Sunday, 27 March 2022 00:00

ጥሩ ነገሮች፣ በቂ አይደሉም!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

 • መጥፎ ነገሮች፣ ሁልጊዜ በቂ ናቸው። ከበቂ በላይ እንጂ። ለዚያም ነው፤ በተቻለ አቅምና ፍጥነት ጦርነትን በቃ ብሎ፤ ቶሎ እንዲያበቃ ማድረግ  ተገቢ የሚሆነው።
 • ጥሩ ነገሮች ግን፤ መቼም ቢሆን በቂ አይደሉም። በትንሽ ውጤት አትርኩ፤ አትኩራሩ የተባለውም፤ ለዚህ ነው።
                                 “ጥሩ ነገር” ሲያጋጥም፣ “ጥሩ ነው” ብሎ ከማመስገን ወይም ከማድነቅ ይልቅ፣… “በቂ አይደለም” ብሎ መናገር፣ በከንቱ መቀናጣት ሊሆንብን ይችላል። “ምን የላቸው፤ እንትን አማራቸው”… ያስብላል።
“ጥሩ ነገሮችን ካገኘ በኋላ፣ በቂ አይደሉም ብሎ የሚያማርርና የሚቀናጣ ሰው፤ የደላው ነው” ቢባልም አይገርምም። እውነት ነው፣ እንዲያ ያስብላል። የአገራችንን ችግር እየተመለከትን፣ ብዛቱን መቁጠር ሲሳነን፣ ክብደቱንም መሸከም ሲያቅተን እያየን፣ “ጥሩ ነገሮች፣ በቂ አይደሉም” ብሎ መናገር ምን ትርጉም አለው?
ግን አትርሱ። ስለ አገራዊ ምክክር፣ እንዴት እየተናገርን እንደሆነ አስቡት። ለሁሉም የፖለቲካ ችግሮችና ህመሞች፤ በቂ መፍትሄ የሚሆንልን ይመስላል-አነጋገራችን። ከዚህ ስህተት ማምለጥ አለብን። ምክክር ጥሩ ነው። ነገር ግን በቂ አይደለም፤ አይሆንም። ይህንም ከትናንት ስህተቶች ማረጋገጥ እንችላለን።
ስለ ዲሞክራሲ ወይም ስለ ምርጫ፣ እንዴት እንዴት ስናወራ እንደነበር አስታውሱ። ዲሞክራሲ ወይም ምርጫ፣ በቂ ሆነው አልታዩንም? “ዲሞክራሲ ነፍሳችን፤ ምርጫ ህይወታችን” ብለን አላሰብንም?
በምርጫ ማግስት፤ ሁሉም የችግር ዓይነቶች የሚፍታቱ፣ ሁሉም የመከራ ሸክሞችም ከነጓዛቸው የሚቃለሉ አልመሰለንም? እንዲያውም፣ የፖለቲካ ምርጫ ሲጎበኘው፣ የአገር በሽታ በሙሉ ፈውስ እንደሚያገኝ፣ የተጣመመው በሙሉ እንደሚቃና ያመኑ ሰዎች ጥቂት አይደሉም።
“ምርጫ ጥሩ ነው፤ በቂ ነው፤” የሚል ስሜት አድሮብን፣… የማይድን ሕመም፣ ብን ብሎ የማይጠፋ ጭንቀት፣ ተጠራርጎ የማይጸዳ እንከን እንደማይኖር፣ በወቅቱ አስበን ነበር። እንደዚያ መስሎን ነበር። ሁሉም ሰው ባይሆንም፣ ብዙ ሰዎች መስሏቸዋል ወይም አስመስለዋል። በእውን ሲታይ ግን፤ እውነታው እንደዚያው አልሆነም። ሊሆንም አይችልም። ምርጫ፣ ጥሩ ነገር ቢሆንም፣ ለሁሉም የሚበቃ፣ ሁሉን አቃፊና ሁለገብ ተአምረኛ መፍትሄ አይደለም።
በእርግጥም ደግሞ፣ ከምርጫ ማግስት፣ የአገርና የኑሮ ችግሮች አልተቃለሉም። የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት፣ እንደምታዩዋቸው ናቸው።
ለምን ይሆን ችግሮች ያልተቃለሉት? ዲሞክራሲ (ምርጫ)፣ መጥፎ ስለሆነ አይደለም። ምንነቱና አገልግሎቱ እስከታወቀ ድረስ፣ ከልኩ እስካላለፈ፣ ከቦታው እስካላፈነገጠ ድረስ፤ ምርጫ፣ ጥሩ ነገር ነው። ግን፣ በቂ አይደለም። በቂ ሳይሆን፣ በቂ ሲመስለን ወይም ስናስመስል ነው የምንሳሳተው፤ የምንዘናጋው፤ ለተጨማሪ ችግር የምንጋለጠው።
ምርጫ ስናካሂድ፣ የሰላም ገነት ውስጥ የምንገባ፣ በማግስቱም የእህል አዝመራ የሚያምርልን፤ በሳልስቱም የሰው ሁሉ ጎተራና ጓዳ ሞልቶ የሚትረፈረፍ የመሰለን ጊዜ ነው የምንሳሳተው። የፖለቲካ ምርጫ፣ በቂ መፍትሄ የሚሆንልን፣ የአገር ድህነትና የኑሮ ችግር የድሮ ታሪክ ሆነው እንዲቀሩ “በምርጫ” አራግፈን የምንጥላቸው ማስመሰላችን፤ የትልቅ ስህተት ምልክት ነው። ወይም የአላዋቂነት አልያም የክፉ አመል ምስክር ነው።
“ምርጫ በቂ ይሆናል” ብለን ስለተመኘን ወይም ስለመሰለን፤ በቂ አይሆንም።  “አገራዊ ምክክር በቂ መፍትሄ ይሆንልናል” ብለን ስለተመኘን ወይም ስላስመሰልን፤ በቂ መፍትሄ አይሆንልንም። ምክክር ጥሩ ነው፤ እናም በቂ አይደለም። ለምን? ጥሩ ነገር በቂ አይደለም። ምርጫም በቂ አይደለም። በተግባር አይተነዋል።
ተጨማሪ ማስረጃ ከፈለጋችሁ፤ በዚህ ሳምንት በበርካታ የኢትዮጵያ ከተሞች የተካሄዱ፣ የብልፅግና ፓርቲ ስብሰባዎችን መታዘብ ትችላላችሁ።
አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ደሴ፣ አሶሳ፣ ወልቂጤ፣ ጋምቤላ፣ … ዋና ዋና የገዢው ፓርቲ መሪዎችና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ በስብሰባዎቹ ላይ ተገኝተዋል።
እንግዲህ፣ ምርጫው ከተካሄደ፣ ገና አንድ አመት አልሞላውም። የምርጫው አሸናፊ ብልፅግና ፓርቲ፣ በዓለ ሲመቱን ያከበረው፤ የዛሬ ስድስት ወር ነው። ምርጫ፣ በቂ መፍትሄ ወይም በቂ ስኬት ቢኖር ኖሮ፤ የሰሞኑ ስብሰባዎች፣ የምስጋናና የሽልማት ድግሶች በሆኑ ነበር። ግን አልሆኑም።
በተቃራኒው፤ በምሬት የሚቀርብ እልፍ እሮሮ የተደመጡባቸው ናቸው- የሰሞኑ ስብሰባዎች። ደግሞም፤ የስብሰባዎቹ አላማ፣ ከመነሻው ከዚህ የተለየ አይደለም።
የፓርቲው መሪዎችና ባለስልጣናት፣ በየአቅጣጫው ለስብሰባ የዘመቱት፣ ከዜጎች ወይም ከየአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ለመነጋገርና የዜጎችን ችግር ለመስማት እንደሆነ ገልጸዋል። ፓርቲው የዜጎችን ሃሳብ ለመስማትና ለመረዳት፣… ለዜጎችም የፓርቲውን ሃሳብ ለመግለጽና ለማስረዳት መሞከሩ፤ ጥሩ ነገር ነው። ለዚህም፣ በየከተማው በርካታ ስብሰባዎችን ማዘጋጀቱና ጥረት ማድረጉ፤  በጎ ነው።
ንግግርና ምክክር፣ በቅንነትና በብስለት እስከተከናወነ ድረስ፤ ጥሩ ነገር ነው። በእርግጥ፤ ይሄም በቂ አይደለም።
ጥሩ ነገር በቂ አይደለም። ጥሩ ነገር በቂ ቢሆንማ ኖሮ፤ ምርጫ ማካሄድ ብቻ በቂ በሆነ ነበር። በየከተማው ስብሰባ ማካሄድና ከዜጎች ጋር መነጋገር ባላስፈለገ ነበር። ግን ከዜጎች ጋር መነጋገር አስፈላጊ ነው። ጠቃሚ ነው። የአገሪቱን ሁኔታና፣ የዜጎችን ኑሮ ይበልጥ ለመረዳት ተጨማሪ መረጃዎችን ወይም ሃሳቦችን ለማግኘት ይጠቅማል (ከዜጎች ጋር በቅጡ መነጋገር)።
የችግሮችን አይነትና መጠን ከምር ለመገንዘብ፣ ለማጣራትና ለማረጋገጥ፣ ዋና ዋናውን አንጥሮ ለማየትና ከነዝርዝሩ አሟልቶ አዋህዶ፣ ከምር ለማወቅ፣ በሙሉ ሃሳብና በሙሉ ልብ እውነታውን  ከምር ለመረዳት በብርቱ መትጋት ያስፈልጋል። ዜጎችን ማነጋገርም፤ ለዚህ አላማ ይጠቅማል። ያው፤ ልኩንና ስርዓቱን የጠበቀ እስከሆነ ድረስ፣ መነጋገርና መወያየት ጥሩ ነው።
በሁሉም ከተሞች በተካሄዱት ስብሰባዎች ላይ፣ ከበርካታ ነዋሪዎች በኩል የተነሱ ችግሮችና ቅሬታዎች፣ እጅግ ብዙ ናቸው። ነገር ግን፤ ተጣርተውና ጎልተው የወጡት ጉዳዮች  ከከተማ ከተማ ብዙ አይለያዩም። በሁሉም ከተሞች የተደመጡት ዋና ዋና ቁምነገሮች ተመሳሳይ ናቸው። ሰላምና ጸጥታ፣ ሕግና ስርዓት፣ ሕይወትና ንብረት፣ ስራና ኑሮ… እነዚህ ዋና ዋና ቁም ነገሮች ናቸው በየከተማው በብዛት ተደጋግመው የተነሱት።
የሰላምና የፀጥታ እጦት፤ የሕግና የሥርዓት መፋለስ ወይም መፍረክረክ፤ በጥቃትና በግጭት የሚጠፋ ሕይወት፣ የሚዘረፍና የሚቃጠል ንብረት፤ ከኑሮ መፈናቀልና ስራ አጥነት፣ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት… እነዚህ ጭንቀቶችና እሮሮዎች፣ አቤቱታዎችና ቅሬታዎች ናቸው፤ … በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ከነዋሪዎች በኩል በምሬት የተገለፁት፡፡
እውነትም፤ ዋና ዋና ቁም ነገሮችንና ችግሮችን ከነዝርዝራቸው ለማወቅ፣ በቅጡ አሟልተንና አዋህደን ለመገንዘብ፤ እንደዚህ አይነት የመነጋገሪያ ስብሰባዎች ጠቃሚ ናቸው፡፡ ጥሩ ናቸው፡፡ ግን ጥሩ ነገሮች በቂ አይደሉም፡፡
ለምን? መነጋገርና ችግሮችን ማወቅ ጥሩ ነገሮች ቢሆኑም፤ በስብሰባው ማግስት፣ ችግሮች ሁሉ መፍትሄ ያገኛሉ ማለት አይደለም።
ለዚያ ለዚያማ፤ ከላይ እንደተገለፀው፣ ምርጫ ማካሄድም ጥሩ ነው፡፡ ጥሩ ነገር በቂ ቢሆን ኖሮ፤ ከምርጫ ማግስት ይሄ ሁሉ መከራና እሮሮ እልም ብሎ በጠፋ ነበር፡፡ የኑሮ ችግርና ምሬት፣ እንዲህ ከምርጫ ማግስትም፤ ባልበዛብን ባልበረታብን ነበር፡፡ ግን፤ ምርጫ ማካሄድ ጥሩ ቢሆንም፤ ከልኩ አያልፍም፤ በቂ አይደለም፡፡ ከዜጎች ጋር በአግባቡ ስርዓትን ጠብቆ መነጋገርም፣ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡ ግን፤ ይሄም በቂ አይደለም፡፡
አንደኛ ነገር “መነጋገር ጥሩ ነው፤ ጠቃሚ ነው” ሲባል፤ ሁልጊዜ ለበጎ ይሆናል ማለት አይደለም። ሁልጊዜ ጠቃሚ ውጤት ያስገኛል ማለት አይደለም፡፡ እንደማንኛውም ጥሩ ነገር፤ እንደማንኛውም ጠቃሚ ነገር፤ ምርጫም ሆነ ውይይት፤ ከልካቸው አያልፉም፡፡
ያለልክና ያለ መጠን፤ ያለ ቦታውና ያለ ጉዳዩ፣ በዘፈቀደ ጥሩ የሚሆንልን ወይም በዘፈቀደ ጠቃሚ ውጤት የሚያስገኝልን ነገር፤ የትም የለም፤ የትም አይኖርም፡፡
በየወሩና በየሳምንቱ፣ በየእለቱና በየደቂቃው፤ አገራዊ የፖለቲካ ምርጫ ወይም ሕዝባዊ ስብሰባና ምክክር ማካሄድ፤ የዲሞክራሲ ጉልላት ወይም ከምርጫ አይነቶች ሁሉ የላቀ ሰገነት አይደለም፡፡ በተቃራኒው የውድቀትና የትርምስ መንገድ ነው፡፡ በእርግጥም፤ የፖለቲካ ምርጫ፣ ወይም ውይይትና ስብሰባ፣ ኑሮ ሊሆኑልን አይችሉም፡፡
ለኑሮ ሊጠቅሙንና ሊያገለግሉን ስለሚችሉ፣ እነ ምክክር እነ ውይይት ጥሩ ናቸው። ግን በቂ አይደሉም። ለህይወትና ለኑሮ በሚያስገኙት የፋይዳ አይትና መጠን ታይተው፤ በተገቢው ልክና ስርአት፣ በቅንነትና በጥበብ ከተከናወኑ ነው- ጠቃሚ የሚሆኑት።
ታዲያ፣ እነዚህን የቅንነትና የጥበብ ቅድመ ሁኔታዎች በማሟላት የተዘጋጁ ምክክሮች ጥሩ ቢሆኑም፣ በቂ አይደሉም። ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ እውነተኛ መረጃዎችና ትክክለኛ ሃሳቦች ያስፈልጋሉ።
ስብሰባ ስለተዘጋጀ ብቻ፣ ተጨባጭ ሁኔታዎችንና አውራ ችግሮችን የሚገልጽ ትክክለኛ ሃሳቦች ይቀርባሉ ማለት አይደለም።
ዘረኝነትን የሚያባብሱ ሃሳቦች የሚጨፍሩበት ስብሰባ ካሁን በፊት አይተናል። በዘረኝነት ሳቢያ የደረሱ ጥፋቶችን በመዘርዘር የሚቀርቡ ሃሳቦች የበረከቱበት ስብሰባም አለ-በሰሞኑ ስብሰባዎች ይህን ሰምተናል።
መንገዶችን ለመዝጋት፣ ኢንቨስትመንቶችን ለማፍረስ ቅስቀሳ የሚካሄድባቸው ስብሰባዎችን በየጊዜው ታዝበናል።
በሰሞኑ ስብሰባዎች ደግሞ፣ ስለ ዋጋ ንረትና ስለኑሮ ውድነት፤ ብዙ ሲነገር አይተናል። እውነትም፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት፣ የምርቶችና የሸቀጦች ዋጋ፤ በአማካይ እጥፍ ገደማ ሆኗል። ከባድ የኢኮኖሚና የኑሮ ቀውስ ነው። ይህን አስከፊ ሁኔታ የሚገልጽ እውነተኛ መረጃና ሃሳብ በስብሰባዎቹ ላይ መቅረቡ ተገቢ ነው።
በአጭሩ፣ ምክክር ውይይት ጥሩ ቢሆንም፤ በቂ አይደለም። እውነተኛና ትክክለኛ ሃሳቦች የሚቀርቡበት መሆን አለበት። ይህም በቂ አይደለም።
ዋና ዋና ችግሮችን በእውነተኛ መረጃ ማረጋገጥና በትክክል መግለጽ፣ ጥሩ ነው። ነገር ግን፤ ችግሮችን ማወቅ ብቻ፤ በራሱ ጊዜ ትክክለኛ የመፍትሄ ሃሳቦችን አይወልድም።
የሰላም እጦትን፣ የፀጥታ ስጋትን፣ ጥቃትንና ጥፋትን ለመግታት፤ የህግ የበላይትን የሚያስከብሩ መፍትሄዎች  ያስፈልጋሉ። ይሄ ትክክለኛ ሃሳብ ነው። በሰሞኑ ስብሰባዎችም ላይ፣ ብዙ ሰዎች ተናግረውታል።
የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትን ለመግታት፤ ነጋዴዎችን በማውገዝ የዋጋ ቁጥጥርና የፍተሻ ዘመቻ እንዲካሄድ መጠየቅ ግን፤ መፍትሄ አይሆንም። እንዲያውም፤ ተጨማሪ ችግሮችን የሚፈጥርና ነባሩን ችግር የሚያባብስ የተሳሳተ ሃሳብ ነው።
በሌላ አነጋገር፤ ምክክርና ስብሰባ ጥሩ ቢሆንም፤ በቂ አይደለም። እውነተኛና አውራ ችግሮችን የማወቅ፣ ትክክለኛ መፍትሄ ሃሳቦችን የመጨበጥ ጥረት ያስፈልገዋል። ሁሉም ጥሩ ነገር እንዲህ ነው። ጥሩ ነገር በቂ አይደለም።

Read 2068 times