Print this page
Saturday, 26 March 2022 10:10

የመንግስትን ግጭት የማቆም ውሳኔ ህውሐት ተቀብያለሁ አለ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(2 votes)

   •  አሜሪካና እንግሊዝ ውሳኔውን በአድናቆት ተቀብለውታል
     •  ውሳኔው የተደረገው በአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛውን
                    
                የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ትግራይ ክልል የሚደርሰው ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀላጠፍና በክልሉ ለሚኖሩ ንፁሃን ዜጎች ሰብአዊ እርዳታ በአግባቡ እንዲደርስ ለማድረግ ከመጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ  ላልተወሰነ ጊዜ  የሚፀና ግጭት የማቆም እርምጃ መውሰዱን መግለፁን ተከትሎ የህውሃት ታጣቂ ቡድን፣ ሰብአዊ እርዳታው በአስቸኳይ የሚደርስ ከሆነ ግጭት ለማቆም እንደሚስማማ አስታውቋል።
በመንግስት በኩል የተወሰደው ለሰብአዊነት ሲባል ግጭትን የማቆም ውሳኔ ከተኩስ አቁም ስምምነት የተለየ ነውም ተብሏል።
ውሳኔው የተፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ በትግራይ ክልል የሚገኙ የህውሃት ታጣቂ ሃይሎች ከማንኛውም ጥቃት እንዲታቀቡና በሃይል ከያዟቸው የአጎራባች ክልል አካባቢዎች እንዲወጡ የሚጠይቅ ነው።
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የታወጀውን ለሰብአዊነት ሲባል ግጭት የማቆም እርምጃን የህውሐት ታጣቂ ቡድን እንደተቀበለው በማህበራዊ ድረ ገፅ አስታውቋል። የህውሃት ታጣቂ ቡድን ባወጣው መግለጫ፤ በበቂ መጠንና ተቀባይት ባለው ጊዜ ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ የሚደርስ ከሆነ የግጭት ማቆም ጥሪውን  እቀበላለሁ ብሏል።
የህውሃት  ቡድን ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ ይፋ ባደረጉት በዚሁ መግለጫ፤ የትግራይ መንግስትና ህዝብ ለሰላም ዕድል ለመስጠት የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን” ብሏል።
መንግስትና የህውሃት ታጣቂ” ቡድን  ተግባራዊ ለማድረግ የተቀበሉትን ለሰብአዊ እርዳታ ሲባል ግጭትን የማቆም ውሳኔ ይፋበ የተደረገው በአሜሪካ መንግስት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዴቪድ ሰተርፈልድን የኢትዮጵያ ጉብኝት ተከትሎ ነው።
አምባሳደሩ  በሳምንቱ መጀመሪያ በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት በነበራቸው ቆይታ፤  ከአፍሪካ ህብረት አፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆና  ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ጋር ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ ለክልሉ ህዝብ ስለሚደርስበት ሁኔታ ተወያይተዋል። የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱ መስተጓጎል የገጠመው የህውሃት ታጣቂ ሃይሎች በሚፈጽሙት ችግር ሳቢያ መሆኑን እንደተገነዘቡና ለዚህም በሁለቱም ወገኖች በኩል የግጭት ማቆም ውሳኔ ላይ ሊደርስ እንደሚገባው መግለጻቸው ተነግሯል። ይህንን ተከትሎም በኢትዮጵያ መንግስት የተወሰነው ግጭት የማቆም እርምጃ የህውሃት ቡድን እንደሚቀበለው አስታውቋል፡፡
ይህንኑ በመንግስት በኩል የተወሰደውን ላልተወሰነ ጊዜ ግጭትን የማቆም ውሳኔ የአሜሪካና እንግሊዝ መንግስታት በአድናቆት ተቀብለውታል። የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ መንግስት የወሰደው እርምጃ የሰብአዊ እርዳታ ለዜጎቹ ለማድረስ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያመለክት ነው ብሎታል።
የእንግሊዝ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚንስትር ቪክፎርድ በበኩላቸው፤ “ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ሲባል በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተወሰደውን ግጭት የማቆም እርምጃ አጥብቀን እንደግፋለን፣ አስላጊውን ድጋፍና ትብብርም እናደርጋለን” ብለዋል።
የአሜሪካ መንግስት የእርዳታ ድርጅት (USAID) ሃላፊ ሳማናታ ፓወር ባስቸኳይ ተፈጻሚ የሚሆነውን ግጭት የማቆም ውሳኔ በበጎ ጎኑ እናየዋለን ብለዋል።  
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት፤ በሰሜን ኢትዮጵያ፣ በትግራይ፣ በአፋርና በቅርቡ አማራ ክልሎች አስር ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ሰብአዊ እርዳታን እንደሚፈልግ አስታውቋል።

Read 12075 times