Saturday, 05 March 2022 13:00

የዶ/ር አለማየሁ ዋሴ "ሚተራሊዮን" ሀገሯ የት ነው?

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(1 Vote)

  ሀገርን ትልቅ ማድረጊያ አንዱ መንገድ ኪነጥበብ ነው፡፡ መጽሐፍ፣ ዘፈን፣ ፊልም፣ ትያትር ወዘተ ለዚህ ተጠቃሽ መሆን ይችላሉ። ሀገራት በእነዚህ የኪነጥበባት ውጤቶች ብሔራዊ አጀንዳቸውን፣ እምነታቸውን፣ የበላይነታቸውን፣ ሥልጣኔያቸውን፣ ጀግንነታቸውን…ያንጸባርቃሉ፡፡
የማንን ፊልም ነው የምናየው? በማን ገንዘብ ነው ዓለም ዓቀፍ ግብይት የምንፈጽመው? የት ሀገር ለመኖር ነው የመኖርያ ፍቃድ የምንጠይቀው? የኛ የኢትዮጵያውያን የአክሱም ጊዜ ሥልጣኔ የት ሔደ? ላሊበላን የሠሩ እጆች አሁን የት ናቸው? ሌላ ሶፍ ዑመር ዋሻ የማይኖረን ለምንድው? ETRSS1 ሰው ሰራሽ ሳተላይታችን ለምን አስፈነደቀችን? ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ በጥቂቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር ለምን በተስፋ ሞላን ?
እኒህን እና መሰል ጥያቄዎችን እያነሳን እየመለስን ስናጠነጥን ኢትዮጵያዊነትን እናገኛለን፡፡ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ኃያልነት ተመኝተው ከጻፉ የቅርብ ጊዜ ደራስያን መካከል በ”ዴርቶጋዳ” ይስማዕከ ወርቁን፣ በ”444” ልዑል ግርማን፣ በ”ሁለተኛው ሰማይ” መልካምሰው አባተን እናገኛለን፡፡
አሁን ደግም ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ እሸቴ “ሚተራሊዮን”ን እነሆ ብሎናል፡፡ ጸሃፊው እንደቀደሙት  ደራስያን ሁሉ በመጽሐፉ ኢትዮጵያዊነትን አግንኖበታል፡፡  ዓለማየሁ ካሁን በፊት በ2008 ዓ.ም “እመጓ”፣ በ2009 “ዝጎራ”፣ በ2010 ዓ.ም “መርበብት” እና በ2013 ዓ.ም “ሰበዝ”ን ለንባብ አብቅቷል፡፡ አሁን ደግሞ “ሚተራሊዮን”ን ለንባብ አብቅቷል። “ሚተራሊዮን” አምስተኛ መጽሐፉ ነው። ደራሲው በመግቢያው እንደሚነግረንም፤ ከቀዳማውያኑ ዐራቱ መጻሕፍት #ዝጎራ;ን ማንበብ "ሚተራሊዮን"ን በተሻለ መንገድ ለመረዳት ይጠቅማል፡፡
በሚተራሊዮን  የዓለማየሁ ዋሴ ኢትዮጵያን እናገኛለን፡፡ ኢትዮጵያ ከመንፈሳዊነት፣ ከሳይንስ፣ ከባሕል፣ ከትውፊት፣ ከሥልጣኔ አንጻር የት እንደነበረች፣ የት እንዳለችና ወደፊት የት እንደምትደርስ በገጸባሕርያቱ አማካይነት ያስተነትናል፡፡
በአንደኛ መደብ እኔ እያለ የሚተርከው ተራኪ፣ በሙያው የብዝኀ-ሕይወት ተመራማሪ ነው፡፡ ሲሳይ ይባላል፡፡ የሚተርክልን ደግሞ ጉስቁል ግን ተስፋ ያላትን ሚተራሊዮንን ነው፡፡ ተራኪው ሲሳይ ሚተራሊዮንን ያያት ተጎሳቁላ  ነው። እናም አዘነላት፡፡ ከገዳማውያኑ ጋር በመሆንም ለችግሯ መፍትሔ፣ ለሕመሟ ፈውስ ለመሻት ሲወርድ ሲወጣ እናያለን፡፡ እንዲህ የሚጨነቅላት ሚተራሊዮን ማናት ለሚለውም በአይኑ ያየውን፣ በአፍንጫው ያሸተተውንና በህሊናው  የተገነዘበውን ይነግረናል፡፡
"አባ አካለወልድ ጠጋ አሉና የሆነ ሥም ሲጠሩ ካቀረቀረችበት ፈገግ ለማለት እየሞከረች ቀና አለች፡፡ አባ መስቀላቸውን አሳለሟት፡፡ እንዲህ ያለ የክርስትናም ሆነ የዓለም ሥም ሰምቼ አላውቅም። ‘ሚተራሊዮን’ ብለው ነበር የጠሯት፡፡ በግርምት አተኩሬ አየኋት፡፡
"ያልተበጠረ ዞማ ፀጉሯ፣ ያልተከረከመው ለስላሳ ጥፍሯ፣ የገረጣው ፊቷ፣ የተዛነፈው ቅርጽዋ፣ የተቀዳደደው ድሪቶ ልብሷ ውበቷን አደበዘዘው እንጂ አላጠፋውም ነበር፡፡ ሥጋ አጥቶ በገጠጠው ቅንድቧ ሥር ዋሻ ውስጥ ያለ ዕንቁ መስለው የሚንከባለሉት ርግብ ዐይኖቿን፣ በደረቀው ከንፈሯ የተሸሸጉት የወተት አረፋማ ጥርሶቿንና በደመና ፊቷ የተጋረደው ቁጥብ ፈገግታዋን ላስተዋለው ግን ግሩም ቁንጅናዋ በአቧራ እንደተሸፈነ ወርቅ ለመደበቁ እርግጠኛ ይሆናል፡፡ ከጉስቁልናዋና ከለበሰችው አዳፋ ልብስ ጋር አብረው የማይሔዱ የሚመስሉ ውብ ቅርጽ ያላቸውን እድሜ ጠገብ ጌጦች በአንገቷ ዙርያ አስራለች…" (ገጽ 62)
ስለማንነቷ ከሚገልጸው ከዚሁ ገጽ  ጀምሮ ቀጥሎ ባለው ገጽ 63 ጭምር ስላሳለፈችው ታሪክና ቤተሰቧ ይተርካል፡፡
“…እየውልህ  ከረጅም ዘመን ጀምሮ ደም ይፈሳታል፡፡ የሚፈሳት ደም ክብሯን፣ ፀጋዋን፣ ሀብቷን፣ አካሏንም ጭምር እንዲህ እንደምታየው አጎሳቁሎታል” አሉ በጥልቅ ትካዜ፡፡ ቀጠሉና፡-
"የዚህ ሁሉ መከራ ምንጭ መንታ ችግር ነው፡፡ በየዘመኑ ያገባቻቸው ክፉና ስግብግብ ባሎቿ እንዲሁም የባሎቿ ራስ ወዳድነትና ጭካኔ የወረሱት አመለ ዥንጉርጉር  ልጆቿ ናቸው፡፡ ጀግናና ፈሪ፣ ጎበዝና ሰነፍ፣ ለጋስና ቀማኛ፣ አማኝና ቀማኛ የወለደችበትን ማህፀኗን ያልበላ አንጀቷን ተደግፈው ሲራገጡ የኖሩት ልጆቿ ችግሯን ካለማወቃቸው የተነሳ ይኸው ለርሷ ጤና ማጣት ለራሳቸው ደግሞ መከራን ጋበዙ። ረሃብ፣ እርዛት፣ ጦርነትና ስደት ዕጣ ፈንታቸው ሆነ፡፡ እርሷም  የወላድ መካን የሆነች ያህል ለሕመሟ ማስታገሻ ለችግሯ መፍቻ ከልጆቿ ዘንድ እስካሁን አላገኘችም…""
እዚህ ጋ ሚተራሊዮን፣ ሚተራሊዮን ብቻ አለመሆኗን እንረዳለን፡፡ በመጽሐፉ  አንዲት ጉስቁል ሴት መስላ ብትቀርብም ተምሳሌታዊ ፍቺ ያላት ይመስላል፡፡ ብርሃኑ ገበየሁ በ”የአማርኛ ሥነግጥም” መጽሐፋቸው እንዳሉት፤ በተምሳሌትነት የሚገባ ቃል ባለ ሁለት ደረጃ ፍቺ አለው፡፡ ምንም እንኳ አሁን ስለ ልቦለድ መጽሐፉ ብናወራም፣ ምሁሩ አማርኛ ሥነግጥምን አስመልክቶ በግጥም ተምሳሌት ያሉት ለልቦለድ ተምሳሌትም ይሠራል፡፡ እናም ሚተራሊዮን ኢትዮጵያን የወከለች ተምሳሌት ለመሆኗ ከመጽሐፉ የተለያዩ አንቀጾች መጥቀስ ይቻላል፡፡
"ልጆቿ ራሳቸው ሕመምተኞች ሆነዋል። እና ሁሉም የግሉን ሕመም እንጂ አንዱ የአንዱን ሕመምና ችግር አያይም፡፡ ሁሉም ጥጉን ይዞ ግማሹ የዳነውን ቁስሉን እየቀረፈ፣ ግማሹ አዲሱን እያመገለ በየቤቱ ሙሾ ያወርዳል፡፡ ‘ተበዳይ ነኝ የሚል እንጂ በዳይ ነኝ’ የሚል የለም፡፡ ሁሉም ‘ተገፋሁ የሚል እንጂ ገፋሁ’ የሚል የለም፡፡ አንዳንዶቹም የአንዱ ቁስል ከሌላው እንደሚበልጥ ትንታኔ በመስጠት ተጠምደዋል… (ገጽ 74)
መጽሐፉን እያነበብን ወደፊት በገፋን መጠን በኢትዮጵያዊ ፍልስፍና፣ ዕውቀት፣ ታሪክ እንመሠጣለን፡፡ የፍልስፍና ምንጩ ደግሞ እንደ ሁልጊዜው በዕድሜና በዕውቀት የገፉ ምሁራን ብቻ ሳይሆኑ እረኞችም ሕፃናትም ናቸው፡፡
ለምሳሌ ገጽ 163 እንዲህ ይላል፡-
"የነቢል መጠን ያለፈ ደስታ፣ የልጆቹ በራስ መተማመን የሆነ ነገር አስታወሰኝ፡፡ አንድ ወዳጄ ሰሜን ተራራ በረዶ ከሚፈላበት ስፍራ እራፊ ጨርቅ የለበሱ እረኞችን አይቶ እሱ ራሱ ደራርቦ ለብሶ ብርዱን አልቻለውም ነበርና ሁኔታቸው ገርሞት፡-
“ልጆች አይበርዳችሁም?” ሲላቸው
“ጋሼ! አገር ይበርዳል እንዴ?” ብለው አሉኝ ብሎ አጫውቶኝ ነበር፡፡
በገጽ 180 ስለሌብነት የተባለው ሰሞኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ላይ ከተነገረው ጋር ተገጣጥሞብኛል፡፡ እነሆ፡-
"ስለ ስርቆት ስናወራ ኪስ የሚያወልቀውን፣ ቤት የሚሠረስረውን፣ በረት የሚገለብጠውን መናጢ ድሃና ተራ ዱርዬ ብቻ የሚመለከት ይመስለናል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሌቦች ባለ ኮትና ክራቫት፣ ባለቆብና ቀሚስ፣ ባለ ኒሻንና ማዕረግ ሆነዋል፡፡ ሌብነት ቢዝነስ ሆኗል። የሚያሳፍር ሳይሆን በወዳጅ ዘመዶችህ እንደ ብልጥና ቀልጣፋ የሚያስቆጥር ሆኗል። ዘርፈህ ቤት ብትሠራ ይጨበጨብልሃል። ሰርቀህ ብትመጸውት  ትመረቃለህ፣ 100 ሚሊዮን የሀገር ሃብት ዘርፈህ አንድ ሚሊዮን ለቤተ ክርስትያን ወይም ለቤተ መስጊድ ብትሰጥ ‘ምዕመናን እልል በሉላቸው’ ይባልልሃል፡፡ ቢሊዮን አጭበርብረህ መልሰህ ሚሊዮን ለመንግሥት ፕሮጀክት ስትለግስ ከሀገሪቱ ባለሥልጣን ጎን ተቀምጠህ ‘የቁርጥ ቀን ልጅ’ ትባላለህ፡፡ ገንዘብ መያዝክን እንጂ ከየት አመጣኸው የሚልህ የለምና ትከበራለህ…"
በገጽ 127 ለዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ከእንግሊዟ ንግሥት ቪክቶርያ የተደረገላቸውን የሽጉጥ ስጦታ መጥፎ ምልኪነት ከመጽሐፉ አንብቡት፡፡ ስለ ሚተራሊዮን ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የቦታ ውስንነት ይገድበናል፡፡  በጥር 2014 ዓ.ም ታትሞ የወጣውና በ262 ገጾች የተቀነበበው መጽሐፉ፤ በ170 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡  
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 2632 times