Monday, 14 March 2022 00:00

ምክንያታዊ (ራሽናል) አስተሳሰብ ይኑረን!

Written by 
Rate this item
(2 votes)


              "--እኛ ትናንሽ ኃሳቦቻችንን እናሻሽላቸውና እናሳድጋቸው! ልጆቻችንንም ነፃ አሳቢ እንዲሆኑ እናዘጋጃቸው!! በትላልቅ ሃገራዊ የጋራ መድረክ ላይ የዳበሩ ሃሳቦችን ሊያቀርቡ የሚችሉ ብቁ (ሙሉ) ሰው እንዲሆኑ እንትጋ፡፡-"

            ምክንያታዊ (ራሽናል) የሆነ ሰው አንድ ሃሳብ ሲመነጭ፣ ከ«ወገኔ» ነው የመጣው ወይስ ከ"ጠላቴ" አይልም፡፡ የሃሳቡ ምንነትና የጋራ ጠቀሜታው ላይ ያተኩራል። ራሽናል የሆነ ሰው ሃሳብን ከምክንያት አንፃር ብቻ ይመረምራል፡፡ የቀረበው ሃሳብ በብልጥነት የቀረበ የዛሬን ብቻ የሚያይና የዕውቀትና የዕድገት ለውጥን የማይቀበል ከሆነ፣ "ይህ አይመጥነኝም፤ አያሳድገኝም፤ ከሌሎችም ጋር በሕብረት አያኖረኝም" ብሎ አይቀበለውም፡፡
ዋና ትኩረት የሚገባው ሃሳቡ ነው፤ ሃሳቡን አመንጪው አይደለም፡፡ በቡድኖች መካከል ከሆነም በመጨረሻ ሊወደድ ወይም ሊጠላ የሚገባው፣ ሁሉም ተወያዮች ለጋራ ጉዳይ ሲሉ የተግባቡበት የጋራ ሃሳብ ነው፡፡
ሀገራት ዛሬ ያሉበት ደረጃ ላይ የደረሱት ታላላቅ ሃሳብ አመንጪዎች ስለነበሯቸው ነው፡፡ ሃሳባቸው የብዙዎችን ሃሳብ አሸንፎና ማርኮ የጋራ ሃሳብ ለመሆን በቅቷል፡፡ የለውጥ ግብ፤ ሰብአዊ ልማት /የግንዛቤ እድገት/ እና ቁሳዊ መሻሻል ማምጣት ነው፡፡ ዕድገቱ አንድ ቦታ ላይ ሲገታ ደግሞ በተመሳሳይ ሂደት ለሌላ አዲስ ሃሳብ ቦታን ይለቅና ሕብረተሰብና የሃገር ጉዞ ይቀጥላል፡፡
በእንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ በሩሲያና በሌሎች የአውሮፓ ሃገራትም የሆነው እንዲሁ ነው፡፡
ተፈጥሮም የሚያስተምረን ይህንኑ ነው። በቤተሰብ ውስጥ ልጆች በሕፃንነት የቤተሰብ ምሪት ይሰጣቸዋል፡፡ ከፍ ሲሉ ዕድሜያቸውና የአእምሮ ብስለታቸው ታይቶ ምክር ይለገሳቸዋል፡፡ በወጣትነት ዕድሜያቸው ደግሞ በቤተሰብ ውይይት ላይ ሃሳብ ሰጪ እንዲሆኑ ይደረጋሉ፡፡ "እኔ ብቻ አስብልሃለሁ" የሚለው ቅን የወላጅ ሃሳብ ለቤተሰባችን የሚጠቅመው "ይህ ቢሆን አይሻልምን?" በሚል ልጆችን በነፃነት ሲያሳትፍ ነው፡፡
ለቤተሰብ የሚያስቡ ልጆች ከሆኑ ስለ ሕብረተሰቡ መወያየት አዲስ አይሆንባቸውም፡፡ በአስተሳሰብ እያደጉ ሲመጡ ለጠባቡ መንደራቸው ወይም ክልላቸው ብቻ ሳይሆን ለጋራ ሃገር ማሰብና መወያየት ያስደስታቸዋል፡፡ ራሽናል ሃሳብ አዳበሩ ማለት ነው፡፡ የሃሳብ ልዕልና ወይም ምክንያታዊነት የምንለው ይህንን ነው፡፡ /Reason becomes the sole measure of everything/.
ራሽናል የሆነ ሰው ለጠባብነትም ሆነ ለትምክህተኝነት ሃሳብ አይመችም፣ አይገዛምም፡፡ የውጪው ቅብ ሳይሆን የውስጥ ምንነት /ውበት/ ነው የሚማርከው።
አልበርት አንስታይንን ስናይ፣ የፀጉሩ መንጨባረር ላይ አይደለም የምናተኩረው፤ የውስጡ /የአእምሮው/ ብስለትና ፍሬያማነት ነው የሚታየን፡፡ እርሱ ራሱ እንዳለው፤ "What matters is not the hair but inside it"
እኛ ትናንሽ ኃሳቦቻችንን እናሻሽላቸውና እናሳድጋቸው! ልጆቻችንንም ነፃ አሳቢ እንዲሆኑ እናዘጋጃቸው!! በትላልቅ ሃገራዊ የጋራ መድረክ ላይ የዳበሩ ሃሳቦችን ሊያቀርቡ የሚችሉ ብቁ (ሙሉ) ሰው እንዲሆኑ እንትጋ።
አሜሪካዊውን ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግን እንወደዋለን፤ ስለ ጥቁሮች ብቻ ነው እንዴ ያሰበው? የታገለውስ አሜሪካ በጥቁሮች ብቻ እንድትተዳደር ነውን? ጥቁሮች በነጮች ላይ በአመፅ እንዲነሳሱ አንድም ጥሪ አላደረገም፤ መርሆው Non-violence ስለነበር!! የነጭ የበላይነትን ሃሳብ፣ በላቀ የሃሳብ ትግል አሸነፈ፡፡
የህንዱን ማህተመ ጋንዲን የምናደንቀው እኮ እንግሊዞች በሀገሩ ላይ ያደረሱትን የግፍ አገዛዝ ለማስወገድ ሰላማዊ ትግል በመምረጡ ብቻ ሳይሆን፣ አንድም ጊዜ "እንበቀላቸውና እናጥፋቸው" የሚል ጥሪ ባለማቅረቡም ጭምር ነው፡፡ የነጭ ቅኝ ገዥዎችን የበላይነት በሰላማዊ የትግል ሀሳቡ አንበረከከና አሸነፈ፤ ስለዚህ ዛሬም ድረስ በጋንዲ የሃሳብ አሸናፊነት ላይ ተመስርታ ሕንድ ለጋራ ጥቅም ከእንግሊዝ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላት ሃገር ሆነች፡፡
አእምሮአችንን፣ አንደበታችንንና ጉልበታችንን ለነፃ ሃሳብና ውይይት እናዘጋጀውና እናለማምደው፤ ከሃሳብ-ግትርነት ነፃ እንውጣ፡፡
ለፈረንሳይም፣ ለእንግሊዝም፣ ለአሜሪካም ሆነ ለሌሎች ሃገሮች፣ የሃሳብና የጽሁፍ ነፃነት ከታገሉና ከሚጠቀሱትም ቀደምት ፀሃፊዎች አንድ የሆነው ሩሶ እንዲህ ብሎ ነበር፡- "Man is born free but is in chains" (ሰው ሲወለድ ነፃ ሆኖ፣ ነገር ግን በእስር ላይ ነው እንደማለት) ሃሳብ ተጫነበትና እንደታሰረ ሰው ሆነ፡፡
ከብዙ እንቅስቃሴ (Enlightenement) በኋላ ነው፣ ራሽናሊዝም /ምክንያታዊነት/ ስር የሰደደውና በጽኑ መሠረት ላይ የቆመው፡፡
እኛስ ምን ላይ ነን? ልጆቻችን እንዴት ይሁኑ? ለወደፊቱ ቀጣይ ትውልድስ?
የደቡብ አፍሪካውን ኔልሰን ማንዴላን ምሳሌነት በተግባር እንከተል፡፡ ሃሳቡ የላቀ ነው፡፡
በነፃነት ትግሉ በተገኘው ድል የተነሳ፣ ነጭ ቅኝ ገዥዎችን ለመጨፍጨፍ፣ ከሃገር ለማባረርና ለመበቀል አልተነሳም፡፡ በምትኩ ግን ራሽናል የሆነ የምክክርና እርቅ ኮሚቴ አቋቋመ- በሟቹ ቢሾፕ ዴዝሞንድ ቱቱ በተመራው የእውነትና ፍትህ አፈላላጊ ኮሚሽን አማካኝነትም፣ በጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ላይ የተፈፀመው ግፍ በዝርዝር ተመዘገበና ሰነዱ ለታሪክ ብቻ ሳይሆን ለመማሪያነት እንዲያገለግል ተደረገ፡፡ ኔልሰን ማንዴላ በነፃ ውድድር አሸንፎ ሃገሪቱን በፕሬዚዳንትነት ከመራ በኋላ ከሚቀጥለው ምርጫ ራሱን አገለለ፤ ሌሎች እንዲወዳደሩ በሩን ከፈተ፤ ታላቅ ሰው!!!
በሃሳብ እንደግ፤ ራሳችንን እንመርምር፤ ነፃ ሃሳብ ይኑረን፡፡ ደግሞም ሃሳቦቻችንን በነፃነት እናንሸራሽር፤ ምክንያታዊነት በየትኛውም ቦታ የጋራ ዕድገትን ሲገታ አልታየምና፡፡  


Read 2186 times