Saturday, 19 March 2022 10:48

“በሽታውን የደበቀ መድሀኒት አይገኝለትም!”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ሰዎች ከርቀት የአንድ አውሬ ቅርጽ ያያሉ።
አንደኛው፤
“ያ የምናየውኮ ጅብ ነው” አለ
ሁለተኛው፤
“ኧረ በጭራሽ፣ ያማ አሞራ ነው” አለ
አንደኛው፤
“እንወራረድ”
ሁለተኛው፤
“በፈለከው ነገር እወራረዳለሁ”
አንደኛው፤
“እኔ አንድ በቅሎ እገባ!”
ሁለተኛው፤
“እኔ እንደውም በቅሎ ከነመረሽቷ እገባለሁ!” መልካም ተስማምተናል። ግን ማየት ማመን ነውና፤ ቀረብ ብለን እንመልከተው ተባባሉና እየተጠጉ መጡ።
አንደኛው፤
“አሁንም በአቋምህ ጽኑ ነህ?”
ይሄ እንስሳ አሞራ ነው፤ የምትል?
ሁለተኛው፤
“ከፈራህ አንተ እፍርታም ሁን እንጂ፣ እኔ አሞራ ነው ብያለሁ አሞራ ነው!”
አንደኛው፤
“እኔ የምፈራ ብሆን፣ ጅብ መሆኑን እያየሁ ቀርበን ካላረጋገጥን እልሃለሁ?” አለው በቁጣ ጭምር።
እየቀረቡ መጡ።
አሁንም የእንስሳው ቅርፅ የቅድሙ ነው።
እጅግ እየቀረቡ ሲመጡ ያዩት እንስሳ አሞራ ኖሮ፣ ተነስቶ በረረ!
ሁለተኛው፤
“አላልኩህም? ይሄው በረረ። አሞራ ነው ማለት ነው። ተበልተሃል!”
አንደኛው፤
“በጭራሽ አልተበላሁም!”
ሁለተኛው፤
“እንዴት? ለምን? አስረዳኝ?”
“ቢበርም ጅብ ነው! መብረር የሚችል ጅብ መኖር አለመኖሩን በምን ታውቃለህ?” አለ ይባላል።
*   *   *
በህይወታችን ውስጥ የዋሸነው የካድነውና በእምቢ ባይነት፣ ግትርነት ፈጽሞ አንቀበልም ያልነው በርካታ ነገር አለ። ስህተትን አምኖ “ይቅርታ ተሳስቼ ነበር” ማለት ያቅተናል። በአይናችን የምናየውን እንክዳለን። የችግራችን ሁሉ መሰረታዊ መነሻ ይኸው ነው! ይቅርታ የመጠየቅና ይቅርታ ማለት እንደ ቃልና እንደ አንደበት  ወግ ሲታይ ዛሬ  “ፋሽን “ፋሽን እንጂ በተግባር የለም። በአሁኑ ጊዜ ለክርስትና አማኒያን ክፉ ነገር መጾም ህጋዊ ጉዳይ እንደሆነ ሁሉ፣ በእስልምና ሃይማኖትም ጉዳዩ ያው ነው። እስከ እውነተኛው የሀገራችን ትንሳኤ ድረስ በዚህ ጉዳይ ላይ መተማመን በጣም ፋይዳ ያለውና የብዙ ነገር መፍቻ ቁልፍ ፍሬ ጉዳይ ነው።
“መሳሳት የሰው፣ ይቅር ማለት የመለኮት ነው!” ይለናል አሌክሳንደር ፓፕ የተባለው ገጣሚ፡-
“To err is human
To forgive is devine!”
ንሥሐ መግባትን የመሰለ መንፈሳዊ አብዮት የለም! መንፈሳዊ ለውጥ ማወቅ የአያሌ ችግሮች መፍቻ ቁልፍ ነው!
“ተሳስቻለሁ… ይቅርታ” ማለት በቀደሙትም ፓርቲዎች፣  አሁንም ባሉት ፖለቲካዊ ፓርቲዎች ዘንድ ብቻ ሳይሆን የመላው  ህብረተሰባችን የወረዳም፣ የክፍለ ከተማም፣ የአገርም ስር የሰደደ ካንሰር አከል በሽታ ነው። የቀደሙት መንግስታትም፣ አሁን ያለውም፣ ምናልባትም ነገ የሚመጣውም መንግስት መሰረታዊ ደዌ ሥራይ ይሄው ላለመሆኑ አዋቂ ዘንድ መሄድ አያስፈልገንም።
(The case of the socialist witch-Doctor) የኢኮኖሚ ጠበብቶቻችን ክፉ የትንተና ጠኔ (Deprivation of economic analysis) ሊሰመርበት የሚገባ ወረርሽኝ ነው- ትላንትም፣ ዛሬም!
እንደ ችግር የምናነሳቸውን መፍትሄም የሚያሻቸው ፍሬ ሃሳቦች እጅግ በርካታ ቢሆኑም፣ አንኳር አንኳሮቹ፤
1. የኢትዮጵያ የቤት ነክ ቢሮክራሲ መሰረታዊ ጉዳይ
2. ተጨባጭ ችግሮችን በሚዲያ ማሳየትና የህዝብን አስተያየት ከጉዳይ አለመጣፍ
3. መንግስት ችግሮች መኖራቸውን መቀበልና ለመፍትሄው ሁነኛ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚባሉ ልባም ምሁራንን አለማወያየት
4. በየደረጃው እገዛ ሊያደርጉ የሚችሉ፣
    - አንጋፋ ምሁራን
    - ትኩስ ኃይል ወጣቶች
    - የሃይማኖት መሪዎች
    - ድርጅቶችና ተቋማት
ዓይነተኛ ተባባሪነት መመናመን ጥቂት መነሻ ሃሳቦች ናቸው።
5. የጎረቤት አገሮችን የመተጋገዝ  ህብረት አለመጠቀም፣
    ጥቂት መንደርደሪያና ፍሬ ጉዳዮች ናቸው። እናስብባቸው!
ከላይ የነቆጥናቸውን ዋና ዋና ተግባራት በመንተራስ፤ የተቀደሰ ተግባር ለማከናወን ፍቃደ  ልቡናችን ክፍት ይሁን! እንወያይ! ችግራችንን እናውጣ! መፍትሄውን አንንፈግ!
ከሁሉም በላይ ግን፣ “በሽታውን የደበቀ መድሀኒት አይገኝለትም!” የሚለውን አባባል ሁሌም በህሊናችን እናኑር!!

Read 12296 times