Saturday, 12 March 2022 12:29

በሁለት አመት ተኩል ብቻ 843 ብሄር ተኮር የጥላቻ መልእክቶች በፌስቡክ ተሰራጭተዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  - ፀያፍ የጥላቻ ንግግሮች-60.5%
   - የንቀት ንግግሮች- 25.03 %
     - ሰብአዊነትን የሚያዋርዱ -14.47 %
                
             በሁለት ዓመት ተኩል ውስጥ ብቻ በማህበራዊ ሚዲያ  በተለይም በፌስቡክ አማራ፣ ኦሮሞንና ትግሬን ኢላማ ያደረጉ 843 ያህል ብሄር ተኮር የጥላቻ  መልዕክቶች መሰራጨታቸውን “ፋክቲፋይ ኢትዮጵያ” ያከናወነው ጥናት ውጤት አመላክቷል።
በፌስቡክ “እኛ” እና “እነሱ” በሚል የሚሰራጩ በጥላቻ ላይ የተመሰረቱ መረጃዎች እንዲሁም “የጨቋኝ ተጨቋኝ” ትርክቶች የማህበረሰቡን የዘመናት ማህበራዊ ትስስርና መስተጋብር ለአደጋ  አጋልጠውታል ብሏል-የጥናቱ ሪፖርት።
ተቋሙ በተለይ ከየካቲት 2011 እስከ ነሐሴ 2013 ዓ.ም በፌስ ቡክ በተሰራጩ የጥላቻ መልዕክቶች ላይ ባካሄደው ጥናት፣ 843 ያህል ብሔር ተኮር የጥላቻ ንግግሮችን መመርመሩን ጠቁሟል።
እነዚህን የጥላቻ ንግግሮች  ያመነጩትም  412 የፌስ ቡክ ገጾች ሲሆኑ ገጾቹም ለ8 ሚሊዮን ያህል የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ተደራሽ እንደነበሩም ጥናቱ ለይቷል።
አብዛኞቹ ጥላቻ ንግግሮችን የሚያሰራጩ የፌስ ቡክ ገጽ አካውንቶችም በሀገር ውስጥ ተቀማጭና በግለሰቦች የተከፈቱ ሲሆኑ የተወሰኑት ደግሞ በውጪ ሃገር በተለይም በአሜሪካን ሳኡዲ አረቢያ ፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ፣ ኬኒያና ጀርመን በሚኖሩ ግለሰቦች የተከፈቱ መሆናቸው ተመልክቷል።
እነዚህ የጥላቻ ጽሁፎች ሲሰራጩ  90 ሺህ ያህል አስተያዮች፣ ማጋራቶችና የስሜት ምላሾች ማስተናገዳቸውም ተጠቁሟል።
በ412 የፌስቡክ ገጾች የተሰራጩት 843 ብሄር ተኮር የጥላቻ መልዕክቶች በአማራ፣ ኦሮሞና ትግሬ ማህበረሰብ ላይ ያተኮሩ መሆናቸው የተጠቀሰ ሲሆን ከ843ቱ መልዕክቶች መካከል 485 (57.53%) ያህሉ ዒላማ ያደረጉት የአማራ ማህበረሰብን ነው ተብሏል።
240 (28.47%) የሚሆኑት የኦሮሞ ማህበረሰብን እንዲሁም 118 (14%) ያህሉ ደግሞ የትግራይ ማህበረሰቡ ላይ ያነጣጠሩ ናቸው ተብሏል።
በአጠቃላይ ከተሰበሰበው መረጃ ውስጥ 510 (60.5%) ያህል ጸያፍ ንግግርን የያዙ የጥላቻ ንግግሮች ሲሆኑ 211 (25.03%) ደግሞ የኝቀት ንግግሮች እንዲሁም 122 (14.47%) ደግሞ ሰብአዊነትን ዝግ የሚያደርጉ መልዕክቶች ናቸው ተብሏል።
የአማራን ማህበረሰብ ኢላማ ያደረጉት 485 የጥላቻ መልዕክቶች በ274 አካውንቶች የተሰራጨ ሲሆን ከይዘታቸው አንጻር ደግሞ 282 የሚሆኑት የአማራውን ማህበረሰብ አስመልክቶ የሚሰራጩ ጸያፍ መልዕክቶች የያዙ ጥላቻ ንግግሮች ሲሆኑ 134 የሚሆኑት ማህበረሰቡን  የንቀት መልዕክት ያላቸው እንዲሁም 69 የሚሆኑት ደግሞ የማህበረሰቡን ሰብአዊ ክብር ዝቅ የሚያደርጉ መልዕክቶች ናቸው - ይላል የጥናት ውጤቱ።
የኦሮሞ ማህበረሰብን ኢላማ ያደረጉት 242 የጥላቻ ንግግሮች በ103 አካውንቶች የተሰራጩ ሲሆን ከይዘት አንጻር 162 የሚሆኑት የኦሮሞ ማህበረሰብን በተመለከተ ጸያፍ አገላለጽን የያዙ፣ 43 የሚሆኑት ሰብአዊነትን የሚነካ ይዘት ያቸው፣ 37 የሚሆኑት ደግሞ የንቀት ይዘት ላያቸው መልዕክቶች ናቸው ተብሏል።
118 የሚሆኑት የትግሬ ማህበረሰብን ኢላማ ያደረጉ የጥላቻ መልዕክቶች 41 በሚሆኑ አካውንቶች የተሰራጩ ሲሆን ከይዘት አንጻርም 68 የሚሆኑት የትግሬ ማህበረሰብን በተመለከተ ጸያፍ አገላለጾችን የያዙ፣ 40 የሚሆኑት ደግሞ የንቀት መልዕክት እንዲሁም 10 ያህሉ የማህበረሰቡን ሰብአዊ ክብር የሚያንኳስሱ ናቸው ተብሏል።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የማህበረሰቡን መስተጋብር የሚያናጉና የሚያውኩ መልዕክቶች ሆነ ብለው እየተሰራጩ እንደሆነና እነዚህ መልዕክቶችም በማህበረሰቡ ላይ  የሚያደርሰውን ስነልቦናዊ፣ አካላዊ፣ ማህበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳት እየጨመረ እንዲሄድ አድርገውታል ተብሏል።


Read 6642 times