Saturday, 12 March 2022 15:05

“እባክህ ዳግመኛ እንዳትነካኝ!”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የታክሲ ሹፌሩ መኪናውን እያሽከረከረ ሳለ ድንገት ከጎኑ የተቀመጠው ተሳፋሪ፣ ትከሻውን መታ መታ ያደርገዋል- ጥያቄ ሊጠይቀው ፈልጎ፡፡ ሹፌሩ  ግን ደንግጦ ይጮሃል፡፡ መኪናውም ከቁጥጥር ውጪ ሆና ከአውቶብስ  ጋር ከመጋጨት ለትንሽ ይተርፋል፤ የእግረኛ መንገድ ላይ ወጥቶ፡፡
ለሰከንድ ያህል በታክሲው ውስጥ ፀጥታ ሰፈነ፡፡ ከዚያም ሹፌሩ፤ “ጌታዬ፤ ዳግመኛ እንደዚህ ያለ ነገር እንዳያደርጉ፤ ገድለውኝ ነበር እኮ!” አለው፡፡
ተሳፋሪውም ይቅርታ ጠየቀውና፤ “በጣም አዝናለሁ፤ ትከሻህን በመንካቴ ብቻ  ያን ያህል ትደነግጣለህ ብዬ አላሰብኩም  ነበር፡፡” ይሉታል፡፡
የታክሲ ሹፌሩም መልሶ፡-
“ጥፋቱ ከእርስዎ አይደለም ጌታዬ፤ ሃቁን ለመናገር ታክሲ ስነዳ ዛሬ የመጀመሪያ ቀኔ ነው፤ ላለፉት 25 ዓመታት የአስክሬን መኪና ሹፌር ነበርኩ፤ እዚያ ደግሞ  ማንም  ትከሻዬን አይነካኝም፡፡” አለው፡፡
* * *
የታደሉ ሽማግሌ  (እንዴት ይደነግጥ?!)
አንድ ታዳጊ በብስክሌት ቀጣሪው እንዲገዛው የላከውን  እንቁላል በቅርጫት ጭኖ በፍጥነት ሲጋልብ  ድንገት ከድንጋይ ጋር ይጋጭና ከእነ ሳይክሉ ይወድቃል፡፡ እንቁላሉም ይሰበራል፡፡ ወዲያው በታዳጊው ዙሪያ ሰዎች ይሰበሰባሉ፡፡ እንደተለመደው ሁሉም ሃሳብና ምክር መለገስ ይጀምራል፡-
“ምነው ተጠንቅቀህ አትነዳም ነበር?!”
“ሰማይ ሰማይ እያየህ ነበር እንዴ የምትነዳው?!” ወዘተ እያለ…
 በዚህ መሃል አንድ ሽማግሌ  ወደ ግርግሩ ይቀላቀሉና የሆነውን ከተመለከቱ በኋላ፤ “ምስኪን! አሁን  ለባለቤቱ ምን መልስ ሊሰጠው ነው?! እሺ እኔ የምችለውን ሁሉ እረዳዋለሁ…” አሉና 10 ዶላር ከኪሳቸው አውጥተው ለታዳጊው ሰጡት፡፡
ከዚያም እንዲህ አሉት፡- “እነዚህ የከበቡህ ሰዎች በሙሉ ጥሩዎች ናቸው፤ ምክር ብቻ ሳይሆን፤ገንዘብም ይለግሱሃል”
 የሽማግሌውን መሄድ ተከትሎም፣ ሁሉም  እንዳቅሙ ከኪሱ ገንዘብ እያወጣ ለታዳጊው ሰጠ፡፡ የተሰበረበትን እንቁላል ብቻ ሳይሆን ሌላ ሁለት ቅርጫት እንቁላል የሚገዛ ገንዘብ በማሰባሰቡም ታዳጊው በደስታ ፈነደቀ፡፡
ከከበቡት ሰዎች መካከል አንደኛው እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “አንተ ታዳጊ፤ ለመሆኑ  እኚያ ሽማግሌ ባይታደጉህ ኖሮ፣ ለባለቤቱ ምን  ትለው ነበር? መቼም  አይለቅህም”
”ታዳጊው ጠያቂውን ቀና ብሎ ተመለከተና፡- “ጌታዬ፤ የሱቅ ባለቤትም  እኮ እሳቸው ናቸው፤” ሲል መለሰለት፡፡
እንዴት ያሉ ብልህ  ሽማግሌ ናቸው!


Read 2912 times