Sunday, 20 March 2022 00:00

ሩስያ፣ ዩክሬን እና የተቀረው አለም በሳምንቱ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ከትናንት በስቲያ አራተኛ ሳምንቱን የያዘው የሩስያና ዩክሬን ጦርነት ተፋፍሞ የቀጠለ ሲሆን፣ የሩስያ ጦር መዲናዋን ኪዬቭ ጨምሮ በማሪፖል፣ ቸርኒቭና ካርኪቭ እንዲሁም ሌሎች የዩክሬን ከተሞችን በከባድ የሚሳኤል ድብደባ ማውደሙን እንደቀጠለ ቢነገርም፣ የብሪታኒያ መከላከያ ሚኒስቴር ግን ሩስያ ከዩክሬን ከፍተኛ ትግል እያጋጠማት ወደ ኋላ እየሸሸች እንደሆነ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
የዩክሬን የጦር ሃይል በበኩሉ፤ 14 ሺህ ያህል የሩስያ ወታደሮችን መግደሉንና 21 ሺህ የሚደርሱትን ማቁሰሉን፤ 108 ሄሊኮፕተሮችን፣ 444 ታንኮችንና 864 የጦር ተሸከርካሪዎችን ማውደሙን ሲያስታውቅ፣ በዩክሬን የአሜሪካ ኤምባሲ ግን የሟች ሩስያውያን ወታደሮችን ቁጥር ወደ 10 ሺህ ዝቅ እንዳደረገው ኒውዮርክ ፖስት ዘግቧል፡፡
የሩስያው ፕሬዚዳንት ባለፈው ረቡዕ ምሽት በቴሌቪዥን ለመላው አለም ባስተላለፉት መልዕክት፤ ጦራቸው በሁሉም ግንባሮች ጥቃቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና በአጭር ጊዜ ድልን እንደሚጎናጸፍ ሲያስታውቁ፣ የዩክሬኑ አቻቸው ቮሎድሚር ዜለንስኪ በበኩላቸው፤ "ሩስያ የአለማችን ቀንደኛ አሸባሪ አገር ናት፤ ቢሆንም እጅ አንሰጥም" ብለዋል፡፡
የአገራቸው ጦር ባለፈው ረቡዕ በማሪዮፖል ከተማ አቅራቢያ በፈጸመው ጥቃት አራተኛውን የሩስያ ጄኔራል መግደሉን ያስታወቁ ሲሆን፣ ለአሜሪካ ኮንግረስ ባደረጉት የቪዲዮ ንግግርም የበለጠ ድል ለመቀዳጀት የሚያስችላቸው የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል። አሜሪካ በበኩሏ፤ ለዩክሬን የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል መከላከያና ድሮኖችን ጨምሮ የተለያዩ ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ ለመስጠት መዘጋጀቷን አረጋግጣለች፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ የሩስያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲንን #የጦር ወንጀለኛ ናቸው; ማለታቸውን ተከትሎ፣ የሰውዬው ንግግር በቋፍ ላይ ያለውን የሁለቱ አገራት ግንኙነት የበለጠ እንዳያሻክረው የተሰጋ ሲሆን፣ የሩስያ መንግስት ቃል አቀባይ ዲምትሪ ፔስኮቭ ለባይደን ንግግር በሰጡት መረር ያለ ምላሽ፤ “በተለያዩ የአለማችን አገራት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በጭካኔ ያጠፋች አገር መሪ፣ ፑቲንን በጦር ወንጀለኝነት የሚከስስበት ሞራል የለውም” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የብሪታኒያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዝ ትሩስ በበኩላቸው፤ ፑቲን የጦር ወንጀለኛ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ተጨባጭ ማስረጃዎች እንዳሉ በመጥቀስ፣የባይደንን ንግግር ማጠናከራቸውን አስነብቧል፡፡
ፑቲን፤ ምዕራባውያን በሩስያ የእርስ በእርስ ጦርነት ለመቀስቀስና አገሪቱን ለመበታተን ታጥቀው ተነስተዋል ሲሉ በመክሰስ ለአገራቱ ማስጠንቀቂያ የሰጡ ሲሆን፣ አገራቸው በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንና ሄላሪ ክሊንተን እንዲሁም ሌሎች 12 የአገሪቱ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣሏን ባለፈው ረቡዕ ይፋ አድርገዋል፡፡
ይህ አደገኛ ጥቃት ጦርነቱ ወደሌሎች አገራት ሊስፋፋና ኔቶን ሊያሳትፍ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት መፈጠሩ የተነገረ ሲሆን፣ የዩክሬኑ መሪ ቮሎድሚር ዜለንስኪም ባለፈው ሰኞ በሰጡት መግለጫ፤ ጦርነቱ ወደሌሎች አገራት ሊዘልቅ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፤ የሩስያ ወታደሮች እጃቸውን እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጦርነቱን በድል ሳያጠናቅቁ እንደማይመለሱ በይፋ ያስታወቁት የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ የሌሎች የውጭ አገራት ዜጎችን ጨምሮ በጎ ፈቃደኞች ከአገራቸው ጎን ቆመው እንዲዋጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ ሶርያውያን ታጣቂዎችን ጨምሮ ከ16 ሺህ በላይ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ወታደሮች ፈቃደኛነታቸውን መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የአሜሪካ የደኅንነትና ጥበቃ የግል ኩባንያዎች፣ ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ የውጭ አገራት ወታደሮችን ለዩክሬን እንዲዋጉ በመመልመል ላይ እንደሚገኙ የተዘገበ ሲሆን፣ ኩባንያዎቹ ግን ወታደሮችን ሳይሆን ዩክሬናውያንን ከአደጋ የሚያተርፉ ሰዎችን ነው እየመለመልን ያለነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
ፍልሚያው ከጦር ሜዳ አልፎ በኢኮኖሚውና በሳይበሩ አውድ ተጧጡፎ የቀጠለ ሲሆን፣ ዩክሬን አለማቀፍ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎችና የመረጃ መንታፊዎች ሩስያን ለማጥቃት ከጎኗ እንዲሰለፉ በይፋ ጥሪ አቅርባለች፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አይቲ አርሚ ኦፍ ዩክሬን የተባለ የሳይበር ክፍለ ጦር ተመስርቶ ከመላው አለም 300 ሺህ ያህል የተለያዩ አገራት አባላትን ማፍራት መቻሉንና በሩስያ ላይ የሳይበር ጥቃት ለመፈጸም በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ለቀናት የኤሌክትሪክ ሃይል በመቋረጡ ሳቢያ ለከፋ የራዲዮአክቲቭ ስርገት አደጋ ይጋለጣል ተብሎ ሲሰጋለት የነበረው የዩክሬኑ የኒውክሌር ማብላያ ጣቢያ ቸርኖቤል፣ ማክሰኞ ዕለት ኤሌክትሪክ ማግኘት መቻሉም ተነግሯል፡፡
ዲፕሎማሲ እና እሳት ቁስቆሳ
በወዲህ ነገሩን ለማብረድ፣ በወዲያ ደግሞ በእሳት ላይ ቤንዚን ለመጨመር የተጀመረው ደፋ ቀና አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ከነፍጥ ይልቅ በንግግር ችግሩን ለመፍታት በማሰብ ባለፉት ሳምንታት ለሶስት ዙር በቤላሩስ አንዴ ደግሞ በቱርክ እያተገናኙ ውይይቶችን አድርገው፣ ይህ ነው የተባለ ውጤት ላይ ሳይደርሱ የተለያዩት የሩሲያና የዩክሬን ተወካዮች፤ ረቡዕ ዕለትም በቪዲዮ የታገዘ ሌላ ውጤት አልባ ውይይት አድርገው ተበትነዋል፡፡
አለማቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ባለፈው ረቡዕ ባስተላለፈው ውሳኔ፤ ሩስያ በዩክሬን ላይ የጀመረችውን ወረራ በአፋጣኝ እንድታቆም የጠየቀ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ለማስፈጸም አቅም እንደሌለውና ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ውሳኔ የተላለፈባቸው አገራት ውሳኔውን ከቁብ እንዳልቆጠሩት በማስታወስ ጉዳዩን ያጣጣሉት መኖራቸውንም ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የፖላንድ፣ ቼክ ሪፐብሊክና ስሎቬኒያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ማክሰኞ ዕለት ወደ አገሪቱ በመጓዝ፣ ከዩክሬኑ መሪ ጋር የተወያዩና አጋርነታቸውን በጽኑ አረጋግጠው የተመለሱ ሲሆን፣ አሶሼትድ ፕሬስ በበኩሉ፤ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት ሰኞ ዕለት ለሁለቱም አገራት መሪዎች ባደረጉት የስልክ ጥሪ ለማግባባት ጥረት ማድረጋቸውን አስነብቧል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከሰሞኑ ወደ ቤልጂየምና ፖላንድ በመጓዝ ከኔቶ አባል አገራት መሪዎች ጋር በጦርነቱ ጉዳይ ዙሪያ ለመምከር ማሰባቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን ጦር 500 ሚሊዮን ፓውንድ የሚገመት ወታደራዊ እርዳታ ያደረገ ሲሆን፣ ጀርመን፣ ፊንላንድ፣ ስዊድን፣ ዴንማርክ፣ ኖርዌይና ስፔንን ጨምሮ ለዩክሬን የጦር መሳሪያዎችን በገፍ የሚያበረክቱ አገራት ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፡፡
እንግሊዝ ከሩስያ ሊቃጣ የሚችልን የአየር ጥቃት ለመከላከል በፖላንድ ዘመናዊ ሚሳኤል ለመትከልና 100 ወታደሮችን ለማሰማራት መወሰኗን ይፋ ያደረገች ሲሆን፣ የቼክ ሪፐብሊክ የመከላከያ ሚኒስትር ጃና ሴርኖቾቫ በበኩላቸው፤ አገራቸው 725 ሚሊዮን ክሮነር የሚገመት የጦር መሳሪያ ለዩክሬን መስጠቷን አስታውቀው፣ በቀጣይም ተመሳሳይ መጠን ያለው መሳሪያ ለመስጠት መታቀዱን እንዳስታወቁ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከሰሞኑ ሩሲያ ቻይናን ወታደራዊ ድጋፍ እንድታደርግላት መጠየቋን አንድ ስማቸው ያልተገለጸ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ተናገሩ የሚል ዜና በስፋት ሲሰራጭ የነበረ ሲሆን፣ ሁለቱም አገራት ግን ዜናው ሃሰተኛና መሰረተ ቢስ ነው ሲሉ እንዳጣጣሉት ተነግሯል፡፡
ታዋቂዎቹን የአሜሪካ ሚዲያዎች ኒውዮርክ ታይምስና ሲኤንኤንን ጨምሮ በርካታ ስመጥር መገናኛ ብዙሃን ሩስያ ከቻይና ወታደራዊ ድጋፍ ጠይቃለች የሚለውን ዜና ሲያራግቡት ቢቆዩም፣ በአሜሪካ የቻይና ኤምባሲ ግን መረጃው ሃሰተኛ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ቻይና ለሩሲያ ወታደራዊ ድጋፍ የምትሰጥ ከሆነ የከፋ ምላሽ ይጠብቃታል ሲል ማስጠንቀቁን የጠቆመው የቢቢሲ ዘገባ፤ የሩሲያ መንግሥት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው፤ አገራቸው የገባችበትን ጦርነት ያለማንም ድጋፍ በድል የመወጣት አቅም እንዳላትና የተባለውን ድጋፍ እንዳልጠየቀች ምላሽ መስጠታቸውን አመልክቷል፡፡
በሰርቢያ መዲና ቤልግሬድ ከሰሞኑ የሩስያውን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና በዩክሬን ላይ ያደረጉትን ወረራ የሚደግፍ ሰልፍ የተደረገ ሲሆን፣ ደጋፊዎቹ አደባባይ ወጥተው የሰርቢያንና የሩሲያን ባንዲራ ከፍ አድርገው ማውለብለባቸው ተዘግቧል፡፡
ምዕራባውያንን ጨምሮ የተለያዩ የአለማችን አገራት በሩስያ ላይ ተጨማሪ አዳዲስ ማዕቀቦችን እየጣሉ ሲሆን፣ ብሪታኒያ የቀድሞውን የሩስያ ፕሬዚዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭን ጨምሮ በ370 ሩስያውያን ግለሰቦችና ተቋማት ላይ ተጨማሪ አዳዲስ ማዕቀቦችን መጣሏን አስታውቃለች፡፡ ብሪታኒያ የቅንጦት ምርቶችን ጨምሮ አንዳንድ ሸቀጦችን ወደ ሩስያ ላለመላክ ከመወሰን ባለፈ በአንዳንድ የሩስያ ምርቶች ላይም ከፍተኛ የቀረጥ ጭማሪ አድርጋለች፡፡
የጃፓን መንግስት ከ17 በላይ የሚሆኑ የሩስያ ባለጸጎችና ፖለቲከኞችን ሃብት እንዳይንቀሳቀስ ያገደ ሲሆን፣ የአውሮፓ ህብረት አገራትም የ4ኛ ዙር ማዕቀቦችን መጣላቸውን ማክሰኞ ዕለት አስታውቀዋል፡፡ የአውስትራሊያ መንግሥት በበኩሉ፤ በ33 የሩስያ ባለሃብቶችና ቤተሰቦቻቸው ላይ አዲስ ማዕቀብ እንደሚጥል ማስታወቁም ተዘግቧል።
የፖላንዱ ፕሬዚዳንት አንድሬ ዱዳ በበኩላቸው፤ የሩስያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱን በድል እንደማያጠናቅቁ ሲገባቸው የኬሚካል ጦር መሳሪያን ጨምሮ ያላቸውን አውዳሚ አማራጭ ሁሉ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን፣ ፑቲን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የኬሚካል ጦር መሳሪያን የተጠቀሙ ብቸኛው የአለማችን መሪ ሊሆኑ እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡
ሩሲያ የኬሚካል ጦር መሳሪያን ከተጠቀመች የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ወደ ጦርነቱ ለመግባት ሊገደድ ይችላል ያሉት ዱዳ፣ ይህም ነገሩን ከሁለቱ አገራት አውጥቶ የአለም ጦርነት ሊያደርገው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
በየቀኑ 75 ሺህ ህጻናት ይሰደዳሉ፤ ጥፋቱ ልክ የለውም
የዩክሬንና የሩስያ ጦርነት በየአንድ ሰከንዱ አንድን ህጻን፣ በየቀኑ 75 ሺህ ህጻናትን እያሰደደ ይገኛል ብሏል የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ፡፡
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ አገራቸውን ጥለው የተሰደዱ ዩክሬናውያን ቁጥር ከ3 ሚሊዮን ማለፉ የተነገረ ሲሆን፣ ግማሽ ያህሉ ህጻናት መሆናቸውንና በአገር ውስጥ የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥርም ከ2 ሚሊዮን ማለፉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ድርጅት ማስታወቁም ተዘግቧል፡፡
የብሪታኒያ መንግስት የዩክሬን ስደተኞችን በመኖሪያ ቤታቸው ለሚያስጠልሉ የአገሪቱ ዜጎች በየወሩ 350 ፓውንድ እንደሚከፍል ባለፈው እሁድ ማስታወቁን ተከትሎ፣ በሰዓታት ውስጥ ከ89 ሺህ በላይ ሰዎች ፈቃደኛነታቸውን መግለጻቸውንም ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የዩክሬን ዋና ዓቃቤ ሕግ ባለፈው ሃሙስ ባወጣው መግለጫ፤ የሩስያ ጦር አገሪቱን ከወረረበት ጊዜ አንስቶ ከ120 በላይ ንጹሃን ህጻናትን መግደሉን እንዳስታወቀ ዩሮ ኒውስ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
ሩስያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ ከየአቅጣጫው የዘነበባት የማዕቀብ ዶፍ የአገሪቱን ዜጎች ገፈት ቀማሽ እያደረጋቸው እንደሚገኝ የተነገረ ሲሆን፣ የዋጋ ንረት በእጅጉ እየጨመረና የምግብ ዋጋ ከ24 አመታት በኋላ ከፍተኛው ደረጃ ላይ መድረሱን ነው አልጀዚራ የዘገበው፡፡
የሩስያ የመገበያያ ገንዘብ ባለፉት 3 ሳምንታት የመግዛት አቅሙ በ20 በመቶ ያህል መቀሰኑን፤ በሩስያ ከፍተኛ የሸቀጦችና የመድሃኒት እጥረት ማጋጠሙን እና በአገሪቱ በርካታ ኩባንያዎች በመዘጋታቸው ሳቢያ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለስራ አጥነት እየተዳረጉ እንደሚገኙም ዘገባው አመልክቷል፡፡
የጦርነቱ ጦስ ለአፍሪካ
የሩስያና የዩክሬን ጦርነት ከራሳቸውና ከጎረቤት አገራት ባለፈ ለአፍሪካም ዳፋው እንደሚተርፍ እየተነገረ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስም ባለፈው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ፤ጦርነቱ በአለማቀፍ ደረጃ የምግብ እጥረትን ሊያስከትል እንደሚችልና በተለይ በአፍሪካ ከፍተኛ የስንዴ እጥረት ሊፈጥር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
ብዙ የአፍሪካ አገራት የሩስያና የዩክሬን የስንዴ ምርት ጥገኛ መሆናቸውን ያስታወሱት ዋና ጸሃፊው፣ ሁለቱም አገራት ወደ ውጭ የሚልኩትን የስንዴ ምርት ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ማቆማቸው በአፍሪካ የስንዴ እጥረትና የዋጋ ንረት ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ዩክሬን እና ሩስያ ከመላው አለም የስንዴ አቅርቦት 30 በመቶውን እንደሚሸፍኑ የጠቆሙት ጉቴሬስ፤ ግብጽ፣ ኮንጎ፣ ቡርኪናፋሶንና ሊቢያን ጨምሮ 18 የአፍሪካ አገራት 50 በመቶ ያህል ስንዴ የሚያገኙት ከሁለቱ አገራት መሆኑን በመግለጽ ጦርነቱ አገራቱን ክፉኛ ሊጎዳቸው እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ በበኩሉ፤ ጦርነቱ በአፍሪካ ሊያስከትል የሚችለውን የስንዴ እጥረት ለማቃለልና በአፍሪካ አገራት የስንዴ ምርትን ለማሳደግ የሚያስችል 1 ቢሊዮን ዶላር ያህል መመደቡን ሃሙስ ዕለት ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ድጋፉ 40 ሚሊዮን ያህል አፍሪካውያን አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡

Read 1153 times