Tuesday, 22 March 2022 00:00

አስቸጋሪው ጊዜ እየመጣ ነው - የጦርነት መዘዞችን ሰብስቦ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

ለ40 ዓመታት ያልታዩ ችግሮች እያስገመገሙ ናቸው። ቀላል እንዳይመስሉን።
የስንዴና የበቆሎ፣ የምግብ ዘይትና የማዳበሪያ፣ የነዳጅና የብረታብረት ችግር፣ የዋጋ ንረትና የዶላር እጥረት፣ አንድ ላይ የተደራረቡበት፣ ሃይለኛ ውሽንፍርና ማዕበል ነው የተፈጠረው-በራሺያ ዩክሬን ጦርነት ሰበብ በፈነዳው ዓለማቀፍ ቀውስ ሳቢያ።
በተለይ ለኢትዮጵያ፣ በክፉ ጊዜ ላይ ነው ተጨማሪ መከራ የሚመጣባት። በውስጣዊ የእርስበርስ ጦርነትና ግጭት እጅግ በተጎዳችበት ጊዜ ነው፤ ዓለማቀፍ ቀውስ የሚጨመርባት።
በርካታ ሚሊዮን ዜጎች በተፈናቀሉበትና በምግብ እጥረት በተጎሳቆሉበት ዓመት፤ ስንዴና ዘይት ለመግዛት እጅ በሚያጥራት አገር ላይ ነው፤ እጥፍ ሸክም የሚጫንባት።
                   በራሺያ ዩክሬን ጦርነት ሰበብ የተፈጠረው ዓለማቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ፤ ሁሉንም አገራት በፍጥነት ያካለለ፣ ኢትዮጵያ ላይም የደረሰ ይመስላል። ገና ምኑን አይታችሁ!! ማዕበሉ ገና ነው።  በእርግጥ፣ ሽውታው ብቻ እንደወላፈን እየሆነብን ነው።
የምግብ ዘይት እጥረት እንዴት እንደባሰበት፣ የዋጋ ግልቢያው ምንኛ እየሸመጠጠ እንደሆነ ተመልከቱ። ይሄ ግን ሽውታው ብቻ ነው። ማዕበሉ ከነግሳንግሱ ሲመጣብን ምን እንደምንሆን እንጃ።
በነባር የኑሮ ችግርና በአገራዊ የዋጋ ንረት ላይ፣ ዓለማቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ ሲታከልበት፣ የባህር ማዶው ማዕከል ሲመጣበት፤ እጅግ ያስጨንቃል።
ክፋቱ ደግሞ፣ ማዕበሉ ገና አልመጣም። ፍንጥርጣሪውን ነው እያየን ያለነው። ከሩቅ ቦታ ሲያስገመግም ነው መስማት የጀመርነው። ጭምጭምታውና የወዲያ ማዶ ብልጭታው ብቻ ነው የመጣብን። ውሽንፍሩና ማዕበሉ ገና ነው።
ለጊዜው፤ የሩቅ አገር ዜና ነው።
የነዳጅ ዋጋ፣ በዓለም ገበያ፣ በአንድ ወር ውስጥ፣ በ30% ጨምሯል።  ይህን ሰምተናል። ለጊዜው፣ ወሬ ብቻ ነው፤ ቃል ብቻ፤ ዜና ብቻ። በኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋና የትራንስፖርት ችግር ላይ ምን ያህል መዘዝ እንደሚያስከትልብን፤ ገና በአካል አይታየንም። የዶላር እጥረትን የሚያባብስና የአገሪቱን ኪስ  የሚያራቁት ከባድ ፈተና እንደሚሆን አትጠራጠሩ። ከትንሽ ጊዜ በኋላ ማለቴ ነው። አሁን ግን መዘዙ ገና በአካል ከደጃችን አልደረሰም። ለጊዜው፣ የባህር ማዶ ዜና ነው፤ ቃል ብቻ ነው፤ ድምጽ ብቻ ነው ፤ከጆሯችን የደረሰው።
አዎ፤ የዓለም ገበያ ቁጥሮችን እና ስሌቶችን፣ በእለታዊ ዘገባዎች ላይ እንሰማለን፤ እናነብባለን። በየሰዓቱ የምናቸው ወቅታዊ መረጃዎችና በካሜራ የተቀረፁ ቪዲዮዎችም አሉ። ግን፣  እሳት ያቃጠለው ሰው፣ በወላፈኑ የተለበለበ ኑሮ ማለት፣ የእሳት ቪዲዮ እንደ ማየት ማለት አይደለም። የዜና ዘገባዎችና ቪዲዮዎች፤ ከምናባዊ ምስል፣ ከምሳሌያዊ አገላለጽ የበለጠ ጉልበት የላቸውም።
 ከባድ ውሽንፍር፣ የዶፍ ዝናብና የደራሽ ጎርፍ ዜና መስማት፣ በቪዲዮ ማየት አንድ ነገር ነው። ውሽንፍር ሲያናውጥህ፣ ዶፍ ሲወርድብህና ጎርፍ ሲደርስብህ ደግሞ፤ ሌላ ነገር ነው።
ምን ለማለት ነው?
የአለማቀፉ ቀውስ መዘዝና ክፉ ማዕበል፤… ገና ዜናውን ሰማን እንጂ፣ ገና ፍንጥርጣሬውን አየን እንጂ፤ በአካል ገና አልደረሰብንም። ሲደርስብን ነው፤ ጭንቁ። አለማቀፉ ቀውስና ሃያሉ ማዕበል፤ እንደመብረቅ አይደለም።  የሐምሌ መብረቅ፣ ሰማዩን የሚሰነጣጥቅ የእሳት ጅራፉን አምባርቆ ከጣለህ በኋላ ነው፣ ዓለምን በነጎድጓዱ የሚያደነቁር። የዘንድሮው ዓለማቀፍ የቀውስ ማዕበል ግን፣ ቶሎ አይማታም። ጉም ጉምታ ብቻ ሆኖ፣ ከባህር ማዶ ከሩቅ ሆኖ የሚበርድለት ይመስላል። ሳይመጣ የሚቀር ስለሚመስል፤ ያዘናጋል።  ግን ይመጣል።
ከተናከሰ በኋላ፣ ዘንጥሎ ሲያበቃ የመጮህ ውሻም አይደለም-ዓለማቀፉ ቀውስ። ከርቀት ሲያስገመግም ቆይቶ የሚመጣ የመብረቅ መዓት፤ ሲያጓራ አምሽቶ ለአደን የሚዘምት የአራዊት መንጋ ነው- አለማቀፉ የኢኮኖሚ ቀውስ።
ለጊዜው፣ ጩኸት ብቻ ነው። ከባህር ማዶ የሚመጣ የሩቅ አገር ዜና ነው። ነገር ግን፤ የነዳጅ ዋጋ አሁን ከተተኮሰ በኋላ፣ ኢትዮጵያ መንግስት ቤንዚንና ናፍታ መግዛት መጀመሩ አይቀርም። ከዚያ በኋላ፣ ጉዳዩ የሩቅ አገር ዜና አይሆንም፤ በአካል ወደ አገር ይገባል። ከዚያ፣ የእንዳንዱን ሰው ኪስና ጓዳ የሚበረብር የሚያመሳቅል መከራ ይሆንብናል።
የዛሬና የሰሞኑ የነዳጅ ፍጆታችን፤ ከወራት በፊት ተገዝቶ የመጣ ነው። ከወራት በፊት በነበረ ዋጋ የተገዛ። በሚቀጥሉት ሳምንታትና ወራት ግን፣ በአዲስ የግዢ ውል፣ በአዲስ ሰማይጠቀስ ዋጋ፣ ኪስን አራቁቶ ነዳጅ የመግዛት ጭንቅ፣ እየበረታ ይመጣል።
10 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ፣ በ250 ሚሊዮን ዶላር ገዝቶ ማስመጣት፣ ለኢትዮጵያ ወትሮም ቢሆን፣ከባድ ሸክም ነው። አሁን ግን፣ የስንዴ ዋጋ ሽቅብ ሄዷል። አስር ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ፣ ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ይፈጃል። ለዚያውም ከበቃ ነው። ለዚውም ዋጋው እየባሰበት ካልሄደ ነው።
የስንዴ፣ የምግብ፣ የዳቦ ነገር በጣም ከባድ ነው። የሚያስጨንቅ የሚያሳስብ። መንግስት፣ ባይጨነቅና እንቅልፍ ባያጣ፣ በጣም ይገርመኛል።
ክፉ ማዕበል እየመጣብን እንደሆነ ካወቀ፤ እንዳላወቀ ሆኖ መተኛት አይችልም። እንዴት ይችላል?
የስንዴ ችግር ብቻ፣ እንቅልፍ ያሳጣል፡፡ ነገር ግን፣ ከስንዴ ይልቅ፣ የነዳጅ ወጪ ከ5 እጥፍ በላይ ይበልጣል፡፡ ካቻምና፣ የነዳጅ ግዢ፣ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ፈጅቷል፡፡ ከዚያ በፊት ደግሞ 2.5  ቢሊዮን ዶላር ገደማ፡፡ የአምና ወጪ ይሻላል።
በኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ፣ የዓለም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሲዳከም፣ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ፣ በበርሜል ከ40 ዶላር በታች ወርዶ አልነበር? በዚያ ምክንያት፣ አምና ለነዳጅ ግዢ የወጣው ገንዘብ፤ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በታች ቀንሶ ነበር፡፡
 የዛሬው የነዳጅ የዓለም ገበያ ግን፣ ከያኔው ጋር ሲነፃፀር የትና የት! ሁለት እጥፍና ከዚያ በላይ ሆኗል - የነዳጅ ዋጋ፡፡
በሚቀጥሉት ወራት፣ በአዲስ የግዢ ውል፣ ሰማይ በተተኮሰው ዋጋ፣ ለቤኒዚንና ለናፍጣ የሚበቃ ዶላር ከየት ይመጣል? የአምናው ያህል ነዳጅ ለመግዛት፣ 4 ቢሊዮን ዶላር ይበቃል? ከኤክስፖርት የሚመጣው ዶላር በሙሉ፣ ለነዳጅ ግዢ ብቻ ይሆናል እንደማለት ነው፡፡ ለዚያውም ከበቃ ነው፡፡
መከራው ይሄ ብቻ ቢሆን፣ “ተመስጌን”፤ “በቀላሉ ተረፍን” የማለት እድል እናገኝ ነበር፡፡ ነገር ግን የማዳበሪያ ግዢ አለ፡፡
በዓመት ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚፈጅ የማዳበሪያ ግዢ፣ ለነገ በይደር የሚያዘገዩት እዳ አይደለም። የማዳበሪያ ግዢ ሲስተጓጎል ይቅርና፣… ሲጓተትም፣ ትልቅ አደጋ ያስከትላል። ማዳበሪያ በጊዜ እየተገዛና እየተጓጓዘ፣ ለእርሻ ሥራ፣ በወቅቱ መድረስ ይኖርበታል።
ዓምና፣ ለማደበሪያ ግዢ፣ 690 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል። አሁን፣ የአለም ገበያው ሲናጋና ዋጋው ሲወደድ፣ ምን ያህል ዶላር እንደሚፈጅ፣ “ፈጣሪ ይወቀው”።
ራሺያና ዩክሬን የስንዴ ሽያጭን ለማገድ ወስነው የለ! ሕንድ እና ሌሎች አገራት ደግሞ፣ የማዳበሪያ ሽያጭን ማገድ ጀምረዋል። ምናለፋችሁ፤ ማዕበሉ እየከፋ ነው።
በእርግጥ፤ የማዳበሪያ  እጥረትና የዋጋ ጡዘት፣ የዚህ ቀውስ ማዕበልና መዘዝ፣ ወደ አገራችን የሚደርሰው፣ ዛሬውኑ ከአለም ዜና ጋር አይደለም። ዜናው ቀድሞ ይደርሳል።ከጥቂት ሳምንታት በኋላ፣ መዘዙ በአካል ይመጣል። የዓለማቀፍ ቀውስ ክፉ ማዕበል፤ የሩቅ አገር ዜና መስሎ የሚቆይ ቢሆንም፤ ማዕበሉ እንደሚመጣ አትጠራጠሩ።
ይሄ ሁሉ የራስ ምታት ለኢትዮጵያ  ያነሰ ይመስላል።  ተጨማሪ ፈተናዎች አሉባት። የምግብ ዘይት ችግር፤ ከባድ የሆድ ቁርጠት ነው፡፡ ከስንዴ ችግር ስር ተከትሎ የሚመጣና የዶላር ኪስን የሚያራቁት ህመም ነው- የምግብ ዘይት ግዢ።
 መድሐኒት፣ ብረታ ብረትና ሌሎች የግንባታ ቁሳቁሶች፣ መኪኖችና ማሽኖች፣ የፋብሪካ ጥሬ እቃዎችና መለዋወጫ መሳሪያዎች፣… ብዙ ዶላር የሚፈልጉ ብዙ ጣጣዎች መኖራቸውንም ስታስቡት፣ በጣም ያስጨንቃል፡፡
መፍትሔውስ?
የማዕበሉና የውሽንፍሩ አስከፊነት፣ በቅጡ ከወዲሁ አስቀድሞ መገንዘብ፣ አብጠርጥሮም ማወቅ፣ ለመፍትሔ ፍለጋ ያግዛል፡፡ በጥንቃቄ ለመዘጋጀት፣ ጊዜ ይሰጣል።
በጥንቃቄና በፍጥነት፣ ሁነኛ የመፍትሔ መላዎችን ከመዘየድና ተግባራዊ ከማድረግ ጎን ለጎን፤ ሌላ ተጨማሪ ጥበብ ሊኖረን ይገባል።
አላስፈላጊ የገበያ ግርግርን ከሚያባብሱ፣ ዝርክርክነትን ከሚያበራክቱ የችኮላ ወከባዎች፣ የዘፈቀደ የስንፍና ትርምሶች መታቀብ!


Read 7737 times