Saturday, 19 March 2022 12:25

አንባቢ በሌለበት ሃገር …ታሪክ አይጻፍም !!

Written by  መላኩ ብርሃኑ
Rate this item
(0 votes)

     ይህንን መረጃ አይቶ የማይደነግጥ ሰው ራሱን ይፈትሽ !!
ኢትዮጵያ 110 ሚሊዮን ህዝብ አላት። ይህ ህዝብ መስከረም 2013 ዓ.ም ላይ ሃገሩ ያተመችው ጋዜጣ ብዛት 6 ብቻ እንደሆነ አያውቅም። ቢያውቅም ግድ የለውም።
መጽሄቶቹ ደግሞ 9 ብቻ ናቸው። ሁለቱን ደምሯቸው …15 !! ….
(የኮፒውን ብዛት ተዉት! 5 ሺህ የዘለቀ ካለ ብረት ነህ በሉት)
የሚገርማችሁ ነገር ከ2001 ጀምሮ እስከያዝነው 2013 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ በ10 ዓመት በአጠቃላይ የተመዘገቡና ታትመው የተነበቡ ጋዜጦችና መጽሄቶች ቁጥር 463 ብቻ ነበር።
ከነዚህ ውስጥ 352 ጋዜጦችና መጽሄቶች (ደፍሬ እናገራለሁ) በዋናነት ገዝቶ የሚያነባቸው ሰው ስላጡ ህትመት አቋርጠዋል፣ ሰርተፍኬት መልሰዋል፣ ፍቃድ ተሰርዞባቸዋል። በሌላ አነጋገር አብዛኞቹ በኪሳራ፣ በጣም ጥቂቶቹ በሟቹ ኢህአዴግ ጉልቤነት ተዘግተዋል።
እንደእንጉዳይ ፈልቶ የነበረ የጋዜጣና መጽሄት ዘመን ወገብ ዛላው ተሰብሮ ዛሬ ያለበትን እያየሁ የኢትዮጵያ የህትመት ሚዲያ የቁልቁለት ጉዞን ባሰብኩት ቁጥር እንደእግር እሳት ያንገበግበኛል።
በመጀመሪያ ዲግሪ ጥናቴ ስፔሻላይዜሽኔ ብሮድካስት ላይ ቢሆንም ነፍሴ አብዝታ የምትረካበት፣ “በፍቅር ጨርቄን የጣልኩለት” ዘርፍ የህትመት ጋዜጠኝነት ነው። ይህ ዘርፍ ጋዜጠኛ ሳትሆን ልዳክርብህ ብትለው በራሱ ጊዜ አንገዋልሎ የሚተፋህ፣ ማንም ባልታጠበ እጁ ሊንቧቸርበት የማይችልበት ዘርፍ ነው። ሁሉም ነገር ቀርቶ በጣም በትንሹ መመዘኛ እንየው ካልን ጥሩ ጸሃፊነትን ይጠይቃል። የጻፍኩትን ስታነቡ ያየሁት ካልታያችሁ፣ የሰማሁት ካልተሰማችሁ ምንም አልጻፍኩም ማለት ነው። ሙያው ይህን ያህል ይረቅቃል።
እንዳለመታደል ግን ኢትዮጵያ የህትመት ውጤቶች ቁልቁል የሚሽቆለቆሉባት ሃገር ሆናለች። ለምን ለሚለው ጥያቄ መልስ እዚሁ ማዘጋጀት አይቻልም። ጥናት ይጠይቃል። የማይካደው አንደኛው ምክንያት ግን አንባቢ አለመኖሩ ነው።
በተለይ በዚህ የፌስቡክ ዘመን የጋዜጣና መጽሄት ዕጣ ፈንታ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል። አንድ ርዕስ ስታነሳ ልተንትን ብሎ ትን እስኪለው የሚጋጋጠው ህዝቤ ከሁለት አንቀጽ በላይ ለማንበብ ኮሶ አጠጡኝ ባይ ነው። (ይህንን ጽሁፍ ማንበብ የጀመረው ሰው ራሱ 100 ቢሆን እዚህ ድረስ የዘለቀው ግን 25 እንኳ ከሞላ ጽድቅ ነው ፣ ከዚህ በኋላ የሚቀጥለው ካለ ደሞ በረከት ወረደ በሉ ..ቂቂቂቂ)
ያም ሆኖ.....
ዛሬም ድረስ ከዚህ መቃብሩ ውስጥ ገብቶ አፈር እየተጫነው ካለ የህትመት ጋዜጠኝነት ጋር ለመዝለቅ በእልህ አንገት ለአንገት ተያይዛችሁ ለምትንገታገቱ ጥቂት የሙያ ባልደረቦቼ ጋዜጠኞች በሙሉ በአክብሮት እጅ እነሳለሁ!!
አንድ ኤፍኤም ላይ ተጥዳችሁ አርሴና ማንቼ፣ ፎንቃና ቅናት፣ ሙዝና ፓፓያ …ምናምን ብትተነትኑ ወይም የሆነ ዩቲዩብ ላይ ተጥዳችሁ “ሰበር ዜና” ምናምን ብትሉ የሚግበሰበሰው ሰው ዛሬ እናንተ ጋ ባይኖርም አንድ ቀን፣ ሃገር ስትሰለጥን ግን we shall prevail !!

  ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Read 11261 times