Saturday, 12 March 2022 15:41

“የልብ ጠጋኙ ማስታወሻ” በወፍ በረር

Written by  አያልቅበት አደም
Rate this item
(0 votes)

 መግቢያ
በ2011 ዓ. ም. የሕክምና ባለሙያዎችን አደባባይ ያወጣ አስተዳደራዊና ሙያዊ ጥያቄ ነበር፡፡ ለጥያቄው መፍትሄ ለማፈላለግ በመስኩ በተለያየ ዘርፍ የሚገኙ ሙያተኞችን ያሳተፈ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት አንድ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በውይይቱ ላይ  ውስጥ የልብ ፅኑ ሕሙማን ስፔሺያሊስትና የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት ማዕከል ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሄለን ይገኙበታል፡፡ ማዕከሉ ያለበትን አስተዳደራዊ ችግር አስመልክቶ ከተናገሩት መካከል የሚከተለው ይገኝበታል፡- ‘’[. .  ማዕከሉ ከቢሮ ኪራይ ከሚያገኘው ገቢ በዓመት 2.5 ሚሊዮን ብር ግብር ይከፍላል፡፡ ለማኀበረሰቡ አገልግሎት የሚሰጠው ግን በነፃ ነው፡፡ እንደ ሕንድ ባሉ አነስተኛ ክፍያ በሚያስከፍሉ አገራት ሒሣብ ካሰላነው፣ ይህ 2.5 ሚሊዮን ብር ለ15ዐ ሕፃናት የልብ ቀዶ ሕክምና ሊውል ይችላል። [. . . ] ‘Consumables’ አላቂ እቃዎች ባለመኖራቸው ምክኒያት ብቻ ልጆቹን "ሌላ ጊዜ ኑ" እንላቸዋለን፡፡ በዓመቱ ሲመጡ ግን ... Operable የነበረው ችግር፣ Inoperable ይኾናል፡፡ . . " (በሣግና በእንባ ተይዘው ይቀጥላሉ)]
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ ማዕከሉ ለምስራቅ አፍሪካ ሊበቃ የሚችል አቅም እያለው በተንዛዛ ቢሮክራሲ ምክኒያት እግር ተወርች ታስሮ ይገኛል፡፡ (“Don’t push us!” በማለት ጠነን ያለ ማስገንዘቢያም አክለው ነበር፤ በንግግራቸው) ሙያተኛው ኀብረተሰቡን ለማገልገል እንደምን ባለ መነሣሣትና መሰጠት እንዳለ በእንባ ነበር የገለፁት፡፡ ከዚህ እንባ፣ ተማጽኖና እልህ ጀርባ ያለውን እውነተኛ ፍልሚያ የሚሳይ ነው የዛሬው ቁባችን፡፡
ጉዳዩ
“የልብ ጠጋኙ ማስታወሻ” በዶ/ር ፈቃደ አግዋር ተጽፎ፣ ነሐሴ 2013 ዓ.ም ለሕትመት የበቃ መጽሐፍ ነው፡፡ ዶ/ር ፈቃደ የልብ ቀዶ ጥገና ሐኪም ናቸው፡፡ መጽሐፉ ከልብ ጠጋኙ ማስታወሻ የተመረጡትን አሥራ ሰባት ንዑሣን ታሪኮች ይተርካል፡፡  የምስጋና እና ማጣቀሻ ገፁን ጨምር በ213 ገጾች የተቀነበበ ነው፡፡
“ቀዶ ጥገና” ወይስ “ቀዶ ሕክምና”?
“ቀዶ ሕክምና” እንጂ “ቀዶ ጥገና” አይባልም የሚሉ ተሟጓቾች አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ (ነፍስሄር) አሥራት ወ/የስ (ፕሮፍ.) በአንድ ወቅት ማብራሪያ ሰጥተው ነበር፡፡ የርሳቸው መከራከሪያ፣ የሰው አካል ይታከማል እንጂ እንደ መኪና ወይንም ሌላ የመገልገያ ቁስ አይበየድምና፣ ጥገና የሚለው ቃል አግባብ አይደለም የሚል ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ የቃላት አጠቃቀም ልዩነቶች በሌሎች የሙያ ዘርፎች ውስጥም አሉ፡፡ ለምሣሌ ጋሽ አስፋው ዳምጤ በሚጽፋቸው ጽሑፎች ውስጥ "የአማርኛ ሥነጽሑፍ" የሚል ቃል አይጠቀምም፡- “የአማርኛ ጥበበ ቃላት” ይላል እንጂ፡፡ በ197ዐዎቹ መጨረሻ በጋብቻ እና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ተከታታይ ጽሐፍ ያቀርቡ የነበሩት አሸናፊ ዘደቡብ አዲስ አበባ፤ Mental Masturbation ለሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “አዕምሯዊ ሽፍደት” የሚል አቻ አማርኛ ይጠቀሙ ነበር፡፡ ስለ ጋብቻ ስምረት ለመግለጽ ደግሞ “ቅንባሮተ ጉልቻ” የሚል ቃል ያዘወትሩ ነበር፡፡ መርቆርዮስ የተባሉ ፀሐፊ “ሽፍደት” ለእንስሳ እንጂ ለሰው መጠቀም አይቻልም፤ “ቀነበረ” ለድፎ ዳቦ እንጂ ለትዳር እንዴት ይኾናል የሚል ውዝግብ ውስጥ ገብተው እንደነበር ይታወሣል፡፡ አንድን ቃል እንደ ዓውዱ ፍቺውን በማጎልበት መጠቀም ቋንቋን ያሣድገዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ “አንዳንዴ ‘አዘለም አቀፈም . . .’ ” ብሎ ማለፍ ደግ ነው።
ወደ ተነሣንበት. . . .
ለማስታወሻው መፃፍ ቀዳሚው ወስዋሽ “እንደ ታላቅ ወንድሜ የማይህ” በማለት የገለፀው ዶ/ር ስንታየሁ ፀጋዬ ነው። “የምርምር ጽሁፎችን እንደምትፅፍ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ይኽን አዲስ ድንበር ከጀመርክ ጀምሮ ብዙ ትልልቅ ስራዎች እንደሰራህ እናውቃለን፡፡ ታዲያ ለምን እነዚህን ስራዎች ሰውኛና ተነባቢ በኾነ መልኩ ፅፈህ ለታሪክ የማታስቀምጠው?” ይኽ ወንድማዊ ውስወሳና “አንድ ልባችሁን አምናችሁ የሰጣችሁኝ . . .” ያላቸው ታካሚዎቹ ጀግንነት፣ ከዚህ ቀደም በአገራችን ከቶም ያልታሰቡና ከባህር ማዶ በሚመጡ በጎ አድራጊዎች ብቻ ይከወኑ የነበሩ ልዩ ልዩ የልብ ቀዶ ጥገናዎችን ያወጋናል፡፡
በእያንዳንዱ ቀዶ ጥገና ነፍስና ስጋው እንዴት እንደሚፈተን ለመረዳት አይከብድም፡፡ ሰው በሙያው እንዲህ ይቸነከራል? በግጥምና በዜማ በቃላት ድርደራ የስሜት ቋት ሆኖ የሚገለፀውን ልብ፣ ዶ/ር ፈቃደ እንደ አንድ ግሩም ቪላ፣ ከኮሪደር ሣሎን እየተንሸራሸረ፣ እየበረበረ ሽንቁር ይደፍናል፤ መስመር ይቀጥላል፣ ወሽመጥ ያስገባል፡፡
በእያንዳንዱ ርዕስ ሥር፣ የታማሚውን ስቃይና ጭንቅ፣ ባልረዘመ መስመር፣ በገዘፈ ስሜት ከታማሚው ነፍስ ጋር ያገናኘናል፡፡ አንዳንዴ ስለ ቤተሰባዊ ከባቢ ሁኔታ፣ ስለ እያንዳንዱ ሕሙም የልብ ችግር፣ የችግሩን መፍትሄ፣ ስለ ሕክምናው አጀማመር በአዘቦት ቋንቋ  ይናገራል፡፡
ፈቃደ የዶ/ር ስንታየሁን አደራ በሚገባ ተወጥቷል፡፡ መጽሐፉ እጅግ ሰዋዊ ነው። የግድ መጠቀስ ካለባቸው ሙያዊ ቃላት በቀር የደረተው ቃል (Jargon) የለም፡፡
በመጽሐፉ ዶ/ር ፈቃደ በዕምነት፣ በሞራል፣ በሙያ ሥነምግባር ሲፈተን ብቻ ሣይኾን ሲቸነከር እናየዋለን፡፡ ሰብዓዊነቱ ዋልታ የረገጠ ነው፡፡ “የመንታ ዘለላ”ን በስንት ጭንቅና ሰቀቀን ነው ያነበብኹት። ለነገሩ ያለ ዕንባ የጨረስኩት ትረካ ያለ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ ቀደም በአገራችን ያልተደፈሩ የልብ ቀዶ ጥገናዎችን ለማካሄድ ሲወስን የሚገባበት ጭንቀትና እንቅልፍ ማጣት ስሜት የሚሰቅዝ ነው፡፡  ራሱን የሚያበረታበትና ነገሮችን ለመሥራት ያለው ዕምነት እንደ ተራራ የገዘፈ ነው፡፡ “ዕውቀት ተግባር ላይ ካልዋለ፣ ሀገርን ካልጠቀመ፣ ተምሮስ መምጣት ለስምና ለወረቀት ፍጆታ መዋል የለበትም፡፡ [. . .] ለእኔም ኾነ ለዚህች አገር ይህ ይበቃል ብዬ ማሰብም መቀበልም አልፈለግሁም፡፡ ለውጥ፣ አዲስ ድል፣ አዲስ ታሪክ፣ አዎን በዚህ ትግል ውስጥ መሰበር፣ ክፉኛ መሰበር፤ አለመነሳት ሊከሰት ይችላል።” (ገጽ 90)
የዶ/ር ፈቃደ ጭንቅ ከቀዶ ጥገናው ክፍል ሥራውን አጠናቅቆ ስለወጣ ብቻ የሚቆም አይደለም፡፡ አንዳንዴ በአካል ከሆስፒታል ይወጣል እንጃ በመንፈስ እዚያው ነው። “ጀግናዬ” በሚል ርዕስ ከተረከልን በእንባ መሃል ፈገግ ያስደረገኝ ሃረግ አለ “[. . .] ሁሉም ነገር መልካም ነው። ማመን አቃተኝ። ወደማይናገረው ከፊቴ ወደተቀመጠው እህል ቃታዬን ያለ ርህራሄ መዘዝኩኝ፡፡ በጣም ርቦኝ ነበር፡፡ ተመገብኩ።” (ደሞ ቃታ መመዘዙ እንጂ)
ከምንም በላይ የታካሚዎቹ ሁኔታ ዕረፍት የሚነሣው ልብ ጠጋኝ በአንዱ ምዕራፍ እንዲህ ይለናል፡-፡ “ዛሬ ልጆቼን ከቤት ትቼ ስወጣ የወንድ ልጄ ሕመም እያሳሰበኝ ነው፡፡ [. . .] ልጆቼ ት/ቤት እንዳይሄዱ አድርጌ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ከተፈጠረ እንዲደወልልኝ አሳስቤ ከቤት ወጣሁ፡፡” (ገጽ፤110) በእንዲህ ዓይነት ስሜት ከቤት የወጣው ልብ ጠጋኝ፣ ከሥራ ወደ ቤት ሲመለስ የኾነውን የገለፀበት መንገድ የተሸከመውን ቀንበርና፣ ግራና ቀኝ ተሰቅዞ የተያዘበት ኹኔታ እጅግ ስሜታዊ የሚያደርግ ነው፡፡ “[. . .] ይሁን እንጂ መብራት ጠፍቶ ቤቱ በጨለማ ተውጦ ነበር፡፡
የወትሮው ጨዋታችንና ደስታችንን ሳናጣጥም የኔም የጭንቀት ሀሳብ ታክሎበት፣ ፍራሽ ላይ ተቃቅፈን ቁጭ እንዳልን፣ ሁላችንንም እንቅልፍ ይዞን ጭልጥ አለ፡፡” (ገጽ 121)
መጽሐፉን እያገባደድኹ በሄድኩ ቁጥር በአንድ ጉዳይ ጭንቀቴ እየጨመረ ነበር። በአንዳንድ ትረካዎቹ ይኽ ስጋቴ ከጫፍ እየደረሰ ከአንዴም ሁለቴ በእፎይታ ተገላግያለሁ፡፡ ምዕራፍ 16ን ግን ማለፍ አልቻልኩም፡፡ ይኽን ምዕራፍ ካነበብኩ በኋላ ቢያንስ ለሁለት ቀናት ያሕል መጽሐፉን ይዤ ከመቀመጥ በቀር ገልጦ የማንበብ ብርታት አልነበረኝም፡፡
በህንድ ቤንጋሉር ናራያና የልብ ሕክምና ማዕከል፣ በልብ ድካምና የልብ ንቅለ ተከላ ልዩ ስፔሻሊት፣ ታዋቂው ከፍተኛ የልብ ቀዶ ጠጋኝ ዶ/ር PV RAO “ክንፍ” ሥር፣ የልብ ቀዶ ጥገና ዕውቀት የቀሰመው ዶ/ር ፈቃደ አግዋር፤ የአገር ውስጡን የልብ ቀዶ ጥገና የትውልድ ቅብብሎሽ ወደ ቀጣይ ደረጃ ከፍ አድርጎታል፡፡
የዶ/ር ፈቃደ ማስታወሻ፤ በእንባና በሣቅ፣ በደስታና በሃዘን እስከመጨረሻው ይዞ የሚያጓጉዝ ነው፡፡ ፀሃፊው በመግቢያው የተሰጠውን አደራ፣ ትረካውን ሰዋዊ በማድረግ፣ ሙያና ሕይወቱን ቆርሶልናል፡፡ ለዚህም ባርኔጣዬን በአክብሮት አነሣለሁ። በቀጣይ የመጽሐፉ ሕትመቶች፣ የፊደል ለቀማ ሥራው እንደገና ቢታይ የሚል ጥቆማ ማከል እወዳለሁ፡፡
እግረ መንገድ
የኢትየጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት ማዕከል በቂ በጀት ባለማግኘቱ ምክኒያት ከአቅሙ በታች እየሠራ ይገኛል፡፡ ይኽ ሸክም የከበደው ወዳጄ ሰሎሞን ሹምዬ፣ ቀደም ሲል በFM አዲስ 97.1 ይተላለፍ በነበረው “ሠርገኛ ወጎች” የራዲዮ መርሃ ግብር፣ የአንድ ሣንቲም ፕሮጀክት በመቅረጽ ለልብ ሕሙማን፣ ለኩላሊት ሕሙማንና ለካንሰር ሕሙማን መርጃ የሚውል ገቢ ለማሰባሰብ ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡ ቢሮክራሲ እድሜው ይጠርና ተሰናከለ፡፡
ይኽን ሃሣቡን ከግብ ካላደረሰ አሁንም ዕረፍት የማይኾንለት ወዳጄ፤ በ#ገበያኑ; ዩቲዩብ ቻናል @Gebeyanu ዘወትር ማክሰኞ በሚተላለፈው “ሠርገኛ ወጎች” መርሃ ግብር፣ የእርዳታ ማሰባሰቢያ ጥሪ በማስተላለፍ ላይ ይገኛል፡፡ ለ”ሠርገኛ ወጎች” መርሃግብር መደገፊያ እንዲውሉ በጎ ፈቃደኞች የሚለግሷቸው ስቲከተሮች ለዚሁ በጎ ዓላማ እንዲውሉ ኾኗል፡፡  
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 333 times