Saturday, 12 March 2022 14:11

“የፍርድ ቤት ዕግድ ተጥሶ የተፈፀመብን በደል በአገራችን ተስፋ አስቆርጦናል

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

    ሲፈርስ ለ6 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ተዳርገናል (ጆርካ ኢቨንት ኦርጋናይዘር)
                         
            የፍርድ ቤት እግድ ጥሶ ቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 5 ያፈረሰብን ግንባታ ለ6 ሚ ብር ኪሳራ ዳርጎናል ሲል ጆርካ ኢቨንትስ  አስታወቀ፡፡ የድርጅቱ ሀላፊዎች ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ድርጅታቸው በ2011 ዓ.ም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ተፋሰስና አረንጓዴ አካባቢዎች ፅ/ቤት ጋር  በተለምዶ ገነት ሆቴል ወረድ ብሎ የሚገኘውን 720 ካሬ ሜትር ቦታ ለማልማት  በ21/10/2011 ዓ.ም ውል መፈራረሙን ያስታውሳል። ውሉ በተፈፀመ በጥቂት ቀናት ልዩነትም (ሀምሌ 2 ቀን 2011 ዓ.ም) ፅ/ቤቱ ለጆርካ ኢቨንትስ በፃፈው ደብዳቤ በውላቸው መሰረት፣ ቶሎ ወደ ግንባታ እንዲገቡ ያሳሰበ ሲሆን ይህንኑ ማሳሰቢያ ተከትሎ ከፅ/ቤቱ በተሰጣቸው ካርታና ፕላን መሰረት በ6 ወራት ውስጥ ግንባታ ማጠናቀቃቸውን ይገልጻሉ ሃላፊዎቹ፡፡
ይህ የህጻናት መጫወቻ፣ የማንበቢያ ቦታ፣ የኢንፎርሜሽ ዴስክ፣ የሰርግና የልደት አገልግሎት፣ የፎቶግራፍ ፕሮግራሞች የሻይ ቡና መዝናኛ፣ከመናፈሻ ውጪ የተለያዩ ግብዣዎች፣የምግብ አቅርቦት መስጠት፣የሰራተኛ ማነቃቂያ መርሃ ግብር፣ኤግዚቢሽንና፣ የዋይፋይ አገልግሎትና እንዲሁም የህዝብ መናፈሻ አገልግሎቶችን እንዲያሟላ የታቀደውና በአልሚው ድርጅት ዲዛይን እንዲሰራ በውል ስምምነቱ ላይ የሰፈረ ስፍራ ያለምንም ምክንያት በቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ አምስት ፅ/ቤት እንዲፈርስ መደረጉን የጆርካ ኢቨንተስ ኦርጋናይዘር ምክትል ስራ አስኪጁ አቶ ታደሰ ታምራት ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
“እኛ ህጋዊ መንገድ ተከትለን በተሰጠን ካርታና ፕላን እንዲሁም በስምምነታችን መሰረት መንግስትን አምነን፣ ጊዜና ገንዘባችንን አፍስሰን ገንብተን ወደ ስራ ለመግባት ስንዘጋጅ ነው፤ ግብረ ሀይል ልከው ያስፈረሱት” ያሉት ም/ስራ አስኪያጅ፤ ምንም ጥፋት ሳይኖርብንና ምክንያቱን ሳናውቀው፣እቃ እንድናወጣ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠን፣ ደክመን የገነባነው ግንባታ መፍረሱ  አሳዝኖናል ብለዋል፡፡
አቶ ታደሰ አክለውም፤ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደነው በክርክር ላይ እያለን ከአንድም ሁለት የፍርድ ቤት እግድ አውጥተን እግዱን በመጣስ ግንባታውን ማፍረሳቸው ለአገሪቱ ህግ የማይገዙ መሆናቸውን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
በግቢው ውስጥ ስራ ለመጀመር ያስገባናቸውን እቃዎች ጨምሮ በርካታ ንብረቶች ተዘርፈውብናል ያሉት አቶ ታምራት፤ በዚህም እስካሁን ለ6 ሚ ብር ኪሳራ መዳረጋቸውንና የሚመለከተው አካል  እንዲፋረዳቸው ጠይቀዋል፡፡ ቦታውን ለማልማት ስንረከብ ተራራ የቆሻሻ ክምር አፅድተን ቦታውን በመደልደል ገንብተን የነበረ ቢሆንም ሆኖም በማን አለብኝነትና በጉልብት መጥተው አፍርሰውብናል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡
በውሉ መሰረት ውል ተቀባዩ ጆርካ ኢቨንትስ፣ የኮንትራት ጊዜውን ሲጨርስ መናፈሻው ውበቱና ፅዳቱ ሳይቀንስ ለመንግስት ያስረክባል የሚል ቢሆንም፣ የወረዳው ባለስልጣናት ግን የውል ጊዜያችንም ሳያልቅና በክርክር ላይ እያለን ቦታውን ከጥቅም ውጪ በማድረግ ንበረታችን  ማዘረፋቸው አሳዝኖናል ብለዋል፡፡” በውሉ ላይ ይፍረስ የሚል ነገር አልተጠቀሰም፤ መፍረሱም ህገ ወጥ ነው” ሲሉ ተናግረዋል የጆርካ ኢቨንትስ አመራሮች፡፡
“ከተሰጠን ውል ውጪ ግንባታ ገንበተዋል በሚል ለተነሳው ክርክር ከክፍል ከተማው በላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አረንጓዴ ልማት ፅ/ቤት መጥቶ አይቶና ለክቶ ከውሉ ውጪ ምንም የገነባነው ነገር እንደሌለ አረጋግጧል” ያሉት አቶ ታደሰ፤ ወረዳው ቶሎ ያፈረሰው ያቀረበው የሀሰት መከራከሪያ ውድቅ እንደሚሆንበትና የራሱን  ጥፋት ለመሸፈን ነው ብለዋል፡፡
በቂርቆስ ክ/ከተማ በቀድሞው ወረዳ 6 በአሁኑ ደግሞ ወረዳ 5 ላይ የሚገኘው ይህ ቦታ በታቀደለት ዲዛይንና ደረጃ መሰረት ተገንብቶ ተጠናቅቆ የነበረ ቢሆንም ስራ ሊጀምር ሲል መፍረሱ ለእኛም ሆነ ለሀገር ኪሳራ ነው ያሉት ም/ስራ አስኪያጁ፤ ሲሚንቶን ጨምሮ በርካታ የግንባታ ቁሳቁሶች  በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተገዝቶ የተገነባው ልማት ሲፈርስ የአገርን ኢኮኖሚም ይጎዳል ብለዋል፡፡ በሀገራችን በወጣትነታችን ተደራጅተን በመስራትና ለሌሎችም የስራ እድል እየፈጠርን ቢሆንም፣ መብታችንን ተነጥቀን፤ ንብረታችን ጊዜያችንና ጉልበታችንን ሁሉ ባክኖ ለሁለንተናዊ ኪሳራ በመዳረጋችን የሚመለከተው የመንግስት አካል ጣልቃ በመግባት  አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጠን እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
በቂርቆስ ክ/ከተማ የወረዳ 5 አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ወይዘሮ ዘይዳ ዲኖ በጉዳዩ ዙሪያ ጠይቀናቸው ሲመልሱ በመጀመሪያም ውሉ ከመሰረቱ ችግር ያለበት በመሆኑ ይህን የተዋዋሉ አመራሮቻች ላይ እርምጃ ወስደናል፣ ከስራ እስከማገድ ቀጥሎም በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ እየሰራን ነው ያሉ ቢሆንም ውሉ ላይ አለ ስላሉት ስህተት ግን ያብራሩት ነገር የለም።
አመራሮቻችሁ አጠፉ ከተባለ እነሱን መቅጣት እንጂ ውል ተቀባዮቹ ምን አጠፉ በሚል ላነሳነው ጥያቄም ጆርካ ኢቨንቶች ለአረንጓዴ ልማት የተፈቀደን ቦታ ላልታቀደ ግንባታ አውለዋል የሚል ምላሽ ቢሰጡም ጆርካ ኢቨንትስ ባደረገው ውል ላይ 60 በመቶ የአረንጓዴ ቦታ 40 በመቶው ግንባታ ሆኖ እንዲለማ ውሉ ላይ ሰፍሯል። ከአንድም ሁለት ጊዜ ባለንብረቶቹ ግንባታቸው እንዳይፈርስ ከፍርድ ቤት እግድ አውጥተው ሲያበቁ እንዴት የፍርድ ቤት እግድ አታከብሩም በሚል ለወረዳ 5 ስራ አስፈጻሚዋ ላነሳነው ጥያቄም “እኛ ህገ-ወጥነቱን አረጋግጠን የካቲት 18 ቀን ካፈረንሰን በኋላ እግዱ የመጣው ከየካቲት 25 ቀን በኋላ ነው  የሚል ምላሽ
ሰጥተዋል። ግንባታው ህገ-ወጥ ነው ካላችሁ ከጅምሩ ማስቆም ስትችሉ እንዴት የሀገር ሀብት ታፈርሳላችሁ ብለናቸው ሲመልሱም በዚህ በኩል የእኛም ስህተት አለ ለዚህ ነው። አመራሮቹ ላይ እርምጃ የወሰድነው በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

Read 439 times