Saturday, 12 March 2022 12:51

በራሽያ ላይ ያጠላው የዓለም ስፖርት ግርዶሽ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  • ከ37 በላይ አገራት በስፖርት አብረን አንሰለፍም ብለዋል
    • ከ30 በላይ ዓለም አቀፍ የስፖርት ማህበራት እግዶችና ማዕቀቦችን ጥለዋል
      • በዓለም ስፖርት በኢንቨስትመንት፤ በተሳትፎ፤ በውጤትና በመስተንግዶ የነበራትን ድርሻ ለመመለስ ይከብዳል


              ከ4 ዓመታት በፊት 21ኛውን የዓለም ዋንጫን በተሳካ ሁኔታ በማስተናገድ ከመላው የስፖርት ዓለም ክብርና ሞገስ የተጎፀፈችው ራሽያ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የዓለም ስፖርት ግርዶሹን ጥሎባታል፡፡ የፑቲን አስተዳደር በዩክሬን ላይ የከፈተው ጦርነት ለግርዶሹ መከሰት ዋንኛው ምክንያት ነው፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የስፖርት ማህበራት እና ተቋማት ራሽያን ከዓለም ስፖርቶች ማናቸውም እንቅስቃሴና ተሳትፎ ላልተወሰ ጊዜ አግደዋታል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበራትን ስፖርታዊ ሃያልነትም አደጋ ውስጥ ገብቷል፡፡ በራሽያና ዩክሬን መካከል ጦርነቱ መፈንዳቱ በኮቪድ 19 የተጎሳቆለው የዓለምን ስፖርት ወደ ፖለቲካው ጎራ እንዲቀላቀል ምክንያት ሆኗል፡፡ በተለይ የአውሮፓና የሰሜን አሜሪካ አገራት በስፖርቱ ያላቸውን ተፅእኖ ፈጣሪነት በመጠቀም በራሽያ ስፖርት ላይ ዘመን የማይሽረው ቀውስ ለመፍጠር ተረባርበዋል። በአውሮፓ እና በአሜሪካ ባለፈው ሰሞን በተካሄዱ ብዙዎቹ የስፖርት ውድድሮች ላይ ራሽያን የሚያወግዙ፤ ከዩክሬን ጎን መቆምን የሚደግፉ ዘመቻዎችን የስፖርቱ ዓለም አስተናግዷል፡፡ በእግር ኳስ ስታድዬሞች እና በሩጫ ውድድሮች ላይ ስፖርተኞችና ደፋፊዎች ጦርነቱን የሚያወግዙ መፈክሮችና የተቃውሞ ተግባራት አሳይተዋል፡፡ ቢጫና ሰማያዊ ቀለማት ያሉበት የዩክሬን ባንዲራም በጀርመንና እንግሊዝ ስታድዬሞች ተውለብልቧል፡፡
የዓለም ስፖርት እገዳዎች፤ ማዕቀቦችና ሌሎችም
የቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር በዩክሬን ላይ ወረራውን ከፈፀመ በኋላ  የዓለም ስፖርትን የሚያስተዳድሩ ማህበራትና ተቋማት አስተዳደሮች ከየአቅጣጫው የተለያዩ እግዶችና ማዕቀቦችን በራሽያ ላይ መጣል  ጀምረዋል። በስፖርቱ ታሪክ ታይተው እና ተሰምተው የማይታወቁ እርምጃዎችም መሰማታቸው ቀጥሏል ፡፡  በዓለም ስፖርት ኢንዱስትሪ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ያላቸው ከ37 በላይ አገራት ከራሽያ ጋር በአንድ የስፖርት መድረክ አንሰለፍም የሚል አቋማቸውን በማራመድ ተባብረዋል፡፡ ከ30 በላይ ዓለም አቀፍ የስፖርት ማህበራት እግዶችና ማዕቀቦችን ከመጣላቸው ባሻገር የራሽያ እና የቤለሩስ ስፖርተኞች በየውድድሮቻቸው እንዳይሳተፉ ከልክለዋል፡፡ በራሽያ ላይ የዓለም ስፖርት ግርዶሹን እንዲጥል ዋንኛው መነሻ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ራሽያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ የኦሎምፒክን  ዓለም አቀፍ ስምምነት ጥሳለች የሚል መግለጫ ማውጣቱ ነው፡፡ ይህኑ ተከትሎም የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እና የዓለም እግር ኳስ ማህበር አስደናጋጮቹን ርምጃዎች መወሰን ጀምረዋል፡፡
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር UEFA በአህጉሪቱ እግር ኳስ ሰፊ ድርሻ ያላትን ራሽያ በይፋ ማውገዝ ከጀመረ በኋላ ከአብይ ስፖንሰሮቹ አንዱ ከሆነው ጋዝፕሮም ጋር የነበረውን ግዙፉን የስፖንሰርሺፕ ስምምነት አፍርሷል፡፡የራሽያው ጋዝፕሮም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመታወቅ ባለፉት 8 ዓመታት ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ጋር በፈፀመው የስፖንሰርሺፕ ውል ከፍተኛ ሚና ተጫውቶለታል፡፡  የብዙ ኮርፖሬሽኖች ጥምረት የሆነው የነዳጅ ሻጭ ኩባንያው ጋዝ ፕሮም ተቀማጭነቱ በሴንትፒተርስበርግ ራሽያ ሲሆን በዓለም ዙርያ ከስፖንሰርሺፕ በተያያዘ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ፈሰስ ያደረገም ነው፡፡ ኩባንያው በዓለም አቀፍ ደረጃ የ2018 ዓለም ዋንጫ እና የ2020 የአውሮፓ ዋንጫዎችን አብይ ስፖንሰር የነበረ ሲሆን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፤ የአውሮፓ ሱፕር ካፕ፤ የአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ፤ የአውሮፓ ሻምፒዮንሺፕ፤ የአውሮፓ ዩዝ ሊግ፤ የአውሮፓ ፉትሳል ሻምፒዮንስሊግ በስፋት ስፖንሰር አድረጎ እየሰራ ቆይቷል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ከራሽያው ጋዝፕሮም ጋር በነበረው ሰፊ የውል ስምምነት በዓመት እስከ 80 ሚሊዮን ዩሮ ገቢ ነበረው፡፡
ጋዝፕሮም ከዩኢኤኤፍኤ ጋር የነበረው የስፖንሰርሺፕ ውል በመፍረሱ ብቻ አይደለም ጉዳት የደረሰበት፡፡ ዋና ስፖንሰር በሆነበት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ  የሻምፒዮንስ ሊግ ላይ የራሽያዋ ሴንት ፒተርስበርግ  የፍፃሜ ጨዋታን እንድታስተናግድ ያገኘችውን እድል ተነጥቃ እድሉ ለፈረንሳይዋ መዲና ፓሪስ ተሰጥቷል። የሻምፒዮንስ ሊጉን ፍፃሜ ያስተናግድ የነበረው የራሽያው ስኬታማ ክለብ ዜኒት ፒተርስበርግ ሜዳ የሆነውና የጋዝፕሮም ስታድዬም ነበር።  የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በጋዝፕሮም ላይ ከወሰደው ርምጃ ባሻገር የራሽያ እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድኖችና ክለቦችን ከአህጉራዊ ውድድሮች ውጭ እንዲሆኑም ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ራሽያ በአውሮፓ እግር ኳስ ላይ ያስመዘገበችው ውጤት ያን ያህል አልነበረም። በተለያዩ አህጉራዊ ውድድሮች ላይ በተሳትፎ፤ በኢንቨስትመንት፤ በስፖንሰርሺፕ እና በሌሎች የስፖርት ኢንዱስትሪው አበይት እንቅስቃሴዎች የሚኖራት ተፅእኖን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጥፋት ግን ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡  ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር  19 ዋና የስራ አመራር ኮሚቴዎች 17ቱ በሞስኮ ድጎማ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውም ለዚህ አንዱ ማስረጃ ነው፡፡
የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦችም ከራሽያ ኩባንያዎችና ሌሎች ግንኙነቶች  ለመላቀቅ የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰዱ ናቸው። በእንግሊዙ ክለብ ቼልሲ ባለቤትነት ለ20 ዓመታት የቆዩት ሮማን አብራሞቪች ጦርነቱ እንደፈነዳ ክለባቸውን በይፋ ለሽያጭ ማቅረባቸውን አስታውቀዋል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ የእንግሊዝ መንግስት በወቅቱ የገበያ ዋጋ ከ1.16 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ እንዳለው የሚገመተውን ቼልሲ መሸጥ የማይችሉበትና ከማናቸው የገቢ እንቅስቃሴ የሚያርቃቸውን ገደቦችን በመጣል ባለሃብቱን ከጨዋታ ውጭ እንዳደረጋቸው እየተዘገበ ይገኛል፡፡  ማንችስተር ዩናይትድ ከራሽያው የአየር ትራንስፖርት ኩባንያ ኤርፈሎት አየር መንገድ ጋር በዓመት ከ52.6 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያገኝበትን እንዲሁም የጀርመኑ ሻልካ ከራሽያው ጋዝፕሮም ጋር በዓመት ከ11 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚወስድበትን የማልያ ስፖንሰርሺፕ ሙሉ ለሙ ማቋረጣቸውን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል የሚነሳው ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋም በራሽያ ላይ የጣለው ማዕቀብ ሲሆን በዓለም ስፖርት ውስጥ የፈጠረው  ውጥረት ቀላል የሚባል አይደለም። ከ4 ዓመት በፊት 21ኛውን የዓለም ዋንጫ በድምቀት ያስተናገደችው ራሽያ ከዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ውጭ ልትሆን የምትችልበትን ውሳኔ ያስቀመጠው  ፊፋ የራሽያን ክለቦች እና ብሄራዊ ቡድኖች ላልተወሰነ ጊዜ ከዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮች ውጭ አድርጓቸዋል፡፡  የሩስያ ብሄራዊ በድኖች በቀጣይ በሚደረጉ አህጉራዊ እና ዓለምአቀፍ ውድድሮች ላይ አለመሳተፋቸውን ብዙዎች ከፖለቲካ ውሳኔ ስፖርቱ ውስጥ ጣልቃ ገብቷል በሚል እንዲያብጠለጥሉ ምክንያት ሆኗል፡፡ ታላላቅ የዓለም የስፖርት ትጥቅ አምራቾች እና ሌሎች ከስፖርት ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ኩባንያዎችም በራሽያ ያሉ ሱቆቻቸውን ዘግተው እየወጡ ናቸው፡፡ ከራሽያ የስፖርት ቡድኖች ጋር ያላቸውን ትስስር ካቋረጡት መካከል ናይኪ፤ ፑማ እና አዲዳስ የሚገኙበት ሲሆን ለራሽያ ቡድኖችና ስፖርተኞች በዓመት እስከ 30 ሚሊዮን ዩሮ የስፖርት ትጥቆችን ያቀርቡ ነበር፡፡ የራሽያ ብሄራዊ ቡድንን ስፖንሰር ያደረገው የጀርመኑ አዲዳስ ከራሽያ ብሄራዊ ቡድን በ10 ሚሊዮን ዶላር የነበረውን የአጋርነት ውል ያፈረሰ ሲሆን ከራሽያ ግዛቶች ሱቆቹን ዘጋግቶ መልቀቅ ከጀመረ በኋላ  እስከ 275 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ገጥሞታል፡፡
የራሽያ አትሌቶች ከዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች በተለይ ከአትሌቲክስ እና ከኦሎምፒክ ከዶፒንግ ቅሌት ጋር በተያያዘ በተላለፈባቸው ቅጣት ተሳትፏቸው ሳይኖራቸው ቆይቷል። ዓለም አቀፉ የዶፒንግ ኤጀንሲ ዋዳ በ2019 እኤአ ላይ የራሽያን ቡድኖችና ስፖርተኞች ካለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች፤ ከዓለም ዋንጫ እና ከኦሎምፒክ እንዳገዳቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ሁኔታም ራሽያን ከሁለት ኦሎምፒኮች እና ሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች ተሳትፎ አርቋታል፡፡ አሁን በተለያዩ የዓለም ስፖርቶች የተጣሉት እገዳዎችም አገሪቱን እስከ 2025 እ.ኤ.አ ከስፖርቱ ዓለም የሚያገል ነው። ባለፉት 10 ዓመታት ግ ከዶፒንግ ቅሌት ጋር በተያያዘ በብዛት ሜዳልያዎችን ከተነጠቁ አገራት ራሽያን የሚስተካከላት የለም፡፡ የአገሪቱ የኦሎምፒክ እና የአትሌቲክስ ቡድኖች ከ2016 ወዲህ በዓለም ስፖርት ያላቸው ዝና እና ክብር እየቀነሰ መጥቷል፡፡  
ራሽያ በአውሮፓና በዓለም እግር ኳስ፤ በዓለም አትሌቲክስ እና በኦሎፒክ መድረኮች ከነበራት ተሳትፎ ከመባረሯም በላይ ከፍተኛ ተሳትፎና ውጤት ከምታስመዘግብባቸው ሌሎች አለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች ውጭ እየተደረገችም ነው፡፡ ቤጂንግ በቀጣይ ሰሞን የምታስተናግደው የ2022 የክረምት ፓራኦሎምፒክ አንዱ ነው፡፡ የራግቢ፤ የሞተር ስፖርት፤ የብስክሌት፤ የቴክዋንዶ፤ የመረብ ኳስ፤ የውሃ ዋና ፤ ባድሜንተን፤ የቦክስ፤ እና የሌሎች ስፖርቶች ዓለም አቀፍ ማህበራትም ራሽያና ቤለሩስን ከአባልነት መብታቸው በተለያየ መንገድ በማገድና ስፖርተኞቾቻቸውን ከውድድሮቻቸው ተሳትፎ ውጭ ያደረጉባቸውን ውሳኔዎች አስተላልፈዋል፡፡
የራሽያ ስፖርት ከዝና ወደ ታላቅ የኢኮኖሚ ጫና
በመላው ራሽያ የሚገኙ ትልልቅ ስታድዬሞች፤ የስፖርት ማዕከሎችና ዘመናዊ የስፖርት መሰረተልማቶች አገሪቱን በዓለም ግዙፍ የስፖርት መድረኮች አዘጋጅነት  ግንባር ቀደም ተመራጭ አድርገዋት ቆይተዋል፡፡ በ2018 እ.ኤ.አ  ላይ ያስተናገደችው የዓለም ዋንጫ ስኬታማነት በተለይ ባለፉት 6 የውድድር ዘመናት  የዓለም ስፖርቶችን ትኩረት እንድትስብ አስችሏታል፡፡ ከእግር ኳስም በላይ የሌሎች ስፖርቶች የዓለም ሻምፒዮናዎች፤ የክረምትና የበጋ ኦሎምፒኮች፤ ዓለም አቀፍ የዙር ውድድሮች፤ በስፖርቱ የሚካሄዱ ትልልቅ ጉባኤዎችና ኮንፍረንሶችን በማስተናገድ የራሽያ ከተሞች ያለተፎካካሪ አውሮፓንና መላው ዓለምን አገልግለዋል፡፡  ራሽያ በዓለም የስፖርት መድረኮች ላይ ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ የምትጠቀስ ታላቅ አገር ናት። በመላው ራሽያ እጅግ ተወዳጁ ስፖርት እግር ኳስ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ አይስ ሆኪ፤ የእጅ ኳስ፤ አትሌቲክስ፤ ቅርጫት ኳስ ቦክስ… እያለ ደረጃው ይቀጥላል፡፡
ክብደት ማንሳት፤ ነፃ ትግልና ጅምናስቲክም ብዙ ተከታታይ አላቸው። በዓለም የስፖርት መድረክ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ሶቭዬት ህብረት ተብላ በ1952 ኦሎምፒክ ስተሰለፍ በብዙ ስፖርቶች ፍፁም የበላይነት አሳይታለች፡፡ በከፍተኛ የሜዳልያ ስብስቧ ከዓለም ሁሉ አገራት  እስከ አራተኛ ደረጃ ውስጥ የምትገባ  ነበረች፡፡ በዓለም የስፖርት መድረክ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ሶቭዬት ህብረት ተብላ በ1952 ኦሎምፒክ ስተሰለፍ በብዙ ስፖርቶች ፍፁም የበላይነት አሳይታለች፡፡ በከፍተኛ የሜዳልያ ስብስቧ ከዓለም ሁሉ አገራት  እስከ አራተኛ ደረጃ ውስጥ የምትገባ  ነበረች፡፡ ከሶቪዬት ህብረት በኋላ ራሽያ በሚል ስያሜ  በዓለም መድረክ ስትወዳደርም ያስመዘገበችው የሜዳልያ ስብስብ በስፖርቱ ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት ካስመዘገቡት ያሰልፋታል፡፡በኦሎምፒክ መድረክ 547 ሜዳልያዎች (196 ወርቅ ፤ 165 ብርና 186 ነሐስ)  በመሰብሰብ ከዓለም 9ኛ ደረጃ እንዲሁም በዓለም አትሌቲስ ሻምፒዮና ላይ 153 ሜዳልያዎች (54 ወርቅ ፤ 47  ብርና 52 ነሐስ) በመውሰድ 3ኛ ደረጃ አላት፡፡
በመላው ራሽያ እጅግ ተወዳጁ ስፖርት እግር ኳስ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ አይስ ሆኪ፤ የእጅ ኳስ፤ አትሌቲክስ፤ ቅርጫት ኳስ ቦክስ… እያለ ደረጃው ይቀጥላል፡፡ ክብደት ማንሳት፤ ነፃ ትግልና ጅምናስቲክም ብዙ ተከታታይ አላቸው። ራሽያ ዩክሬንን ከመውረሯ ጋር ተያይዞ በዓለም ስፖርቶች  የተጣሉ እገዳዎችና ማዕቀቦች በአገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድሩት ጫና ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ብሄራዊ ቡድኑን ከዓለም ዋንጫ ለመሰረዝ የሚያንደረድር እግድ መጣሉ፤ የራሽያ ስፖርተኞች ከዓለም ሻምፒዮና እና ከአትሌቲክስ እየራቁ መምጣታቸው ከፍተኛ ኪሳራ ሊያስከትል እንደሚችል ተገምቷል። በተለያዩ የስፖርት ማህበራት የተጣሉት እገዳዎች የራሽያ የስፖርት ኢንዱስትሪ ገቢን መቀነሳቸው ብቻ ሳይሆን በየስፖርቶቹ እድገት ላይም ጉዳት የሚያደርስ ይሆናል። ከእገዳው በኋላ ወደተለያዩ የዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች  በተፎካካሪነት ለመቅረብ ፈታኝ ሊሆንባት እንደሚችልም ተሰግቷል። የራሽያ ምርጥ ስፖርተኞች አገራቸውን በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ ለማስጠራት እና ህዝቦቻቸውን በስኬት ለማነቃቃት የሚችሉበትን እድል ያጡታል፡፡
ራሽያ በ2014 እኤአ ላይ ለክረምት ኦሎምፒክ ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንዲሁም በ2018 እኤአ ላይ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ከ14.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ በማድረግ የዓለም የስፖርት ኢንዱስትሪን በገቢ አነቃቅታለች፡፡ ሁለቱ ግዙፍ የስፖርት መድረኮች  53 ሚሊዮን ዶላር እና 5.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢን እንደቅደምተከተላቸው ለራሽያ ኢኮኖሚ ገቢ አድርገዋል፡፡ በቀጣይ አምስት አመታት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን አለማስተናገድ ይህን የመሰሉ የገቢ እድሎች ማጣት ነው፡፡ በራሽያ የስፖርት ኢንዱስትሪ ላይ በዓመት ውስጥ ከ180 ሚሊየን ዩሮ በላይ ወጭ ሆኖ የሚንቀሳቀስ ሲሆን፤ በተለያዩ የንግድና የስፖንሰርሺፕ ውሎች ከ618 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ኮንትራቶች ተፈርመዋል፡፡ የራሽያ ኩባንያዎች እና ብራንዶቻቸው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በ1 የውድድር ዘመን ከ419 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሚያወጡ ውሎች ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን ከዚህ በጀት ውስጥ ከ132.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለእግር ኳስ የዋለው ነው። አገሪቱ በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች ተሳትፎ ማጣቷም በአገር ውስጥ የሚካሄደውን የህን የሞቀ የስፖርት ኢንዱስትሪ ሊያቀዘቅዘው ይችላል፡፡ የራሽያ ስፖርት ሚኒስትር፤ የእግር ኳስና የሌሎች ስፖርቶች ፌደሬሽኖች ሌሎች አገር አቀፍ የስፖርት ተቋማት በዓለም ስፖርት በወረደባቸው የቅጣት ናዳ ላይ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እና ፊፋ ባሳለፉት የእግድ ውሳኔ ላይ ራሽያ ለዓለም አቀፉ የስፖርት ክርክሮች ገላጋይ ፍርድ ቤት CAS ክስ እንደምታቀርብ ታውቋል፡፡
ፑቲን በተከበሩበት ስፖርት ደግሞ መዋረዳቸው
ፑቲንና የሩስያ ቢሊየነሮች በእግር ኳስ አፍቃሪነታቸው ዓለም ያውቃቸዋል፡፡ ከ22 ዓመት በፊት ፑቲን ወደ ክሬምሊን ሲገቡ መጀመርያ ወደ ቤተመንግስቱ የጋበዙት የጁዶ አሰልጣኛውን ነበር፡፡ የራሽያው መሪ ለዋና፤ ለፈረስ ግልቢያ ፍቅር ያላቸው፤ ሆኪ በጣም የሚወዱ እና ሌሎች ስፖርቶችን በማስተዋወቅ የሚታወቁ እና በአሳ አጥማጅነት ዓለም የሚያውቃቸው ናቸው፡፡ ፑቲን ስፖርቱን በመደገፍ ካላቸው ዝንባሌ ጋር የፖለቲካ መሳርያቸውም አድርገውታል፡፡ ላለፉት አምስት አመታት ከዓለም የአትሌቲክስ የውድድር መድረኮች ራሽያን ያገለለላት የዶፒንግ ችግር በመንግስት እንደተቀነባበረ መጠቀሱ ይህን ነው የሚያመለክተው ፡፡ ከዚያም ውጭ የፑቲን አስተዳደር የአገሪቱን ቱጃሮች፤ፖለቲከኞች የቀድሞ ስፖርተኞች በቅርበት በመያዝ በስፖርቱ ተፅእኖ እንዲፈጥሩ ሰርተዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም ራሽያውያንና ኩባንያዎቻቸው ዓለምአቀፍ የስፖርት መድረኮችን በማዘጋጀት፤ በስፖንሰርሺፕ እና በአመራር ድጋፍ ሰጭነት የሚታወቁ ሊሆኑም በቀትዋል፡፡የራሽያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማት እና ማህበራት የተበረከተላቸውን የክብር ሽልማቶችና የስፖርት ማዕረጎቻቸውንም ተነጥቀዋል፡፡ የስፖርት ሽልማቶችና የክብር ማዕረጎችን በተለያዩ ግዜያት ሲቀበሉ የነበረው አገራቸው በስፖርት ውድድሮች መስተንግዶ፤ የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ እና አስተዳደራዊ ስራዎች ያደረጓቸው አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ ገብቶ ነው፡፡  ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በኦሎምፒክ እንቅስቃሴ ከፍተኛ የክብር ማዕረግ የሆነውን የኦሎምፒክ ኦርደር መንጠቁ የመጀመርያው ርምጃ ነው፡፡በቀጣይ የዓለም አቀፉ ጁዶ ፌደሬሽን ጥቁር ቀበቶ የሰጣቸውን የስፖርቱ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉትንና ስለጁዶ ስፖርት መፅሃፍ የደረሱትን  የክብር ፕሬዝዳንቱን ከሰጣቸው ማዕረግ አንስቷቸዋል፡፡ የዓለም የውሃ ዋና ፌደሬሽን ልዩ የክብር ሽልማታቸውን የገፈፈ ሲሆን፤ የዓለም ቴክዋንዶ የሰጣቸውን የብር ጥቁር ቀበቶ ነጥቋቸዋል፡፡

Read 1001 times