Print this page
Sunday, 20 March 2022 00:00

የአውሮፓ ጦርነትና - የዘረኝነት እባጭ

Written by  ከኢሳይያስ ልሳኑ (ከቤተሳይዳ ሜሪላንድ-አሜሪካ)
Rate this item
(1 Vote)

  የሩስያና የዩክሬን የጦርነት ዜና እንደተጋጋለ ነው፡፡ በሀገር ቤት ያለውን አተያይ አላውቀውም እንጂ በመጨረሻው ዘመን (ምፅዓት ማለቴ ነው) ’የጦርነት ወሬ ትሰማላችሁ’ የሚለውን ትንቢት ነቅሰው አውጥተው፣ አሁን የደረሰ አስመስለው ፈርተውና አስፈርተው የሚናገሩ ሰዎችን ማግኘት እዚህ የተለመደ ሆኗል፡፡ ለነገሩ የጦርነት ዜና ነገር ከተነሳ እኛም በሀገራችን ያላለቀ ጦርነት ታቅፈን ቁጭ ማለታችንን አልዘነጋሁትም፡፡ ሌላ የሚቆረቁርና የሚሸነቁር ተጨማሪ ችግር (አይጣል ይበሉ እንጂ) በዚያና በዚህ እንደ ግንደቆርቁር እንዳይፈለፍለን እሰጋለሁ፡፡ እየፈለፈለን ነው እንጂ የሚለኝ ላይጠፋ ይችላል፡፡ የመዘናጋት ወይም እንደሌለ አድርጎ የመመልከት አዚም የወረደብን እንመስላለን የሚሉ ወገኖችም እንዳሉ እሰማለሁ፡፡
ጦርነት የሰው ህይወትን ማጥፋቱ ንብረትን ማውደሙ ብቻ አይደለም ያለው መዘዝ፡፡ የሰውን መንፈስ ያቃውሳል። ሰብዓዊ ዕሴትን ያነትባል፡፡ የአብሮ መኖርን ተስፋ ያቀጭጫል፡፡ ከሁሉም በላይ የነበረው እንዳልነበረ ይሆናል። አሜሪካዊቷ ደራሲ ክርስቲን ሃና (The Nightingale) በተሰኘ አቢይ ወግ ድርሰቷ፤ “ከዚህ ከረዥሙ የህይወቴ ምዕራፍ የተማርኩት ነገር ይህ ነው” ብላ ጀመረች፣ “በፍቅር ውስጥ መሆን የምንፈልገውን ወይም የምንሻውን እናገኛለን፡፡ በጦርነት ውስጥ ግን ማን እንደሆንን እናውቃለን፤ እናገኛለንም፣” ትላለች፡፡ እውነት እኮ ነው። በዚያ አስከፊ እልቂትና መገዳደል ውስጥ ሰው ማን መሆኑን ይበልጥ ይረዳል፡፡ በፈተናውና በተግዳሮቱ ውስጥ እሳትና እቶን በሚወርድበት ሰዓት - ሰው የእግዚአብሔር (የአላህ) ፍጥረት መልካሙን እንዳሰበ፣ መፍትሄውን ከልቡናው እንዳውጠነጠነ ይገኛል ወይስ በክፋቱ ደንድኖ ሰይፉን ስሎ - ‘መገዳደሉን’ ያጸድቃልን? ብሎ መጠየቅም ይገባል፡፡
ከክፋት ጥግ ዳርቻ - ከአውሬነቱ ተፈጥሮ መፍቻ ሰው ደርሶ ማንነቱን በጦርነት ውስጥ ሊያሳይ ይችላል፡፡ ጭካኔና ክፋቱን አክፍቶ ሊያሳይም ጭምር፡፡ በጦርነት ውስጥ ጎራ ለይቶ አንጻር አስልቶ ሰው መዋጋት - መጋደል ሲጀመር የሚጠየቅ ጥያቄ አለ፡፡ ሰው በዚያች ሰዓት በተፈጥሮው ውስጥ ከክፉው ጫካ መካከል የደግነት ችግኝን ይተክላል ወይስ- የክፋትና የግድያ ክራንቻውን ይስላል? ከጥላቻው የበቀል መርዝ ውስጥ የይቅርታ መድሃኒትን - ከእንጋደል ጩኸት ጣልቃ ውስጥ እንግባባ ፈልጎ ያሳያልን? ብሎም ይጠየቃል፡፡ በግልም በወልም የሰው ልጅ ደራሲዋ እንዳለችው ‘ማን መሆኑን’ ሰው ራሱን ይለይበታል፡፡ ለራሱ ከሚሰጠውና ከሚያኮሸው (ከሚያጋንነው) አንደበቱ ይልቅ፣ ጦርነትና ግጭት የሰውን አዳም ገላ ያሳያል፣ ያጋልጣልም፡፡ አንዳንዴ ለገዛ ራስ የሚገርምም - የሚደንቅም ማንነትን የሚያበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ እንዲህ ርህሩህ ነኝ እንዴ? እንዲህ ከልቡናዬ የዘለቀ ስር የሰደደ የበቀልስ ስሜት አለኝን? ብለን መልሰን ራሳችንን የምንፈትንበት አጋጣሚም ይከሰታል፡፡ አዝነን ሆደ ቡቡ ነን የምንል - ለይቅርታ ልባችን የተከፈተ ብለን ራሳችንን የምናሞካሽ የቁርጡ ቀን ላይ - በጦርነቱ አንፃር ባንፃር ቆመን ስንገኝ፣ ሁሉም የግልምቢጥ ይሆንብን ይሆናል፡፡
ታዲያ አውሮፓ የጥቁር ዘረኝነት ምሰሷዋ መሆኑን - የነጭ የበላይነት መረማመጃዋ የመሆኑን እውነታም ዛሬ ጎኗን የሰቀዛት ጦርነት ፍንትው አድርጎ ገልቦ አሳየባት፡፡ በዚያ አስከፊ ጦርነት ነፍሳቸውን በጥርሳቸው አንጠልጥለው ከሚሮጡት ተርታ - በተማሪነት - በእንግድነት - በሌላም ሳቢያ ከአውሮፓዋ ዩክሬይን የነበሩ አፍሪቃውያን ወገኖቻችን ተለይተውና ተነቅሰው ከሚገፉበት ወደ ሌላ ሀገር ከሚጓጓዙበት ተሽከርካሪ እንዳይሳፈሩ የሚታገዱበትን ሁኔታ በዓይናችን በብረቱ ዓየን፡፡ ከሀገር ሀገር አቆራርጠው በእግራቸው እንዲጓዙ ሲነገራቸውና ሲታዘዙም ሰማን፡፡ “ይሄ ባቡር - ይሄ መጓጓዣ አውቶብስ” ተብሎ ለነጮች ብቻ ይፈቀዳል የሚባልበትንም ዘረኝነት ዓይተን መሰከርን፡፡ ይህች ናት አውሮፓ፡፡
ለነገሩ ወትሮስ ዘረኝነቱና ጸረ-ጥቁርነቱ የቀለምና የዘር መድልዎ መች ጠፋ፡፡ የምወደው ኢትዮጵያዊ ጸሀፊ ሃማ ቱማ በአንድ መጽሐፉ መጀመሪያ ላይ የእናቱን አነጋገር የጠቀሰበትን አስታውሳለሁ፡፡ “ከሁሉ የሚከፋው ባርያ ራሱን ነጻ አድርጎ የሚያስብ ነው” ይላሉ እናቱ፡፡ እና ብዙውን ጊዜ ‘ዘረኝነቱ ጠፍቷል’ ‘ነፃ ሆነናል’ የሚለው አስተሳሰብ ነው የሚያዘናጋን፡፡ የባሪያ ፍንገላ ፊታውራሪዎች የነበሩት ያስተማሩትና የቀለሱትን ዲሞክራሲ - ምሳሌ አድርገን ተታለን ከኪሳቸው የገባን ብዙ ነን፡፡
ከሁሉ በላይ የአስተሳሰባችን ነገር ፈታኝ ይመስለኛል፡፡ እዚህ እኖርበት አሜሪካ የደረሰና የሚፈትነን ችግርም አለ። የአካል ባርነት አንድና አንድ ግልጽ ነው፡፡ የሚታይ የሚዳሰስ በመሆኑ መፍትሄም ለመፈለግ ይመቻል፡፡ ዛሬ ያለው ተግዳሮት ግን የአእምሮ ባርነት ነው፡፡ ደግሞ ለምዕተ ዓመታት የተሠራበት - የተዘመተበት መሆኑን ማጤን ያሻል፡፡ የ’ነጭ’(የአውሮፓ) የሆነ ሁሉ ትልቅና መልካም አድርገን የምንቆጥር ተደርገን የተዘጋጀንበት ሂደት የከፋ ነው፡፡ ዛሬ ስለ ሀገርም ስንወያይ የመፍትሄ መሰላላችን - የእሳቤ ሳጥናችን አውሮፓዊ ቅድ (ዘዬ) ነው፡፡ እኛ ‘ጥቋቁሮቹ’ የምናዜማው ዜማ የምንመታው ጊታር የአውሮፓ የነጫጮቹ መሆኑን የዘነጋነው እንመስላለን፡፡ ከሁሉም የከፋ ባርነት ነፃ ነኝ ብሎ ማሰብ ነው’ ያለው ነው ሃማ፡፡
በዚህ መካከል ደግሞ እንዲህ በመሰለ የጦርነት ዜና ከመጋረጃው ጀርባ የተደበቀውን ዘረኝነቱን እናያለን፡፡ በፈገግታና አብሮ ከነጭ ጋር ፎቶ በመነሳት የሌለ የሚመስለው መድልዎም ይጋለጣል፡፡ በጦርነት ከምትታመሰው ከዩክሬይን ነፍሱን ለማትረፍ ቀዳዳ የሚሻ የኮንጎ ተማሪ  ደግሞ እንዲህ አጋጠመው፡፡ ከአስፈሪው ግጭት እንደሀገሬው ሰዎች ለማምለጥና ህይወቱን ለማትረፍ አንድ አውቶብስ ላይ ሊሳፈርና ወደ ፖላንድ ሊሄድ አስቦ ነው፡፡
“አንተማ ቆይ” ብለው ይገፉታል አስተባባሪዎቹ “እንደውም መሳሪያ ይስጡህና ተዋጋ” ብለውት አረፉ፡፡
-”ለማን ነው የምዋጋው?” ይጠይቃል፡፡
“ለዩክሬይን ነዋ!” ብለውት አረፉ፡፡
ይህ አሳዛኝ ክሰተት የተስተዋለው በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡ ይህ እንዲያበሳጫችሁ ግን አያስፈልግም፡፡ ከዚያ አልፈው አውሮፓውያኑ ተፋላሚዎች ‘ቅጥር ነፍሰ ገዳዮችን (ታጣቂዎችን’) ለመቅጠር በይፋ በአፍሪቃ አንዳንድ ሀገራት ማስታወቂያ ማውጣታቸውን ማየት ይቻላል፡፡ ሰውየውን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ ይላል የአዛውንቱ ብሂል፡፡ አፍሪቃውያንን ለጦርነት ማገዶ ምልመላ መታሰቡ - ድህነታችንን አስታኮ ቢሆንም ንቀትም ነው፡፡ ለአንድ ቅጥረኛ እስከ $3‚000 ይከፈላል መባሉን የሰማ የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገር ኬንያ ተወላጅ አንድ የዜና ወኪል ለዩክሬይን ተቀጥሮ የመዋጋት ነገር ሲያነሳበት “በአንዴ ሀብታም የመሆን ህልሜን ማሳኪያ ይሆነኛል፣” ማለቱን የዘገበውን በሀዘን አንብቤያለሁ፡፡ አፍሪቃን በድህነቱ ቁስል ሰርስሮ የመግባቱ ነገር ራሱን የቻለ ጉዳይ ነውና እሱን ለጊዜው እንተወው። ዘረኝነቱ ከዚያ ጋር የመነጨው ንቀቱ ግን መረሳት የለበትም፡፡
በዚህ የዩክሬይን ጦርነት ዙሪያ የታየው የቀለምና የዘር መድልዎ የተገለጸበት መንገዱ ብዙ ነው፡፡ ነፃ የሚመስሉንና እንደ አርአያ የምናያቸው ወይም የምንጠቅሳቸው የኮርፖሬት ሚዲያዎቹም የተገለጡበት ነበር፡፡ “ዩክሬይን እንደ አፍጋኒስታንና ኢራቅ ለአስርታቱ ዓመታት ግጭት እንደታየባቸው ቦታ አይነት አይደለችም፣” ብሎ ጀመረ የሲ.ቢ.ኤስ. የውጭ ዜና ዘጋቢው ቻርሊ ዲአጋት፣ “ይልቁንም የሰለጠነና አውሮፓ ነው፡፡ ይህን መሰል ክስተትም የማይጠበቅበት ስፍራ ነው፣” አለ በይፋ፡፡ አውሮፓና የሰለጠነ - ግርግርና ግጭት የማይነካው እየተባለም ተነገረ። በብሪታኒያው የዜና ወኪል ቢቢሲ ላይ የዩክሬይን የቀድሞ ምክትል አቃቤ ህግ በቃለ ምልልስ ደግሞ “ለእኔ ይህ ጦርነት ስሜታዊ ያደርገኛል፡፡ ምክንያቱም ወርቃማ ቀለም ያለው (ብሎንድ) ጸጉርና ሰማያዊ ዓይን ያላቸው አውሮፓውያን በየቀኑ ስለሚሞቱ፣” ብለውን አረፉ፡፡ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች በሀገራችን ጦርነት ውስጥ የነበራቸውን ሚና ስለተመለከትን ብዙም ከእነርሱ ባንጠብቅም የዚህ ሰሞነኛው ዘረኝነት የተላበሰው ሪፖርታዣቸው ግን የሚያመለክተን ሚዲያዎቹን ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም የአውሮፓ ስር የሰደደ የነጭ የበላይነት በሽታንና የነተበውን አስተሳሰብ ነው፡፡
አውሮፓ በዘረኝነት እባጭ መጉበጧን ያየንበት ሌላው አስረጂ ስደተኞችን በመቀበል ዙሪያ ሀገራት ያሳዩት መረባረብ ነው፡፡ ሲጀምር የዩክሬይን ስደተኞች መረዳታቸውን የሚቃወም የለም። ነገር ግን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አፍሪቃውያን ወንድምና እህቶች ያለቁበትን የሜዲትራኒያንን ባህር በጀልባ ተሻግረው - ባገኙት ቀዳዳ ለስደት የተጓዙትን አውሮፓ የጠበቃቸው የሽቦ አጥር ሠርቶ - የጦር መሳሪያ በታጠቁ ወታደሮች ወሰኑን ዘግቶ ነው፡፡ እና አትገቡም - የተባሉበትን ሰብዓዊ ቀውስ ከዓይነ ልቡናችን ብዙም አልራቀምና እንጠይቃለን። ያኔ ስደተኛ ከአፍሪቃና ከመካከለኛ ምስራቅ የተሰደደች እናት እኔ ባልተርፍ ብላ ገና ወገቧ ያልጠናውን ለጋ ልጇን በአጥሩ ሽቅብ የወረወረችበት አሳዛኝ ታሪክም ከትውስታችን አልጠፋም፡፡ በ2015 እ.ኤ.አ. ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች ከሶሪያ - ከአፍጋኒስታንና ከአፍሪቃ ወደ አውሮፓ የሄዱበት ቀውስ ትዝ ይለናል። ያኔ “እኛ ስደተኛ የምንቀበልበት አቅም የለንም፣” ብለው በአደባባይ የተናገሩት የአውሮፓ ሀገራትን - “እውነት አቅማቸው ሳስቶ ይሆናል” ብለን በደምሳሳው ምክንያታቸውን የተቀበልናቸው ነበሩ። ስደተኞችን በሽብርተኝነት ፈርጀው ያሰቃዩበትንም ሁኔታ መለስ ብለን እናስበው ዘንድ እንገደዳለን። ዛሬ ግን በዩክሬይን በተቀሰቀሰው ግጭት ሳቢያ እነዚያ አቅም የለንም ያሉት ሀገራት፤ “በራችንን ወለል አድርገን ከፍተናል ኑልን - እኛ ጋ ተቀመጡ፣” ሲሉና ሲያውጁ ስንሰማ ልባችን ያዝናል፡፡ ስደት በቀለምና በዘር ተወስኖ እንደማይቀር ግን ምስክሩ ዛሬ የምናየው ታሪክ ሆነ፡፡ በገዛ ሀገራቸው ቀድሞውኑ ከሚያስመስሉና ከሚሸነግሉን - ‘መርጠን የምናስገባው ስደተኛ አለን’ ቢሉንም እንዲህ ዛሬ ባላንገበገበን ነበር፡፡
እኖርባት አሜሪካም በዚህ ረገድ የምትጠየቅበት - ራሷንም የገለጠችበት አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ መንግሥታችን ‘ለዩክሬይን ስደተኞች ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድን’ መስጠቱን ይፋ አድርጓል፡፡ እና በሜክሲኮ አዋሳኝ ድንበር በኩል ወደ ዩ.ኤስ. አሜሪካ በመቶዎች የሚቆጠሩ የዩክሬይን ተወላጆች እንደገቡም በቴሌቪዥን መስኮት አየን፡፡ ጥያቄ ያስነሳው በዚያ ድንበር አቅጣጫ የላቲን አሜሪካ ስደተኞች በአብዛኛው በሩ ተዘግቶባቸው - ከዚያ እንዳይንቀሳቀሱ ተደርገው - የተቀመጡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ጥገኝነት ጠያቂዎች አሉ፡፡ ጉዳያቸው በዓመታት መፍትሄ ያልተሰጣቸው እንዳሉበት ይነገራል። ጊዜያዊም የመኖሪያ ፋታ ሊሰጣቸው የተገቡ ስደተኞች ብዙ አሉ፡፡ እና የፕሬዚዳንት ባይደን መንግሥት ለ’ዩክሬይን ተወላጆች’ ብሎ መርጦ ሲፈቅድ የዘረኝነትን ቅድ የሚያሳይ ነው። በሀገሪቱ ሰነድ አልባ ተብለው ተሳደውና ፈርተው የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ (11 ሚሊዮን ይደርሳሉ) ስደተኞች አሉ፡፡ የእነዚህ ምስኪኖች ጉዳይ የፖለቲካ መጫወቻ ሆኖ ዓመታት ሲቆጠሩ ‘ወርቃማ ጠጉርና ሰማያዊ ዓይን’ ግን ልዩ መብት ሲቀዳጁ ማየት ያሳዝናል። ሼክስፒር በሃምሌት ተውኔቱ ላይ “በዴንማርክ መንግስት ውስጥ የበሰበሰ ነገር አለ፣” እንዳለው ይሆንብኛል፡፡
በእርግጥም ዘረኝነት በቀላሉ የሚጠፋ - እፍ ሲሉት የሚበን አይደለም፡፡ ተቋማዊ የሆነ የዘረኝነት አስተሳሰብና ልማድ በዓለማችን ለበርካታ ትውልዶች የተተከለ መሆኑን ማሰብ ያሻል፡፡ አፍሪቃዊ የሆኑ ታሪኮቻችን ከስራቸው ተነቅለው - በአውሮፓዊ ስሮች ተተክተው እኛው አፍሪቃውያን መልሰን የተማርንባቸውና እኛን ‘አዋቂ’ ያሰኘንን አውሮፓዊ አስተምህሮ መፈተሽ ይገባል፡፡ የፖለቲካ ፈላስፋው ፍራን’ዝ ፋነን “ጥቁር ቆዳ ነጭ ጭምብል” የሚለው አይነት ነው። በላያችን ላይ በ’ትምህርት’ ስምም ይሁን በሌላ ራሳችንን እንድንጠላ የተደረገበትንም ሂደት መርሳት አንችልም፡፡ የአእምሮው ባርነት ክፉ አደጋው ደግሞ ራሳችንን የአውሮፓውያን ምትክ ጥላ ያደርገናል። የራሳችንን የምንረግም የነጩን በጉጉት የምንናፍቅና የምናደንቅ፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ መመርመርና መፍትሄ የመፈለግ ግዴታችንን እንድናስበው ግድ ይሆናል፡፡
ልብ እንበል፡፡ አውሮፓ (የነጩ ዓለም) አሁንም እኛን ጥቁሮች (አፍሪቃውያንን) በዘረኝነት ዓይን ነው የሚመለከተን። የቀለምና የዘር መድልዎው የሚገለፅበት ወይም የሚታይበት ሁኔታ ሊለያይ ይችላል፡፡ ከዘመኑ ጋር እየተወሳሰበም መጥቷል፡፡ በፊት ለፊት የዘረኝነት መለያዎችን ማየት ያዳግትም ይሆናል፡፡ እዚህ እምንኖርበት አሜሪካ “እኔ በቀለም ልዩነት አላምንም፣” እያለ የሚምልና የሚገዘት ሰው፤ ‘ልጅህን ጥቁር እጮኛ ያዘች’ ሲባል ጎራዴ እስከሚመዝ ሲፎክር ልትሰሙት ትችላላችሁ፡፡ በግል እንደዘበት የሚታዩት ያልተለወጡ አስተሳሰቦች በወልና ለረዥም ጊዜ ከተሠራባቸው ዕሳቤዎች ጋር ተዳምረው ሊፈጥሩ የሚችሉትን ደግሞ ማሰብ ይቻላል፡፡
ዛሬ በአውሮፓ የተፈጠረው ግጭት አስከፊ ቢሆንም የሚያስፈራ እውነተኛ ማንነት እንድናይ ግን አስችሎናል፡፡ በእርግጥ እንደ ትምህርት ከተቆጠረ ተምረው ያልፉበታል፡፡ እንደ ማስጠንቀቂያ ደወልም ከሆነ ለአፍሪቃውያን ተደውሏል፡፡ ወደ ውጭ ከመመልከት ወደ ውስጥ የማየትና የመፈተሽ ብቃትን ይጠይቃል።
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 3190 times