Saturday, 12 March 2022 14:17

“ብልፅግናዎች የሌብነቱን ሁኔታ እናጠራለን ካሉ ፓርቲው ይፈርሳል”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

                - (ኢ/ር ዘለቀ ረዲ፤ ፖለቲከኛ)              በዚህ ጉባኤ “ብልጽግና የሚባለው ፓርቲ ይፈርሳል፤ አይስማሙም” ብለው የሚናገሩና ይህንንም የሚጠብቁ ሰዎች አጋጥመውኛል። በእኔ እምነት፤ ሀገር የሚመራ ፓርቲ ሲፈርስ፣ የአንድ ቤት  ምሰሶ ሲወድቅ ቤቱ ሁሉ እንደሚወድቀው አይነት ችግር ነው የሚገጥመን ብዬ ነው የማስበው። አደገኛ ነገር ነው። በዚያ ላይ “ውስጣችንን እናጠራለን” እያሉ እየፎከሩ ነው፡፡ “ሌቦችን እንቀንሳለን” የሚልም ድንፋታ ነበር። ይህን ክፍል የሚነካኩት ከሆነ ሌባ እናጠራለን ብለው እስከ ሥር ከነካኩ ግን ፓርቲው ይፈርሳል የሚል ስጋት አለኝ።
ለምን ከተባለ አብዛኛው ሰው ከዚሁ ከሌብነቱ ጋር የተነካካና በዚሁ የታጠረ ነው። አብዛኛው አመራርም የመጣው ከድሮው ኢህአዴግ ስለሆነ አመለካከቱም የዚያው የበፊቱ ነው። ከላይ ያለውን እናጠራለን ብለው ቢነሱም፤ ከስር ያለው በቀልቱም ሌባ ነው። ከዚህ አንጻር  የሌብነቱ ሴራ በደንብ ከተነካካ በብልጽግና ላይ አደጋ ይመጣል የሚል ስጋት አለኝ። ምክንያቱም አሁንም አገሪቱ እንዳትረጋጋ ያደረጓት ሌቦቹ ናቸው። አገር ከተረጋጋች የሌብነቱ ነገር ተስፋ አስቆራጭ ይሆንባቸዋል። የሰረቁትንም መብላት አይችሉም። ስለዚህ አገሪቱ እንዳትረጋጋ አጥብቀው ይሰራሉ። በሌላ በኩል፤ ሌቦቹን እናስወጣለን ካሉ፣ ማንን አስወጥተው ማንን ሊያስቀሩ ነው? በአንጻራዊነት አንዱ ሌባ ከአንዱ የከፋ  ነው እያሉ ካልቀነሱ በስተቀር ማለቴ ነው።
ከስብሰባው ሹምሽር  ትጠብቃለህ ወይ ላልሽኝ… አዎ እጠብቃለሁ። ወጣም ወረደ አብዛኞቹ 27 እና 30 ዓመት ከዛም  በላይ የሰሩ ናቸው። በአዳዲስ የመተካት ፍላጎት ሊኖራቸው ይገባል። በሀገራችን አንድ ባለስልጣን እስኪሞት ድረስ ስልጣን ላይ እንዲቆይ እንፈልጋለን። ይሄ አግባብ አይደለም። የሚነሱበት መንገድ ግን በሌብነት ወይም፣ በሙስና ነው ከተባለ ግን ችግር ይገጥማቸዋል። ነገር ግን አንድ ሰው ደክሞታል ይቀየር  ካሉ ደግሞ የሚቃወም ብዙ ሰው ስለማይኖር፣ በዚህ መልኩ ሊሆን ይችላል። እርግጥ ከውስጡ የማይሰርቁ ሰዎችም አሉ ጥቂት ይሆናሉ እንጂ። አሁን ፕ/ር ብርሃኑ ነጋን በሌብነት ስሙን ልትጠሪ አትችይም። ለም ብትይ… የራሱ ሀብት ያለው ሰው ነው። በዚህ ላይ ትምህርት ሚኒስቴር ላይ እየሰራ ያለውም ሪፎርም ቀላል የሚባል አይደለም። የማይሰርቁ ሰዎች በውጪ ሊኖሩት ይችላሉ። ከላይ ከላይ ያለውን ቀስ በቀስ ከሌብነት ካጸዳው፣ ከላይ ያለው ደግሞ ከስሩ ያለውን እያጸዳ የተሻሉትን ሰዎች እያስቀመጠ ይቀጥላል። ነገር ግን እርግጠኛ ነኝ አሁን በሌብነት ከተባለ ማን ሄዶ ማን ይቀራል። ምናልባት በስራ የተሻሉ ሰዎችን ወደ ላይ ሊያመጣ ይችላል። አሁን በብልጽግና ውስጥ ማን ነው የተሻለ  ብለሽ ስታስቢ፣ ሰዎች ጠፍተው አይደለም። ነገር ግን ደህና ያልሻቸውን ወስደሽ እዚህ ቦታ ላይ ስታስቀምጫቸው ነው ሌብነቱን የሚጀምሩት። የቀድሞው የሌብነት ሲስተም ስላልተበጠሰ ሲስተሙ ደህና ያልሻቸውንም ሰዎች ይውጣቸዋል።
በዋናነት ምን ምን ጉዳዮች በአጀንዳነት ይነሳሉ ለተባለው፣ በርካታ ጉዳዮች ሊነሱ ይችላሉ። ለምሳሌ ዛሬ ተነጋግረው የሚፈቱት ባይሆንም፣ በሌላ በኩል የኑሮ ውድነቱ ዓለማቀፋዊነትን እየተላበሰ ቢሆንም የኑሮ ውድነቱ ይነሳል የሚል እምነት አለኝ። ቢያንስ በኑሮ ውድነቱ ላይ ሲነጋገሩ ህገ-ወጥ  ነጋዴዎችን የሚቆጣጠሩበትን ጉዳይ ያመቻቻሉ የሚል እምነት አለን፡- እሱን ካዘጋጁ
ቢያንስ ነጋዴው እጁን ከዘረፋ እንዲያነሳ እና እንዲተባበር ማድረግ ይችላል።
ሌላው የሰሜኑ ጦርነት፣ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑም ጉዳይ ይነሳል የሚል እምነትም አለኝ። የሰሜኑ ጦርነት መስመር እየያዘ የመጣ ይመስላል። አሁን ላይ ከትግራይ ህዝቡ እየለቀቀ እየወጣ ነው። እየተሰደደ ነው። ይህንን በሁለት መልኩ እንየው፡፡ አንደኛ ህውሃት ሆን ብሎ አማራ ክልልን ለማጣበብ ያደረገው ተንኮል ሊሆን ይችላል። ሁለተኛ ህዝቡ መሮትና ኑሮ ከብዶት እየተሰደደ ሊሆን ይችላል። በዚህ ሁኔታ ትግራይ ባዶ መሬት ሆነ ማለት ነው። በዚህ ምክንያት ጦርነቱ እየተገባደደ ነው ማለት ይቻላል።
ህዝቡ ትግራይን ከመልቀቅና ከመፈናቀል ቀጥሎ ወደተቃውሞ ይዞራል። ያኔ ወያኔ ለማን እታገላለሁ ይላል? ይህን ይህን ስታይው፣ ጦርነቱ እያለቀ ነው ማለት ነው። በሌላ አነጋገር እነሱም (ብልፅግናዎች) ከዚህ በኋላ “ስራ አለብኝ እንጂ ጦርነት አለብኝ” ማለት አግባብ ስላልሆነ በዚህ ስብሰባቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይህንን ጉዳይ በሽምግልናም ይሁን በሌላ መንገድ ለመፍታት ተነጋግረው ይወስናሉ የሚል ግምት አለኝ።
አገራዊ ውይይቱን (ናሽናል ዲያሎግ) በተመለከተም በቅርቡ የተጀመረ ስለሆነና ወደ ተግባር መገባት ያለበት ስለሆነ በምን መልኩ እናስኪደው ብለው የሚነጋገሩበት ይመስለኛል። በአጠቃላይ በኑሮ ውድነቱ፣ በሰሜኑ ጦርነት፣ በናሽናል ዲያሎጉና በሹም ሽር በኩል በርካታ ነገሮችን እጠብቃለሁ።


Read 1020 times