Saturday, 19 March 2022 12:19

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by  መላኩ ብርሃኑ
Rate this item
(2 votes)

 አንድ ነገር ልንገርህ? ቀና አትበል.. !!
                            
           ኑሮ “ጣራ ነክቷል” ከሚለው ቃል ይልቅ “ሰማይ ረግጧል” የሚለው የበለጠ ይገልጸዋል። ትናንት እንደቀልድ “ድሮ” ሆኗል። ከሁለት ዓመት በፊት የተጋቡ ሙሽሮች “ኑሮ በኛ ጊዜ” እያሉ የሚተርኩባት ሃገር ላይ ነን ያለነው።
ብዙ ጊዜ እንደምለው “ኢትዮጵያ ውስጥ ትናንት ከዛሬ የተሻለ ነበር። ዛሬ ደግሞ በሁሉም መስፈርት ከነገ ይሻላል” ...
ይደክማል...በጣም ይደክማል...ሰርተህ ያጠራቀምከው መቶ ብር ባንክ ተቀምጦ በዓመት 35 ብር ይቀንሳል። ኪስህ ዳጎስ ብሎ ኮንደሚኒየም እገዛለሁ ብለህ ያጠራቀምከው ገንዘብ፣ ከባንክ ሲወጣ ቤት ቀርቶ የቤት እቃ ለመግዛት አይበቃህም። የዛሬ ሁለት ዓመት 350ሺህ ብር ሲሸጥ የነበረ ቪትዝ ለመግዛት አቅደህ በብድርም፣ በስራም ያገኘኸውን ገንዘብ አጠራቅመህ ‘ሞላልኝ’ ስትል ዋጋው ካለህ ገንዘብ በሁለት እጥፍ አድጎ ይጠብቅሃል። ያንተ ብር ለባጃጅም የማይበቃበት ቀን እየበረረ ሲቀርብ በአይንህ ታየዋለህ።
ትለፋለህ...አቀርቅረህ ውለህ አቀርቅረህ ታድራለህ...ጉልበትህ እስኪዝል ትሰራለህ...በታክሲ ተንከራትተህ ...ጸሃይ ጠብሶህ...በእግርህ ኳትነህ ከምታገኘው ጥሪት ላይ ነገን የተሻለ ለማድረግ ከራስህም ከልጆችህም ጉሮሮ ነጥቀህ ታጠራቅማለህ...ገንዘብህ ወደ ታች ሲጓዝ ኑሮ ወደ ላይ እየወጣ የማይገናኙ ‘”ደሃና ገበያ’ ይሆኑብሃል። አሁን ባለው ፍጥነት ኑሮን ግን በሩጫ አትቀድመውም... አንተ ባለ በሌለህ አቅም ብትሮጥም፣ እሱ ሁለት ሶስት ዙር በማራቶን ፍጥነት ደርቦህ ታገኘዋለህ። በዚያ ልክ እፈጥናለሁ ብትል..ልብህ ይፈነዳል።
እዚህ ሃገር በጣም ለፍቶ አዳሪዎች አሉ። በደንብ ታያቸዋለህ። ሲሰሩ..ሲታትሩ...ለመሻሻል ሲተጉ ታያቸዋለህ። ..ሰው ከደረሰበት ልድረስ ብለው ሳይሆን፣ ከትናንት በተሻለ ዛሬ ለመኖር የሚተጉ ሞልተዋል። እነርሱ ናቸው ብልሆች።
በዚያኛው ወገን ደግሞ ሃብት በላይ በላዩ ሲቆለል ታያለህ... ጎተራ ሞልቶ ይፈስሳል...ገንዘብ እንደወረቀት ይበተናል። አዲስ አበባ ለቅንጦት አልበቃው ብላ ውሎና አዳሩ ‘በምትመጥነው’ ዱባይ ላይ የሆነ ስንት ሰው አለ።
ወዳጄ! ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዉ ከመንግስት በላይ ሃብታም ሆኗል። የአዲስ አበባ አስፓልት ለጎማው ስለማይመች ብቻ ላምቦርጊኒ መግዛት ባለመቻሉ የሚያማርር ብዙ ነው። ደህና መንገድ ከሌለህ ላምቦርጊኒ...ሚዘራቲ... ሮልስሮይስ... አልፋሮሚዮ...መኪና ምችት ብሎህ አትነዳም!! ...ስለዚህ ልትማረር ነው ማለት ነው።
ወጣ በል እስኪ...ቦሌ አካባቢ...ለቡ..ሲኤም ሲ...ከሰሞኑ ደግሞ ለሚ ኩራ...ሂድ። መንገድ ላይ ሽንጠ ረጃጅም ...ቁመተ ግዙፍ መኪኖች አልበዙብህም? የሶስት ቪትስ ቁመት የማያህላቸው እነ ጂኤምሲ...ሬቮ...ፎርድ...ታኮማ በአጠገብህ የታንክ የሚያካክል ጎማቸውን ከአስፓልት እያፋጩ... በሞተራቸው እንደ አንበሳ እያገሱ አይተላለፉብህም?... ሃመር መኪናን ‘ፋሽኑ አለፈ’ ብለው የሚንቁ ሰዎች አልበዙብህም?...
አትያቸው! ፈጽሞ ቀና አትበል። አቅርቅርና የጀመርከውን ብቻ ጨርስ። የራስህን ኑር... የራስህን ስራ... ከነርሱ አትፎካከር። አይበልጡህም። በጭራሽ!!
ምክንያቱን ልንገርህ...
ቀና ብለህ ብታያቸው በቅንጦት መሪውን የሚዘውሩት አንገታቸው ላይ ሰንሰለት ጌጥ ያጠለቁ...ክንዳቸው በታቱ ያበደ...ሪዛቸው የረዘመ...መነጽራቸው መስኮት የሚያህል...ባለ ልዩ ኮፍያ ወጣቶች ናቸው። ብዙዎቹ ባንተ እድሜ ሳይሆን ካንተ እድሜ በታች ያሉ፣ በመድሃኒት ሃይል ሪዝ ካበቀሉ ገና ሁለት ዓመት ያላለፋቸው ወጣቶች ናቸው። ለአንድ መኪና 12 ሚሊዮን ብር ከየት አምጥተው ከፈሉ? አንድ ቤት በ60 በ70 በ 80 ሚሊዮን ብር ከየት አምጥተው ገዙ? ...እመነኝ ሌቦች ናቸው።
ሌብነት ከሰው መስረቅ ብቻ አይደለም...አጭበርብሮ መበደር.. በተጭበረበረ መያዣ በተገኘ ብድር ሃብት ማገለባበጥ...አጭበርብሮ መሬት መሸጥ... ባለጊዜ ሆኖ የህዝብ ሃብት መቀራመት... በስልጣን..በአምቻ ጋብቻ በሃገር ሃብት ላይ መጠቃቀም... በዘመድ ጨረታ ማሸነፍ...ቀረጥ ሳይከፍሉ እቃ አስገብቶ መቸብቸብ ...ይህ ሁሉ ነው ሌብነት።
ገንዘቡ የመጣው እንዲህና እንዲያ ሆኖ እንጂ ተሰርቶና ተለፍቶ አይደለም። አንድ የ28 እና 30 ዓመት ወጣት በኢትዮጵያ ኑሮና እድገት ለዚህ የሃብት ጣሪያ መድረስ እንዴት ቻለ?...ሌላው ሌላው ሁሉ ቀርቶ እድሜው ብቻውን አይፈቅድለትም እኮ!!
ለዚህ ነው ቀና አትበል የምልህ...ቀና ብለህ እነዚህን ካየህ ተስፋ ትቆርጣለህ... ልፋትህና ፍላጎትህ ተራርቆ ለዛሬ ስላልደረሰልህ ትናደዳለህ... የጀመርከውን ትተዋለህ... ያሰብከውን ትሰርዛለህ...እጅህን ታጣጥፋለህ.... ባንተ ተስፋ ያዘለ ቤተሰብህንና ስንት የሚጠብቀውን ጠንካራውን ራስህን የበለጠ ትጎዳለህ። በአጭር አማርኛ ብቻህን ማውራት ትጀምርና ‘ትለቅቃለህ’። ተስፋ መቁረጥን የሚያህል የሰው ልጅ ጠላት የለም። ተስፋ እንዳያስቆርጡህ!
ቀና እንዳትል። አቀርቅረህ የጀመርከውን መንገድ ቀጥል...የጥቂት አመታት ጉዳይ እንጂ ፍሬ ታፈራለህ። ይህ ሁሉ ወፍ ዘራሽ ፣ ንፋስ አመጣሽ ሃብት መራገፍ ሲጀምር ...ያኔ እንደ ማዕበል የሚናጠው... ከኢኮኖሚክስ ትንታኔ በላይ የሆነው... ያበደው ገበያ ጸጥ ይላል። ያኔ አንተም በተመኘኸው ልክ ባይሆንም በተሻለ ሁኔታ ትኖራለህ...በሰራኸው በለፋህበትና ባገኘኸው ገንዘብ ብቻ። ያ ቀን መቼ ነው? ዋቃ ያውቃል።
...ኢትዮጵያ ውስጥ ህይወት በጣም ያደክማል... በእያንዳንዱ ቀን ብዙ ሰዎች ከቤታቸው እርጥባን ጥየቃ አደባባይ እየወጡ ነው... በዚሁ ልክ መንገዱ በቅንጡ መኪኖች ጠቧል...ተዘግቶ የሚጠጣባቸው ቤቶች በርክተዋል... ገንዘብ እንደወረቀት ይበተናል። ሃብት እንደጉድ ይፈስሳል። መሬት ዋጋው አይቀመስም...ግን እንደጉድ ይቸበቸባል። 50 ሚሊዮን ብር የአንድ ቤተሰብ የወራት በጀት እየሆነ ነው። ፈረንጅ ሃገር ዘና ብሎ የሚኖረው ማነው? ዕድሜው ገፋ ያለው ሰው..ሞርጌጅ ከፍሎ የጨረሰው ሰው...ከእዳ የተላቀቀው ሰው ብቻ ነው። ወጣቱስ? ወጣቱማ ኑሮን ለመቋቋም ሲለፋ...ሲታገል ... ሲጥር ነው የምታየው። እኛ ሃገር ና። ... 40 ዓመት ሰርተው ጡረታ የወጡት ኑሮ ከብዷቸው (ካላቸው) ቤታቸውን እያከራዩ፣ ከሌላቸው ዘበኝነት ተቀጥረው ኑሮን ሲገፉ ወይም እንደደኸዩ ሲያልፉ ታያለህ። ገና እጁ አካፋ ያልነካው ወጣት ደግሞ በማይታመን ፍጥነት፣ ሰው ባላወቀው መንገድ ተጉዞ ወደላይ ‘ሲተኮስ’ ትታዘባለህ።
ኢትዮጵያ ሁሌም የተቃርኖ ሃገር ናት። ብዙ አብዮት ሄዶ ብዙ አብዮት ቢመጣም ለውጥ የለም። ከትናንት ዛሬ የማይሻልበት ህይወት የምትገፋባት ሃገር፣ የኛይቱ ኢትዮጵያ ናት።
እና ወንድሜ!! ...በቃ ...ቀና አትበል! ዘመነኞቹን አትያቸው! እርሳቸው። ተስፋ ያስቆርጡሃል...’ያጨልሉሃል’ ...ኑሮህን ዝም ብለህ ኑር። ስራህን ብቻ ስራ።


Read 10865 times Last modified on Saturday, 19 March 2022 12:25