Tuesday, 15 March 2022 00:00

የትልቁ ዓሳ ህመም

Written by  ወንድወሰን ተሾመ መኩሪያ (አልታ ካውንስሊንግ)
Rate this item
(3 votes)

 #--ትናንትና እና ነገን የዛሬ በረከቶች ማድረግ የእያንዳንዱ ሰው ምርጫ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ቀን ምርጫ ይቀርብልናል፡- የሠላምንና የተስፋን መንገድ የመምረጥ ምርጫ ወይም ቀኑን በመርገም፣ በመኮነንንና በሃዘን የማሳለፍ ምርጫ! የቱ ይሻልዎታል? ---የሚሻልዎትን እርስዎ ያውቃሉ፡፡--;

                ከዛሬ አንድ መቶ ዓመት በፊት በ1873 ካርል ኮቢየስ (Dr. Karl Mobius) የተባለ ተመራማሪ፤ ሰው ሰራሽ የውሃ ገንዳ ሰራና አንድ ትልቅ አሳ (The Pike) እና ትናንሽ አሳዎች በገንዳ ውስጥ ጨመረ፡፡ ትልቁ አሳ በራበው ቁጥር ትንንሾቹን አሳዎች ይበላል። ኮቢየስ አንድ ነገር አደረገ፡፡ ገንዳውን በመስታወት ግድግዳ ሁለት ቦታ ከፈለውና ትልቁን አሳ በአንድ በኩል ትንንሾቹን አሳዎች በሌላ በኩል አንዲሆኑ አደረጋቸው። ትልቁ አሳ በራበው ቁጥር እንደለመደው ዘሎ ትንንሾቹን አሳዎች ለመብላት ሲሞክር መስታወቱ አፉን ይመታዋል፡፡ በተደጋጋሚ ሲሞክር አፉን ያመው ጀመር፤ ከዚህም የተነሳ ተስፋ ቆረጠ፡፡ ተመራማሪው ኮቢየስ በዚህን ጊዜ ቀስ ብሎ ገንዳውን ሁለት ቦታ የከፈለውን  መስታወት አነሳው፡፡ ትንንሾቹ አሳዎች ገንዳውን ከዳር እስከ ዳር ሞሉት፤ ትልቁ አሳ ግን አልበላቸውም፡፡ ትልቁ አሳ “አሁንም የመስታወቱ ግድግዳ አለ” ብሎ አምኗልና ህመሙን እያስታመመ መራቡን ቀጠለ፡፡ ዛሬ ግን የመስታወቱ ግድግዳ የለም፤ ግድግዳው ያለው በትልቁ ዓሳ አዕምሮ ውስጥ ነው፡፡ ዛሬ በፊቱ ያለውን ዕድል እንዳይጠቀምና በመላው ገንዳው ውስጥ በነፃነት እንዳይንቀሳቀስ የትናንትናው ህመም ገድቦታል፡፡ ይህ አይነቱ ክስተት የትልቁ ዓሳ ህመም (The Pike Syndrome) ይባላል፡፡  
በትልቁ አሳ አዕምሮ ውስጥ “ትናንትና” እና “ነገ” ሸክም ሆነውበታል፡፡ የመስታወቱ ግድግዳ “አቁስሎኛል” ብሎ ከሩጫው መገታቱ ከትናንት ተሞክሮው የመጣ ነው፡፡ የመስታወቱ ግድግዳ “እንደገና ቢመታኝስ?” የሚለው ጭንቀት ደግሞ የነገ ስጋት ነው። በዚህም ምክንያት ዕድሎች እያመለጡት ነው፤ በሙሉ ሃይሉ በነፃነነት መንቀሳቀስ እና ከርሃብ መላቀቅ በፊቱ ያሉ ዕድሎች ነበሩ። ነገር ግን በትናንትና ህመምና በነገ ስጋት ምክንያት ዛሬን በደስታ ማሳለፍ አልቻለም፡፡
ብዙ ሰው በትናንትና እና በነገ ጉዳይ ዛሬ ላይ ተስፋ ቆርጦ ይኖራል፡፡ “ትናንትና” እና “ነገ” ሸክም የሆኑባቸው ሰዎች በርካታ ናቸው፡፡ በብዙ ሰው ትናንትና ውስጥ ፀፀት፣ ቁጭትና ሃዘን አለ፡፡ ፀፀት ማድረግ ሳይገባን ያደረግነው ነገር ሲሆን ቁጭት ደግሞ ማድረግ ሲገባን ሳናደርገው የቀረነው ነገር ነው፡፡ ሃዘን ደግሞ የደረሰብን ጉዳት የፈጠረብን ስሜት ነው፡፡ በነገ ውስጥ ደግሞ “ይህ ቢሆንስ?” እና “ይህ ባይሆንስ?”  በሚሉ ጥያቄዎች ብዙ ሰዎች በጭንቀትና በስጋት ይኖራሉ፡፡ ዛሬ ላይ ግን በደስታ፣ በሰላም እና በጤና መኖር ይፈልጋሉ፡፡ ሰላም፣ ጤና እና ደስታ ውድ እሴቶች ናቸው፡፡ እነዚህን ውድ እሴቶች እንዳናገኝ አዕምሯችን በትናንትና ውስጥ ተተክሏል፤ ወይም በነገ ውስጥ ተቸክሏል። ዛሬን ማን ይኑራት? ዛሬን ማን ይታደጋት? --- ዛሬ ተዘንግታለች፣ ዛሬ ነፃነቷን አጥታለች! ዛሬ ለእኔና ለአንተ/ቺ መስጠት የሚገባትን መልካም ነገሮች ልትሰጠን አልቻለችም፡፡
ትናንትን በሁለት ነገር ልንዘጋው ያስፈልጋል፡- አንደኛው ራሳችንን ይቅር በማለት የምናገኘው እፎይታ ነው፡- (---ስምህን አስገብተህ “---እስከዛሬ ላጠፋኸው፣ ላበላሸኸው እና ለተሳሳትከው ነገር ይቅር ብዬሃለሁ፤ እስከዛሬ ከኖርካቸው ዓመታት ይልቅ ለአንተ ዋናው ዛሬና ነገ ነው” በልና ራስህን ይቅር በለው) ምክንያቱም የሚፀፅተንና የሚቆጨን ነገር ከማድረጋችንና ካለማድረጋችን ጋር የተያያዘ በመሆኑ ለትናንትና ስህተቶቻችን ራሳችንን ይቅር ልንለው ይገባል፡፡  የማይሳሳትና የማያበላሽ ሰው የለም፡፡ ትናንት በፈጠርነው ስህተትና ችግር ራሳችንን ከቆመ ፖል ጋር እያጋጨን መኖር የለብንም፡፡ ዛሬ ራሳችንን ለማሻሻል ከትናንትና ትምህርትን መውሰድ ያስፈልገናል፡፡
የትናንትናን መልካም ትዝታዎች  ለዛሬ ስንቅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ ላይ ከትናንት ያገኘናቸውን ወዳጆች፣ የትምህርት ስኬቶች፣ የመሰረትነው ትዳር፣ ያፈራናቸው ልጆች ወዘተ እንደ ስንቅ ልንይዛቸው ይገባል። እንዳንድ ሰው “ላለፉት አምስት አመታት ምንም አልሰራሁም” ብሎ ራሱን ሲኮንን ልናገኘው እንችላለን፡፡ ጠጋ ብለን ህይወቱን ስንመረምር ግን ባለፉት አምስት አመታት ሥራ ሲሰራ ቆይቷል፣ ቤተሰብ አስተዳድሯል፤ የህይወት ተሞክሮ አግኝቷል፣ ትምህርት ተምሯል፣ ትዳር መስርቷል፤ ልጅ ወልዷል፣ ነግዶ አትርፏል ወዘተ፡፡ ለሱ ግን እነዚያ አምስት ዓመታት ባዶ ሆነው ይታዩታል እና ዛሬ ላይ ይቆዝማል፤ ያዝናል፤ ስለ ነገ ተስፋ ይቆርጣል፡፡
ሁለተኛው ሌሎችን ይቅር ማለት ነው፡- በሌሎች ለደረሰብን ጉዳትና ሃዘን ሌሎችን ይቅር በማለት ዛሬን ሰላም ማግኘት ይገባል። ይቅርታ የዓዕምሮ ጤና ጉዳይ ነው፡፡ ይቅር የሚሉ ሰዎች ይቅር ከማይሉ ሰዎች ይልቅ ደስታ፣ሰላም እና የአዕምሮ ጤና እንዳላቸው የተጠኑ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የጎዱንን ሰዎች በመጉዳት የምናገኘው ሰላም የለም፤ የምናገኘውም ፅድቅ የለም፡፡
ስለ ነገም ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡ አንድ ሳይኮሎጂስት “አብዛኛው ሰው የሚጨነቀው ገና ባልደረሰበት ችግር ነው” ይል ነበር ፡፡ ስለ ነገ ስናስብ የሚያስጨንቀን ምንድነው? በነገው ውስጥ ለሚያሰጋን ነገር ዛሬ ላይ ነጋችንን የሚያሻሽል ነገር በመሥራት ልንለውጠው እና ነገን የተሻለ ልናደርገው ይገባል፡፡ በነገ ውስጥ የማንቆጣጠረውንና የማንለውጠውን ነገር ደግሞ ለፈጣሪ ሰጥቶ ወይም የሚመጣውን ነገር ተቀብሎ ለመኖር ወስኖ ዛሬን በሰላም መኖር ያስፈልጋል፡፡ ትናንትና እና ነገን የዛሬ በረከቶች ማድረግ የእያንዳንዱ ሰው ምርጫ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ቀን ምርጫ ይቀርብልናል፡- የሠላምንና የተስፋን መንገድ የመምረጥ ምርጫ ወይም ቀኑን በመርገም፣ በመኮነንና በሃዘን የማሳለፍ ምርጫ! የቱ ይሻልዎታል? ---የሚሻልዎትን እርስዎ ያውቃሉ፡፡ ቸር እንሰንብት!!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 8305 times