Saturday, 19 March 2022 11:30

ኢትዮጵያ በቤልግሬድ 2022 ላይ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

    • ባለፉት 17 ሻምፒዮናዎች ኢትዮጵያ 44 ሜዳልያዎችን (26 ወርቅ 8 ብርና 10 ነሐስ) በመውሰድ ከዓለም 11ኛ ከአፍሪካ አንደኛ
          • በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ 3 የሻምፒዮናው 7 የዓለም ሪከርዶች የኢትዮጵያውያን ናቸው


             18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ትናንት በሰርቢያ ዋና ከተማ ቤልግሬድ ውስጥ ተጀምሯል፡፡ ሻምፒዮናውን የሚያስተናግደው በ70 ሚሊዮን ዩሮ የተገነባው ዘመናዊው ስታርክ አሬና ቤልግሬድ ስታድዬም ሲሆን በ13 የሩጫ እና የሜዳ ላይ ስፖርቶች 26 የውድድር መደቦች ተዘጋጅተዋል፡፡ 137 አገራትን የወከሉ ከ687 በላይ አትሌቶች ይሳተፉበታል፡፡
በዓለም  የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ላይ 14 አትሌቶችን የያዘው የኢትዮጵያ ቡድን በመካከለኛ ርቀት የሩጫ ውድድሮች በሁለቱም ፆታዎች የሚሳተፍ ይሆናል፡፡ በ800 ሜትር ሴቶች ሃብታም አለሙና ትእግስት ግርማ፤ በ1500 ሜትር ጉዳፍ ፀጋይ፣ ሂሩት መሸሻ እና አክሱማይት አምባይ፤ በ3000 ሜትር ዳዊት ስዩም፣ ለምለም ሃይሉና እጅጋየሁ ታዬ ናቸው፡፡ በ1500 ሜትር ወንዶች ታደሰ ለሚና ሳሙኤል ተፈራ እንዲሁም በ3000 ሜትር ሰለሞን ባረጋ፣ በሪሁ አረጋዊ እና ለሜቻ ግርማ ይሮጣሉ፡፡   ትናንት በወንዶች 3000ሜትር እና በሴቶች 1500 ሜትር የማጣርያ ውድድሮች የተካሄዱ ሲሆን እንዲሁም በሴቶች 800 ሜትር እና 3000 ሜትር የፍፃሜ ውድድሮች ተደርገዋል፡፡ ዛሬ በወንዶች የ1500 ሜትር ማጣርያ እና በሴቶች 1500 ሜትር የፍፃሜ ውድድሮች ሲካሄዱ፤ በነገው እለት ደግሞ በወንዶች የ3000 ሜትር ፍፃሜ ይሆናል፡፡
በ2018 እኤአ ላይ የእንግሊዟ በርሚንግሃም  ባስተናገደችው 17ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በተለያዩ የውድድር መደቦች 11 የወርቅ ሜዳልያዎችን የወሰዱ  ሻምፒዮኖች በቀጥታ ተሳትፎ አግኝተዋል፡፡ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ የዙር ውድድር ላይ ጠንካራ ውጤት ያላቸውም አትሌቶችም መሳተፋቸውም ፉክክሩን ያደምቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ታሪክ በሁለቱም ፆታዎች ከአፍሪካ ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ ግንባር ቀደም እንደሆነች ይታወቃል፡፡ ስለሆነም በ1500 እና በ3000 ሜትር በሁለቱም ፆታዎች በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ የኢትዮጵያ ቡድን ከፍተኛ ውጤት እንደሚያስመዘግብ ተጠብቋል፡፡
በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ላይ በ1500 ሜትር የተጠበቀችው  የ25 ዓመቷ ጉዳፍ ፀጋይ ስትሆን፤ በዓለም አቀፍ ውድድር የመጀመርያ የወርቅ ሜዳልያዋን ለማግኘት ታነጣጥራለች፡፡  ባለፉት 6 የውድድር ዘመናት በ3000 ሜትር 9 ውድድሮችን ያሸነፈችው አትሌቷ በያዝነው የውድድር ዘመን በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ በቶሩንና በማድሪድ ከተሞች በማሸነፍ ምርጥ ብቃት ማሳየቷ ይታወቃል፡፡ ጉዳፍ ፀጋይ በ2016 እኤአ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ3000 ሜትር፤ በ5000 ሜትር ደግሞ በ2019 እኤአ በኳታር ዶሃ  በ17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ እንዲሁም በ2021 እኤአ በ32ኛው ኦሎምፒያድ በጃፓን ቶኪዮ 3 ነሐስ ሜዳልያዎችን  ተጎናፅፋለች፡፡ በሴቶች 1500 ሜትር ባለፉት 5 ሻምፒዮናዎች  ላይ የወርቅ ሜዳልያዎችን የወሰዱት ኢትዮጵያውያን ወይም ትውልደ ኢትዮጵያውን አትሌቶች ናቸው፡፡  ገንዘቤ ዲባባ በ2018 እና በ2012፤ ቃልኪዳን ገዛሐኝ በ2010 እንዲሁም ገለቴ ቡርቃ በ2008 እኤአ ላይ በ1500 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ሲወስዱ፤ በ2012 ላይ አበባ አረጋዊ ለስዊድን እንዲሁም ሲፋን ሃሰን ለሆላንድ በ2014 እኤአ ላይ የርቀቱ ሻምፒዮኖች ነበሩ፡፡   በቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናው በወንዶች 1500 ሜትር ከኢትዮጵያ አትሌቶች ቅድሚያ ግምት የተሰጠው ደግሞ የ22 ዓመቱ ሳሙኤል ተፈራ ነው፡፡ በ2018 እኤአ ላይ በበርሚንግሃም በተካሄደው 17ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በርቀቱ የወርቅ ሜዳልያውን ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን ዘንድሮ የሚወዳደረው ሻምፒዮንነቱን ለማስጠበቅ ነው፡፡
በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ላይ በሁለቱም ፆታዎች በሚደረጉት የ3000 ሜትር ውድድሮችም ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች  ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ትናንት በሴቶች  3000 ሜትር ከተደረገው የፍጻሜ ውድድር በፊት ባለፉት 17 ሻምፒዮናዎች በርቀቱ 8 የወርቅ ሜዳልያዎችን የወሰዱት የኢትዮጵያ አትሌቶች ናቸው።   የኢትዮጵያ ቡድን የተሳተፈው ይህን ክብር ለማስጠበቅ ነው፡፡ በሌላ በኩል በወንዶች 3000 ሜ  ሻምፒዮንነቱን ለማስጠበቅ የሚወዳደረው የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ሰለሞን ባረጋ ነው፡፡ ሰለሞን በ17ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ3000 ሜትር የወርቅ ሜዳልያውን አሸንፎ ነበር፡፡  
በ1985 እኤአ ላይ ዎርልድ ኢንዶር ጌምስ በሚል ስያሜ መካሄድ የጀመረው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኮቪድ 19 ሳቢያ  ባለፉት 4 የውድድር ዘመናት  አልተካሄደም ነበር፡፡ የሰርቢያዋ ቤልግሬድ ከተማ ከምታስተናግደው 18ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኋላ  በ2023 እኤአ  የቻይናዋ ናይጂንግ እንዲሁም በ2024 እኤአ  የስኮትላንዷ ግላስኮው ከተሞች 19ኛው እና 20ኛውን የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች እንደቅደምተከተላቸው እንደሚያዘጋጁ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር አስታውቋል፡፡
በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አህጉር በሁለቱም ፆታዎች ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት። ከ17 የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በ16ቱ በመሳተፍ በሜዳልያ ስብስብ እና እስከ 8ኛ ደረጃ በተገኙ ውጤቶች 420 ነጥብ በማስመዝገብ ከዓለም 11ኛ ከአፍሪካ አህጉር 1ኛ ሆና ተቀምጣለች። ለኢትዮጵያ 44 ሜዳልያዎችን (26 ወርቅ 8 ብርና 10 ነሐስ) ያስመዘገቡት 14 ወንድና 15 ሴት አትሌቶች ናቸው፡፡ ከሜዳልያ ውጤት ባሻገር  11 ጊዜ አራተኛ፤ 5 ጊዜ አምስተኛ፤ 5 ጊዜ ስድተኛ፤ 2 ጊዜ ሰባተኛ እንዲሁም 2 ጊዜ ስምንተኛ ደረጃዎችንም አግኝተዋል፡፡ ባለፉት 17 የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ላይ የኢትዮጵያ ቡድን በወንዶች ምድብ በ211 ነጥብ ከዓለም 11ኛ የሆነው 20 ሜዳልያዎች (13 ወርቅ 2 ብርና 8 ነሐስ)  እንዲሁም 6 ጊዜ አራተኛ፤ 5 ጊዜ አምስተኛ፤ 3 ጊዜ ስድስተኛ፤ 2 ጊዜ ሰባተኛ ደረጃዎችን በማስመዝገብ ነው፡፡ በሴቶች  በ209 ነጥብ ከዓለም 11ኛ ላይ የተቀመጠችው  ደግሞ ሲሆን 24 ሜዳልያዎች (13 ወርቅ 6 ብርና 5 ነሐስ) ፤ 5 ጊዜ አራተኛ፤ 2  ጊዜ ስድስተኛ፤ 2 ጊዜ ስምንተኛ ደረጃዎችን  በመያዝ ነው፡፡
በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ በሁለቱም ፆታዎች ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው  5 የወርቅ ሜዳልያዎችን በ1500 እና በ3000 የሰበሰበችው  ገንዘቤ ዲባባ ናት፡፡ ኃይሌ ገብረስላሴ ደግሞ ከኢትዮጵያ አትሌቶች  በወንዶች ምድብ ከፍተኛውን ውጤት የያዘው በ3ሺ ሜትር 3 እንዲሁም በ1500 ሜትር 1 በድምሩ 4 የወርቅ ሜዳልያዎች በመውሰድ ሲሆን በ31 ነጥብ ከወንድ አትሌቶች ከዓለም 9ኛ ደረጃ ይዞበታል፡፡ አትሌት  መሰረት ደፋር በ7 ሻምፒዮናዎች ላይ በመወዳደር በኢትዮጵያ ከፍተኛውን ተሳትፎ ያስመዘገበች ሲሆን በ3000 ሜትር 4 የወርቅ 1 የብርና 1 የነሐስ በድምሩ 7 ሜዳልያዎችን በመጎናፀፍ ደማቅ ታሪክ አስመዝግባለች፡፡ ይህ ውጤቷም በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የምንግዜም ውጤት ደረጃ ላይ በ52 ነጥብ ከዓለም 6ኛ ደረጃ አስቀምጧታል፡፡ አትሌት መሃመድ አማን በ2012 እኤአ ላይ በ18 ዓመት ከ61 ቀናት እድሜው በ800 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ በማሸነፍ ወጣቱ ሻምፒዮን ነው፡፡  የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 3 ክብረወሰኖች በኢትዮጵያውያኑ ተመዝግበዋል፡፡ ሁለቱ የሻምፒዮናው ክብረወሰኖችን ኃይሌ ገብረስላሴ በ1500 ሜትር በ1999 እኤአ ሜምባሺ ጃፓን ላይ 3፡33.17 በሆነ ጊዜ እንዲሁም በ3000 ሜትር በ1997 እኤአ በፈረንሳይ ፓሪስ ላይ 7፡34.71 በሆነ ጊዜ ያስመዘገባቸው ናቸው። ገለቴ ቡርቃ ደግሞ በ2008 እኤአ ላይ በስፔን ቫሌንሽያ በ1500 ሜትር የውድድሩን ክብረወሰን 3፡59.75 በሆነ ጊዜ ይዛለች፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ የኢትዮጵያ አትሌቶች በሁለቱ ፆታዎች 7 ሪከርዶች ይዘው ይገኛሉ። በወንዶች 1500 ሜትር ሳሙኤል ተፈራ 3፡31.04 በ2019 እኤአ በርሚንግሃም፤ በ1 ማይል ዮሚፍ ቀጀልቻ 3፡47.01 በ2019 እኤአ በአሜሪካ ቦስተን እንዲሁም በ5000 ሜትር ቀነኒሳ በቀለ 12፡49.60 በእንግሊዝ በርሚንግሃም በ2004 እኤአ ላይ 3 የዓለምን ሪከርዶች በቤት ውስጥ አትሌቲክስ አስመዝግበዋል፡፡ በሴቶች ደግሞ በ1500 ጉዳፍ ፀጋይ 3፡31.04 በሌይቨን ፈረንሳይ በ2019 እኤአ ላይ ስታስመዘግብ፤ የገንዘቤ ዲባባ 3 የቤት ውስጥ አትሌቲክስ የዓለም ሪከርዶች በስዊድኗ ስቶክሆልም ከተማ ላይ በ2006 እኤአ ላይ በ1 ማይል 4፡13.31፤ በ2014 እኤአ ላይ በ3000 ሜትር 8፡16.60 እንዲሁም በ2015 እኤአ ላይ በ5000 ሜትር 14፡18.86 በሆነ ጊዜ እንደያዘችው ነው፡፡፡

Read 19756 times