Print this page
Saturday, 12 March 2022 14:57

እየጋለ የሚቀጠቀጠውን ብረትም፤ ወናፉንም አትሁን! እሳቱን ሁን!

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 በህንዶች አፈ-ታሪክ ውስጥ የሚተርክ አንድ የወፎች ተረት እንዲህ ይላል። ጊዜ ገና ሀ ተብሎ በተቆጠረበትና ፍጥረት መኖር በጀመረበት ወቅት፤ የምድር አእዋፍ ተሰብስበው ንጉሥ የሚሆነን ወፍ እንምረጥ ይባባላሉ።
 ስለዚህ በምርጫ አስፈጻሚነት ገዴ የተባለው ደረቱ ነጭ፣ ጀርባው ጥቁር የሆነ አሞራ ተመደበ። ገዴ ግራ ቀኝ ብሎ ስብሰባውን አመቻችቶ፣ ለንጉሥነት የታጩትን ስም ዝርዝር መዝግቧል። ወፎች ዙሪያ-ገባውን ይታደማሉ።
ይሄ ለንጉሥነት የተመረጠ ወፍ፣ መሪም፣ ገዢም፣ ጠባቂም፣ ጌታም፣ አለቃም ሆኖ የሚያገለግል ይሆናል አሉ። በምድር ላይ ሊያገኙት የቻሉትን ወፍ ሁሉ ወደ ስብሰባው ጠሩ። ሰፊ ክርክር ካደረጉ በኋላ ጉጉት ንጉሥ እንዲሆን ተመረጠ።
“አንተን መሪ አድርገን የመረጥንህ ብልህ በመሆንህና ማሰብ ስለምትችል ነው። ንጉሥ ለመሆን ፈቃደኛ ነህ?” ተብሎ ተጠየቀ።
“አዎን፤ በደስታ ንጉሣችሁ ለመሆን ፈቃደኛ ነኝ!” አለ ጉጉት።
ወፎች ለስርዓተ ንጉሱ የሚያስፈልገውን ዘውድ፣ ካባና በወርቅ የተከፈፈ ዙፋን አዘጋጁ። ስርዓተ -ንጉሡ ሊፈጸም ሲል፣ ድንገት አንድ ቁራ በሰማይ እያንዣበበ ሲያልፍ ተመለከቱ። ይሄኔ ስነ-ስርዓቱን አቁመው እርስ በርስ ተንሾካሾኩ።
“ቁራን ወደ ስብሰባው አለመጥራታችን በጣም ትልቅ  ስህተት ነው። ለእርሱም ንጉሡን የመምረጥ ዕድል  ሊሰጠው ይገባ ነበር። ምን እንደሚያስብ መጠየቅ ነበረበት። አሁን እንጠይቀው በቃ” ተባባሉ።
አንደኛው ሰው ወደ ቁራው ዞሮ፤ “ጉጉትን ንጉሥ አድርገን መምረጣችንን እንዴት ታየዋለህ?” ሲል ጠየቀው።
ቁራም፤ “በጭራሽ አልቀበለውም!” አለ።
“ለምን?” አሉት።
ሁ ለምን መሰላችሁ… እስቲ ልጠይቃችሁ? ዳክዬ ወይም ዝዬ፣ ወይም ጣውስ አሊያም ኩኩ- መለኮቴ፣ ወይም እርግብ ወይም በቀቀን፣ አሊያም ማናቸውም የወፍ-ዘር፤ ለምን ንጉሥ አልሆነም? ለምን ጉጉት ተመረጠ?”
“መቼም” አሉ ወፎቹ፤ “መቼም እንደምታውቀው…” ቁራው ቶሎ ስላልነገሩት ትዕግሥቱ አልቆ አቋረጣቸው።
“እስቲ ዝም ብላችሁ ጉጉቱን ተመልከቱት። በጣም አስቀያሚ ፍጡር ነው። በዛ ላይ አይኑ ጠንጋራ ነው። አፍንጫው ጠማማ ነው። በዛ ላይ ቁጡና አኩራፊ ነው። እስቲ አስቡት--- በዛሬው በንግሥናው ቀን ይህን ከመሰለ፣ መቼ ነው ደስተኛ መልክ የኖረው? በዚህ ዓይት ሲናደድ ምን ሊመስል ነው? ይህን የመሰለ ንጉሥ እንዴት ገዢያችን ይሁን ትላላችሁ?
“እንግዲህ ያለ ፉንጋ ፍጡር፣ በጭራሽ ንጉሥ አይሆንም- አይገባምም!”
ወፎቹ የቁራውን ንግግር ካዳመጡ በኋላ፣ ምናልባት ውሳኔአችን ስህተት ሳይሆን አልቀረም፣ መባባል ጀመሩ። ሲያመናቱ ቆዩና በቀያችንስ በዓሉ ዛሬ አይደረግም ተባባሉ!” ሌላ ቀን ሌላ ስብሰባ አድርገን እንመርጣለን” አሉ። ስብሰባው ተበተነ።
ከቁራው በስተቀር ሁሉም ወደ ቤታቸው፣ ሁዴ። ያማረው ዙፋን ላይም ጉጉቱ ብቻውን ጉብ አለ!
“ግን ለምን እንዲህ ያለ ክፋት በኔ ላይ ፈጸምክ?” ሲል ጉጉቱ ቁራውን ጠየቀው።
“እንደዛ ያለ እኩይ ንግግር አድርገህ ስርዓተ- ንግሴ ውስጥ ጣልቃ ገባህ! ምን አድርጌህ ነው? ያንን ንግግርህን እስከ ዕድሜ ልኬም አልረሳውም! ካሁኗ ደቂቃ በኋላም አላናግርህም! ከእንግዲህ እኔና አንተ እሳትና ጭድ ነን።”
“ጉጉት ሆይ! በጭራሽ አንተን ለመጉዳት ብዬ አልተናገርኩትም። ላበሳጭህም ፈጽሞ ፍላጎቴ አልነበረኝም።  እንድንለያይም አልሻም።” ጉጉቱ ግን ይህን የሚያዳምጥበት ጊዜ አልነበረውም። ዱሮ አየሩን ሰንጥቆ በሮ ሄዷል።
ቁራ በፀፀት ስረት ተዋጠ። “በጣም አጥፍቻለሁ። ምን የመሰለ ወዳጄን በደልኩት። እስቲ ያን ሁሉ ክፉ በቀል ምን ልሁን ብዬ ተናገርኩ? ከሌሎች ጋር ለትንሽ ጥቅም ብሎ መጋጨት ደደብነት ነው! ግፍም ነው። ሳያስቡ መናገር ድቁርና ነው።አሁን ምን ለማድረግ እችላለሁ?” አለ።
ቁራ የፈጸመውን በደል ለማረም ምን  እንደሚያደርግ መላው ጠፍቶት ግራ እንደተጋባ፣ ይኸው እስዛሬ ግራ እንደተጋባ ከቦታ ቦታ ሲንከራተት ይኖራል።
*   *   *
የምንናገረውን አስበን፣ አውርደን- አውጥተን እንናገር። ለማጥቂያ ብለን የሰነዘርነው ዓረፍ ነገር በየት በኩል ቀስቱ ወደኛው እንደሚዞር አናውቀውም- ፈረንጆቹ ራስ- አጥቂ ቀስት (ጣመም አድርገው ሰርተውት ተመልሶ የላከውን ሰው እንዲመታ፣ አውስትራሊያዊ አቦሬጂኖች ያበጁት የቅዝምዝም ዓይነት ነው) (Boomerang-ቡመራንግ ይባላል) እንደ ባፍ ይጠፋል በለፈለፉ፤ እንደ ተንጋለው ቢተፉ፣ ተመልሶ ባፉ፣ ለሰው ያሰቡት በራስ ይደርሳል፤ የምንለው ነው።
ስብሰባዎች በብዛት በተጠሩ ቁጥር ያለሃሳብ የሚናገረው  እየበዛ ይመጣል! አንዳንዱ ድርጅታዊ/ ፓርቲዊ ኃላፊነት ነው በሚል ብቻ ይናገራል፡- ያለመጠበቂያ እንደተተወ ሽጉጥ፣ በተነካካ አጋጣሚ ሁሉ የሚባርቅ ነው! እንዲህ ያለ ፖለቲከኛ ባልጠረጠረና ይሄ ይመጣል ባላለ  ተሰብሳቢ ላይ ቃታ ይስባል። በሀገራችን እንዲህ ያለ የድንገቴ ጉዳይና ሟች ነገረ-ሥራ፣ የቀን-ተቀን ክስተት ሆኗል!
እንደ ዛር አዲስ ቀን እየጠበቀ አረፋ የሚያስደፍቅ ፖለቲካ፣ ምሱ መጠፋፋት ነው! ይህ በየግምገማው፣ በየሴሚናሩ፣ በየምዘና ሸንጎው (Retreat)፣ የሚከሰት ዕውነታ ነው። ቀኑ የደረሰው ከመድረኩ ይሰናበታል! ባለተራ ሰዓቱን ይጠብቃል። ያላደለውን የጎመጀውን ዘውድ አሳይቶ ይነሳዋል። የተጠናና በቀመር የተሰላ ስብሰባ የብልጥ ድል ምንዝር፣ ታጋይ ሳንል ሲቪል፣ የወጣውን ለማውረድ ሳይሆን የወደቅነውን ለማንሳት ተጋግዘን እንደግ! እናስብ፤ እንተሳሰብ፣ እንሰባሰብ!!
በጋለው ላይ ተጥደን አንቃጠል!
እየጋለ የሚቀጠቀጠውን ብረትም፣
 ወናፉንም እንሁን! ወና- አፉንም አንሁን!
ይልቅ እሳቱን እንሁን!!

Read 12461 times
Administrator

Latest from Administrator