Saturday, 12 March 2022 12:31

በፈተና የተወጠረው “ብልጽግና”

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

“የብልጽግና ፓርቲ ቀጣይ ፈተናው እራሱ ብልጽግና ነው”
                         
                  በበርካታ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ክፉኛ የተወጠረው የብልጽግና ፓርቲ ቀጣይ ህልውናው ወሳኝ ነው የተባለውን የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ነው። ፓርቲው ትናንት የጀመረውና ዛሬ በሚያጠናቅቀው ጠቅላላ ጉባኤው፤ የፓርቲውን ፕሮግራም ለማጽደቅ፣ አዳዲስ አመራሮችን ለመምረጥና የፓርቲውን የቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርት አዳምጦ ውሳኔ ለማሳለፍ አጀንዳ ይዟል-ተብሏል።
“ከፈተና ወደ ልዕልና” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ባለው የፓርቲው አንደኛ ጠቅላላ ጉባዔ 1600 የፓርቲው አባላት  በድምጽ፣ 400 ደግሞ ያለ ድምጽ እንዲሁም  41 የውጪ አገራት እህት ፓርቲዎች- የአገር ውስጥ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የተለያዩ የማህበረሰቡ ክፍሎች እየተሳተፉበት መሆኑ ታውቋል።
ጉባዔው ፓርቲው የተጋረጠበትን ፈተናና ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ውሳኔዎች ይተላለፉበታል ተብሎ እንደሚጠበቅና በጉባኤው የሚመረጡ አዳዲስ አመራሮች ፓርቲውን ከገባበት የቁልቁለት አዘቅት የሚያወጡበት መልካም  አጋጣሚ ሊሆን እንደሚችል የፖለቲካ ምሁራኑ ይገልጻሉ።
ለአዲስ አድማስ  አስተያየታቸውን የሰጡት ምሁራኑ፤ ፓርቲው ጉባኤውን  ራሱን በአግባቡ በመፈተሽ ከፈተና ለመውጣት የሚችልበትን መንገድ የሚቀይስበት እንደሚሆን ተናግረዋል።
በአንድ የግል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በፖለቲካል ሳይንስ መምህርነት የሚያገለግሉት ዶ/ር ሰለሞን ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ እንዳስረዱት፤ የብልጽግና ፓርቲ ከገባበት የፖለቲካ አጣብቂኝና ፈተናዎች  ለመውጣት ከፍተኛ ስራ ይጠብቀዋል። ፓርቲው ራሱን በአግባቡ ፈትሾና ጉድለቶቹን አስተካክሎ ካልወጣ ግን ያገኘውን የህዝብ ይሁንታ በቀላሉ ያጣዋል ብለዋል።
አገር እያስተዳደረ ያለው የቀድሞው ኢህአዴግ፣ የአሁኑ ብልጽግና ፓርቲ፣ የፓርቲው አድራጊ ፈጣን ከነበረው “የህውሃት” ቢነጠልም ቀድሞ የዘረጋው ስርዓትና በብልጽግና  ውስጥ ተሰግስገው የቀሩት ካድሬዎች ለብልጽግና  ከባድፈተና መጋረጣቸውን ነው ምሁሩ የሚናገሩት።
“ብልጽግና ፓርቲ ራሱን በሚገባ ካላጠራና የአባላቱን ስነልቦና በአግባቡ ካልገነባ በስተቀር ፈተናው  ለብልፅግና ህልውና አደገኛ ነው” ያሉት ዶ/ር ሰለሞን አባላቱ ለውጡን ምን ያህል ተቀብለውታል ራሳቸውን ለመለወጥስ ምን ያህል ተዘጋጅተዋል? የሚሉት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የዶክተር ሰለሞንን ሃሳብ የሚጋሩት የሕግ ባለሙያውና የፖለቲካ ምሁሩ የሆኑት አቶ ኢሳይያስ ታምሩ በበኩላቸው፤ ፓርቲው ራሳቸውን በአግባቡ ባላጠሩ፣ ኢህአዴጋዊ (ህውሃታዊ) አስተሳሰብ በተጠናወታቸው ካድሬዎች የተሞላ መሆኑ ፈተናውን የከፋ ያደርገዋል።” ይላሉ። የብልጽግና አመራሮች የህዝብን መሰረታዊ ጥያቄ ለመመለስ ዝግጁነት የማይታይባቸውም ራሳቸውን በአግባቡ ያላጣሩ በመሆናቸው ነው ሲሉም እንደ አንድ ማስረጃ ቀርባሉ።
የብልጽግና ካድሬዎች የጠራ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ያላቸው አይደሉም የሚሉት አቶ ኢሳይያስ፤ በየክልሉ ያሉት የብልጽግና ፓርቲ አመራሮችም ራሳቸውን በአግባቡ ሊመለከቱና ውስጣቸውን ሊፈትሹ ይገባል ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ከአመሰራረቱ ጀምሮ ችግሮች እንደ ነበሩ በማስታወስም፤ የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤውን በማካሄድ ፕሮግራሙንና መተዳደሪያ ደንብን ለማጽደቅ  ጊዜ አለማግኘቱን በማሳያነት ይጠቅሳሉ።
የብልጽግና ሌላው ፈተና፣ በአሸባሪ ቡድኖቹ ኦነግ ሸኔና ህውሃት እየተሳበበ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ክልሎች  በንጹሃን ላይ እየተፈፀሙ ያሉት የንፁሃን ግድያዎችና መፈናቅሎች እንደሆኑ ምሁሩ ያስረዳሉ። ይህን ከባድ ፈተና በዘላቂነት  ለመወጣትም በራሱ በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ለኦነግ ሸኔ ድጋፍ የሚያደርጉ አመራሮች መኖር አለመኖራቸው ሊፈትሽ ይገባል ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ራሱን ከኢህአዴጋዊ አስተሳሰብ አላቆና በብልጽግና ስም የሸፈነውን ኢህአዴጋዊ ስነልቦና ገላልጦ ራሱን ማጥራት ካልቻለ ከተጋረጠበት የህልውና አደጋ መውጣት አይችልም የሚል እምነት አለኝ ብለዋል- ምሁሩ።
ፓርቲው ከትናንት ጀምሮ እያካሄደ በሚገኘውና ዛሬ በሚጠናቀቀው ጠቅላላ ጉባኤው፣ ለፓርቲው ፈተና ይሆናሉ ተብለው የሚታሰቡ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት የእርምትና የማስተካከያ እርምጃ ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል።

Read 11099 times