ በተረፈ ግን “የአድዋን ድል ያለ ምኒልክ ማሰብ አይቻልም፣ ትዝብት ላይ አትውደቁ” ማለት ነው የምፈልገው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ፣ የሚቀጥለው 127ኛው የአድዋ በዓል፣ በግንባታ ላይ ያለው “አድዋ ዜሮ ዜሮ” ሕንፃ ስለሚጠናቀቅ፣ በዚያ እንደሚከበር አስቀድመው አስታውቀዋል። በግሌ “ዜሮ ዜሮ” የሚለው ስያሜ ጥሩ አልመሰለኝም፡፡ ከዜሮ ይልቅ  “አድዋ ሀ” ቢሉትም ይሻላል።
በነገራችን ላይ በጦርነት ውስጥ የመጀመሪያ አሸናፊነት ዋጋ የሚኖረው ሌላ ጦርነት ካልተነሳ ነው፡፡ አድዋ ላይ ማሸነፋችን  በኋላ ከመወረር እንዳላዳነን መታወቅ አለበት። አድዋን ማክበር የቻልነው የሁለት ጊዜውን የሞቃዲሾ ወረራ እንዲሁም  የኤርትራን ጦርነት በማሸነፋችን  ነው።
ክብር በየጊዜው በሀገራችን ላይ የሚነሱ ጥቃቶችን መክተው ድል ላጎናጸፉን  ሁሉ!!!


Read 5375 times