Print this page
Saturday, 12 March 2022 12:28

የዜግነት ስነ ልቦናን ለማበልጸግ ያለመው “ኢትዮጵያዊነት” ድርጅት ስራ ጀመረ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 የኢትዮጵያውያንን የጋራ እሴቶች መሰረት በማድረግ የተሸረሸረውን የዜግነት ስነ-ልቦናና ኢትዮጵያዊነት ለማሳደግ እንቀሳቀሳለሁ ያለው የኢትዮጵያ የዜጎች መብት ማስከበሪያ ድርጅት በድጋሚ መመስረቱ ታውቋል።
ከዚህ ቀደም በ1984 ዓ.ም በቋንቋ ላይ የተመሰረተውን የፖለቲካ አካሄድ አደገኛነት በተገነዘቡት በዶ/ር ደጃዝማች ዘውዴ ገ/ስላሴ፣ በክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ፣ ቢትወደድ ዘውዴ ገ/ህይወት፣ ልጅ ሚካኤል እምሩ፣ ጀነራል ጀጋማ ኬሎ፣ አፈንጉስ ሀጎስ ተ/መድህንና ወዳጆቻቸው ተመስርቶ የነበረው “ኢትዮጵያዊነት” የተሰኘውን ማህበር መነሻ አድርጎ በ2012 በድጋሚ የተቋቋመውና በ2013  እውቅና ያገኘው ድርጅቱ፤ በዛሬው እለት ለመጀመሪያ ጊዜ የመተዋወቂያ መርሃ ግብሩን በ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ያካሂዳል።
በዚህ የመተዋወቂያ መድረክ ላይ የድርጅቱ አላማ እና ግብ ለታዳሚያን በዝርዝር የሚቀርብ ሲሆን የመንግስት ባለስልጣናት፣ ምሁራንና የሲቪክ ማህበረሰብ ተወካዮች  ይታደሙበታል ተብሏል።
ድርጅቱ ኢትዮጵያውያንን ያስተሳሰሩ እሴቶችን አጉልቶ በማውጣት ባለፉት 30 ዓመታት በልዩነቶች ላይ ያተኮሩ ፖለቲካዊ ትርክቶችን በመርህ፣ በእውቀትና በመረጃ በታገዙ ትምህርቶች ለማስተካከል ጥረት ያደርጋል ተብሏል።
ድርጅቱ በዋናነት የኢትዮጵያውያንን የጋራ እሴቶች  የመርመር፣ ስለ ጋራ እሴቶች የማስተማር እንዲሁም ህዝቡን በተለይም ወጣቱን የማቀራረብና የማስተማር አላማን ማንገቡ ተገልጿል።
በተጨማሪም “ኢትዮጵያዊነት” የተሰኘው ማህበር የተሸረሸረውን የዜግነት ስነ-ልቦና እንደገና ለማዳበርና ለማሳደግ በቋሚነት የሚያስተምር ማዕከል በመፍጠርም የተዛቡ ትርክቶችን በመረጃ ለማስተካከልም ጥረት ያደርጋል ተብሏል።


Read 6024 times