Saturday, 12 March 2022 12:43

“በአፋርና አማራ ክልል በጦርነቱ 759 ንጹሃን ተገድዋል” - ኢሰመኮ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  በአማራና በአፋር ክልል ለ3 ወራት በዘለቀው የህውሃት ሃይሎች የጥቃት እንቅስቃሴ 759 ንጹሃን መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ ምርመራ አከናውኖ ትናንት (አርብ) ይፋ ያደረገው ሪፖርት አመልቷል።
በምርመራ ሪፖርቱ መሰረት፤ በአፋርና በአማራ ክልል በነበረው የህወሃት የ3 ወራት እንቅስቃሴ 346 ንፁሃን ዜጎች በቀጥታ ኢላማ ተደርገው ሲገደሉ፣ 403 ያህሉ ሰዎችን አንደምሽግ በመጠቀም የተገደሉ ናቸው ተብሏል።
ተቋሙ በሁለቱ ክልሎች 50 ቦታዎች ላይ ምርመራውን ያከናወነ ሲሆን በዚህ የምርመራ ወቅት 427 ሚስጥራዊ ቃለ-ምልልሶች፣ 136 የጋራ ስብሰባዎች እንዲሁም 12 የቡድን ስብሰባዎች መደረጋቸውንና የሆስፒታል መረጃዎች መሰባሰባቸውን አስታውቋል።
ኢሰመኮ 153 ገጾች ባዘጋጀው የምርመራ ሪፖርት፤ የተፈጸሙ ግድያዎችን ከነመለያ ቦታቸውና ድርጊቱ ያመለከተ ሲሆን አብዛሃኞቹ ንፁሃን የተገደሉት በህወሃት ሃይሎች በቀጥታ በተተኮሱ መሳሪያዎችና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎች መሆናቸውን፤ ህወሃት በቀጥታ ግድያዎችን በመፈጸሙም ለንጹሃን ሞት ምክንያት መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
ህወሃት ሰዎችን በጅምላ ጎጂ የሆኑ ፈንጂን የመሳሰሉ ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች በመጠቀም ጭምር ጥቃትን መፈጸሙን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ በፌደራል መንግስት ሃይሎች በኩልም ሲቪልዎችንና ተቋማትን ከጉዳት ለመከላከል ተገቢውንና የተሟላ ጥንቃቄ ባለማድረግ ጦርነቱን ማካሄዱ ለብዙ ንጹሃን ህይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት ንብረትና መሰረተ ልማት ውድመት፤ የዜጎች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል ብሏል- ሪፖርቱ።
በመንግስት ሃይሎች ከዳኝነት ውጪ ህወሃትንና ኦነግ ሸኔን ትደግፋላችሁ በሚል  የተፈጸሙ ግድያዎችንም ኢሰመኮ በሪፖርቱ በዝርዝር አስቀምጧል።
የትግራይ ሃይሎች የጅምላና ተናጠል ግድያዎችን ከመፈጸማቸውም ባሻገር በቁጥጥራቸው ስር በገቡ የአፋርና የአማራ ክልል አካባቢዎች ነዋሪዎችን “ገንዘብ አምጡ፣ መረጃ አምጡ፣ የደበቃችሁትን መሳሪያ አውጡ” በሚልና በመሳሰሉት ምክንያቶች በሲቪል ሰዎች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ድብደባ፣ ማዋረድና ማሰቃየት ተግባር መፈጸማቸውም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፤
የትግራይ ሃይሎች ከአፋር ክልል 8 ሰዎችን አስገድደው በመውሰድ መሰወራቸውንና ኋላም ተገድለው መገኘታቸውን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ መጠነ ሰፊ ጭካኔ የተሞላበት የአስገድዶ መድፈር ድርጊትም በተናጠልና በቡድን መፈጸማቸውን የድርጊቱ ሰለባዎችን እማኝነት በማቅረብ በሪፖርቱ አመልክቷል። በዚህም በመቶዎች በሚቆጠሩ ሴቶች ላይ አስገድዶ የመድፈር ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጫለሁ ብሏል- ኢሰመኮ።
ኢሰመኮ ሪፖርቱ፣ በጦርነቱ ወቅት በአፋርና በአማራ ክልል በንብረትና በመሰረተ ልማት ላይ የደረሱ ጉዳቶችንም በዝርዝር ይፋ አድርጓል። በአማራ ክልል 2343 የጤና ተቋማት 1025 ት/ቤቶች ሙሉ ለሙሉ፣ 3082 ደግሞ በከፊል ሲወድሙ፣ በአፋር ክልል ደግሞ 66 የጤና ተቋማት፣ 65 ት/ቤቶች ሙሉ ለሙሉ እንዲሁም 138 ደግሞ በከፊል ወድመዋል- ብሏል-ሪፖርቱ።
የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትና ክልከላን በተመለከተና የተፈናቃዮችንም ሁኔታ ኢሰመኮ በሪፖርቱ በሰፊው ዳሷል።
ተቋሙ ባቀረበው ምክረ ሃሳብም፤ በአስቸኳይ ጦርነቱ እንዲቆም፣ አጥፊዎች ሁሉ በወንጀላቸው እንዲጠየቁና ተበዳዮች ፍትህ እንዲያገኙ ጠይቋል።

Read 10597 times