Saturday, 19 March 2022 11:16

ግራጫ - ሐሳቦች በፍርንዱስ

Written by  ሳሙኤል በለጠ (ባማ)
Rate this item
(3 votes)

  “ፍሬዘር የማንነት ገጣሚ ነው። የፍልስፍና ፈልፋይ ነው። የቃል ዲታ ነው። በተቃርኖ ነገር እንደ መደበኛ ሐሳብ መጫወት ይችላል! በጥልቀት እንድናስብ፤ ከሄድን በኋላ ተመልሰን እንድንጠይቅ የሚያስገድዱ ፤ አያሌ ተጠቃሽ መስመሮች አመራማሪ ሐረጎች አሉት። እውነት!;
           
           “ገጣሚ ዐይደለሁም ግጥም ‘ራሱን እንጂ" (I am not a poet but, the poetry itself I am) የምንል እኛ የመሬትን ስበት በመግታትና በኃይል የምናብ ከፍታ ከሕዋ በላይ በመገኘት ሂደት ውስጥ ያለን እኛ፤ ገሀዱን እንድንመሰጥርና ምስጢራትን እንገልጥ ዘንድ ተፈጥረናል (To visualize the invisible and/or the reverse, created we are) በማለት በሥነ-ግጥም ቅኝትና ትርጓሜ የምናስብና ኑሯችንም እራሱ ግጥም የሆነ እኛ ...ያሰብነውን ለማሳሰብ ወይም ያልታሰበ ለማሰብ፤ አሊያም በማንበብና በመጻፍ መስተጋብር ውስጥ እንደሚገባ ለመተሳሰብ፤ ሥነ-ግጥምን እንደ ብርሃን ድልድይ ስንጠቀም፣ ከአለንበት ወደ ሌለንበት ስሜትን እውነትንና ጥበብን ይዘን፤ እንዲሁም በእርሱ ተይዘን እንደሆነ እናምናለን። “[የገጣሚው መግቢያ (X XI )]
 ሥነ-ግጥም ራሱ ግጥም ባልሆነ ከያኒ ሲሞከር፤ ለውበት ለእውነት፣ ለሐሳብ፣ ለቀለም ንክር አይሆንም፡፡ ፍሬዘር አድማሱ በአማርኛ ሥነ-ግጥም እምብዛም ያልተሄደበትን መንገድ መርጦ ሄዷል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፤ ሰለሞን ደሬሳ ሙከራዎቼ ናቸው ባላቸው በ#ልጅነት; እና በ"ዘበትልፊቱ" መድበሎች አዲሴ የአገጣጠም ስልት አስተዋውቆናል። ሳርተር እንደሚለው፤ “ማንኛውም ግለሰብ ፍጹም ሉአላዊ ስለሆነ የራሱን ግንዛቤ መሠረት አድርጐ፣ የሕይወት ትርጉሙንና ሥነ ምግባራዊና ሥነ-ውበታዊ እሴቶቹን ፈጥሮ የመኖር ሥልጣንና ኃላፊነት አለው፡፡ “ስለዚህ ገጣሚያን ግላዊ ነጻ ምናባቸውንና እሳቤያቸውን ተጠቅመመው ግጥም የመደርደር ያልተጻፈ መብት አላቸው፤  ቅፅበታዊ ጥበባዊ ስሜት (automatic impression) ሌላው የሥነ-ግጥም መነሻ ነው። የእነ ሰለሞን ደሬሳ፣ ከበደች ተክለአብ፣ ስንቅነህ እሸቱ መንገድ ይሄ ነው።
የፍሬዘር ግጥም፤ “ያሰብነውን ለማሳሰብ ይሆነናል፤ ያልታሰበ ለማሰብ ራሱ ከእኛ ቀድሞ ይንደረደራል።"
“...ሰውነት የሚያሰኝ ይሄ ስብዕና
በሕልቆ መሳፍንት በዐይለከት ቁና
ከዘላለም በስቲያ የሚኖር ነው እና
አምላክ ሆነህ ዝለቅ አንተን ፍጠርና።
[ፍርንዱስ ገጽ-18] ሰውነት ትርጉም ለመፍተል ሲፍጨረጨር፣ ትርጉሙ “ራስን መፍጠር” ‘ሚል ቅርጽ ያዘበት፡፡ ፈረንሳዊው ፈላስፋ ሬኔ ዴካርት በ“principles of philosophy” ላይ “የመፍጠርንና የአፈጣጠርን” ጉዳይ ይብከነከንበታል። “በፈጣሪና በዩኒቨርስ መካከል ያለው ግንኙነት በሰዓት ሰሪውና በሚሰራው ሰዓት ይመሰላል። የሰዓት ሥራ አንድ ጊዜ ሰዓቱን ከሰራው በኋላ የሰዓቱ እንቅስቃሴ የሚወሰነው በራሱ በሰዓቱ ላይ ነው” ይላል። ሰው መሆን ጉዞ የውስጥ ሰብዕና በውጫዊ የጊዜ ክብቦሽ ይሽከረከራል። በዐፍታና ዘላለም ተደባልቀው መከራና ደስታ ሙዳ ሥጋውን ሲሰሩት፣ በውስጠ ታዋቂነት የነፍሱ መቅደስ ታንጾ ወደ ምጽዓት ይሸበልላል (ሰው)፤ ገጣሚውም
“...የዚህ ሐሳብ ሎሌ ሞቶ የወለደው
 እንዲህ እያለ ነው
 በሕይወቴ ጫፍ ላይ ጭራ ሆኖ ያለው
 ልደቴ ትዝታ ሞቴ ተስፋዬ ነው።
 ይኸው ነው !
[ፍርንዱስ ገጽ-32]  
የበረደው የትዝታ ልደት ሲጃጃ ተስፋ ሆነው፤ ግጥሙ ረዥም ነው። ነገር ግን ጥፍር የሚያንቀጠቅጥ ‘ምስጢር የከተተ ‘ሚናዘር የግጥም አደራደር ስልት ነው። ‘ሚጠቀመው  “በለስ የቀናት ለት / ሕይወት እንደዚህ ናት / ሞትን መገነዣ፣ ስዉር ስፌት አላት!” (ስውር ስፌት ነቢይ መኮንን) ያ ስውር ስፌት ተስፋ ይሆን ?
ከ-ወ-ደ
የጊዜን ሂደት ገፍቼ
ቅጽበቱን እጅግ አፍጥኜ
ጅምሩን ለወግ አብቅቼ
ሞቼ ጉድ አይቼ!
በኋላን ቅድም አድርጌ
ነበር ለመባል ያለሁት
የማይገባ ድካሜን
ለመቼ በአግባብ ባረፍኩት
በሞትሁት!
[ፍርንዱስ ገጽ-80]
ልብሱ የተበጣጠቀ በሐሳብ ያበደ አንድ ጊዜን የተሸከመ ሽማግሌ፤ እየመደመር ፣ እየመቀነስ ነው። እኛ ማባዛት ማካፈል ነው ‘ምናቀው፤  የሚያውቀው መዝምታ ወርቅነቱ፣ ውስጠ ውስጠት ውስጥ ከእስከ መሆን ተቅበዘበዘ  ሞት ያስመኛል ዐይደል? ለምንድነው? መደመር መቀነስ እብደት አይደል?  ለዚህ የኅላዌ ተቃርኖ አያ መንግስቱ ለማ ቅኔ ቋጥረዋል። “ምንድነው ሰበቡ..” ለምንድነው አልኩኝ፤ ስለምን ምክንያት፤/ ይህ ዓለም መኖሩ አዱኛ ሕይወት፤ /ሕጻን መወለዱ አርጅቶ ሊሞት፤ /ለምንድነው አልኩኝ /ለምን ምክንያት? (መንግስቱ ለማ ገጽ-3) “ነበር” እንደ ጨለማ በቅጽበት ጭን ውስጥ ተሸጉጦ “ነበር” ውስጥ ሞት ቀድሞ ለጊዜው ቃተተ፥ ልፋት ተጨመተ፣ የምንም መጋረጃ ላይከፈት !
ዋጋ
በቁጥር መስመር ላይ
ዜሮ ሆነህ ስትሮር
‘ሚናህ የሚለየው
የአንዶችን ዋጋ
መቀየር ስትችል ነው።
[ፍርንዱስ ገጽ 79]
“የሰው ልጅ የማንነቱ መገለጫ ባሕርይ (በዚህ ዐውድ ለሰው መኖር እንበለው) ከኅልውናው ይቀድማል። (essence precedes existence)"  ይህ ግጥም ኤፍሬም ሥዩምን “ብዙ ተባዙን” ያስታውሰናል። “ሰውን በመፍጠሩ እግዜር ‘ሚጠቀመው/ ሰውም በመፈጠሩ ከእግዜር የማያገኘው/ አንዳች ነገር ባይኖር፣ አንዳች ድብቅ ነገር / ምድሪቱን ለመሙላት ከብት ይበቃ ነበር ! (ሶልያና የግጥም ሲዲ)
ጊዜያት
ንግርት ሆኖ አይቀርም
ይፈጸማል ቃሉ
የጃጁ ቅድሞች
አሁን ይሞታሉ
ነፍሰጡር ዛሬዎች
ነገን ይወልዳሉ።

የሕይወት ውድቅቶች
የመከራ ሌቶች
ማልደው ይነጋሉ
እውን ሁኔታዎች
ሕልም ሆነው ያልፋሉ
የታሙሙ አሁኖች
ነበር ይሆናሉ
ንግርት ሆኖ አይቀርም
ይፈጸማል ቃሉ።
እያንዳንዱ ችግር
ከመፍትሄ ጋር
ሕብረት እሚያደርገው
ከሐዘን ማህጸን
ደስታ እሚወለደው

ያዳገተ ሒደት
ድርጊት የሚሆነው
እንቁላሉ ጊዜ
ጫጩት ሲሆን ነው።
[ፍርንዱስ ገጽ132-132]
ጊዜ ከትናንት ዛሬ ፣ ከዛሬ ነገ ያለውን አንድነትና ሥስትነት ቀጥታዊ ትስስር በሰው ልጅ “ጊዜያዊነት” ይንጸባረቃል። የጊዜ ማዕቀፍ አለመኖር የሕይወትን ግብ በዘበትነት ይሸመቅቀዋል። ጊዜ ሁነትን (አሁነንትን) ብቻ ሳይሆን ትናንትን አዝሎ፣ ዛሬን አንጠልጥሎ ወደ ነገ የሚደረግ ማዝገም ነው ማለት ነው። ስለዚህ ጊዜ (Time) ለአንዳንዶች ምንም ትርጉም የሌለው መጥበርበር ሲሆን፤ ለሌሎች ደግሞ ኅልውናን ከጊዜ ውጭ ማሰብ መራራ ነው። ጊዜ በኅልውና ላይ ምን ዓይነት ጫና እንዳለው በግልጽ ባይታወቅም፣ የጊዜ እሳቦት ግን በግለሰብ ዘለለት ጫና አለው። ጊዜና ሰው ግራና ቀኝ ከሆኑ፣ ኅልውና እንደሚደፈርስ በዕውቀቱ ሥዩም በአንድ ግጥሙ ስሎታል። “ምኞቴ እሹሩሩ”  የምኞቴ ሥዕል፥ ከግባሬ አንስቼ / ብብቴ ስር ደበቅሁ/ በሥውር ጎምዥቼሽ ፥ ስንት ዘመን ማቀቅሁ /ሳትቀጥሪኝ ቁጭ ብዬ ፥ አንቺን እየጠበቅሁ። [የማለዳ ድባብ ገጽ-74] የነፍሱን ምኞት፥ በገጹ ጻፈ ጊዜን (መቼን ስላልተረዳ) ዘላላለም ሥዕሉ ደበዘዘበት:-
ገጣሚና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን ስለ ፍርንዱስ (ፍሬዘር) በጀርባ አስተያየቱ (Blurb) እንዲህ አለ፡- “ፍሬዘር የማንነት ገጣሚ ነው። የፍልስፍና ፈልፋይ ነው።
የቃል ዲታ ነው። በተቃርኖ ነገር እንደ መደበኛ ሐሳብ መጫወት ይችላል! ቅሜ ብለን እንድናስብ፤ ከሄድን በኋላ ተመልሰን እንድንጠይቅ የሚያስገድዱ፤ አያሌ ተጠቃሽ መስመሮች አመራማሪ ሐረጎች አሉት። እውነት!;

Read 3971 times