Print this page
Saturday, 12 March 2022 15:42

የካህሊል አማልክት ‹‹Beloved prophet››

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(1 Vote)

   ‹‹እንግዲህ ታሪኬን ሰምተኸዋል፡፡ እናም ቦስተን የመገኘቴ ምሥጢር ለከተማዋ ባለኝ ፍቅርም ሆነ ለኒው ዮርክ ባለኝ ጥላቻ መነሻነት አይደለም፡፡ ይልቁንስ እዚህ የመገኘቴ ምሥጢር ግሩም ድንቅ ወደ ሆነ የሚያስጎመጅ ነገዬ የምትመራኝ፣ በሐብትም ሆነ በዕውቀት ልቄ እንድገኝ መንገዴን የምትጠርግልኝ መልዓክ አከል እንስት፣ አዎ ያቺ ሴት እዚህ በመሆኗ ምክንያት ነው፡፡››
         
                 በካህሊል ጅብራን ሕይወት ውስጥ የሜሪ ኤልዛቤት ሀስከል ድርሻ እስከምን ድረስ ነው የሚለው ከጥርጣሬ፣ ከአሉባልታ ባለፈ ለመግለጽ የሚፈትን ነበር፡፡ ዓለም ሁለቱ ሰዎች በካህሊል የኒው ዮርክ ስቱዲዮም ሆነ በኬምብሪጅ የሜሪ ትምህርት ቤት በተደጋጋሚ ስለመገናኘታቸው፣ ስለ ቦስተን ሽርሽሮቻቸው፣ ስለ ፍንደቃዎቻቸው፣ ስለ ቀዳሚዎቹ ዓመታት ተስፋ አስቆራጭነት፣ ሀሴት፣ ብጥብጥ እና ጥብቅ ጉድኝታቸው የሚያውቅበት መንገድ አልነበረውም፡፡ እነዚህ የደብዳቤዎች ስብስቦች እስኪታወቁ ድረስ ስለ ካህሊልና ሜሪ ሀስከል ደፍሮ ለመናገር የሚያስችል መነሻ ማግኘት አልተቻለም፡፡
የእነዚህ ሁለት ሰዎች የደብዳቤዎች ስብስብ የተደረሰበት ከጅብራን ሕልፈት በኋላ ነው። መጀመሪያ [የካህሊል ደብዳቤዎች] በራሷ በሜሪ ሀስከልና በጅብራን ረዳት ባርባራ ያንግ በካህሊል ስቱዲዮ በጥንቃቄ በሣጥን ተደብቀው ተገኙ። በዚያች ሣጥን የታጨቁት ደብዳቤዎች ሜሪ ከካህሊል ጋር የነበራትን የሕይወት ዘመን ግንኙነት የሚያመሰጥሩ ሆኑ፡፡ ሜሪም በበኩሏ ከካህሊል ይደርሷት የነበሩትን ደብዳቤዎች በጥንቃቄ አስቀምጣለች፡፡ ካህሊል እንደ እርሷ ሁሉ ደብዳቤዎቿን በቅጡ ሰብስቦ ስለማስቀመጡ የምታውቀው ነገር ስላልነበራት፣ የራሷን የእጅ ጽሕፈት የተሸከሙ ደብዳቤዎቿን ስታገኝ የተሰማትን ሀዘን፣ ደስታ፣ የስሜት መደበላለቅ ጥልቀት ማንም ሊገምተው አይችልም፡፡ ሜሪ ደብዳቤዎቻቸው እርሷ ስለ ካህሊል የፈነደቀችባቸውን መደነቆች፣ ዓለም በዘመናት ሂደት የሚካፈልበት ለነገ በጥንቃቄ የተሰነዱ ውድ ሀብቶች መሆናቸውን ታምናለች፡፡ መጀመሪያ ደብዳቤዎቹን የዕድሜ ዘመኗን አመሻሽ ወደ ኖረችበት ሳቫናህ ጆርጂያ ወሰደቻቸው፡፡
ካህሊል በ1931 ዓ.ም በኒውዮርክ ከተማ ውስጥ ሲሞት የ48 ዓመት ጎልማሳ ነበር። በጊዜው በአሜሪካና በመካከለኛው ምስራቅ እንደ ሰዓሊ፣ ገጣሚና ትንንሽ ጥቋቁር መጻሕፍት ደራሲነት መጠነኛ ዝና አካብቷል፡፡ ከሕልፈቱ በኋላ ግን እነዚያ ሚጢጢ የሚመስሉ The Madman, The Forerunner, The Prophet, Sand and Foam, እና Jesus Son of Man የተሰኙ መጻሕፍቱ፣ ዘወትር የሚያድግ የንባብ ፍላጎት ከዓለም ዙሪያ መሳብ ጀመሩ፡፡
ማንም ሊገምት በማይችለው መጠን ዛሬም ከሕልፈቱ አርባ ዓመታት በኋላ በአሜሪካ መጻሕፍቱ በዓመት በአማካይ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ቅጅዎች ይሸጣሉ። በኮሌጆች ውስጥ ከኢየሱስና አያን ራንድ እኩል አባባሎቹ ይጠቀሱለታል፡፡ ቃላቶቹ የማጥመቅ፣ የጋብቻ፣ የግንዘት መነባንቦች ውስጥ ተካትተውለታል፡፡ የሚሊዮናት ልቦች ማለሉት፡፡ ‹The Prophet› ከታተመ ከሀምሳ ዓመታት በኋላ በድምሩ አራት ሚሊዮናት ቅጂዎችን ከመሸጥ አልፎ ዛሬም በየሳምንቱ ተጨማሪ ሰባት ሺህ ቅጂዎች ይቸበቸባል፡፡
ሲሞት እንደ ሰዓሊም መጠነኛ ዝና ተቀዳጅቶ በርካታ ስዕሎችንም አበርክቷል። ብዙዎቹ ስዕሎቹ በታላላቅ ቤቶች ግድግዳዎች ላይ ማረፍ ሲታደሉ፣ አምስት የሚሆኑት ደግሞ በኒው ዮርክ ሜትሮፖሊታን ሙዝየም ስብስቦች ውስጥ ተካትተውለታል፡፡
በ1931 ዓ.ም ሲሞት በባለ አንድ ክፍል ስቱዲዮ አፓርትመንት፣ 51 ምዕራብ አስረኛው፣ ኒው ዮርክ ውስጥ ይኖር ነበር። በዚህች ክፍል ውስጥ ለሀያ ዓመታት ኖሮባታል፡፡ ክፍሏ በመጋረጃ የተሸፈነች፣ ራቅ ራቅ ብለው የተቀመጡ ሶፋዎች፣ አነስተኛ ጠረጴዛ፣ ተንቀሳቃሽ ወንበሮችና ምድጃ ያቀፈች ሰፋ ያለች ናት፡፡ ካህሊል ቤቷን ‹‹በኣት ነች›› ይላታል፡፡
የጅብራን ጤና የሚያስመካ ሆኖ አያውቅም፡፡ ለወዳጆቹ በሚጽፋቸው ተከታታይ ደብዳቤዎች ላይ አዘውትሮ፣ ጉንፋን፣ ኢንፊሉዌንዛ፣ የልብ ምት መዛባት፣ የሆድ ሕመም፣ የጥርስ በሽታና ከመሞቱ በፊት ለበርካታ ጊዜያት ልዩ ልዩ በሽታዎች ያጠቁት እንደነበር አትቷል፡፡ ይህ ሁሉ ተከታታይ የማይጨበጥ ሕመም ስለምን ያጠቃው እንደነበር የምናውቀው ነገር የለም። ወደ ሞት በተጣደፈባቸው የመጨረሻዎቹ ዓመታት ሕመሙ ጭራሽ መስራት ከልክሎታል፡፡ ስቃዩ ወዳጆቹን ሁሉ ተስፋ አስቆርጧል፡፡ አባክኖታል፡፡
ለወትሮውም ለምግብ ግድ ያልነበረው ካህሊል፣ በሕመሙ ጭራሹኑ የምግብ ፍላጎቱ ቀንሶ፣ መጣጣ የነበረውን ሰው ይበልጥ አቀጨጨው፡፡ ወደ ሕክምና እንኳን አይሄድም፡፡ ቢሆንም ሲጨንቀው ጥቂት የሕክምና ባለሙያዎችን አማክሯል፡፡ አንደኛው ሐኪም ቢያንስ ለጊዜው የቅብና የስነ ግጥም ሥራዎቹን አቁሞ በሕይወት የቀረች ብቸኛ እህቱ ቤት፣ ቦስተን እረፍት ማድረግ እንዳለበት ምክሩን ሰጥቶታል። እህቱ ማሪያና ማረፊያውና መሸሸጊያው ነበረች፡፡ ካህሊልም ምክሩን ተቀብሎ ይህ የሕይወት ዘይቤ ለውጥ፣ ለጤናው መሻሻል ሊያመጣ ይችል በሚል በ1925 ዓ.ም የመኖሪያ ክፍሉን ለሌላ ሰው አከራይቶ፣ ከኒው ዮርክ ወደ እህቱ ቤት ቦስተን ተዛወረ።
የልብስ ስፌት ባለሙያ የሆነችው እህቱ ማሪያና፣ ወንድሟን መንከባከብ ያስደስታታል፡፡ ጤናው እንዲሻሻል አጥብቃ ትመኝ ነበር፡፡ የሚወዳቸውን የሊባኖስ ምግቦች ታዘጋጅለታለች፡፡ እሱን ፍለጋ የሚመጡ የሀገሩ ልጆችንም ታስተናግዳለች። በበጋው አየር ጥቂት ወጣ እያለ በእግሩ እንዲንሸራሸር ታበረታታዋለች። እርስ በእርስ ከልብ ይዋደዳሉ፡፡
በ1928 ዓ.ም ካህሊል በሪህ በሽታ ተጠቃ። በመጋቢት 1929 ዓ.ም ካህሊል አሁንም እንደገና ያላወቅነው በሽታ ለከፈው። በ1930 ዓ.ም ጭራሽኑ ብሶበት ዘወትር የሚመኘው የመልካም ጤንነት ሁኔታ ፈጽሞ የማይመለስ መሰለ፡፡
ብዙዎቹ የካህሊል ወዳጆች ለስዕሎቻቸው መነሻ የሚሆኑ ሞዴሎችን የሚጋሩት፣ ሙዝየሞችን አብረውት የሚጎበኙ፣ ሰዓሊያን ነበሩ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በእርሱ ብሩሽ የተሳሉ፣ የስነ ግጥም መዓዱን ለመታደም የሚመጡ ወይ ደግሞ በሚናገራቸው ቃላት የብዙዎችን ልብ ማስደንበር የሚችል ይሄን ዓይናፋር ሰው በሚገባ ለመረዳት የሚመኙ ነበሩ፡፡ ገጣሚያ፣ ደራሲያን፣ የልጅነት ጎረቤቶቹ፣ ከሁሉም መደብ የተወጣጡ ሶሪያዊያን ጭምር ከወዳጆቹ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የሜሪ ሀስከል ግን ይለያል፡፡ የነበራቸውን ጥብቅ ቅርርብ ከእህቱ ማሪያና ውጪ ሌላ ማንም ሰው አያውቅም፡፡ ሜሪ ሠላሳ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ የጅብራን ሕይወት አካል ሆናለች፡፡ በሞተ ጊዜ የነበረውን ጥሪት ሁሉ ያለእረፍት እየታከተች ስራው ላይ ብቻ እንዲያተኩር ትረዳው ለነበረችው እህቱ ማሪያና፣ ለሜሪ ሀስከልና ለተወለደባት፣ ሁለመናው ለተሰራባት፣ አየሩን፣ አፈሩን፣ ቀለሙን ዙሪያ ገባዋን በመናፈቅ ዘወትር እንደቃተተላት ለኖረው፣ ግን በድኑ ብቻ ለተመለሳላት የልጅነት መንደሩ ብሻሪ ትቶላቸው አልፏል፡፡
ማሪያና እና ሜሪ ዘወትር ጥብቅ ቅርርብ ነበራቸው፡፡ መዋደድና መከባበር መሀላቸው ሰምሯል፡፡ የተሰሩባቸው ዓለማት ውስጥ ጉልህ የሚባል ልዩነት ቢኖርም፣ አንዳቸው ለአንዳቸው ይዋደቃሉ፡፡ ሁለቱም ሴቶች ገር፣ ንጹህ ልብ የታደሉ፣ ያልተወሳሰበ ጣዕም ያዳበሩ ነበሩ፡፡ አላማቸው አንድና አንድ ብቻ! ካህሊልን ማገዝ፣ በሚፈልገው ማናቸውም መንገድ ራሱን መግለጽ፣ ስኬትን መቀዳጀት ይችል ዘንድ ዘወትር ከጎኑ መቆም፡፡ ካህሊልን የማላቅ ሕብረታቸው የጠነከረ ነበረ፡፡
ሜሪ በቦስተን በተከናወነው የካህሊል ጅብራን ቀብር ላይ ተገኝታለች፡፡ ማሪያና በዚያ ለተሰባሰቡት ሁሉ የካህሊል ወዳጅ [ምናልባት ተራ ጓደኛ] እንደነበረች አስተዋወቀቻት፡፡ እዚያ የነበሩት አብዛኞቹ ሲያነፈርቁ ሜሪ ደስተኛ መስላ ቀረበች። የጂብራንን የዓመታት ውስጣዊ ትግል፣ ወደ የሚጽፈው ነገር ሁሉ አካል የሆነው ስም የለሹ ቅዱስ መንፈስ ለመጠጋት የሚያደርገውን መፍገምገም በሚገባ ታውቀዋለች፡፡ ሜሪ የጅብራን ሕልፈት ለወዳጆቹ ልብ የሚሰብር ቢሆንም፣ በእንባ ሊቀበሉት የተገባ እንዳልሆነ ራሷን አሳምናለች፡፡ ቢያንስ በሕልፈቱ ዘመኑን መሉ ሊጠጋው ሲማስንለት ከነበረው መንፈስ ጋር ተገናኝቷል፡፡
ካህሊል ጅብራን በሊባኖስ ብሻሪ በመጋቢት 6፣ 1883 ዓ.ም ተወለደ፡፡ ቤተሰቦቹ በሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ስር የሆነቸው የማሮናይት ክርስትና ተከታዮች ነበሩ፡፡ ለሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ተገዢ ቢሆኑም በሶሪያዊ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓታቸውና በሚያገቡ ካህናቶቻቸው የሚለዩ ክርስቲያናዊ ማኅበረሰቦች ናቸው፡፡
አባቱ ገበሬ፣ ጠንካራ መስህብ ያለው በትምህርት ያልገፋ፣ ዘወትር ሰካራም፣ ጠብ ፈላጊ፣ ባለቤቱንና ልጆቹን የሚጨቁን ሰው ነበር፡፡
በአንጻሩ እናቱ ካሚላ ራሀሚ፣ የካህን፣ አብዱል ሰላም ራህሚ የተባለ ሰው አግብታ ፒተር የተባለ ልጅ የወለደች ፈት ሴት ነበረች፡፡ ምንም አልተማረችም፡፡ ግን የቤተሰባቸው ቁጥር ካህሊልን እና ሁለቱን እህቶቹን ማሪያናን ጨምሮ ወደ ስድስት ሲያድግ፣ ከባልየው ይልቅ ለተሻለ ሕይወት መትጋት መረጠች፡፡
በ1895 ዓ.ም ቤተሰቡ የ18 ዓመቱን ፒተር፣ የአስራ ሁለት ዓመቱን ካህሊልን እና ሁለት ለጋ ሴት ሕጻናትን አካትቷል፡፡
አባትየው ለወትሮውም የማታወላዳ ገቢውን በአብዛኛው የሚያውለው ለመጠጥ ብቻ ነው፡፡ ምግብ በቂ ሆኖ አያውቅም። ታዳጊዎቹ ልጅነታቸውን ያሳለፉት በሚያሰቅቅ ድህነት ውስጥ ዘወትር በጭንቀትና በጠብ የተመላ ከባቢ ነበር፡፡
ጅብራን በማርሳርኪስ ገዳም ዋሻ አካባቢ ለብቻው ቁጭ ብሎ በእርሳስና አንዳንዴም በከሰል በመሳል ያሳልፋል፡፡ ብቸኝነቱን አጥብቆ ይወደዋል፡፡ አንዳንድ የሕይወት ታሪኩን የዘገቡልን ጸሐፍት ከሰባት ወይም ስምንት ዓመቱ ጀምሮ የሊኦናርዶ ዳቪንቼና የሚካኤል አንጀሎ ሥራዎች ተጽዕኖ አድርገውበታል ይላሉ፡፡ ግን ልጅነቱ በምን ዓይነት አሰቃቂ ሕመም እንዳለፈች ለምናውቅ ለእኛ ይሄን ለመቀበል አስቸጋሪ ይሆንብናል። በአካላዊ ትምክህትና ጀግነነት የሚያምነው አባቱ፣ ስዕሎችን ሲነድፍ ባገኘው ጊዜ ሁሉ ካህሊልን ይደበድበዋል። በዚህ ጊዜ ለልጆቿ የተሻለ ሕይወትን የምትመኘው እናቱ ስለስደት ማሰብ ጀምራለች፡፡
በ1894 እናቱ ካህሊልን እና አራት ልጆቿን ይዛ አሜሪካ ደረሰች፡፡ (አንዳንዶች ዘመኑ ሰኔ 1895 ነው ይላሉ) ሆኖም አባትየው የስደቱ አካል አልሆነም፡፡ ምናልባት የስደት ጉዞው የተከናወነው አባትየው እስር ቤት ውስጥ እያለ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሆኖም ሜሪ ካህሊልን ዋቢ አድርጋ በግለ ማስታወሻዋ ላይ እንደዘገበችው፤ አባትየው በጉዞው ውስጥ ያልተካተተው በሌላ ምክንያት ነው፡፡
እንግሊዝኛ ቋንቋ መናገርም ሆነ የሀገሯን ቋንቋ መጻፍ ማንበብ ለማትችለው እናት የለመደችውን ያደገችበትን ቀዬ ጥላ ባህር ተሻግራ እንግዳ መሬት ላይ መገኘት ሁኔታዎችን ተስፋ አስቆራጭ ያደረጉባት ይመስላል፡፡ ቤተሰቡ ከኒው ዮርክ ተነስቶ ወደ ቦስተን በመቀጠል በቦስተን ‹ቻይና ታውን› አካባቢ ማረፊያውን አደረገ፡፡ በቦስተን ኸድሰን መንገድ አካባቢ አነስተኛ የሶሪያ ማኅበረሰብ ነበረ፡፡ ቤተሰቡ እዚያው አካባቢ ኢንቦሮ መንገድ አጠገብ ሰፈረ፡፡
እዚህ ካረፉ በኋላ ሁሉም በተገኘው የሥራ መስክ ሲሰማሩ፣ ትንሹ ካህሊል ወደ ትምህርት ቤት ገባ፡፡ ከሦስት ዓመታት በኋላ ወደ ቬሩት ተመልሶ በማሮናይት ካህን የሚመራ አል ሂክመት ትምህርት ቤት ገባ፡፡ ካህሊል በጊዜው የበለጠ በአረብኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ስነጽሁፋዊ ትምህሮች ላይ ያተኮረ ይመስላል፡፡ ተማሪዎች እንዲማሯቸው ከሚጠበቁት ትምህርቶች ይልቅ የሚፈልጋቸው ላይ ብቻ መርጦ ተመስጧል፡፡
ጂብራን በዚያው ዓመት ክረምቱን በ ብሻሪ አሳለፈ፡፡ በዚህ ጊዜ አባቱ የመጠጥ ልክፍቱ ብሶበት ስለነበር አብረውት ለመኖር የሚቻል አልሆነም፡፡ እዚያ የነበረውን ጊዜ በአንደኛዋ አክስቱ ቤት ተጠልሎ ተወጣው።
በ1899 የመጸው ወራት እንደገና ወደ ቦስተን ተመለሰ፡፡ በቦስተን ወደ ትምህርት ቤትም ሳይሄድ፣ ለሥራም ሳይሰለፍ ሥዕልና ጽሑፎቹ ላይ ብቻ ማተኮርን ወደደ፡፡ በቀጠሉት ሁለት ዓመታት እናቱና ሁለቱ እህቶቹ በልብስ ሰፊነት ሥራ ላይ ሲሰማሩ፣ ወንድሙ ፒተር ሱቅ ውስጥ ተፍተፍ ይል ጀመር፡፡ ካህሊል አሁንም የንድፍና የጽሁፍ ሥራዎቹ ላይ ብቻ ተጥዷል፡፡
በ1902 ዓ.ም እህቱ ሱልጣና በሳንባ ነቀርሣ ምክንያት ሕይወቷ አለፈ፡፡ በ1903 ዓ.ም ፒተርም በዚሁ በሽታ መነሻነት እስከወዲያኛው አሸለበ፡፡ በዚያው ዓመት በሰኔ ወር እጅጉን የሚወዳት እናቱ በካንሰር በሽታ አንቀላፈች፡፡ (በዚህ መጽሐፍ የውስጥ ገጾች እንደሚነበበው ከጥቂት ዓመታት በኋላ የእህቱ ማሪያና የልብ ወዳጅ የሆነችው ሜሪ ሀስክል፣ እነዚህ ሦስት ተከታታይ ሞቶች በካህሊል ጅብራ ሥነልቦና ላይ ስለፈጠሩት ጠባሳ እህቱን ጠይቃታለች፡፡)
ማሪያና በሥራዋ ላይ ቀጥላ በወር በምታገኛት ስድሳ ዶላር፣ የካህሊልና የእርሷን ወጪዎች ለመሸፈን መታገል ቀጠለች፡፡ በ1904 ዓ.ም ፍሬድ ሆላንድ ዴይ የተባለ የታወቀ የፎቶግራፍ ባለሙያ ካህሊል የስዕል ሥራዎቹን ያሳይበት ዘንድ ስቱዲዮውን ፈቀደለት፡፡ ዴይ ስቱዲዮውን ከመፍቀድ በተጨማሪ ትውውቃቸውን ተጠቅሞ ለሜሪ ኤልዛቤት ሀስክል፣ የዚህን የ21 ዓመት ታዳጊ የስዕል ሥራዎች መጥታ እንድትጎበኝ ግብዣውን ጻፈላት፡፡ በዚህ ጊዜ በ1897 ዓ.ም ከእህቷ ጋር ያቋቋሙት ሀስከል-ዲን የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት አስተዳዳሪ ነበረች፡፡
በግንቦት 10 ቀን 1904 ዓ.ም የ31 ዓመቷ ሜሪ ሀስከል፣ የታወቀው የባንክ አስተዳዳሪና የኮንፌደሬት አርሚ ዘማች ልጅ ሜሪ ሀስከል እና ካህሊል ጅብራን በሚስተር ደይ ስቱዲዮ ተገናኙ፡፡
ሜሪ በታህሣሥ 11፣ በ1873 ዓ.ም በኮሎቢያ ሳውዝ ካሮሊና ተወለደች። አምስት እህቶችና አራት ወንድሞች ነበሯት፡፡ አባቷ አሌክሳንደር ሺቬዝ ሀስከል ይባላሉ፡፡ ማዕረጋቸው ብዙ ቢሆንም ከእርስበእርስ ጦርነቱ በኋላ ቤተሰቡ ድሃ ሆኗል፡፡ ሕይወት ፈትናቸዋለች፡፡ ያም ሆኖ ሜሪ ከልጅነቷ ጀምሮ ያዳበረችው ገንዘብ የመናኘት የለጋስነት ልምዷ እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ አብሯት ዘልቋል፡፡ ለራሷ የሚሆን ነገር መግዛትም ሆነ በባንክ ማስቀመጥ አይሆንላትም፡፡
መልበስ ቢያስፈልጋት እንኳን ትራቆታታለች እንጂ ገንዘቧን ለዚህ ዓላማ አታወጣም፡፡ ገንዘቧ የሆኑ ወጣት ሰዓሊያንን ሸክም ለማቅለልና ሥራቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ለማስቻል ወይም መማር ያልቻሉ ታዳጊዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ከዋለ ደስታዋ ወደር አይኖረውም፡፡ በዌስሌይ ተማሪነት ዘመኗ ዘመዶቿ ሊጎበኟት ሲመጡ ለምሳ ግብዣ የሚወጣውን ገንዘብ ለምና በጥሬው ተቀብላ መጻሕፍትን ታድንበት ነበር፡፡
በ1897 ዓ.ም ከተመረቀች በኋላ ቦስተን ከእህቷ ሉዚያና ጋር መኖር ጀመረች። በ1902 ወይም 03 እህቷ ሉዚያና ሬናልድ ዳሊ የተባለን ግለሰብ ለማግባት ቦስተንን ስትሰናበት ሜሪ የትምህርት ቤቱን የአስተዳዳሪነት ቦታ ተረከበች። በመጀመሪያው የግኙነታቸው ዕለት በሚስተር ዴይ ስቱዲዮ ካህሊል በንድፍ ሥራዎቹ ውስጥ ምን ዓይነት ጭብጦችን እንደፈለቀቀ ለሜሪ አብራርቶላታል፡፡ ሜሪ ከዚያ ወጣት የጥበብ የሰው የሆነ ነገሩ ሁለመናዋን ገዝቶታል፡፡
በማግስቱ ኤሚል ሚሼል ለምትሰኝ የትምህርት ቤታቸው ፈረንሳይኛ ቋንቋ መምህርት፣ ስለ ካህሊል ጅብራን አወራቻት። ሚሼል ተወዳጅና ጨዋ ሴት ነበረች፡፡
ከስዕል አውደ ርዕዩ መጠናቀቅ በኋላ ጂብራን የስዕል ሥራዎቹን ሜሪ በምታስተዳድረው ትምህርት ቤት ውስጥ የማሳየት ዕድል አግኝቷል፡፡ በዚያም ሜሪ ሚሼልን ከካህሊል ጋር አስተዋውቃታለች። ሚሼል መስህብ ያላት፣ የተረጋጋች ደግ ሴት ነች፡፡ ካህሊል በተደጋጋሚ የፊት ገጽዋን ሥሎታል፡፡ በኋላ ለትምህርት ወደ ፓሪስ ባቀናበት ጊዜ ጎብኝታዋለች። ከተደጋጋሚ የፓሪስ ግንኙነታቸው በኋላ ሁለቱም ሰዎች በተናጠል ለሜሪ ሀስከል ደብዳቤዎችን ጽፈውላታል፡፡ ጭብጣቸው ሚሼል የካህሊል አካላዊ እና አዕምሯዊ የጤና ሁኔታ፣ ካህሊል ሚሼልን በማግኘቱ ስለመፈንደቁ፣ ስለጤናዋ ሁኔታ ያሉትን ስጋቶች ያካትታል።
ካህሊልና ሜሪ ሁለቱም ዓይናፋርና ቁጥብ ቢሆኑም፣ የትምህርት ቤቱ የስዕል አውደርዕይ ይበልጥ አቀራርቧቸዋል፡፡ ካህሊል ዘወትር ረቡዕና አርብ ምሽት ሜሪን መጎብኘት ጀመረ፡፡ ሆኖም ያለሜሪ ግብዣ ፈጽሞ ዝር ብሎ አያውቅም፡፡ በ1904 ዓ.ም ሜሪ ካህሊልን ወደ ፓሪስ ልኮ ማስተማር የሚል ሐሳብ ብልጭ አለላት፡፡
በእቅዱ ላይ ከእህቱ ማሪያና ጋር ከተወያዩበት በኋላ ካህሊልን የትራንስፖርት ወጪውን ልትችልና በወር ሰባ አምስት ዶላር እንደምትልክለት ቃል ገብታ አሳመነችው። ሀሳቡን ተቀብሎ በሰኔ 13 1908 ዓ.ም ፓሪስ ደረሰ፡፡ ከሜሪ ቀድማ ቃል ባስገባቻት መሰረት፣ ሚሼሊን ካህሊልን አንዲት ክፍል ቤት በማፈላለግ አገዘችው፡፡
ካህሊል በፓሪስ እያለ የጎበኘችው ሌላኛዋ የሜሪ ጓደኛ ቻርሎቴ ቴለር ነበረች፡፡ የመምረጥ መብት ተሟጋችና የተውኔት ጸሐፊ የሆነችው ቻርሎቴ፣ በወንድ የብዕር ስም ያልተሳኩ የተውኔት ድርሰቶችን ጽፋለች፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ሜሪ ከካህሊልም በተጨማሪ ቻርሎቴንም በገንዘብ ረድታታለች፡፡ ቻርሎቴም በመቶዎች የሚቆጠሩ ረጃጅም ስለጥበብ፣ ድራማ፣ ፍልስፍናና ታሪክ የሚያትቱ ደብዳቤዎችን አዥጎድጉዳላታለች፡፡
ቻርሎቴ ስለ ካህሊል የፓሪስ መሻሻሎችም ደብዳቤዎችን ጽፋለች፡፡ ቻርሎቴ በ1908 ዓ.ም በተደጋጋሚ፣ በ1909 የበልግ ወቅት ደግሞ አልፎ አልፎ ትጎበኘው ነበር፡፡ በሰኔ ወር 1910 ከልጅነት የሊባኖስ ወዳጆቹ አንዱ አሚን ሪሃኒ ፓሪስ ደረሰ፡፡ ሁለቱ ተያይዘው ሙዝየሞችን ለመጎብኘት ወደ ለንደን አቀኑ።
ጅብራን ጥቅምት 28 ቀን 1910 ዓ.ም ኒው ዮርክ ደርሶ በማግስቱ ወደ ቦስተን ተጓዘ። ጓዙን ከእህቱ ማሪያና ጋር ካደረሰ በኋላ ሜሪን ያገኛት ዘንድ ወደ እርሷ ተጣደፈ። በየካቲት 12፣ 1908 ለጓደኛው አሜን ጉሬይብ በጻፈለት ደብዳቤ
‹‹And now since you have heard my story you will know that my stay in Boston is niether due to my love this city, nor to my dislike for New York. My being here is due to the presence of a she -angle who is ushering me toward a splendid future and paving for me the path to intellectual and financial success.››
‹‹እንግዲህ ታሪኬን ሰምተኸዋል፡፡ እናም ቦስተን የመገኘቴ ምሥጢር ለከተማዋ ባለኝ ፍቅርም ሆነ ለኒው ዮርክ ባለኝ ጥላቻ መነሻነት አይደለም፡፡ ይልቁንስ እዚህ የመገኘቴ ምሥጢር ግሩም ድንቅ ወደ ሆነ የሚያስጎመጅ ነገዬ የምትመራኝ፣ በሐብትም ሆነ በዕውቀት ልቄ እንድገኝ መንገዴን የምትጠርግልኝ መልዓክ አከል እንስት፣ አዎ ያቺ ሴት እዚህ በመሆኗ ምክንያት ነው፡፡››
***
ከአዘጋጁ፡- (ለመጽሐፉ በአርታኢዋ ከተጻፈ መግቢያ ላይ ተወስዶ፣ ለጋዜጣ እንዲመች ተስተካክሎ የቀረበ፤ 1971 እ.ኤ.አ)   Read 1630 times