Print this page
Sunday, 20 March 2022 00:00

ሱዳን በተቃውሞ ማዕበል ስትናጥ ሰንብታለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ዳቦ፣ ህዝባዊ መንግስት፣ የዘገየ ደመወዝ፣ ወታደሮች የደፈሯት ተማሪ


            መላዋ ሱዳን ከዳቦ ዋጋ ጭማሪ፣ ከህዝባዊ መንግስት ጥያቄ፣ ከመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ መዘግየትና ወታደሮች በአንዲት ሴት ላይ ከፈጸሙት የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ህዝባዊ ቁጣና ተቃውሞ ስትናጥ ነው ሳምንቱን ያሳለፈችው፡፡
ከ3 አመታት በፊት የዳቦ ዋጋ ጭማሪ በቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ የረጅም ጊዜ መሪዋን ከስልጣን ባወረደችው ሱዳን ከሰሞኑም የዳቦ መሸጫ ዋጋ በ40 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ፣ ካለፈው ሰኞ አንስቶ የአገሪቱ ዜጎች በቁጣ አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን ማሰማት የጀመሩ ሲሆን፣ ህዝባዊ አመጹ በቋፍ ላይ ያለችውን አገር ወደ ሌላ ቀውስ እንዳያመራት ተሰግቷል፡፡
የዳቦ ዋጋ ጭማሪው የተከሰተው ከዩክሬንና ሩስያ ጦርነት ጋር በተያያዘ መሆኑን የዘገበው ሮይተርስ፣ የመሸጫ ዋጋው ከጦርነቱ በፊት ከነበረበት 35 የሱዳን ፓውንድ ወደ 50 ፓውንድ ከፍ ማለቱን፤ ከነዳጅ እጥረት ጋር በተያያዘ የትራንስፖርት ዋጋም በግማሽ ያህል መጨመሩንና ይህም ባለፈው ሰኞ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያንን አስቆጥቶ አደባባይ ማስወጣቱን አመልክቷል፡፡
መዲናዋን ካርቱም ጨምሮ አትባራና ኡምዱርማንን በመሳሰሉ የሱዳን የተለያዩ ከተሞች የመንግስት ሰራተኞችና ተማሪዎች ተቃውሞውን መቀላቀላቸውንና ተቃዋሚዎች ከዋጋ ጭማሪው ባለፈ ወታደራዊው መንግስት ስልጣኑን ለሲቪል መንግስት እንዲያስረክብ መጠየቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ የሱዳን ፖሊስ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ዜጎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ መጠቀሙ ተነግሯል፡፡
በአትባራ ከተማ ባለፈው ወር ደሞዝ ያልተከፈላቸው የባቡር ጣቢያ ሰራተኞች ተቃውሞና የስራ ማቆም አድማ ያደረጉ ሲሆን፣ ፖሊስ በደቡብ ዳርፉር ኒያላ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመምህራን ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ፣ መምህራን ተቃውሞ መውጣታቸውና ስራ ማቆማቸውም ተነግሯል።
ባለፈው ረቡዕ በመዲናዋ ካርቱም በአንዲት ደቡብ ሱዳናዊት ወጣት ሴት ተማሪ ላይ የሱዳን ወታደሮች በቡድን የአስገድዶ መድፈር ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ፣ በርካታ ሱዳናውያንና ደቡብ ሱዳናውያን አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውንም ኦል አፍሪካን ኒወስ ዘግቧል፡፡
በሳምንቱ በካርቱምና ኡምዱርማን በተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች ብቻ 133 ያህል ሰዎች የመቁሰል አደጋ እንዳጋጠማቸውና 3 ሰዎች በፖሊስ መኪኖች መገጨታቸውን ሱዳን ትሪቢዩን ዘግቧል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ፤ በደቡብ ሱዳንም የምግብ አቅርቦት መስተጓጎሉን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ወደ ዘረፋና ህገወጥ አመጽ መግባታቸውን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ በአገሪቱ 8.9 ሚሊዮን ያህል ሰዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ገልጧል፡፡

Read 4281 times
Administrator

Latest from Administrator