Print this page
Saturday, 19 March 2022 10:49

ከአድዋ በዓል ጋር ተያይዞ የታሰሩ ወጣቶች እንዲፈቱ ኢዜማ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  ከዘንድሮው የአድዋ በዓል አከባበር ጋር ተያይዞ ያለ አግባብ የታሰሩ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ የጠየቀው ኢዜማ መንግስት   ሃሳባቸውን በነፃነት የገለፁ ወጣቶችን ከማሸማቀቅ እንዲቆጠብ አሳስቧል፡፡
“ሰላም ሁላችንም ዘብ የምንቆምለትና የምንታገልበት ዋና ጉዳያችን ነው፤ በምንም መንገድ የከተማችንን ሠላምና ፀጥታ የሚያውኩ  ለህግ የማይገዙ ሃይሎችን አጥብቄ አወግዛለሁ” ያለው ኢዜማ፤ ይሁን እንጂ በሠላም ማስከበር ሰበብ ሃሳባቸውን የገለፁት ዜጎች ላይ የሚካሄድ መንግስታዊ አፈናን አጥብቄ እቃወማለሁ ብሏል፡፡
ከአድዋ በዓል አከባበር ጋር በተያያዘ ቁጥራቸው በርከት ያለ የአዲስ አበባ ወጣቶች እየተለቀሙ እየታሰሩ መሆኑን መረዳቱን የገለፀው ኢዜማ፤  መንግስት ይህን አይነቱን እርምጃ በመውሰድ የከተማዋን ወጣቶች አንገት ለማስደፋት በከፍተኛ ሁኔታ እየሠራ ነው ሲል ተችቷል፡፡
በበዓል አከባበሩ ላይ ዜጎች ያነሷቸውን ጥያቄዎች እንደመሰረታዊ  ጥያቄ ወስዶ መነጋገር ሲገባ፣ ዜጎች የመጠየቅ መብታቸውን እንዳይጠቀሙና ማህበረሠባዊ ተሳትፎ እንዳይኖር የሚያደርገው ጥረት ተቀባይነት የለውም ብሏል-ፓርቲው በመግለጫው፡፡
በአድዋ በዓል አከባበር ላይ የተፈጠሩ የተቃውሞ፣ ድምፆች፣ መንግስት ቀደም ብሎ በፈፀማቸው ጠብ አጫሪ ድርጊቶች ሰበብ የመጡ መሆናቸውን በመግለጫው ያወሳው ኢዜማ በእለቱ ወንጀል የፈፀሙ አካላት ካሉ ተጣርተው ለህግ እንዲቀርቡ ማድረግ ሲገባ ወጣቶችን በጅምላ ወደ እስር ቤት ማጋዝ ከህግ አግባብ ውጪ ነው ብሏል፡፡
ኢዜማ በዚሁ መግለጫው፣ የከተማዋን ፀጥታ ለማስጠበቅ 50 ሺ የፖሊስ አባላትን ከተለያዩ  ክልሎች ለመመልመል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የያዘውን እቅድም እንደሚቃወም አስታውቋል የከተማዋ የፖሊስ ምልመላ ከከተማዋ ነዋሪዎች መሃከል ብቻ ሊሆን እንደሚገባው በማመልከት፡፡ ዜጎችን የተቃውሞ ድምጽ ባሰሙ ቁጥር ማፈንና ማሠር ፀረ ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ነው ያለው ኢዜማ፤ ከበዓሉ አከባበር ጋር ተያይዞ የታሰሩ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዲፈቱ በሌላ በኩል ወንጀል ሠርተዋል ተብለው የተጠረጠሩ በገለልተኛና ለህዝብ ክፍት በሆነ ችሎት ጉዳያቸው እንዱታይ ታሳሪዎች በቤተሰቦቻው የመጎብኘት መብታቸው እንዲጠበቅ እንዲሁም የከተማዋ ፖሊስ ከከተማዋ በተወጣጡ ዜጎች እንዲጠናከሩ ኢዜማ  በመግለጫው ጠይቋል፡፡

Read 11540 times