Saturday, 19 March 2022 10:45

የህዝብ እንባ ጠባቂ ብልፅግና አራት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ እንዲሠራ አሳሰበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  ባለፈው ሳምንት የመጀመሪያ ጉባኤውን ያካሄደው ብልፅግና ፓርቲ፣ ሃገሪቱ አሁን የተደቀኑባትን አራት መሰረታዊ ፈተናዎችን እንዲሰራ የህዝብ እንባ ጠንቂ ተቋም በመደበኛና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያከናወነውን የቁጥጥርና ምርመራ ስራን መሰረት አድርጎ ባወጣው መግለጫው አመልክቷል፡፡
የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዝርዝር ጉዳዮችን በዳሰሰበት መግለጫው የህግ የበላይነትና ማስከበር ቀዳሚ ተግባር በማድረግ፣የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ቁጥጥርንና ድርቅን መከላከል እንዲሁም የጠራ ፖሊስና ማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎችን መተግበር ላይ የብልፅግና መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የመንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂን በተመለከተ ባለፉት ሶስት ዓመታት የታዩ የህግ የበላይነት አለመከበር ችግሮች፣የኑሮ ውድነትና በመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ መፋዘዘዞችና የውስጥ ችግሮች ግልፅ ካለመሆን የሚመነጩ ናቸው ያለው ተቋሙ፤ ይሄን ለመፍታት የጉባኤውን ውሳኔዎች ጨምሮ ሃገሪቱ በግብርና በትምህርት በጤና፣በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በአጠቃላይ በማህበራዊን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች በመንገድ ተግባራዊ መሆኑን ያመላከተው የተቋሙ መግለጫ መንግስት ይሔን ሃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ አለመሆኑን አመልክቷል፡፡
የመንግስት የህግ የበላይነት ለማስጠበቅ ውሳኔ ከማሳለፍ ባሻገር ተግባራዊነቱ ላይ ሊበረታ እንደሚገባውና በተለይ በአፋር ፣በትግራይ፣በአማራ ፣በቤኒሻንጉል ጉምዝ ተፈናቅለው ያሉ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ አበክሮ የሚሰራ ግብረ ሃይል በማቋቋም በአፋጣኝ ወደ ተግባር እንዲገባ እንዲሁም የፀጥታ መደፍረስ ባለባቸው አካባቢዎች መንግስት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ አሳስቧል፡፡
በሶማሌ፣ኦሮሚያና ደቡብ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ አስመልክቶም በጊዜያዊነቱ መንግስት እርዳታ ማቅረብ ላይ አበክሮ እንዲተጋ፣ በዘላቂነት ደግሞ ድርቅን መቋቋም የሚያስችሉ ፖሊስና ስትራቴጂዎችን ቀርፆ በአፋጣኝ ወደ ተግባር እንዲገባ ጥሪ አቅርቧል-ተቋሙ፡፡
የኑሮ ውድነት በተለይ የመሰረታዊ ፍጆታ ሸቀጦች የዋጋ ንረትን በተመለከተም እየተከናወኑ ካሉ ጊዜያዊ መፍትሄ አምጪ ስራዎች ባሻገር አጠቃላይ  ማይክሮ ኢኮኖሚ የሚመራበት ግልጽ ፖሊሲ እንዲዘጋጅ፣አርሶ አደሮቹ ለፋብሪካ ግብአት የሚሆኑ መርሆች ላይ እንዲሠሩ ማበረታታት፣ በአርሶ አደና በግል ባለሃብቱ ያልተሸፈኑ ክፍተቶችን የመንግስት እርሻ ጣቢያዎችን በማቋቋም ወይም በክልል መንግስት የሚተዳደሩ የልማት ድርጅቶች በግብርናው ዘርፍ ተሰማርተው ክፍተቱን እንዲያሟሉ ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ እንዲፈጥር በአጠቃላይ የሃገሪቱ የዘይት ፍጆታ 95 በመቶው ከውጭ የሚገባ መሆኑን የጠቀሰው ተቋሙ፤ መንግስት ይሄን ለማስተካከል ወደ ውጪ የሚላኩ ቅባት እህሎች በተለይ የአኩሪ አተር፣ ሰሊጥና ሱፍ እዚሁ ባሉ ፋብሪካዎች በቀጥታ ጥቅም፣ ላይ የሚውሉበት መንገድ እንዲፈለግም ተቋሙ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
የንግድ ስርአቱን በጥልቀት ፈትሾ ማመሻሻልና የደላላዎችን ሚና መቀነስ የሸቀጦች ገበያ ትስስሮሽን ለማቀላጠፍ ይጠቅማሉ ብሏል- የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም ባወጣው ወቅታዊ መግለጫው፡፡

Read 11573 times