Saturday, 19 March 2022 11:34

በኮሮና የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከሚነገረው በ3 እጥፍ ይበልጣል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   በአለማችን የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ጭማሪ አሳይቷል

             ሶስተኛ አመቱን የያዘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በመላው አለም ለህልፈተ ህይወት ዳርጓቸዋል ተብሎ በይፋ የሚነገረው  6 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ቢሆንም፣ ትክክለኛው ቁጥር ግን ከዚህ በ3 እጥፍ እንደሚበልጥ አንድ መረጃ አመለከተ፡፡
በቅርቡ በ191 የአለማችን አገራት ትክክለኛውን የሟቾች ቁጥር ለማጣራት ታስቦ የተሰራ አንድ አለማቀፍ ጥናት ወረርሽኙ በመላው አለም ለሞት የዳረጋቸው ሰዎች ቁጥር 18 ሚሊዮን እንደሚደርስ ማረጋገጡንና አብዛኛው ሞት ሳይመዘገብ በመቆየቱ ልዩነቱ ሊፈጠር መቻሉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት በበኩሉ፤ በአለማቀፍ ደረጃ ከአንድ ወር በላይ ለሚሆን ተከታታይ ጊዜ መቀነስ አሳይቶ የነበረው የአዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፈው ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ መጨመር ማሳየቱን የገለጸ ሲሆን፣ የኦሚክሮን ዝርያ በፍጥነት መስፋፋቱና አገራት የጥንቃቄ ስርዓታቸውን ማላላታቸው ለጭማሪው ምክንያት መሆኑንም አመልክቷል፡፡
የአዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፈው ሳምንት በ8 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የጠቆመው ድርጅቱ፤ በሳምንቱ በመላው አለም 11 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸውንና ከ43 ሺህ በላይ የሚሆኑ መሞታቸውንም አክሎ ገልጧል።
የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በዚህ ሳምንት ከ463 ሚሊዮን ማለፉ የተነገረ ሲሆን፣ አሜሪካ በ79.6 ሚሊዮን ተጠቂዎችና 970 ሺህ ሟቾች ከአለማችን አገራት በቀዳሚነት እንደምትቀመጥም ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡


Read 1879 times