Saturday, 26 March 2022 10:08

በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረው አደገኛው ረቂቅ ህግ - HR6600

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(2 votes)

  • ሴኔቱ በጉዳዩ ላይ ለመወያየት የያዘውን ቀጠሮ በአንድ ሳምንት አራዝሞታል
     • ረቂቅ ህጉ ወደ ሴኔቱ የተመራው ህጋዊ አሰራሩን ጥሶ ነው ተብሏል
     • ረቂቅ ህጉ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ያልተገባ ጫና እና በደል ነው
                  
            የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት በኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ ተፈጻሚ ሊደረግ በታሰበው HR 6600 ረቂቅ ህግ ላይ ለመወያየት የያዙትን ቀጠሮ በአንድ ሳምንት ያራዘሙት ሲሆን፤ ረቂቅ ህጉ በሴኔቱ አባላት ተቀባይነትን አግኝቶ የሚጸድቅ ከሆነ አሜሪካ በኢትዮጵያ የደህንነት፣ የፋይናንስና ኢምግሬሽን ጉዳዮች ላይ አዲስ ማዕቀብ ትጥላለች፡፡
በኒውጀርሲው የኮንግረስ አባል ቶም ማሊኖወስኪ ለአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተዋወቀው ረቂቅ ህጉ፤ ለምክር ቤቱ አባላት የቀረበው የኢትዮጵያ የመረጋጋት የሰላምና የዴሞክራሲ ህግ በሚል ነው፡፡
ረቂቅ ህጉ በኢትዮጵያ መንግስትና በትግራይ ኃይሎች መካከል በሚካሄደው ጦርነት የተኩስ አቁም ስምምነት ወይም ድርድር እንዳይደረግ እንቅፋት በፈጠረ፣የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን፣የዘር ማጥፋትና ሌሎች ወንጀሎችን በፈፀመ እንዲሁም የሰብአዊ እርዳታ እንዳይደርስ እንቅፋት በፈጠረ፣ የእርዳታ ስራ ላይ በተሰማሩ የተባበሩት መንግስታት፣የአፍሪካ ህብረትና የሌሎች እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ሠራተኞች ላይ ጥቃት በሰነዘረ ወይም ለመሰንዘር ባቀደ ወገን ላይ ተፈፃሚ እንደሚደረግ ረቂቅ  ሕጉ ያመለክታል፡፡
ረቂቁ ህጉ በሴኔቱ ተቀባይነት ካገኘና ከፀደቀ፣ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የደህንነትና የፀጥታ ድጋፍ ታቋርጣለች፣ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በኩል የሚሰጡ ብድሮች ወይም የብድር ማራዘሚያዎች እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፎች እንዳይፈቀዱ አሜሪካ ተሰሚነቷንና ድምጽ የመስጠት መብቷን ተጠቅማ ታሳግዳለች ይላል፡፡
ክልክላው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትና ወረርሽኞችን ለመከላከል የሚደረጉ ድጋፎችን አይመለከትም፡፡
ረቂቅ ህጉ፤ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለሚመረምሩ አካላት የአሜሪካ መንግስት መረጃዎችን እንዲያጋራ ግዴታ የሚጥል ሲሆን የፋይናንስና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፎችን ማድረግ እንደሚኖርበትም ያመለክታል፡፡ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያብብ፣ የሰብአዊ መብት እንዲጠበቅና እርቅ እንዲወርድ የማድረጉ ተልዕኮ የአሜሪካ መንግስት ተቋማት ተልዕኮ እንደሚሆን ረቂቅ ሕጉ ይደነግጋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ህጉ በኢትዮጵያ መረጋጋትና የዲሞክራሲ ስርዓት እንዳይኖር ምክንያት ናቸው በተባሉ ግለሰቦች ላይ የንብረት እግድና የቪዛ ማዕቀብ እንዲጣል የሚያዝ ነው፡፡
በአሜሪካኑ ሴኔት ለውይይትና ለውሳኔ ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቀውን ረቂቅ ህግ የሚቃወመው ረቂቅ ህጉ በሴኔቱ አባላት ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቶ ቢፀድቅ አገሪቱን የከፋ ችግርና የደህንነት ቀውስ ውስጥ የሚከታት በመሆኑ ሊፀድቅ አይገባውም የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ፣ ህጉ ጦርነት ለማስቆምና በዜጎች ላይ የሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለማስቆም የሚያስችል በመሆኑ አፋጣኝ ውሳኔ ሊያገኝና ሊጸድቅ ይገባዋል የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡
የኤች አር 6600 ረቂቅ ህግ በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና እና በደል ለማድረስ ታስቦና ሆን ተብሎ የተዘጋጀ ረቂቅ ህግ ነው የሚሉት አሜሪካዊው የፖለቲካ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን፤ ረቂቅ ህጉ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በመላው አፍሪካ ሰላምን ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት የሚያደናቀፍ ነው ብለዋል፡፡
ረቂቅ ህጉ በአሜሪካው ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበርና በታችኛው ምክር ቤት በሚገኙ የዲሞክራት አባላት ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘቱን ያመለከቱት የፖለቲካ ተንታኙ፤ ውሳኔው አገሪቱ በማዕቀብ ለማዳከም ታስቦ የተደረገና ህጋዊ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው ሲሉ ይተቻሉ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርና የወጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ሰሞኑን በምስራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ከሆኑት ዴቪድ ሳተርፊልድ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ እንደተናገሩት፤ #የኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ህጎች፣ የአሜሪካና የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት ከግምት ውስጥ ያላስገቡ ናቸው፡፡ ህጎቹ በምክር ቤቱ አባላት ተቀባይነትን አግኝተው ከጸደቁ በይበልጥ የሚጎዱት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፤ ከዚህ አንጻር አሜሪካ ህጉን ታጸድቀዋለች የሚል እምነት የለኝም" ብለዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ህጉ የኢትዮጵያ መንግስት ቀደም ሲል ምላሽ  የሰጠባቸው ጥያቄዎችን የሚያነሳና በሰብአዊ መብት ጥሰት፣ለሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት እንቅፋት መሆንና በመሳሰሉ ጉዳዮች የኢትዮጵያን መንግስት ተጠያቂ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
መንግስት የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን የተመለከቱ ምርመራዎች እንዲካሄዱ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ያመለከቱት አምባሳደር ዲና፤ ያልተገደበ የሰብሰአዊ እርዳታ ስርጭት እንዲኖርና አቅርቦቱም እንዳይስተጓጎል በመንግስት እየተደረገ  ያለው ጥረት በህወኃት ቡድን በኩል በተደጋጋሚ ሲደናቀፍ በዝምታ እንደሚታለፍ ጠቁመዋል፡፡ በረቂቅ ህጉ ላይ የተመለከቱት አንኳር ጉዳዮች በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ሙሉ ምላሽ የተሰጠባቸው እንደሆኑም አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የተናጥል ተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ፣የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት፣አጠቃላይና ሁሉን አካታች ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ ዝግጅት እያረገ መሆኑ ለሠላም ያለውን ቁርጠኝነት የሚያመለክት ነው ተብሏል፡፡
የረቂቅ ህጉ መፅደቅ አገሪቷን ለከፍተኛ ችግርና የደህንነት ቀውስ ሊዳርጋት ይችላል የሚሉት የህግ ባለሙያና የፖለቲካ ምሁሩ አቶ አህመድ ኢሳ፤ #አገሪቱ ብዙ የደህንነት ስጋቶች ባሉበት የአፍረካ ቀንድ እንደመገኘቷና የአፍሪካ ቀንድ የሠላም አስከባሪነት ሚናን ለረዥም ጊዜ ስትወስድ የቆየች አገር እንደመሆኗ፣ አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች ድጋፍ ያስፈልጋታል፤ ይህ ውሳኔ ፀደቀ ማለት ግን አገሪቱ የምታገኘው ድጋፍም ተቋረጠ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቀጠናው ሰላም እንዲያጣና በመላው አፍሪካ  ያለመረጋጋት  ስጋት እንዲፈጠር ያደርጋል; ብለዋል፡፡
"ከዚህ በተጨማሪ ረቂቅ ህጉ ቢፀድቅና ተግባራዊ ቢደረግ መንግስት የጀመራቸውን የሰላም ጥረቶች የሚያከሽፍና አገሪቱን ወደ ባሰ ችግርና ጦርነት ውስጥ የሚከታት ይሆናል፡፡ ሠላም ለማስከበር ተብሎ ሠላም የሚያጠፋና የከፋ ቀውስ ሊያደርስ የሚችል ውሳኔን ለማጽደቅ መሯሯጡ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ሠላምና ለዜጎቿ ደህንነት ደንታ የሌላት መሆኑን የሚያመላክት ነው;  ብለዋል፤የፖለቲካ ምሁሩ፡፡
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶ/ር ሰለሞን ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበት ሁኔታ ኢኮኖሚዋ መነቃቃት የጀመረበት በርካታ ኢንቨስተሮች አይናቸውን ወደ ኢትዮጵያ መጣል የጀመሩበት ወቅት ከመሆኑ አንጻር ይህ ረቂቅ ህግ የሚጥለው የኢንቨስትመንት ገደብ በአገሪቱ ላይ በቀላሌ ሊቀረፍ የማይችል ከፍተኛ ጉዳት ያደርስባታል ብለዋል፡፡ አገሪቱ በትምህርት፣በመሰረተ ልማት ግንባታና በጤናው ዘርፍ ለምታከናውናቸው ስራዎች የገንዘብ ብድርና ድጋፍ የሚያስፈልጋት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በዚህ ረቂቅ ህግ መነሻነት በነዚህ ጉዳዮች ላይ እቀባና ክልከላ ማድረግ ጉዳቱ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ብለዋል፡፡
አገሪቱ በአሁኑ ወቅት እያካሄደች ባለችው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥ በርካታ ግዙፍ የውጭ ኩባንያዎች ገበያውን እየተቀላቀሉ መሆኑን ያመለከቱት ባለሙያው፤ ረቂቅ ህጉ በአገሪቱ ላይ በሚጥለው የኢንቨስትመንት ገደብ ሳቢያ እነዚህ ሁሉ ኢንቨስተሮች ስራቸውን ለማቆም እንደሚገደዱና ይህም በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ተናግረዋል፡፡ ኢኮኖሚው ሲናጋ ደግሞ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በቀላሉ መገመት ይቻላል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በሌላ ወገን ረቂቅ ህጉ በአገሪቱና በዜጎቿ ከላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ይልቅ በመሪዎችና በጥቂት ስልጣን ላይ ባሉ ግለሰቦች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ይከፋል የሚሉት የፖለቲካ ምሁሩ አቶ ሚካኤል ተስፋ፤ ለሠላም መስፍን ሲባል በሁለቱም ወገን በኩል ማዕቀብና ክልከላ መደረጉ አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡
ረቂቅ ህጉን በጥልቀት ብንመረምረው ትኩረት የሚያደርገው በመንግስትና በጦርነቱ ወቅት በንፁሃን ላይ በተፈፀሙ የመብት ጥሰቶች ላይ ተሳታፊ ወይም ተጠያቂ በሆኑ ግለሰቦች ላይ ነው፡፡ ስለዚህም የመንግስትን ግትር አቋም በማላዘብ ለሰላም የሚደረጉ ጥረቶች ፍሬያማ እንዲሆኑ ለማድረግና በጦርነቱ ወቅት በተፈፀሙ ወንጀሎች ላይ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦችን ተጠያቂ  ለማድረግ የረቂቅ ህጉ መፅደቅና ተግባራዊ መደረግ እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ለአሜሪካው ሴኔት የቀረበው የኤች አር 6600 ረቂቅ ህግ፣ ለምክር ቤቱ እንዲቀርብ የተደረገበት መንገድ ከዚህ ቀደም የነበሩ ህጋዊ አሰራሮችን የጣሰና የውጭ መንግስታትን በሚመለከት የሚረቀቁ የህግ  አካሄዶች ተግባራዊ ከሚደረጉበት መንገድ የወጣ እንደሆነ የሚናገሩት ምሁራኑ፤ ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት ረቂቅ ህጎች ሲወጡ የሁለቱም አገራ ዜጎች አስተያየታቸውን እንዲሰጡበት ጥሪ እንደሚደረግና ረቂቅ ህጉ ለአሜሪካ መንግስት ምን ጥቅም ያስገኛል? ኢትዮጵያውያንንስ ምን ዓይነት ችግር ላይ ይጥላቸዋል በሚለው ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት ይደረግበት እንደነበር ያስታወሱት አንድ የፖለቲካ ተንታኝ፤ የአሁኑ ረቂቅ ህግ ግን እነዚህን አካሄዶች ሳይከተል በቀጥታ ወደ ምክር ቤቱ መግባቱን  ጠቁመዋል፡፡
በመጪው ሳምንት በሴኔቱ ውይይት ይደረግበታል ተብሎ ቀጠሮ የተያዘለት የኤችአር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ህግ፤ እንዳይፀድቅና  እንዳይተገበር  የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ሲሆን የፊርማ ማሰባሰብ፣ ጉዳዩን ለምክር ቤት አባላት የማሳወቅና ለአሜሪካ ተመራጭ አባት ስልክ የመደውል እንቅስቃሴዎች አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡


Read 11400 times