Saturday, 05 March 2022 13:05

የገብሩ ስጋቶች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

      የኢትዮጵያ ቡድን ከሊቢያ ጋር ላለበት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ወደ ትሪፖሊ ይሄዳል፡፡ የሚጓዘው በጣሊያን ወይም በግሪክ በኩል አድርጎ ነው፡፡ ቡድኑ ሸበሌ ሆቴል ነው ያለው፡፡ ገብሩ ወ/አማኑኤል  ክፍሉ ውስጥ ቁጭ ብሎ ይቆዝማል፡፡ በሐሳብ ወዲያ ወዲህ  ይዋልላል፡፡ በቀጣይ ቀናት የህይወቱን መስመር መለወጥ ይኖርበታል፡፡ ከገባበት አጣብቂኝ ካልወጣ ለእሱም ለቤተሰቡም ጥሩ አይደለም። ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ የኢ.ህ.አ.ፓና የኢ.ዲ.ዩ ደጋፊዎች ነበሩበት ስለሚባል “ምንጠራ” ይጀመራል፡፡ ጊዮርጊስ ክለብ ከፈረሰ ጥቂት ጊዜያት ያለፈ ቢሆንም፣ አሁንም ከክለቡ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ጣጣ ገብሩን እያሳሰበው ነው፡፡ በቀጣዩ ሁለት ቀናት ከዚህ አገር መጥፋት አለበት፡፡ በሐሳብ ላይና ታች በሚልበት ሰዓት የክፍሉ ስልክ አንቃጨለ፡፡
ደንግጦ ስልኩ ላይ አፈጠጠበትና ሄዶ አነሳ፡፡ የደወለችው ሴት ነች፡፡
 “ሐሎ” አለችው
“አቤት…ማንን ፈለግሽ?”
“ገብሩ ነህ?”
“አዎ ፤ማነሽ?”
“እኔ ነኝ” (ስሟን ነገረችው፡፡ ያውቃታል፤ ዘመዱ ነች፡፡)
“ደህና ነሽ?”
"ደህና ነኝ፡፡… መቼ ነው ሊቢያ የምትሄዱት?”
“ከነገ ወዲያ”
“ከየት ነው የምትሄዱት?”
“ከግሪክ ወይም ከጣሊያን”
“ትመለሳለህ እንዴ?”
“ምን አልሽ!!” (ገብሩ ደነገጠ)
“ልትጠፋ ነው አይደል?;
"እንዴት እንዲህ ልትይ ቻልሽ?”
“ማለቴ…..!”
“ኧረ ተይ !!”
ሁለቱም ስልኩን እንደያዙ ቀጣዩን ነገር መነጋገር አቆሙ፡፡ ገብሩ መደንገጥ ብቻ ሳይሆን በርግጓል፡፡ ልጅቷን ያውቃታል። ከምን ተነስታ እንደጠየቀችው ግራ ገብቶታል። ስልኩ ሊጠለፍ ይችላል፡፡ ይህ የመጨረሻ እድሉ ነው፡፡ ከተነቃበት አለቀለት። በኩብለላ ከተጠረጠረ ከብሔራዊ ቡድኑ ይባረራል፡፡ መሰናበት ብቻ ሳይሆን ደርግ ያለፈ ታሪኩን ከደረሰበት እስር ቤት መግባቱ ነው፡፡ ከዚያ የሚደረገውን ይደረጋል፡፡ ስለዚህ ይህን የስልክ ጥሪ ከመዝጋቱ  በፊት ውይይታቸውን የጨዋታ ማስመሰል አለበት፡፡ እየሳቀ “እየቀለድሽ ነው አይደል” አላት፡፡
- “በግምት እኮ ነው”
- “ሴቶች ቀልድ አልተቻላችሁም”
-“ምን አልክ?”
-“ድምፅሽን ቀይረሽ አወቅኩሽ”
-“አንተም እየቀለድክ ነው”
-“ስመለስ ምን ይዤልሽ ልምጣ”
- “ምንም….እኔ ግን….”
ልጅቷ ሐሳቧን ሳትጨርስ ቻው ብሎ ስልኩን ዘጋባት፡፡ እንደሚመለስ ነግሯታል። ስልኩ የተጠለፈ ቢሆን እንኳ “ስመለስ ምን ላምጣልሽ” ማለቱ እንደማይጠፋ ተናግሯል። የሚያስፈልገው ደግሞ  መናገሩ ነው፡፡ ነገሩን በዚሁ መቋጨቱ ጥሩ ነው፡፡ ለመኮብለል ማሰቡና  መዘጋጀቱ ከታወቀ አደገኛ ነው፡፡ ገብሩ “እንደምንጠፋ ተመልካቹም ያውቃል ምክንያቱም  በጨዋታ ተቀዛቅዘናል፤ ሞራላችን ወርዷል፤ በሁሉም ነገር ደስተኛ እንዳልሆንን ያስታውቃል፤ ልጅቷም ስትደውል ለክፋት  ብላ ሳይሆን  እንዳልመለስና እንድጠፋ ለማበረታታት ነው፡፡”
ገብሩ አስደንጋጩ የስልክ ጥሪ ስጋት ውስጥ ስለከተተው፣ ከሆቴሉ ወጣ ብሎ መንፈሱን ማረጋጋት ጀመረ፡፡ ሰዎች ሲያዩት ሁሉ የጠረጠሩት ይመስለዋል፡፡ ግን የሚያዩት ኳስ ሜዳ የሚያውቁት ሰዎች ናቸው፡፡ ወደ ክፍሉ ተመለሰ፡፡  ከጓደኞቹም ጋር ቁጭ ብሎ መጫወት ጀመረ፤ ግን አልተረጋጋም፡፡ ለመኮብለል የተዘጋጁ ሁለት ተጫዋቾች በፖለቲካ  ተጠርጣሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች ቁጭ ብለው እያወሩ ከኦሜድላ ክለብ የተመረጠው ኃይሉ ጎሹ ወደ ክፍላቸው ገባ፡፡ መቃለድ ጀመረ፡፡ ቤቱን ሲመለከት ምንም የተዘጋጀ ነገር የለም፡፡ አያቸውና፤ “ሻንጣ የላችሁም እንዴ?” አላቸው
“የምን ሻንጣ?”
 “የጉዞ ሻንጣ”
 “አለን”
“ታዲያ የታለ?”
“እነ እንትና ክፍል ነው….”
ገብሩ ደነገጠ፡፡ ለመጥፋት ስላሰቡ ሻንጣ አልያዘም፡፡ ይህ ጥያቄ ከኃይሉ ጎሹ መምጣቱ እንጂ ቡድን መሪው ወይም ከቡድኑ ጋ ያሉት የደህንነት ሰዎች ጠይቀው ቢሆን ኖሮ ይጠረጥራሉ፡፡
በዚህም የተነሳ ያለምንም ጥያቄና ቅድመ ሁኔታ ያባርሯቸዋል፡፡ ያኔ ደግሞ ትንሽ ፍንጭ ከተገኘ ስንብት ነው፡፡ ገብሩ ቶሎ ወደ ቤት ሄዶ ሻንጣ ይዞ መጣ። የማይኮበልል ተጫዋች ማረጋገጫው ሻንጣ መያዝ ነው፡፡ የገብሩ ደግሞ ትልቅ ሻንጣ ነው፡፡ ከፍ ያለ ሻንጣ ከያዘ ብዙ እቃ ይገዛል። ከገዛ ተመላሽ ነው፡፡
ኢህአፓ ተማሪውን ይዟል
ሸበሌ ሆቴል ውስጥ ማታ ሁሉም ተጫዋቾች ተጠሩና ስብሰባ ተደረገ፡፡ የመንግስት ካድሬዎች ናቸው የመጡት። ከጥቂት  ወራት በፊት የወጣት ቡድን ተጫዋቾች ወደ አልጀሪያ ሲሄዱ  ጣሊያን ላይ ኮብልለው ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ የውጭ ሚዲያዎች፣ ተጫዋቾቹ  የሚጠፉት ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ነው በሚል ዘግበው ስለነበር፣ ኩብለላው ደርግን በጣም አስቆጥቶታል፡፡ ገብሩ “አሁን  የመጡት ካድሬዎች በመኮብለል ምንም ጥቅም እንደማይገኝ ይመክሩን ጀመር፡፡ ካድሬው ረገጥ አድርጎ “ለመጥፋት የፈለጋችሁ መሄድ ትችላላችሁ፡፡ እኛ ማንንም አንለማመጥም። እነ መንግስቱ  ወርቁ እንኳ ስንት ዓመት አገልግለው አንድ ቀን ኮርተው አያውቁም፤ አልኮበለሉም፡፡ እናንተ ግን ልባችሁ ውጪ ነው ያለው፡፡ እዚህ አገር ምን ጎደለባችሁ?" አለ፡፡
ካድሬው በቁጣ ውርጅብኝ ጣለብን፡፡  እንደገና ቀጠለና፤  #እነ ሲበን ባለፈው ጣሊያን ላይ ጠፍተው በረንዳ ላይ ነው የሚያድሩት፤ አሁን ከባድ ችግር ላይ ወድቀዋል፡፡ ወደ ሐገር ለመመለስ እንደሚፈልጉ ሰምተናል፡፡ እኛ ደግሞ ሐገር የከዳን ሰው እንደማንቀበል አሳውቀናል፡፡ እናንተም  የምትጠፉ  ከሆነ የእነሱ እጣ ፈንታ ነው የሚጠብቃችሁ” በማለት ካድሬው  ከተናገረ በኋላ  ወደ ተጫዋቾቹ እያየ፤
“በዚህ ላይ አስተያየት አላችሁ?” አለ
(ዝም)
“ከእናንተ ውስጥ መጥፋት የሚፈልግ አለ?”
(ዝም)
 “አትናገሩም?!”
(ዝም)
ካድሬው ወደ ገብሩ ያያል፡፡ ገብሩም ድንገት ነው ወይስ ሆን ብሎ ነው ወደ እኔ የሚመለከተው?  ብሎ ግራ ተጋባ፡፡ ልጅቷ ስትደውል ስልኩ ተጠልፎ ይሆን? ብሎ ጠረጠረ፡፡ የገብሩ ኢ.ህ.አ.ፓ ታሪኩ  ከኋላው ይከተለዋል፡፡ ሲጀመር እንዲህ ነበር፡፡
በ1996 ዓ.ም ወጣቱ በፖለቲካ ትኩሳት እየነደደ ነው፡ በየት/ቤቱ ረብሻ አለ፡፡ ለውጥ ፈላጊውም በዝቷል፡፡ በተለይ  ወጣት  ተማሪዎች የለውጥ ድርጊቶች ናቸው፡፡ በወቅቱ “እድገት  በህብረት  የእውቀትና የስራ ዘመቻ” በሚል ከ10ኛ ክፍል በላይ የነበሩት ተማሪዎች 1967 ዓ.ም ታህሳስ ወር ወደ ገጠር ዘምተው ነበር፡፡ ቁጥራቸውም 60 ሺህ ይጠጋል፡፡ ገብሩም ከዘማቾቹ አንዱ ነው፡፡
ነገር ግን ለብሔራዊ ቡድን በመመረጡ ለጊዜው ሳይሄድ ቀርቷል።  ሆኖም ተማሪዎቹ ዘመቻ የጨረሱበት ሰርተፊኬት ካላገኙ ትምህርታቸውን አይቀጥሉም። ስራም አያገኙም፡፡ ገብሩ ለብሔራዊ ቡድን ሲመረጥ “ ሰርተፊኬቱ ካልተሰጠኝ አልጫወትም እዘምታለሁ” የሚል ጥያቄ ያቀርባል፡፡
("ኢህአፓ እና ስፖርት" ከተሰኘው የገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) መጽሐፍ የተቀነጨበ)


Read 1033 times