Print this page
Saturday, 05 March 2022 12:57

የፍሬዘር ወጎች

Written by  ሳሙኤል በለጠ
Rate this item
(0 votes)

ፍሬው ዘሪሁን (ፍሬዘር) ዲፕሎማት ነው። ከዲፕሎማትነቱ በዘለለ ደራሲ ነው። በድርሰት በቆየባቸው ጥቂት አመታት “ዣንተከል” እና “ራስ” የተሰኙ ልቦለዶች  ለአንባቢያን አድርሷል። አሁን ደግሞ እየሳሳ ባለው በወጉ ዘርፍ አንድ መጽሐፍ በቅርቡ አበርክቷል።
ወግ ምንድነው?
የእንግሊዝኛው ቃል (Essay) Essayer ከሚለው የፈረንሳይኛ ቃል የመጣ ሲሆን “to try” or “to attempt” (መሞከር) የሚል ትርጉም አለው፡፡ ስለዚህ የእንግሊዝኛው (Essay) “trial” or “an attempt”  (ሙከራ) ማለት ይሆናል፡፡ ፈረንሳዊው Michel Montaigne በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ቃሉን ለጻፋቸው ልዩ ልዩ መጣጥፎች  መጠሪያነት ተጠቅሞበታል። ይህ ደራሲ ቃሉን የተጠቀመው  ሐሳቡን በጽሑፍ ለማስፈር የተደረጉ ሙከራዎች መሆናቸውን ለማጠየቅ ነበር፡፡
"ወግ” የእንግሊዝኛውን “Essay” ለመተካት የተጠቀምንበት  ቃል ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ባለቅኔ ደበበ ሠይፉ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) እንደተጠቀሙት፣ በደራሲ መስፍን ሀብተማርያም "የቡና ቤት ስዕሎች እና ሌሎችም ወጎች" መጽሐፍ "ማለፊያ ምዕራፍ” በሚለው ርዕስ ስር ተጠቅሷል። ነገር ግን ቃሉ የእንግሊዝኛው “Essay” የያዘውን ሐሳብ በከፊል እንጂ በሙሉ እንደማይገልጽ ራሳቸው ባለቅኔ ደበበ ሠይፉ መናገራቸው ይታወቃል፡፡ ወግ የሚለውን ቃል ካገኘን፣ ‘ወግ’ በአንድ በተወሰነ ጭብጥ ላይ ትኩረቱን አድርጎ በዝርው ተጽፎ የሚቀርብ የጽሑፍ ዐይነት ነው። ገጠመኞች፣ ጉዞአዊ፣ ንጽጽራዊ፣ ቀልድ አዘል፣ ነባራዊ ጽሑፎችን ‘ወግ’ ስንላቸው፣ በጥቅሉ ወግ ሲባል ማንኛውም ጉዳይን አስመልክቶ ሁሉንም ነገር አጠር አድርጎ የሚገልጽ የፈጠራ ጽሑፍ ነው።
 “አለቃና ምንዝር” ፍሬዘር በሁለት ክፍል በሁለት መቶ ስልሳ ስምንት ገጽ በገጠመኝና በዕይታዎች ሲያዋቅረው፣ አጠቃላይ ስያሜ አልሰጣቸውም፡፡ እንደ እኔ “ወግ” ቢባሉ ተገቢ ነው።(ለመጽሐፉም ቅርጽ ይሰጠው ነበር፤) ስለ መጽሐፉ ቁመና ስናነሳ የሽፋን ምስሉ እጅግ ማራኪ ነው። ስለ አርትዖት ጉዳይ ከተነሳ ዘወትር የምናየው ችግር ትንሽ ቢቀረፍም የተለመዱ የአርትዖት ስህተቶች ግን  አሉ፡፡
የወግ መገለጫ(ወግ ሲባል)
ደራሲና ሐያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ “ወግ ሲባል ከሁለቱ ኃውልቶች … እስከ ጠጠሮቹ”  ብሎ አዲስ አድማስ ላይ የዲያቆን ዳንኤል ክብረትን የወግ ስብስብ ባሔሰበት መጣጥፉ፣ ቨርጂኒያ ዎልፍን ጠቅሶ እንዲህ ይላል፡- “አንድ መልካም ወግ መጋረጃውን በዙሪያችን ማንዘርፈፉ ቋሚ መስፈርቱ ነው። ታዲያ እኛን ከመጋረጃው ውጭ ማስቀረት ሳይሆን ውስጡ ሰብስቦ ማስገባት መቻሉ ግዴታው ነው፡፡” ( “A good essay must have this permanent quality about it, it must draw its curtain around us, but it must be a curtain that shuts us in not out”) ፍሬው ዘሪሁን፤ በመደበኛ ወጉ እና በኢ-መደበኛ ወጉ (informal Essay) በንጽጽር፣ በአስረጂ፣ በተዋስኦ (Dialogue) ስሜታችንን ሰቅዞ በተህዝናኖት ውስጥም እያዋለለን (እያሳሳቀን) ይተርካል። ጸሃፊው በመቼና የት በክብቦሽ በጋረደው መጋረጃ ገብተናል( ተአምር፣ ሳቅ፣ ሲቃ ከመቼና የት ሐረግ ይመዘዛል) ከስሜቱ፣ ከቀልዱ፣ ከመብከንከኑ ተዋስበዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
የወግ አተራረክ ስልት
ታላቁ ባለቅኔ ደበበ ሠይፉ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) የወግ አጻጻፍ ስልቱ እንዴት መቃኘት እንዳለበት የቡና ቤት ስዕሎች በሚለው የወግ ስብስብ መግቢያ ላይ እንዲህ ይላሉ፡- “ለወግ ደርዳሪዎችስ፣ ነገር በምሳሌ ጠጅ በብርሌ” ዐይደል ነባር የወግ አዝማቻቸው? ሳይጠቀስ ሊታለፍ እማይገባው ሌላው ተጨማሪ ነጥብ፣ Informal Eassy (ታዲያ የፍሬውን ክፍል አንድን ኢንፎርማል እሴይ፣ ክፍል ሁለትን ፎርማል ኢሴይ ብንለው) በደራሲውና  በተደራሲው መሐል አንዳች ውስጣዊ ትውውቅን፣ ጥብ ግብብነትን የመፍጠር ባሕርይው ነው። የነዚህ ማለት የደራሲውና የተደራሲው - ግብብነት፣ ከአስተማሪነትና ከተማሪነት እሚመነጭ ዓይነት ዐይደለም፡፡ የአለቃና የምንዝር ብጤም። ይልቅስ የወዳጅነት ዓይነት ነው፣ የእኩዮሽ ተደማማጭነት። ደራሲው ይህን ታውቃላችሁ ሳይሆን፣ ይህን አስተውላችኋል የማለት ያህል ስንዝሮቹን ሲደረድር፣ ተደራሲው እውነትህንኮ ነው እያለ በአዎንታ ራሱን እየነቀነቀ እንደሚመልስ ብጤ። እንደዚህም በመሆኑ Informal Eassy እጅጉን  ትምህርታዊ ሳይሆን ትዕዛዛዊ፣ ይበልጡን ውይይታዊና አዝናኛዊ ባሕሪይ ነው ያለው - እንደ ወግ ሁሉ። ቋንቋውም ብዙውን ጊዜ መደባዊ (ጽሑፋዊ) ሳይሆን፣ ኢ-መደባዊ (ንግግራዊ) መሆኑ በዚህ ምክንያት ነው።”(የቡና ቤት ሥዕሎች ገጽ-4) ይላሉ የፍሬዘርን ክፍል አንድ ኢንፎርማል ኢሴይ፣ ክፍል ሁለትን ፎርማል ካልነው። ወጉ እንዴት ይተረክ? ወግ ሲጻፍ አንባቢን ከ Eectopic (ከባይተዋር) ስሜት እንዲነጠል ማገዝ አለበት፤ ጉዳዩ በእኛ ውስጥ ሁለ-ቅርጽ መስራት አለበት፥ በዚህ መስመር ስሜቱ ያጫውታል። የስሜቱ ፊገር ሲታይ ስሜትን የመሰቀዝ፣ የሚያዝናና ሊሆን የተገባ ነው።
ለወግ  ማራኪ ኪን ጉጉት ነው(ከ “ወ” ወደ “ግ” ለመዝለል ‘ተረኩ’ እንዴት አድርጎ ሊጨርሰው ይሆን? ማለት አለበት፤ አፍቃሬ አንባቢ “ከዚህ ቀደም ሲዖል እንዳለ እርግጠኛ አልነበርኩም። አሁን ግን ሳስበው መኖር አለበት። አለበለዚያ ሌኒንና ትሮትስኪ ወዴት ይሄዳሉ?” ዊንስተን ቸርችል (አለቃና ምንዝር ገ-228 ደቡብ ሱዳን) ስለምን ሊነግረን ነው ብለን እንጠይቃለን መቼም! ወጎች ውስጥ የትዝብት ወይም የምጸት ድምጸት መኖሩ እሙን ነው። በአዝናኝ ገለጻዎች የተሞላ ትችት ነው ልንለው እንችላለን፡፡  ለአስረጂ ማርቼ 8 ገ-149 ቅንጫቢ ወግ እንመልከት:-
“እርግጥ ነው ወንድ በጉልበቱ በአእምሮው አሁን ያለውን ዓለም ጠፍጥፎ ሰርቷል። ግን ሠራተኛ እንጅ ባለሙሉ ስልጣን ዐይደለም። በግብጽ ጡብ የደረደሩ እስራኤላውያን ወይም ሮምን ጠፍጥፈው የሰሯት ባሪያዎች ባበጇቸው ከተሞች ላይ ሊያነሱ ከሚችሉት የባለቤትነት ጥያቄ በመጠኑ የተሻለ ሞግዚትነቴ ብቻ ነው ያለው። እነዚያ ከጀርባ አለንጋ የያዙት ፈርዖንና ቄሳር በጌትነት አቤት እንደሚሉት ሁሉ እዚህም ከኋላ ያሉት አሰሪዎች ሴቶች ናቸው።(ከዚህ በመነሳት ባለም ላይ ያለው ‘የሴቶች ጭቆና’ የሚባለውን ነገር ምናልባት ወንዶች ነጻነታቸውን መልሰው ለማቀናጀት የሚያደርጉት ያልተቀናጀ አብዮት ሊሆን ይችላል። በየዋህነት ሲገ ‘ዛ የኖረ ሕዝብ ድንገት ጭቆናው የበራለት ዕለት እንደሚነሳው ያለ።)
በዚህ ዘመን ‘ሴት ማንኛውም ወንድ የሚሰራውን መስራት ትችላለች!’ የሚል መነባነብ አለ። ዓይን ያወጣ ውሸት ነው። አትችልም።(ትፈልጋለች ወይ የሚለው ሌላ ጥያቄ ሆኖ።) ፓርላማውን በሺ ሴት ታጥለቀልቀው ይሆናል። ዓለሙ ሁሉ ግን ስለ ፓርላማ ዐይደለም። ወይም አንዲት ዳምጠው የምትነዳ ፈርጣማ ሴት ማሳየት የምድሩን መልክ አይለውጠውም።” ጸሐፊው ሴትና ወንድ ‘የአንድ ወፍ ሁለት ክንፍ’ መሆናቸውን ያጸናሉ፤ ኦሾ “በአካል ሴት የሆነ በአይምሮም ሴት፣ በአካል ወንድ የሆነ በአይምሮም ወንድ ይሆናል” የሚል አባባል አለው፤ በቀልድ፣ በቁምነገር፣ በእዛና እዛ በመርገጥ የተለያዩ ሐሳቦችን ያነሳሉ። ይህ ብቻ አይደለም፤ ሌላም ሌላም። Dead Toad scrolls በሚል መጽሐፉ በስፋት የሚታወቀው Kilroy J. Oldster “ወግ መጻፍ ከራስ ጋር በተዋስዖ ማውራት ማለት ነው፣ ግለ ሐሳብን ወስዶ እንደ ወይን በመጨፍለቅ ጥሩ ወይን ለቤት የመፍጠር ሂደት ነው።” ይላል (“Personal essay writing, dialectic discourse with the self, is a process of taking ideas and crushing them like grapes to create a homemade wine”) በዚህ ረገድ  ፍሬዘር ተሳክቶለታል።
መውጫ....
ወገኛ ምጡ አያልቅም፤ የጊዜ፣ የሰው መንሸራተት ያሳስበዋል። ላለፈው ይጨነቃል፤ ለነገ እንደጨለማ ለብርሃን ይጨነቃል። የተዋበውን ያከብራል፥ ላስተምር አይልም ይማራል፤ ላጫውት አይልም ያጫውታል። ፍሬዘር ይህ ተሳክቶለታል፡፡ ጎበዝ ደራሲ እንደሆነ አስመስክሯል። እንዳይረሳን፣ እንዳንረሳው ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡

Read 1499 times