Print this page
Saturday, 12 March 2022 15:37

“ከወገብ በላይ ታቦት፣ ከወገብ በታች ጣዖት” (መጣጥፍ)

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

  "--ከግብፅ ባርነት ወጥተው በምድረ በዳ ለተቀመጡት እስራኤላዊያን አሮን ጣኦት ሰራላቸው፡፡ ራሳቸው ያዋጡትን ወርቅ ተጠቅሞ የወርቅ ጥጃ እንዲያመልኩ አነፀላቸው፡፡ ለተሰራላቸው ምስል ራቁታቸውን ሆነው ሰገዱ፡፡አመለኩ፡፡-";
                        ሼርውድ አንደርሰን የሚባል ደራሲ ነበር፡፡ በአጭር ልብ ወለድ ድርሰት ረገድ ሃያኛውን ክፍለ ዘመን፣ በአንዲት የአጭር ልብ ወለድ መድበል ያነቃ ነው፡፡ መፅሐፏ፤ “Winsburg, ohio" ትሰኛለች፡፡ ሼርውድ አንደርሰን የሚባል ደራሲ ነበረ፤ ድርሰቱ ግን አሁንም አለ፡፡
በአንዲት ትንሽ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ የተለያየ ማንነት ያላቸውን ሰዎች በጥልቀት የሚገልጡ ሃያ ሁለት የአጭር ልብወለድ ትረካዎችን የያዘች መፅሐፍ ናት፡፡ ደራሲው በዚህ ድርሰቱ የተገለጠበትን አቅም በሌላ ስራው ላይ አልተከሰተም፡፡ “አንድ ይሻላል ከመቶ” ብለን እኛም እቺን የጥበብ ገፀ በረከት በድጋሚ አገላበጥናት፡፡
 እንደ ፅላት የማይደክም ሃይል ያለው ነገር በእያንዳንዱ ታሪክ ውስጥ አለ። አንዲቱ የልብ ወለድ ቤሳ ድርሰት ግን ከሌሎቹ በበለጠ የቀልቤን አጥር ጥሳ ገባች። የአርዕስት እጀታዋን መያዝ ከፈለጋችሁ “The book of the grotesque” ትሰኛለች፡፡
የመፅሐፉ አብዛኞቹ ታሪኮች የሰውን ልጅ የነብስ ምስል እንደ ኤክስሬይ ፎቶግራፍ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ የብርሃን መቀስ ቀርፆ የሚያሳየው ምስል ግን አይደለም፡፡ የሰው ልጆችን በስቃይ ክምርነታቸው የሚገልጥ ነው፡፡ ክምሩ ደግሞ… ወይንም ክምሩ ላይ ደግሞ የታሪኩ ባለቤት የሆነው ገፀ ባህርይ፣ እንደ ከንቱው አውራ ዶሮ… በራሱ ኩስ ክምር ላይ ወጥቶ ሲያቅራራ የሚሰማበት ነው፡፡ የደራሲው ብዕር  በገፀ ባህሪው ማቅራራት ተደልሎ ወይንም ተለባብሶ የሚቀርብ አይደለም፡፡
የሰው ልጆችን ጥልቅ ስነልቦና ስብራት በአንድ የጨለምተኝነት ሰንደቅ ስር አስማምቶ፣ በተለያየ የዘመን አድራሻ የሚኖሩ የሰው ልጆችን  ራሳቸውን መልሰው እንዲመለከቱበት እነሆኝ ብሎ ያቀርባል። ራሳቸውን እንዲመለከቱበት ያቀበላቸው የፊደል መስታወት ተስፋ ሰጪ አይደለም፡፡
በሼክስፒር “ቴንፐስት” የተሰኘ ትያትር ላይ ካሊባን (Caliban) የተሰኘ የተጣመመ አውሬ መሳይ ፍጥረት አለ፡፡ ካሊባንን ከመስታወት ጋር ፈት ለፊት ሲገናኝ የሚያሳየው ባህሪ ሁለት ነው፡፡
ካሊባን የራሱን የአውሬ መልክ በመስታወት ውስጥ ተንፀባርቆ በማየቱ፣ በራሱ አፍሮ ወይንም ተበሳጭቶ፣ የራሱን መልክ ፍንትው አድርጎ ያሳየውን መስታወት ሊሰባብረው ይችላል፡፡ ወይንም ደግሞ፣ በተቃራኒው፣ ካሊባን በመስታወት ያየው ፊት ሳቢ እንዲሆን ተደርጎ ተቀባብቶ ቢቀርብለት…. የመልአክ ፊት፣ የመልካም ሰው ፊት ተደርጎ ተውቦ ቢቀርብለት፣ ቢንፀባረቅለት… የራሱን  መልክ ራሱ አውሬው ጠንቅቆ ስለሚያውቅ፣ ዶሮ ማታው፣ ማታ ሲመጣ ምንም እንደማይመጣ እየተደለለ፣ እየተሸነገለም ሳለ ስለሚገባው፣ ተዋሸሁ ብሎ፣ ተደለልኩ በሚል በድጋሚ መስታወቱን ይሰባብረዋል፡፡ መጀመሪያም በንዴት፡፡ ሁለተኛውም ጊዜ በንዴት፡፡ አንደኛው ጊዜ እውነትን መቀበል አቅቶት። ሁለተኛው ጊዜ ሽንገላን መቀበል አቅቶት፡፡ ውሸት እና እውነቱ በመስታወቱ ምክኒያት አንድ ይሆናሉ፡፡ መስታወቱ ሁሌ ሀቀኛ ነው፡፡ የተመልካቹን መልክ ሳይጎረባብጥ፣ ሳያተልቅ/ ሳያሳንስ፣ ሳያጣምም ሳያዛንፍ እስከገለጠው ድረስ… መስታወቱ እና ነፀብራቁ ሁሌ እውነት ነው፡፡
እውነቱ ግብ የሚመታው ግን ተቀባዩ ላይ ነው፡፡ ተመልካቹ ላይ፡፡ ተደራሲው ላይ፡፡ የመስታወቱ ነፀብራቅ  ተቀባዩ ዘንድ ሲደርስ፣ አቀባበሉ ላይ እውነቱ ወደ እምነት ይቀየራል፡፡ ካሊባን መስታወቱን ተመልክቶ አውሬነቱን መቀበል መጀመሩም የእምነት አይነት ነው፡፡ መልዐክነቱን ቢቀበልም ያው የእምነት አይነት ነው፡፡
ምናልባት፣ የካሊባን የአውሬነት ሚስጢር በራሱ ላይ፣ እንደ ራሱ ራሱን ችሎ ያለ ሳይሆን፣ ከመስታወቱ ላይ በነፀብራቅ አማካኝነት ከሚያነሳው እምነት የሚያገኘው ባህሪያዊ ማንነት ሊሆን ይችላል፡፡ የተመለከተበት አኳሁዋን ነው ለተመልካቹ አንዳች መልክ ፈጥሮ፣ ራሱን በራሱ አይን ለራሱ እንዲገልጥ የሚያደርገው፡፡
መፅሐፍ መስታወት ነው፡፡ መፅሐፍ ጣዖት ነው፡፡ ወይንም የተውኔት ድርሰት ፀሐፊው እንዳለው፤ “ከወገብ በላይ ታቦት፣ ከወገብ በታች ጣዖት”፡፡
እና… እንደ አቀባበላችን ነው፡፡ እንደ አነባበባችን፣ እንደ አረዳዳችን፡፡ ከድርሰቱ ላይ ፈቅፍቀን የምናነሳው እምነታችንን ሳይሆን፣ በተቃራኒው እንዲያውም… ማመን የምንፈልገውን ነው እመስታወቱ ላይ ለድፈን የምናጣብቀው፡፡ ማየት የፈለግነውን ብቻ ነው አጉልተን በመስታወቱ አማካኝነት የምናየው፡፡ ወይንም በመፃፍ አማካኝነት ድርሰት አድርገን የምናሳየው፡፡ … ራሳችንን እንደ አዛባ ክምርም እንደ ወርቅ ንክርም እንዲህ ተመልክተን ልንቆጥር እንችላለን። ከተመለከትነው ውስጥ እምነታችንን እንጨልፋለን፡፡ ወይንም ከእምነታችን ምልከታችንን፣ ከአመለካከታችን ደግሞ መልካችንን፡፡
እና በዚህ የአመለካከት ቅኝት ነው የሼርውድ አንደርሰን “Whinsburge,ohio” የአጭር ልብ ወለድ ድርሰት መፅሐፍን ያቀረብኩት፡፡ ቀርቤ የገለጥኩት፣ ያገላበጥኩት፡፡
በስብስቡ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ታሪክ የሚገልጠው የአንድ ግለሰብ መልክ አለው፡፡ መልኩ የስጋ፣ የነፍስ እና የመንፈስ ጥምረት ያለው ነው፡፡ ቁም ነገሩ ያለው ግን (አሁንም ልብ በሉልኝ) እመስታወቱ ላይ ሳይሆን የተመልካቹ አመለካከት ላይ ነው፡፡ በአጭሩ የአንባቢው፡፡ ይሄም መጣጥፍ እንደዛ ነው፡፡ ወይንም ስለዚያ ነው፡፡ ስለ’ኔ ስለ አንባቢው እና ስለ አነባበቤ፡፡
በተለይ “The book of the grotesque” (“የጠማማዎች/ የአስቀያሚዎች መፅሐፍ” የሚል ውርስ ትርጉም ሊሰጠው ይችላል)… የሚለው አጭር ልብ ወለድ ላይ ቀልቤ አረፈ፡፡ ይሄንን ልብ ወለድ ከሌሎቹ ለየት የሚያደርገው፣ የታሪኩ ዋና ጭብጥ፣ በገፀ ባህሪ ላይ ሳይሆን  በሃሳብ ላይ በመሆኑ ምክኒያት ነው፡፡ ሃሳብ ባይኖረው ታሪኩ ላይ ያለው ገፀባህሪ ምንም የተለየ ነገር መፍጠር ባልቻለ ነበር፡፡ ከደጅ ቆሞ ወደ ልብ ወለዱ መስታወት የሚያጮልቅ ተመልካች/ አንባቢ የሚያየው ምንም የተለየ ነገር ባልነበረ፡፡
ገፀ ባህሪውን የተሸከመው ሃሳብ እንደሚከተለው የሚቀርብ ነው፡፡ ገፀ ባህሪው ፀሐፊ ነው፡፡ እድሜው ከስልሳዎቹ አልፏል፡፡ …. ከመስኮቱ አጠገብ የተዘረጋው አልጋው ዝቅ ያለ ስለሆነ ከፍ አስደርጎ  አስመንድጎ፣ ማዶ አሻግሮ  ማየት እንዲችል አድርጎ ለማሳነፅ አናጢ ሲቀጥር ነው ታሪኩ የሚጀምረው፡፡ አናጢው በጣም ከፍ አድርጎ ስለሰራለት ወደ አልጋው ለመውጣት በወንበር መታገዝ ነበረበት፡፡ … እና አልጋው ላይ ጋደም ብሎ ራሱን እያደመጠ ያሰላስላል። በውስጡ ያረገዘው አንዳች ሃሳብ ነበረ፡፡ ያ የተረገዘ ሃሳብ… በአረጀ ሰውነቱ ውስጥ ሆኖ የሰውየውን መንፈስ ወጣት አድርጎታል፡፡ ጥሩር እንደለበሰ ተዋጊ ሞገስና ሃይል የሚያላብስ ሃሳብ ነው፡፡ ከሞቀ አልጋው መውጣት ከባድ ቢሆንም፣ ከአልጋው ወጥቶ ጠረጴዛው ላይ ተቀምጦ መፃፍ ይጀምራል፡፡
በዐይኑ ላይ የብዙ ሰዎች ምስል እየመጣ ያልፋል፡፡ ምስሎቹ በሙሉ ጥመት ያላቸው ናቸው፤ አስቀያሚ የሆኑ፡፡ ደራሲው በህይወት ዘመኑ ያውቃቸው የነበሩ ሰዎች ሁሉ… ጥመት ያላቸው የአውሬ እና የሰው ድብልቅ መሆናቸውን ለመፃፍ እየተንደረደረ ሳለ ተገነዘበ፡፡ ሙሉ ታቦት መሳይ ግማሽ ጣዖቶች፡፡
እነዚህ የሚታዩት ጠማማ የሰው አይነቶች ግን፣ ሁሉም መልከ ጥፉ ወይንም ክፉ የሚባሉ አይደሉም፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ በአይን ሲታዩ ደስ የሚሉም ከመሃላቸው አሉበት፡፡ ለምሳሌ አንዷ እየፃፈ ሳለ የመጣችበት ሴት ከጥመቷ የተነሳ ከቅርፅ ሁሉ የወጣች ናት፡፡ ጥመቷ እንደ ውሻ በመሰለ ሲጥ የሚል ድምፅ ያስቃስታታል፡፡ ብዙ ይሄንን መሰል ፊቶች በአዕምሮው ዐይን ላይ ተሰልፈው ካለፉ በኋላ… ብዕር አንስቶ መፃፍ ይጀምራል፡፡ የፃፈው ፅሁፍ በሃሳብ መልክ ሲጠቃለል የሚከተለውን ይመስላል።
….ዓለም ገና ለጋ እና በጅማሮዋ አጥቢያ ገደማ ላይ ሳለች… በምድር ገፅ ላይ እጅግ አያሌ ሃሳቦች ነበሩ፡፡ … ሃሳቦች ነበሩ እንጂ… እውነት የሚባል ነገር ግን … ራሱን ችሎ… እርግብግቢቱ ጠንቶ በምድር ላይ አልነበረም፡፡
… እውነትን የፈጠረው የሰው ልጅ ራሱ ነው፡፡ አንዳንዱ እውነት የታነፀው… ብዙ አሻሚ እና ጭል ጭል የሚሉ ሃሳቦችን እንደ ግብዐት በመጠቀም ነበር፡፡
እንዲህም ሆነ… በዓለም ዙሪያ ብዙ ውብ- ውብ እውነቶች በዚህ አኳሃን ታነፁ። ስለታነፁት እውነቶች ስለያንዳንዳቸው ልዘረዝርላችሁ አልችልም… ይለናል የአጭር ልብ ወለድ ደራሲው፡፡ የአጭር ልብ ወለዱ ደራሲ ሼርውድ አንደርሰን፤ በልብ ወለዱ በውስጥ እንደ ደራሲ ተደርጎ የተቀረፀው ግን ሽማግሌው ፀሐፊ ነው። … ሁለት መስታወቶች ትይዩ ተደርገው ከተቀመጡ… እርስ በራሳቸው በሚፈጥሩት ነፀብራቅ ማለቂያ የሌላቸው የመስታወት ድግግሞሽ ከራሳቸው ትይዩነት ውስጥ ይሰራሉ፡፡ ደራሲው፣ ደራሲውን ሲፅፈው… በድግግሞሹ ነፀብራቅ የምንፈጠረው የትየለሌ አንባቢያን፣ እኔ እና እናንተ ነን፡፡
ድርሰቱ ውስጥ ያለው የሽማግሌው ሃሳብ ይቀጥላል፡፡ ሰው እውነትን በምድር ላይ ከሃሳብ ተነስቶ ፈጠረ፡፡ እስከዚህ ድረስ ሁሉም ውብ ነበር ይላል ደራሲው፡፡
…እስከዚህ ድረስ ሁሉም ውብ ነበር… ከዛ… ጭልጭል ከሚሉ የሃሳቦች ክምችት የፈጠረውን እውነት ሰው ማምለክ ጀመረ። ወይንም ራሱ በፈበረከው እውነት ለመኖር ቆርጦ በመጣጣር ላይ ተጠመደ፡፡ እንደዚህ በመጣጣር ላይ ያሉ ገፀ ባህሪዎች በአዕምሮው ዐይን ላይ ሲያልፉ ተራ በተራ ደራሲው ሽማግሌ መፃፍ ጀመረ፡፡ ፅሁፉ እየበዛ፣ ገፀ ባህሪዎቹ እየተበራከቱ መፅሐፍ አከሉ፡፡ መፅሐፉን “The book of the grotesque” ሲል ሰየመው፡፡ መፅሐፉ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ እውነቶችን ፃፈ፡፡ …. ሁሉንም ልዘረዝርላችሁ አልችልም… ይለናል የተራኪው ድምፅ፡፡
ስለ ድንግልና ያለውን እውነት… ስለ ፍቅር ያለውን እውነት… ስለ ሀብት እና ስለ ድህነት… ስለ ገንዘብ ቋጣሪነት እና ስለ አባካኝነት… ስለ ግድ መስጠት እና ግዴለሽነት… ፀንቶ ስለ መቆየት እና ስለ ኮብላይነት…
ብዙ መቶ እውነቶችን ሽማግሌው በፅሁፍ ዘረዘረ፡፡ የዘረዘራቸው ሁሉ ደግሞ ውብ ነበሩ፡፡ ከዛ የዘረዘራቸውን እውነቶች ተከትለው ሰዎች መጡ፡፡ ተቀባዮች መጡ፡፡ አምላኪዎች፡፡ እውነቱ በአምላኪዎች ዘንድ ገብቶ እውነት ሲሆን ጣዖት ወይንም ታቦት እንደ አቀባበላቸው መሆን ጀመረ፡፡ ወይንም የሁለቱም ድብልቅ፤ ከወገብ በላይ አንዱን፣ ከወገብ በታች ሌላውን፡፡ ራሱ የፈጠረውን ለማምለክ ሲጀምር ነው፣ ባርነቱ የተጎነጎነ ሰንሰለት የሚሆነው፡፡
ከግብፅ ባርነት ወጥተው በምድረ በዳ ለተቀመጡት እስራኤላዊያን አሮን ጣኦት ሰራላቸው፡፡ ራሳቸው ያዋጡትን ወርቅ ተጠቅሞ የወርቅ ጥጃ እንዲያመልኩ አነፀላቸው፡፡ ለተሰራላቸው ምስል ራቁታቸውን ሆነው ሰገዱ፡፡አመለኩ፡፡
አንዳንዱ ለአንድ እውነት ሰገደ፣ ወይንም አቅም ያለው ደግሞ ደርዘን እውነቶችን ዘርፎ ሄደ… ይለናል የልብወለድ ድርሰቱ፡፡  እውነቱ ሰዎቹን አጣመማቸው፡፡ ያመኑትን እውነት ነፀብራቅ ለመሆን ሲጥሩ፣ የራሳቸውን ቀለም እና የተፈጥሮ እውነት አጡ፡፡
…የሽማግሌው ድርሰት ይሄ ነው… ይላል የአጭር ልብወለዱ ተራኪ፡፡ የፃፈውን ድርሰት ሽማግሌው ሳያትመው ቀረ፡፡ ማሳተም አልፈለገም፡፡ ያልፈለገበት ምክኒያት፣ መስታወቱን ወደ ጣዖት ላለመቀየር ሲል ነው፡፡ እሱም ለመፃፍ ሲቀመጥ… የመጣለትን ሃሳብ እውነት ብሎ ሲፈጥረው ውብ ነበር፡፡ መፅሐፍ አድርጎ አሳትሞ… ራሱ የፈጠረውን ነገር የስሙ መጠሪያ አድርጎ ማምለክ የጀመረ ዕለት የጣዖትነት ጥመቱ ተወልዶ መዳህ ይጀምራል፡፡
ድርሰቱን በፅሁፍ ወልዶ በህትመት ፀድቆ መዳህ እንዳይጀምር ከልክሎ ሆነ ብሎ አስቀመጠው፡፡ የእውነቱን ውበት እንደጠበቀ ለማቆየት ደራሲው መረጠ፡፡
“መረጠ” ብሎ ስለ ደራሲው “በዋይንስበርግ፣ ኦሃዮ” የተሰኘ መፅሐፉ ደርሶ፣ አሳትሞ የሚያስነብበን ግን ሼርውድ አንደርሰን ነው፡፡ መፅሐፉን አሳትሞ ዝናው በአለም ናኘ፡፡ ሽማግሌው የደበቀውን ታሪክ እሱ ይፋ አወጣው፡፡ ታቦት እና ጣዖት በዚህ መልክ ነው ፊት እና ጀርባቸው (እንደ ጃኑስ) ገጥሞ ወደ ገበያ በመስታወት ስም የሚቀላቀሉት፡፡
ካሊባን ጭራቁ፣ የራሱን መልክ ስላሳየው የሰበረው መስታወት እና “የራሴን መልክ አላሳየኝም” ብሎ የሚሰብረው መስታወት፣ ሁለቱም ተቀላቀወለው በመስታወት ገበያው ላይ ይቸበቸባሉ፡፡ ከመስታወቱ በፊት የተሰበረውማ… ካሊባን ራሱ ነው መጀመሪያውኑ፡፡
የአጭር ልብወለድ ታሪኩን እንደ መስታወት ትኩር ብዬ ስመለከት ይሄ ሁሉ ታየኝ፡፡ ወይንም እስከዚህ ድረስ፡፡ እኔ በታየኝ ውስጥ እናንተ ሊታያችሁ የሚችለውን ደግሞ… እዚህ ቁጭ ብዬ እየፃፍኩ መገመት አልችልም፡፡ ሰው የሰራውን ነገር መልሶ ማምለክ የሚጀምረው በሌሎች መረዳት ውስጥ ነው፡፡ ሌሎች የሰራውን ሲወዱለት ነው ለሰራው ነገር ቦታ መስጠት የሚጀምረው፡፡ በሰራው ወይንም በፈጠረው እውነት ስም ደግሞ ለራሱ መደላደያ ከፍ ያለን ስፍራ ይመርጣል፡፡ በመረጠው ከፍታ ላይም የተፈኘ ይመስለዋል፡፡ ከፍታው የራሱ አዛባ ክምርም ሊሆን ይችላል፡፡
አውራ ዶሮውም እንደ ቆመበት የፍግ ክምር ከፍታ ጫፍ… በመንቁር አንደበቱ እውነቱን እየጮኸ ይለፍፋል፡፡ ታቦቱ እና ጣዖቱ የሚደባለቁት እዚህ ነጥብ ላይ ነው። ሁሉም እንደ አመለካከቱ ከሁለት አንዱን መርጦ ያጎላል፡፡ እውነቴ ብሎ ይቆጥረዋል፡፡ በሼርውድ አንደርሰን አገላለፅ… ችግሩ ያለው እውነቱ ላይ ሳይሆን  “እውነቴ” ብሎ ጠሪው እና አስጠሪው ላይ ነው፡፡

Read 539 times