Saturday, 19 March 2022 12:18

ትዝታን ሽሽት

Written by 
Rate this item
(2 votes)


          ትዝታን ሽሽት


ባይተዋርነትን ድል ልነሳ
ሽንቁሬን ልሞላ
ፍቅርን በማሰስ ሳለሁ
ዕድል ፈንታ ካንቺ አጋመደኝ፡፡
ቀቢፀ ተስፋ ፅላሎቱን ያጠላበትን
ዘመኔን ሊኩል
እህል ዉሃ አንቺን ሸለመኝ፡፡
የሐዘንን ድር ፈትለን
የደስታን ሸማ ለበስን፡፡
ምድር ጠበበን፡፡
አይ ጊዜ
ዛሬማ፥ ልብሽ ቂም አርግዟል፡፡
ርቀሻል
ሙዚቃ ድምፅሽን አልሰማም፡፡
የዐይንሽን ብርሃን አልሞቅም፡፡
ይቅር በይኝ የእኔ ዓለም
ነፍሴን ፀፀት ገርፎታል፡፡
ዐለት ልቤን አፍርሷል
ቅስምሽን የሰበረዉ የቃሌ ሾተል፡፡
በሽሽቴ ያረገፍሽዉ የዕንባሽ ደለል፡፡
አስታዉሽ አካሌ ደጉን ዘመን
መደብ ሳንመዛዘን
የልማድን እግር ብረት ሰብረን
በአብሮነት የተጋራነዉን፡፡
ትዝ ይበልሽ የፈጀሽዉ ዕድሜ
ለድሌ የሰዋሽዉ፡፡
ይዘከር የፈፀምኩት ጀብድ
ታሪክ ያልመዘገበዉ፡፡
ተመለሽ የእኔ ርግብ
ያለፈዉን ረስተሽ በምህረት ክንድሽ እቀፊኝ
ጡቶችሽ መሐል ልንደድ፡፡
ገመናችን አይገለጥ
ስደትሽን ባእድ አይስማ
በጎጇችን ሰላም ይዉረድ፡፡
አዉቃለሁ ፥ ዛሬማ ክህደት ቅስምሽን
ሰብሮት
ትዝታችንን ደምስሰሻል፡፡
ግብዝነቴን መዝነሽ
እምነትን የሚሸረሽር ርእዮት ገንብተሻል፡፡
አልነቅፍሽም፡፡
እኔ፥ የታሪካችንን ቅሪት ዘወትር
አመነዥካለሁ
በተዉኔት ያልተኳለዉን፡፡
ልጅነት የገነባዉን፡፡
ዛሬም የትዝታሽ ቁራኛ ነኝ
አጨብጭቤ የቀረሁ
አመፃ የመከረኝ፡፡
ተራራ ልቤ የማይሰንፍ
ጨዋታሽን የናፈቅኩ
ተስፋ ያጐሳቆለኝ፡፡
የፍቅር ሚዛኑስ
በደልን መሻር አይደል፡፡
የአብሮነት ዉሉስ
ትምክህትን መናድ አይደል፡፡
      (መኮንን ደፍሮ)  


Read 1724 times