Saturday, 12 March 2022 15:35

ምልጃና ኅያው ግጥሞቹ

Written by  ሳሙኤል በለጠ (ባማ)
Rate this item
(1 Vote)

 አሻም ቲቪ ላይ ገጣሚና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን፣ በሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ግጥሞች ላይ ትንተና ሲያቀርቡ፣ ስለ Timeliness poems (ወቅታዊ ግጥሞች) እና Timelessness poems (ዘላለማዊ ግጥሞች) መግቢያ ሰጥተዋል። ገጣሚ ወቅቱን ጠብቆ ከመጻፍ ወቅታዊ ይባላል። እድሜና ጊዜ ከፈቀደለት፣ ያ ግጥም ወደ ዘላለም ይሸጋገራል። ዘላለማዊነት (Timelessness) ከዘመን ያልፋል፤ ይላሉ ነቢይ፡፡ እንደውም አንድ የሎሬትን ግጥም አቅርበው ጸጋዬ በዚህ ግጥሙ ወቅታዊ የሆነ ይመስለኛል፤ ብለዋል። -
“ሥነ-ግጥም ልብን ውበት የሚመግብ ሕብስት፤ የውስጥን የሕመም ጥም የሚቆርጥ ጽዋ፤ በነፍስ ጥልቀት የጸለለ ረቂቅ መንፈስ ነው። በዚህ መሳይና አምሳል ያልመጣ ግጥም ሃሳይ መሲህ ነው። እኛ በጭብጨባ ጥሞና በመድረክ ረሃብ ተይዘናል፤ ግጥሞቻችንም ከፍርጎ ከብደውን በባዶ ጩኸታቸው ተጨንቀናል። በዘላለም ክበብ ከፍታ ላይ ሆናችሁ ቁልቁል የምትታዘቡን የቅኔ ነብያት መንፈሶች ሆይ:- ለረቂቅ ሐሳቦቻችን መኖሪያና ለተላላ ነፍሶቻችሁ መናጋሻ ወዳቆማችኋቸው ምኩራብ አቅርቡን። ሥነ- ግጥም የኅያዋን እስትንፋስ መሆኑ ቀርቶ ሸቀጥ ከሆነበት ዓለም ሥር ወድቀናል፤ እናንተ እውነተኛ ባለቅኔዎች ሆይ! ይቅር በሉን።” [የገጣሚው መውጫ፤ ምልጃ ገጽ-118]
የሥነ-አዕምሮ ሳይንስ ልሂቃን እንደሚሉት፤ ገጣሚዎች በጥበብ ተመስጦ ውስጥ በሚሆኑ ጊዜ ከላዕላይ ኅሊናቸው(consious mind) በላይ ወደ ሆነው ወደ ታህታይ -ኅሊናቸው (unconsious mind) ዓለም ሲጓዙ፣ በቅጽበቱ በንሸጣ ግጥም ይደረድራሉ፤ ወደ ጥሊቁ-ዓለም እንደ መግባት ክስተት ነው። አስቡት፤ በዚህ አኳኋን የሚወለድ ግጥም ምን ያህል የወደኋላና የወደፊት የጊዜ ጥልቀት(Time depth) ሊኖረው እንደሚችል። በሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የገነነው ገጣሚ ዋላስ ስቲቨንስ፤ “ገጣሚ ውበትን በቃላት ሲቀምር ከገሐዱ ዓለም ወዲያ ማዶ ሲባትል፣ ለምድሩ ዳቦ ፍለጋ መላ ነገር አይዘይድም፤ ወቅታዊ ገጣሚ ካልሆነ በስተቀር፡፡ ጥሩ ገጣሚ ማለት የረቂቁ ዓለም ካህን ነው።” በማለት የጥሩ ገጣሚነትን ልኬት ይነግረናል።
ምልጃ፤ የሥነ-ግጥም ስብስብ በሠማኒያ ስድስት ግጥሞች፣ በአንድ መቶ አስራ ስምንት ገጽ በማራኪ የሽፋን ምስል ተዋቅሮ በቅርቡ ታትሞ ለገበያ በቅቷል። የሥነ-ግጥም ስብስብ በረጅም ጊዜ ተምሰልስሎት እዚህ እንደደረሰ እንደሆነ የሚነግረን ብዙ ነገር አለ፤ ሁሉንም ግጥሞች በጥሞና ካነበብናቸው ዜማው የተስተካከለ ፍሰት ያለው፡ የቋንቋ ምትሀቱና የግጥም አደራደር ጥበቡ ግሩም ነው። በሥነ-ግጥሙ ዘርፍ የሚያሳርፈው በጎ ተጽኖ(positive Influence) ቀላል አይደለም። እስቲ በጥሞና ሥስት ግጥሞቹን እንመርምራቸው:-
ምልጃን አንብቤ ከተመሰጥኩባቸው ብዙ ግጥሞች አንዱ “ለምን ይሆን?” (ከገጽ-59 እስከ 61) ‘ሚለው ዘለግ ያለው ግጥም ነው። ከትዝታ ፍርፋሪ ጋር በሐዘን እየደፈቀን በስውር ገጣሚው ቁስሉን ይሰፋብናል። ወሰን የለሽ ቁስል፤ ነፍስን የሚያስለቅስ ሕመም ነው። ሰቆቃው አይቀዘቅዝም፣ ማንንም ተጠያቂ አያደርግም፤ ግን የጋራ ኅልዮሻቸው ግድግዳቸው ፈርሶ በትዝታ ብርድ፣ ነፍሶች ሲቆፈኑ እናነባለን:-
“...ምንሽ ይሆን ውስጤ ላንቺ፥
የሚያላዝን ዕንባ ለብሶ
የሚጨመት ሲያይሽ ደርሶ
የሚቆየኝ ሐዘን ሰርቶ
የሚወረኝ ተንሰራፍቶ
ምኔ ይሆን ገጽሽ ከቶ?...”
[ምልጃ ገጽ-61] “የትኛው ድብቅ ስብራትሽ ይሆን፥ ነፍሴ ደርሶ የምቆዝም?” ይላል። ሐዘን ይፈጥራል። ይህ ግጥም የእያሱ አሰፋ (ቪክቶር) ያልታተመ በበይነ መረብ ያየሁትን ግጥም ያስታውሰኛል። ይቅርታ! “...ተስፋ አርግዤ ላላማማጥኩሽ፣/ ነገን ለብቻ ስላጋፈጥኩሽ፣/ ምንም የለኝም/ አንቺን የሚያድን ፀፀት ከሞላው ከግጥም በቀር/ ድንገት ከረዳሽ ይህን እወቂ ‘ሞክሬ ነበር’!
ዕዉቋ ባለቅኔ አን ሴክስተን፤ “ግጥም ሕዋሳትን ማሸበር አለበት፤ የአንባቢን ስሜት እስከ ማደፍረስ” ትላለች:-
አመድ አፋሽ
አይኔ እየነዳ፥ በመውደድ ጎህ ጸዳል
ልቤ ጽድቅ ሲያዘምር፥ በእምነትና በቃል
መንፈሴ ሲተጋ፥ ንጡር ሕይወት ጸንሶ
አረዳኝ አጸፋሽ፥ ውጥኔን ቀንሶ
ሕልሜን አሳንሶ።
በልቦናሽ እልፍኝ፥
ስፍራ አልባ ስፍራ ላይ የሆነ ዳርቻ
እንዳይሆን ተጥሎ፥ አይሆኑ ስርቻ
ሕያው ነው ያልኩትን፥
የፍቅሬን መስለምለም፥ ጣሩን ሰምቻለሁ
(መዝጊያዬን አትምቺ)
ከማለዳ በፊት፥ ከመርዶሽ ቀድሜ እርሜን አውጥቻለሁ።
[ምልጃ ገጽ-23]
መለየት ቀለሙ ድቅድቅ ነው። መለየት ከሕብር ግንድ መሰንጠር ነው። ያጣት(‘ሚያጣት) ቀለም-አለመሆን ሆና ልትቀዘቅዝ ሆነ። ግሪኮች ቀመር ሠሩ፤ መኖር ማለት ፀሐይ ማየት ነው። መሞት ማለት ደግሞ “ጨለማ” ነው። ስለዚህ ፀሐይ ስትጠልቅ ሰው “ባይተዋር” ይሆናል። ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የ“ፀሐይ መግባት” ፍርሃትና ድንጋጤን ይጠራል!” ተብሎ በዘፍጥረት 15÷12 ላይ ተጽፏል። የፀሐይ መግባት የእነዚህን ተቃራኒ ይጠራል፡፡ መጻኢው “መጥፎ ዕድል” ተብሎ ተደገመ፤ የገጣሚውም ጣር መለየት ነው። ገጣሚት ትዕግስት ዓለምነህ፣ ይህን እሳቦት የሚደግፍ ቅኔ አላት “...ልክ እንደ አራስ እናት፣/ያለ ምንም ስስት ራሴን ሰጥቼ፣ በፍቅር ‘ያጋቱ ጡቶቼን አጥብቼ፣ ለዚህ ባደርሰውም፣/ “እሄዳለሁ ካለ “አትሂድ አልለውም።/ አንጀቴን አጥፌ እመርቀዋለሁ ወይ እረግመዋለሁ፣/ “ወልደህ እየው” ብዬ ቆሜ እሸኘዋለሁ[ዕልልታና ሙሾ ገጽ-14]
ዐልቦ!
ወለፈንድ ኅሊዌ፥ መገን ሕይወት ግራ
ካላጣችው ሙያ፥ እርሾ ተቸግራ
ዕንባ እያነጎተች፥ ሰቀቀን አዙራ
የእድሜን ሌማት ሞላች፥ ሲቃ ብቻ ጋግራ
ትንግርተኛ ሰማይ፥ ገዝፎ የናወዘ
ከሰነፍ ሕይወት ጋር፥ ሞት አቅፎ የያዘ
ልክፍት እንደ ግርሻ፥ ሕመም አልሽር ያለው
ከፍክ ገጹ ኋላ፥
ድልመት ይሸርባል፥ አዚም እየጣለው።
ልጓሙን ላይቸረን፥
ጠልፎ ያሳፈረን፥ ጊዜስ ምን ረዳን
‘ወዴት ነው?’ ሳይለን፥ አግድም ነው የነዳን።
ሁሉም!
ሁሉም!
በጌጠኛ ወረት፥
ቀን ሞሽሮ ውሎ፥ ዕድሜ እያዘናጋ
ከተስፋ ዘሃ ሥር፥
ቀቢጽ ገምዶ ጥሎ፥ ጽናት እያናጋ
በሰመመን መጋዝ፥
የእስትንፋስን ጅማት፥ እየገዘገዘ
በቀሊል ጣቱ ሽር፥
ያባብላል እንጂ፥ ቁም እየገነዘ
ከእንግልት በቀር፥
ለአማኝ ልብ ‘ሚሆን፥ ትርጉምም አልያዘ።
[ምልጃ ገጽ-115]
የተነሳው ጥልቅ ፍልስፍና ያመራምራል። ግጥሙ ከላይ ወደታች፣ ከታችው ወደላይ ቢነበብ ጣዕም አለው፡፡ ሊቁ ብርሃኑ ድንቄ፣ ሳሙኤል ቴይለር ኮልሪጅን ጠቅሰው፤ “No man was ever yet a great poet, without being at the same time a profound philosopher.” ብለዋል (አስቀድሞ አንድም ገጣሚ ጥልቅ ፈላስፋ ሳይኾን፣ ታላቅ ገጣሚ አልነበረም፤ እንደማለት ነው።) ‘አልቦ’ ነው። ‘ርዕሱ ግጥም የሕይወትን ወለፈንዲነት (Absurdity) ይገልጸዋል። አዳም ረታ በወለፈንዲ (Absurdity) ፍልስፍና በሚፈከረው ትረካው(በእቴሜቴ የሎሚሽታ ከረሜላዎቹ)፤ የልቦለዱ መውጫ ላይ የሕይወትን ወለፈንዲነት እንዲህ ያለዝበዋል። “ዛሬ እዚህ ሆነን ስናስበው(በጊዜ እዚህ ሆነን) ነገ በጉያዋ የያዘችው ‘ሚስጥር አዲስ ይመስለናል። መንጋቱ አይቀርምና ነግቶ ያቺ የቋመጥንላት ነገ ስትቀድ ጀምሮ እንደ ወተት ብንጠባት፣ ብናቆላምጣት ካለፍናት ትላንትና የምትለይበት ብዙ መሰረታዊ ነገር ላይኖራት ይችላል።”[እቴሜቴ የሎሚሽታ ገጽ-127]
የገጣሚው የወለፈንዲ ክብበት ግን መከራ አለው፡፡ የወለፈንዲ ክብበት ሕይወትን እንደሚያወይብ የወለፈንዲ ፍልስፍና አቀንቃኙ አልበር ካሙ ‘The stranger’ በሚለው መጽሐፉ በተምሳሌት እንዲህ ገልጾታል፡- “በሩስያ አውራ ጎዳና ውሻው የታሰረበትን ገመድ እየመነጨቀ ፤ ሳልማኖ ደግሞ ወደራሱ እየጎተተው ልታዩዋቸው ትችላላችሁ።
እንዲህ ሲሆን ሽማግሌው ያንባርቅና ውሻውን ሲደበድበው ይታያል፤ ይሄኔ ውሻው እየለገመ  ይቀራል ። ጎታች ሽማግሌው ይሆናል። ውሻው እንደገና ረስቶት ጉተታና ምንጨቃውን ሲጀምር፣ ማንባረቁንና ዱላው ይከተላል። ይሕ ሲሆን እግረኛው መንገድ ላይ ይቆምና ውሻው በፍርሃት፣ ሽማግሌው በጥላቻ ይፋጠጣሉ።” [the stranger (ባይተዋሩ) ገጽ-28 ]’ሚሸጥ ሥጋ ያለው? የሚለው የስንቅነህ አንድ ቅኔው የመዝጊያ አርኬ፣ አንድም ለግጥሙ ሁለትም ለዘበትነት ሕሳቤ  ማጠናከሪያ ነው። “...ይህ ልቤ፣ ይህ ዓይኔ፣ የራሴኑ ራዕይ/ እንጉል ሲኒማ መልሶ-መላልሶ እያጫወተልኝ፣/ ሕይወት ዝግንትሏ ቀለማም ጠፋብኝ!’
መውጫ
የአንተነህ የብዕር ትባት ውጤት ፍሬ አፍርቷል። ግጥሞቹ ከኁለንታ ለመቆራኘት፣ ስቃይን ለመግለጽ፣ ልብን ሐሴት ለመመገብ ይንደረደራሉ፤ ፍልስፍናቸው እምቅ ነው። እውቋ አሜሪካዊት ገጣሚ ኢሚሊ ዲከንሰን፤ እንደ እኔ አይነት ነገር ገጥሟት ነው መሰለኝ እንዲህ አለች “If I read a book and it makes my whole body so cold no fire can ever warm me, I know that is poetry.” (“መጽሐፍ አንብቤ የሰራ አካሌ በጣም ከቀዘቀዘና እሳት ፈጽሞ ሊሞቀኝ ካልቻለ፣ ያ የማነበው መጽሐፍ ግጥም እንደሆነ አውቃለሁ።”)

Read 322 times