Print this page
Saturday, 26 March 2022 10:03

ወሎ ዩኒቨርስቲ ከ90 በመቶ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ጀመረ

Written by  ፍቆት ዮሴፍ (ከደሴ)
Rate this item
(1 Vote)

  ዩኒቨርስቲው በጦርነቱ 12 ቢ. ብር የሚገመት ሀብት ወድሞበታል
                      
                  የህወሃት ሃይሎች በፈጸሙት ወረራና ጦርነት ከፍተኛ ውድመት የደረሰበት ወሎ ዩኒቨርስቲ፤ ከ90 በመቶ በላይ ተማሪዎቹን ተቀብሎ ማስተማር መጀመሩን አስታወቀ፡፡ ዩኒቨርስቲው በጦርነቱ በደረሰበት ውድመት 12.ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብቱ እንደወደመበት ገልጿል።
በ1999 ዓ.ም የተቋቋመውና በዩኒቨርስቲዎች ላይ በተካሄደው የልየታ ሥራ “የአፕላይድ ሳይንስ” ዩኒቨርስቲ ሆኖ የሚያገለግለው ወሎ ዩኒቨርስቲ፣ በመደበኛ፣በርቀትና በተከታታይ ትምህርት ዘርፎች  ከ26 ሺህ በላይ  ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ሲሆን፣ በጦርነቱ በደረሰበት ጥቃት ሁለት መንታ የጤና  እና የህክምና ሳይንስ ኮሌጁን ህንጻዎች ጨምሮ እጅግ ትልልቅ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን፣ ቤተ መፃህፍት፣ አዳራሾች የተማሪዎች ማደሪያ ክፍሎች የኮቪድ ምርመራ ማዕከል፣ የአይስቲና ዳታ ሴንተር  የገቢ ማስገኛ ኢንተርፕራይዝ የላብራቶሪ ክፍልና በርካታ ሀብቶቱ ተዘርገፈውና ወድመው ጉዳት ላይ መቆየቱን የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት መንገሻ አየነ(ዶ/ር) ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ባለፉት ሶስት ወራት ሌት ተቀን በተደረገ ርብርብ የተማሪ መኝታዎችና የመማሪያ ክፍሎች ጥገና፣የጎደሉ  እቃዎችን በተወሰነ መጠን ከሌሎች ዩኒቨርስቲዎች በልገሳ በማግኘትና በሁለንተናዊ ጥረት የመማር ማስተማር ሂደቱ ከትላንት በስቲያ ሀሙስ መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም መጀመሩን ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል፡፡
“ይህን ጥረት አድርገን ትምህርት መጀመራችን  ጠላትን ከማሳፈር የተሻገረ ትልቅ ትርጉም አለው” ያሉት መንገሻ አየነ(ዶ/ር)፣ ይህ ማለት ግን ዩኒቨርስቲው ከደረሰበት መጠነ ሰፊና ዘርፈ ብዙ ውድመት አጋግሟል ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አግልግሎት ከጀመረ ገና አንድ ዓመት ብቻ የሆነው የአስተዳደር ህንጻ ሳይቀር በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት  ዝናብ ዘንቦ ጎርፍ ከቢሯችን እየጠረግን ነው እየሰራን ያለነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህንንም ቢሆን በፅናት እናልፈዋለን ብለዋል፡፡
ትምህርት ለመጀመር ለተማሪ ጥሪ ስናቀርብ ተማሪዎች ይቀሩ ይሆን የሚል መጠነኛ ሥጋት እንደነበር የገለፁት ዶ/ር መንገሻ ሆኖም ተማሪዎች እንዲገቡ በተደረገው በመደበኛ የጥሪ ቀናት በዋናው ግቢም ሆነ በኮምቦልቻ ካምፓስ ከ80 በመቶ በላይ ተማሪዎች ጥሪውን ተቀብለው ወደ ግቢ መግባታቸውንና ለተጨማሪ ሁለት ቀናት የጥሪውን ጊዜ በማራዘማቸው ከ90 በመቶ በላይ ተማሪዎች ገብተው ትምህርት መጀመራቸውን ገልፀው በተሰጡት  የማራዘሚያ ቀናት ሙሉ ለሙሉ ገብተው ትምህርታቸውን እንደሚቀጥሉ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
በትምህርት መጀመሪያው ዋዜማ ማለትም ረቡዕ መጋቢት 14 ቀን 2014 ዓ.ም የደሴ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች፣ከሁሉም ሀይማኖቶች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች የስነ ልቦና ባለሙያዎች እና የዩኒቨርስቲው አመራሮች በተገኙበት በተማሪዎች የመመገቢያ አዳራሽ (ዋናው አዳራሽ በመጎዳቱ) በተደረገ የውይይትና የማነቃቂያ መድረክ ተማሪዎች ከስጋት ነፃ ሆነውና ተረጋግተው እንዲማሩ፣ ለዩንቨርስቲያቸውና ለትምህርታቸው ታማኝ እንዲሆኑ፣ ለዩንቨርስቲው ህጎችና ደንቦች ተገዢ እንዲሆኑ ከመካከላቸው ሆን ብሎ ረብሻና ብጥብጥ ለማስነሳት አዝማሚያ የሚያሳይ ተማሪ ካለ እንዲያጋልጡ፣በአለባበስና በፀጉር አቆራረጥና አሰራር የትምህርት ቤቱን ደንብ እንዲያከብሩ ዘርፈ ብዙ ሥልጠናና ምክር ከባለሙያዎች፣ ከሀይማኖት አባቶችና ከዩኒቨርስቲው የተማሪ ተወካዮች አግኝተዋል፡፡
በቀጣዩ ሳምንት ዩኒቨርስቲው ስለደረሰበት ሰፊና ዘርፈ ብዙ ውድመት በቀጣይ ምን እንደታሰበ፣ ስለዩኒቨርስቲው አጠቃላይ ሁኔታና በመሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት መንገሻ አየነ(ዶ/ር) ጋር ያደረገነውን ሰፋ ያለ ቃለ ምልለስ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል፡፡


Read 11761 times