Monday, 14 March 2022 00:00

“መቅረዝ” ሆስፒታል ከ3-6 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ይከፈታል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   በቅርቡ በከፍተኛ የህክምና ባለሙያዎች የተመሰረተው “መቅረዝ የጤና አገልግሎት አክስዮን ማህበር” በጤናው ዘርፍ መጠነ ሰፊ ተግባራትን ለማከናወን በዝግጅት ላይ ነው።  አክስዮን ማህበሩ ምን አላማና ግብ ይዞ ነው የተቋቋመው? ባለቤቶቹ እነማን ናቸው? ምን አይነት የህክምና አገልግሎት ይሰጣል? መቼ አገልግሎት ይጀምራል? የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ከአክስዮን ማህበሩ መስራችና የክሊኒካል ሰርቪስ ቡድን አስተባባሪ ከሆኑት የውስጥ ደዌ ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የልብ ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ናትናኤል ታየ ጋር  የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል።



              “መቅረዝ” የጤና አገልግሎት አክስዮን ማህበር እንዴት ተቋቋመ? ውጥኑ ምንድን ነው?
ሃሳቡ የተጠነሰሰው የዛሬ 3 ዓመት ተኩል አካባቢ ነው። ለዚህ መነሻ በርካታ ምክንያቶች ነበሩን። በወቅቱ የተሰባሰብነው 11 የጤና ባለሙያዎች ነበርን።  የተለያዩ ስትራቴጂካዊ ጥናቶች ላይ ተሳትፈን ባገኘነው መረጃ መሰረት፣ በጤና ዘርፉ ላይ ሰፊ ክፍተት እንዳለ የበለጠ ተገነዘብን። ይህን ክፍተት እንዴት ማቃለል ይቻላል? እኛ ምን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን? በምን መልኩ ዘርፉን ማገዝ እንችላለን? የሚለውን ስናስብ፣ መቅረዝን ለማቋቋም ሰፊ ምክንያት አገኘን። አንደኛው፣ የተለያዩ አሃዛዊ መረጃዎችን ስንመረምር ከአለማቀፍ የጤና አቅርቦት መመዘኛዎች ጋር ሰፊ ልዩነት መኖሩን ተገነዘብን። ለምሳሌ በወቅቱ  (2018 እ.ኤ.አ) በወጣ አንድ ጥናት ላይ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ያለው ሽፋን 55 በመቶ ብቻ ነው። በተሻሻሉ የጤና ሽፋኖች ደግሞ ያለው እጅግ በጣም አናሳ ሆኖ እናገኘዋለን። ሌላው ደግሞ የሆስፒታል አልጋዎች ብዛት ነው።  የአለም ጤና ድርጅት ከሚያስቀምጠው ዝቅተኛ የአቅርቦት መጠን ጋር እንኳ በእጅጉ ይራራቃሉ። የአለም የጤና ድርጅት ዝቅተኛ ሽፋን አድርጎ የሚያስቀምጠው አምስት  አልጋ ለአንድ ሺህ (5 ለ1000) ሰው ነው። ከዚህ አንጻር የኛን ሃገር ስንመለከተው፣ አምስት አልጋ፣ ከሃያ አምስት ሺህ እስከ 50 ሺህ ሰው ነው ምጣኔው። ይህ እንግዲህ አዲስ አበባን ጨምሮ ከተሞች አካባቢ ያለ አሃዛዊ መረጃ ነው። ወደ ገጠር አካባቢ ደግሞ ከዚህም በእጅጉ የባሰበት ነው። ሌላው የጤና ባለሙያዎች ቁጥር ነው። የዓለም የጤና ድርጅት ዝቅተኛ ብሎ የሚያስቀምጠው አንድ ሃኪም ለአንድ ሺህ ሰው ነው። ወደ እኛ  ሃገር ስንመጣ፣ በቅርብ የወጣውን የ2013 የጤና ጥበቃ ሪፖርትን እንኳ ብናየው፣ አንድ ነጥብ አስራ ስምንት (1.18) ዶክተር ለ10 ሺህ ሰው ብሎ ነው የሚያስቀምጠው። ይሄም እጅግ በጣም ሰፊ ልዩነት እንዳለ ያመለክተናል።
ሁለተኛው የሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦት ነው። በዚህ ረገድ እጅግ በጣም ውስን የሆኑ የመድሃኒት አቅራቢ ፋብሪካዎች ናቸው ያሉት። እነሱም ቢሆኑ የመድሃኒቱን ዋና ቅመም ከውጭ እያስገቡ የሚያመርቱ ናቸው። ከዚያ ውጪ ግን ሁሉም መድሃኒትና ሁሉም የህክምና መሳሪያ በሚባል መልኩ ከውጪ የሚገባ ነው። ሶስተኛው ምክንያታችን ብዙ ሰው የተሻለ ወይም የተራቀቀ ህክምና ሲያስፈልገው፣ ከሃገር ወጥቶ ለመሄድ ይገደዳል። በዚህ ረገድ እንደ አህጉር አፍሪካ ላይ ያለውን፣ እንደ ሀገር ደግሞ ኢትዮጵያ ላይ ያለውን ጫና፣ እንደ ግለሰብም በእያዳንዱ ዜጋ ላይ ያለውን ጫና መረመርን።
የ2015 እና የ2016 ጥናት እንደሚያሳየው፣ እንደ አህጉር ከአፍሪካ በአመት ቢያንስ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ወደ ህንድ፣ ታይላንድና  የተለያዩ ሀገሮች ይወጣል። ከኢትዮጵያ ደግሞ በአመት ከ150 ሚሊዮን እስከ 2 መቶ ሚሊዮን ዶላር-በጤና ቱሪዝም ወደ ተጠቀሱት ሃገሮች ይወጣል። በግለሰብ ደረጃ ስንመለከተው ደግሞ አንድ ሰው ከሚያወጣው ሚሊዮን ብሮች ባሻገር የቋንቋ አለመግባባት፣ ህክምናውን በአግባቡ ያለማግኘት፣ የሕክምና ቀጠሮዎችን ተከታትሎ  ለመፈጸም የአቅም ውስንነት ማጋጠምና በዚህም ማቋረጥ፤ አንዳንዶች ደግሞ ለህክምና ሲሉ ያላቸውን ሁሉ ይጨርሱና ጎዳና ላይ እስከ መውጣት ሲደርሱም እንመለከታለን። እነዚህን ሁሉ ችግሮች ስንመለከት አንድ የተደራጀ የሕክምና አገልግሎት ሰጪ ተቋም ማቋቋም እንዳለብን ለመወሰን እንድናመነታ አያደርግም። የጤና አቅርቦት፣ የአልጋ ችግር፣ የባለሙያ እጥረት፣ የተራቀቀ ህክምና ችግሮችን እንቀርፋለን በሚል የተቋቋመ ድርጅት ነው-መቅረዝ የጤና አገልግሎት አ.ማ።
እርስዎ ጥናቶችን አጣቅሰው የዘረዘሯቸውን የጤናው ዘርፍ ክፍተቶችን የመቅረዝ መቋቋም ምን ያህል ይሞላል?
አሁን በምንቋቋምበት ደረጃ ገና ልጅ ነው። ግን ልክ እንደ ልጅ እያደገ ራሱን እያጠናከረና እያሰፋ የሚሄድ ነው። አሁን በተቋቋምንበት ደረጃ የዲያግኖስቲክ አገልግሎት ይጀምራል። ይህ አሁን በአንድ ማዕከል ነው የሚጀምረው። በቀጣይ ግን በየክልል ከተሞች ጭምር ይስፋፋል። ተርሸሪ ሆስፒታሉንም በተመሳሳይ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች  የማስፋፋት ውጥን ነው ያለው። አሁን እንኳ እነዚህን ውስን አገልግሎቶች ስንጀምር፣ በተወሰነ መልኩ ለህክምና ወደ ውጪ የሚደረግን ጉዞን መቀነስ እንችላለን፡፡ የዛሬ 5 እና 10 አመት ግን ለህክምና ወደ ውጪ የሚደረግ ጉዞ መቀነስ ወይም ማስቀረት ብቻ ሳይሆን  ከውጪ ወይም  አጎራባች ሃገራት ለህክምና ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣበትን ሁኔታ የመፍጠር እቅድ ነው ያለን። ተርሸሪ ሆስፒታሉ ሲቋቋም በተሻለ አቅም ወደ ውጪ የሚሄደውን ሃገር ውስጥ እናስቀራለን ብለን እናስባለን። አሁን ስራ በሚጀምረው ጠቅላላ ሆስፒታሉ ግን ውስን የሆኑ አገልግሎቶችን ነው የምንጀምረው። ይሄ ሆስፒታልም በውስን ደረጃም ቢሆን ውጪ የሚካሄድባቸውን ህክናዎች ይጀምራል። ለምሳሌ የኩላሊት ንቅለ ተከላ እንጀምራለን። ከአይን ጋር ተያይዞ ያሉ ህክምናዎችን እንጀምራለን። በቀጣይ ሁሉም የህክምና አይነቶችን በሃገር ውስጥ ለማስቀረት እንችላለን። አሁን ግን በተወሰኑት እንጀምራለን።
በአገራችን ብዙዎች የሚጨነቁበትና ፈታኝ የሆነው የኩላሊት ህመም ነው። ይህን ህክምና መቼ ትጀምራላችሁ?
የኩላሊት ንቅለ ተከላ ጉዳይ የህግና መመሪያ ዝግጅትም ያስፈልገዋል። የሰውነት ህዋስን  ከአንዱ ሰው ወደ ሌላ ማዘዋወር የራሱ ጥንቃቄና የህግ ሂደት ይፈልጋል። የጤና ጥበቃ የሚያወጣው ህግ ላይ ይኖራል። እንደ አለም የሚሰራበት ህግም አለ። ስለዚህ ይህ የሕግና መመሪያ ጉዳይ በጤና ጥበቃ በኩል በደንብ እየተሰራ ነው። ያ ህግ ጸድቆ የግል ሆስፒታሎች መስራት ይችላሉ ብሎ ጤና ጥበቃ በሚፈቅድበት ወቅት ወዲያው አገልግሎቱን እንጀምራለን። ስለዚህ  መቼ እንጀምራለን የሚለውን የሚወስነው የዚህ  መመሪያ ጸድቆ ስራ ላይ የሚውልበት ጊዜ ነው። በኛ በኩል በባለሙያም ሆነ በሌላው በቂ ዝግጅት አለን። በባለሙያ በኩል እንደሚታወቀው በሃገሪቱ ከ5 የማይበልጡ በኩላሊት ንቅለ ተከላ የተካኑ ስፔሻሊስቶች አሉ። እነዚህ ደግሞ ሁሉም በሚባል ደረጃ የመቅረዝ ጤና አገልግሎት አ.ማ ባለአክስዮን ናቸው። የቦርድ ሰብሳቢያችን ሳይቀሩ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ስፔሻሊስት ናቸው።  ኩላሊት ላይ በሚገባ ትኩረት አድርገን እንሰራለን፤ ወገናችንንም በተቻለን አቅም ከዚህ መስተጓጓል ለመታደግ እንሰራለን።
በተለየ ሁኔታ ትኩረት የምታደርጉባቸው ሌሎች የህክምና አገልግሎቶችስ?
በጠቅላላ በሆስፒታላችን የኩላሊት ንቅለ ተከላ፣ የአይን ህክምና የመሳሰሉትን እንሰጣለን ምንድን ናቸው? በቀጣይ በተርሸሪ ሆስፒታሉ ግን ሁሉንም የህክምና አገልግሎት እንሰጣለን። በተለይ የካንሰር ህክምና ላይ ሰፊ ስራ እንሰጣለን። ይህ ህክምና በኛ ሃገር በጣም ውስን የሚባል ነው። ስለዚህ ተርሸሪ ሆስፒታላችን የካንሰር ክትትልና ህክምና ማዕከል ይኖረዋል። ይሄም ቀዶ ጥገናውን፣ የጨረር ህክምናውን ሁሉ ያካተተ ይሆናል። በሰውነት ህዋስ ከአንዱ ወደ አንዱ የሚዘዋወር ህክምናም በኩላሊት ብቻ የተገደበ አይደለም። የጉበት መተካት ህክምና፣ የልብ መቀባት ህክምና ይኖሩታል። በአጠቃላይ ከፍኛ ጥራትን በጠበቀ መልኩ ሁሉንም ህክምዎች ማለትም አንድ ሰው ታይላንድ ወይም ህንድ ሄዶ የሚያገኘውን ህክምና ሁሉ የሚሰጥ ይሆናል።
በአሁን ወቅት እንቅስቃሴያችሁ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አክስዮን ማህበሩ  የመጀመሪያ ስራ ብሎ የያዘውና ለተርሸሪ ሆስፒታሉም እንደ መስፈንጠሪያ ያግዘኛል ብሎ ያመነበትን ጠቅላላ ሆስፒታል ጀምሯል። ጠቅላላ ሆስፒታል አሁን ባለው ሁኔታ ቤቱን በኪራይ ነው የጀመረው። ይሄም የሆነበት ምክንያት እንደሚታወቀው አንድ አክስዮን ተሸጦ ህንጻ ገንብቶ ስራ መጀመር ሲታሰብ፣ የብሩን ዋጋ እየገደለው ይሄዳል። ግንባታው ጊዜ ስለሚወስድ። ስለዚህ ስራውን ህንጻ ተከራይቶ እየሰሩ፣ ጎን ለጎን የተርሸሪ ሆስፒታል መገንቢያ ቦታ መንግስትን ጠይቀናል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ አፋጣኝ ምላሽ ይሰጠናል ብለን እናስባለን። እነሱ በሚሰጡት ቦታ ላይ ሆስፒታሉን እየገነባን፣ ጎን ለጎን አገልግሎቱን እየሰጠን እንሄዳለን ማለት ነው።
አሁን የተከራያችሁበት ህንጻ ላይ ስራ ጀምራችኋል?
ቤቱን ከተከራየን በኋላ የውስጥ አርክቴክቸራል ዲዛይኑ ተሰርቶ አልቋል። አሁን ያንን የውስጥና የውጪ ክፍሉን ለሆስፒታል እንዲመች የማድረግ ስራ የሚሰራ ድርጅትን አወዳድሮ የመዋዋል ስራ በቀናት ውስጥ ይከናወናል። ጎን ለጎን የሕክምና ቁሳቁሶችን ከሚያስመጡ ድርጅቶች ጋር ንግግር ተጀምሯል።
ስለዚህ ከ4 እስከ 6 ወር  ባለው ጊዜ ውስጥ ሆስፒታሉ እንደ ፈጣሪ ፈቃድ እውን ይሆናል ብለን ነው የምናስበው። ቦታውም ባንቢስ አካባቢ፣ እናት ታወር  ፊት ለፊት ያለው የቀድሞ ዮርዳኖስ ሆቴል ነው። ሆቴሉን ነው ወደ ሆስፒታሉ የምንቀይረው።
አገልግሎታችሁን የህብረተሰቡን አቅም ያገናዘበ ከማድረግ አንጻርስ  ምን አስባችኋል?
እንደሚታወቀው የጤና አገልግሎት ብዙዎቹሃገራችን ላይ በጣም ውድ እየሆነ መጥቷል። ከቀን ተቀን ዋጋውም እየጨመረ ነው ያለው። ቁሳቁሶችና የሕክምና ግብአቶች በሃገር ውስጥ የሚመረቱ ባለመሆናቸው  አንድ ምክንያት ነው። ነገር ግን መቅረዝ ሲነሳ ምናልባት ጥራት ላይ እናተኩራለን ስንል፣ ተገልጋዩ ውድ ሊመስለው ይችላል፤ ግን እንደዛ አይሆንም። አሁን አገልግሎት እየሰጡ ካሉ ሆስፒታሎች ዋጋ የማይበልጥ ሆኖ፣ ነገር ግን ጥራቱ እጅግ የተሻለ ማድረግ ነው አላማችን። ጥራታችንን ስንጨምር በምንም መልኩ ዋጋውን በተለየ አንጨምርም። ሁለተኛ ደግሞ መቅረዝ ይዞት የመጣ ሌላ አላማ አለ። ማህበራዊ ሃላፊነትን መወጣት የሚል አላማ አለው። ስለዚህ አቅማቸው የማይፈቅድላቸው ሰዎችን ማገዝብና መርዳት አንዱ ማህበረሰባዊ ግዴታችን ይሆናል። ይሄንንም ለማድረግ ዝግጁ የሆኑ ባለሙያዎች አሉት።
የዚህ አክስዮን ማህበር መስራቾች እነማ ናቸው? ካፒታሉስ ምን ያህል ነው?
11 የጤና ባሙያዎች ናቸው የጀመሩት፤ የዛሬ 1 አመት አካባቢ ደግሞ 102 ባለሙያዎች ተጨምረውበት፣ ወደ አክስዮን ማህበር አሳደጉት። ሃሳቡ ሲጀመር በ11 ቢጀመርም በኋላ ላይ 102 ባለሙያዎች ከእነዚህ ውስጥ 8ቱ የጤና ባሙያዎች፣ ቀሪዎቹ 16 ያህሉ የማናጅመንት ባለሙያዎች በአክስዮን መስራችነት አካቶ እየተንቀሳቀሰ ያለ ተቋም ነው። ካፒታሉን በተመለከተ ባለፈው አመት 1ኛ አስቸኳይ ጉባኤው ላይ በተፈቀደው መሰረት 1 ቢሊዮን ብር ካፒታል ነው ይዞ የሚንቀሳቀሰው። ይህ ለመጀመሪያ ስራዎቹ ነው በቀጣይ ወደፊት ተርሸሪ ሆስፒታል ሲገባ እስከ 10 ቢሊዮን ብር ድረስ የሚያስፈልገው ፕሮጀክት ነው የሚሆነው። እንደሚታወቀው ፕሮጀክቱ በአክሲዮን ሽያጭ ብቻ የሚሆን አይደለም። የባንክ ብድር ይኖራል። አሁን ባለው ሁኔታ የአክስዮን አባላት ቁጥራችን ወደ 2 ሺህ 4 መቶ አካባቢ ደርሷል። ካፒታላችን ወደ 127 ሚሊዮን ብር የተከፈለ፣ ቃል የተገባው ወደ 150 ሚሊዮን ብር አካባቢ ደርሷል። ይህ በ1 አመት ጊዜ ውስጥ የሆነ ነው። አሁን ሆስፒታሉ የሚጀምረውም በዚህ ብርና ጎን ለጎን አክስዮን እያሳደገ፣ ከባንክም  በሚያገኘው ገንዘብ ይሆናል።
ሆስፒታሉ መቼ ነው ወደ ሙሉ አገልግሎት የሚገባው?
የመጀመሪያ ዙር እና ሁለተኛ ዙር ብለን የከፋፈልናቸው ስራዎች አሉ። መቅረዝ የሚሰማራባቸው አጠቃላይ ዘርፎች በሶስት ትላልቅ ዘርፎች ይከፈላሉ። አንደኛው የጤና (ህክምና) ዘርፍ ነው፣ ሁለተኛ የትምህርት፣ ሶስተኛ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ነው። የጤና ዘርፉን በተመለከተ በመጀመሪያ ዙር የሚጀመሩት የጠቅላላ ሆስፒታል አገልግሎት፣ የአሜጂንግ ዲያግኖስቲክ አገልግሎት፣ መድሃኒት ማስመጣትና ማከፋፈል፣ የጥናትና ምርምር አገልግሎቶች በቀጣይ አንድ አመት ተኩል ውስጥ ሁሉም ወደ ስራ ይገባል። ከጤናው ጋር ተያይዞ በቀጣይ የምንሰራቸው ስራዎች ደግሞ ጠቅላላ ሆስፒታል በየክልሉ መገንባት፣ የአሜጂንግ ዲያግኖስቲክ አገልግሎቱን በየክልሉ ማስፋፋት፣ የተርሸር ሆስፒታሉን መገንባት፣ የትምህርት ተቋማትን መገንባት፣ ማኑፋክቸሪንጉ በቀጣይ ከ5 እስከ 10 አመት ባለው ጊዜ ወደ ስራ ይገባል፤ ተርሸር ሆስፒታሉ ግን በ5 አመት ውስጥ ያልቃል። ማኑፋክቸሪንጉ የሕክምና ግብአትን ማምረት (መድሃኒትን ጨምሮ) ስለሆነ ትንሽ ልምድ፣ አቅም እውቀት ይፈልጋል። ለዚህ ነው እስከ 10 ዓመት ገፋ ያደረግነው። ቀጣይ 10 ዓመታት ውስጥ መቅረዝን በሙሉ አቋሙ “መቅረጽ የጤና አገልግሎት” የምናገኘው ይሆናል።
ባለሙያዎችን ከማሟላት አንጻርስ ምን አስባችኋል?
እንግዲህ አንዱ ዋነኛ ተግዳሮት የሚሆነው የጤና ባለሙያዎችን ማሟላት ነው። እኛ ደግሞ አንዱ ጠንካራ ጎን ብለን የምናነሳው የጤና ባለሙያዎች ስብጥራችንን ነው ሃገር ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ ስፔሻሊስትና ሰብ ስፔሻሊስት ሃኪሞች የመቅረዝ አባላት ናቸው። ከሃገር ውጪ ከ2 መቶ በላይ የሚሆኑ በአሜሪካና በአውሮፓ ትላልቅ ተቋማት የሚሰሩ ከፍተኛ የሕክምና ባለሙያዎች በሙሉ ተቀላቅለዋል። እነሱ በእጅጉ ያግዙናል። እዚህ ሲመጡ የእውቀት ሽግግር ስራን ይሰራሉ። እውቀታቸውን አስተላልፈው አሰልጠነው ባለሙያዎችን ብቁ የሚያደርጉበትን ሁኔታ እንፈጥራለን። በዚህ መልኩ ብቁ ባለሙያዎችን እናፈራለን የሚል ውጥን አለን።

Read 1385 times