Saturday, 19 March 2022 10:39

መንግስት የዶ/ር ቴዎድሮስን ክስ መሰረተ ቢስ ነው ሲል አጣጣለ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(0 votes)

   - መድሐኒቶችንና የህክምና ቁሳቁሶችን ወደ ትግራይ ክልል ለማስገባት ለዓለም ጤና ድርጅት ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡
     - 20 ምግብና 3 ነዳጅ የጫኑ መኪኖች ወደ መቀሌ ለመሄድ ትናንት ከሰመራ ተነስተዋል
                    
               የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ የኢትዮጵያ  መንግስት መድሃኒቶችንና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን ወደ ትግራይ ክልል ለማስገባት እንዳንችል ፈቃድ ከልክሎናል ሲሉ መክሰሳቸውን መንግስት አጣጣለ፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት “መንግስት ፈቃድ ከልክሎናል” በሚል ያቀረበው ክስ መሰረተ ቢስ ነው ብሎታል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት 95 ቶን መድሃኒትና የህለክምና ግብአቶችን ወደ ትግራይ ክልል ለማስገባት ፈቃድ ጠይቆ ፈቃድ የተሰጠው መሆኑን ያመለከተው የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፤ ይህ ባለበት ሁኔታ ድርጅቱ ፈቃድ ተነፍገናል ሲል ያቀረበው ክስ ከእውነት የራቀ ነው ብሎታል፡፡ ጉዳዩ የአገርን ገፅታ ለማበላሸትና በሃሰተኛ ክስ የዓለምን ትኩረት ለመሳብ የተደረገ  ሙከራ መሆኑንም አመልክቷል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት መጋቢት 2 ቀን 2014 ዓ.ም ለጤና ሚኒስቴር በላከው ደብዳቤ ከመጋቢት 12 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 12 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ለአንድ ወር ወደ ትግራይ ክልል የህክምና ቁሳቁሶችን ለማስገባት እንዲችል ፈቃድ ጠይቆ የተሰጠጠው መሆኑን ያመለከተው የኮሚሽኑ መግለጫ፤ ድርጅቱ በተገለፀው ጊዜ ግብአቶቹን ወደ ክልሉ ለማስገባት  ይልቅ “ፈቃድ ተከልክያለሁ” ብሎ በመንግስት ላይ ሃሰታተኛ ክስ ማቅረቡ አግባብነት የለውም ተብሏል፡፡
መንግስት በክልሉ ለሚገኙ ወገኖች የተለያዩ ሰብአዊ ድጋፎችን ለማቅረብ እየሰራ እንደሆነ ያመለከተው መግለጫው፤ በትናትናው ዕለት ብቻ የተለያዩ የምግብ ቁሳቁሶችን የጫኑ 20 መኪኖችን  እንዲሁም 3 ነዳጅ የጫኑ ተሸርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል ለመሄድ ከሰመራ መነሳታቸውንም ጠቁሟል፡፡ በቅርቡ ወደ ክልሉ የሚሄዱትን ምግብ የጫኑ ተሽካርካሪዎች ቁጥር 40 ለማድረስ እየሰራ ነው ብሏል፡፡
ኮሚሽኑ እስከ አሁን 17 የሚሆኑ አለም አቀፋዊ ድርጅቶች (አጋር ተቋማት) ክትባቶችን ጨምሮ የተለያዩ የህክምና ግበአቶችን ወደ ትግራይ ክልል እንዲያስገቡ ፍቃድ ማግኘታቸውንና 11 አጋር ተቋማት 257 ሺ 192 ኪ.ግ የህክምና ግብአቶችን በአየር በረራ ወደ ክልሉ ማስገባታቸውን አመልክቷል፡፡

Read 11402 times