Print this page
Saturday, 26 March 2022 10:29

የአርበኞቻችን ትግል - በማይጨው ጦርነት መባቻ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

 "ሀገራችን ኢትዮጵያ ጠላቶቿ ብዙ ቢሆንም፣በቁጥር እጅግ በርካታ ጀግኖችን የወለደች ታሪካዊት ሀገር ናት፡፡ በየጊዜው አበባዎቿን ከብበው የሚበቅሉ ጠማማ እሾሆች ቢኖሩም ሁሉን አሸንፋ፤ በጠነከረ ተጋድሎና በጸና ባህል ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡ ለዚህም የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪ የሆነውን አምላክ ተስፋ አድርጋለች!... ዛሬም በሌላው  የአርበኞች ተጋድሎ ትውስታ ጊዜ፤ ታሪኳም ተስፋዋም አልተቀየረም፡፡ ኢትዮጵያ በሁሉም ሕዝቧ ተጋድሎና ጥንካሬ እዚህ ደርሳለች፤ ወደፊትም ትቀጥላለች፡፡"
      

                 ሮማዎች በፖለቲካ ገናና ሆነው ግሪኮችን ቢያሸንፉም፤ ግሪኮች ግን በባህል እንዳሸነፉ ሆራስ የተባለው የዘመኑ ሃያሲ መስክሯል። ዘመናዊ ፖለቲካዊ ስልት የነበራቸው ሮማውያን፤ ጥሩ ጥሩ መንገዶች፣ ታላላቅ ድልድዮች፣ እልፍኞችና ህንጻዎችን ቢገነቡም፣ ግሪኮች ግን ከትውልድ ትውልድ የሚዘልቅ የአእምሮ ጓዳዎችን ማርከዋል። ስለዚህም ከታሪክ ገጽ፣ ከፍልስፍና ዐምድ፣ ከሰዎች ሕሊና ያነቀነቃቸው አልነበረም። በርግጥም ባለ ብዙ አውታር ገጾች የነበሯቸው ግሪኮች፤ የድላቸው ፍሬ መሬት ላይ ከተዘረጋው የፖሊስ ውቅር ይልቅ ገዢ ሆኖ ኖሯል።
ለግሪክ ጥበብ ባህል ነው።… ዲሞክራሲም ልጅ ማሳደጊያ ጡጦ ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያም አጀማመሯ የጥበብ፣ አካሄዷ የስልጣኔ፣ ግዛትዋ የተከበረ በመሆን የዘለቀች ናት። ምናልባትም ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ዓለምን የሚያስደምም ባህልና እምነት ያላት፣ በጠንካራ ገዢዎችዋ ልዕልናዋን አስከብራ የኖረች፣ የጥቁር ዓለም ቀንዲል ናት።
ምዕራባውያን አፍሪካን በሚቀራመቱበት የጨለማ ዘመን “ጧፌን አትንጠቁኝ” ብላ የተቆጣችው ግስላ እርሷ ናት። ይሁንና የተፈጥሮ ሀብቷና የአየር ጠብታዋ ያጓጓቸው ምዕራባውያን፣ በኢጣልያ ተወክለው ተደጋጋሚ ጦርነት አካሂደውባታል። በዓለም አደባባይ የደመቀ ድል ሆኖ በብርሃኑ የዓለምን ታሪክ ግድግዳ ካጥለቀለቀው የአድዋ ድል በፊት ትንንሽ ትንኮሳዎችን ልክ ካስገቡት ራስ አሉላ፣ እስከ ማይጨው ጦርነት፣ ከዚያም የቀጠለው የአርበኝነት ገድል አሳይታለች። ይህም ኢትዮጵያ የፖለቲካ የበላይነትን ሰብሮ የሚያልፍ ጠንካራ ባህል እንዳላት የሚያሳይ ነበር።
ጣሊያኖች  በዳግም ወረራው ወቅት ህልማቸው፣ የአድዋን ሽንፈት መበቀል ብቻ የሚመስላቸው ቢኖሩም፣ ተጨማሪ ምክንያት እንደነበራቸው በታሪክ ተመራማሪዎችና ጉዳዩ በሚመለከታቸው ሁሉ ይነገራል። እንደ ፍንጭ እንውሰድ ብንል፣ ብዕረ ሸጋው ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ፤ “ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስ አበባ” በሚለው መጽሐፋቸው፣ ቀጣዩን ሀሳብ አስፍረዋል፡-
"…ጣልያን ወደ ኢትዮጵያ የዘመተችው፣ በዐድዋ ምክንያት ደም ለመመለስ ብቻ ሳይሆን፣ ግሪን ፊልድ የሚባል ጸሐፊ እንደገለጠው፤ ተስማሚ የአየር ጠባይ ያላትና ለእርሻ ልማትም አመች ስለነበረች ነበር። ሕዝቧንም ልታሰፈርና ሰፋፊ እርሻዎች ተመስርተው ያገሯን ህዝብ ለመቀለብ ነበር።--"
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ፣ የደረጀ ባህልና እምነት የነበራት ታላቅ ሀገር ስለነበረች፣ ጠመንጃዋን የሚያሸንፍ ባህል ስለነበራት፣ ያንን ድል የለመደና፣ በባሩድ እየታጠነ የኖረ ባህል መነጠቅ አልቻለችም። እናም ይህ ባህል ለጠላቶቿ፣ አላስነካ ብሎ ዘልቋል።… በቅኔ፣ ሀገር ውስጥ በተጠነሰሰ ዜማ፣ ከነጻነት ጋር በተፈተለ ንጽህና፣ ቆሻሻውን አራግፋ፣ ንጽህናውን ይዛ ዘልቃለች!
ኢትዮጵያ ከማይጨው ጦርነት ማግስት!
የጥንታዊ ታሪክ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ከጉያዋ (ሰከላ) የሚፈልቀው ዓባይ፣ የብዙ በረከት መነሻ የመሆኑን ያህል፣ ለብዙ ጥፋትም ምክንያት ሆኗል። ዓባይ የሥልጣኔ መነሻ፣ የከተሞች፣ የምርምር፣ የሳይንስ ማማ ለመሆን መብቃቱን ስናደንቅ፣ ለጦርነት መንስዔ መሆኑ ደግሞ ያንገሸግሸናል።
የሀገራን ታሪክ በደም መጻፍ፣ ድንበራችን በአጥንት መታጠሩም፣ በየትውልዱ የውሃ ሀብታችንን ተከትሎ የሚነሱብንን ወረራዎች ለመከላከል በምናደርገው የማያባራ ጦርነት ምክንያት ነው። ንጉሦቻችን እንቅልፍ ያጡት፣ ፈረሶቻቸውን ጭነው፣ ስንቃቸውን ሸክፈው የባዘኑት በዚሁ፣ የሀገራችንን የተፈጥሮ ሀብት ንጥቂያና ዘረፋ፣ በሚነሱብን ጠላቶች ነው።
ምንም እንኳ ግዙፍ የምንላቸው ውጊያዎች በዳግማዊ ምኒልክ መሪነት በዐድዋና በንጉሥ ኃይለ ሥላሴ በማይጨው የተደረጉት ጦርነቶች ቢሆኑም፣ ከዚያም በኋላ በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም በምስራቅ ኢትዮጵያ የተደረገውና ሌሎችም በርካታ ጦርነቶችን እንጠቅሳለን።
እነዚህ ጦርነቶች “ኮንቬንሽናል” የሚባሉት ሲሆኑ፣ ሌሎችም ለሀገር የተደረጉ ተጋድሎዎች በእጅጉ ዋጋ ያስከፈሉ፤ ሕይወትን ያሳጡ ናቸው። ከእነዚህ ደግሞ በኢጣሊያ መንግስት ሁለተኛው የቅኝ ግዛት ጦርነት ምክንያት በማይጨው ጦርነቱ ካበቃ በኋላ፣ የአርበኞች በዱር በገደሉ ያደረጉት፣ መራራ ተጋድሎ ነው።
የአርበኞቻችን መንገድና ባንዲራዎች
የአርበኞች ተጋድሎ፣ ሚያዚያ 26 ቀን 1928 ዓ.ም ጣሊያን አዲስ አበባ ከመግባቱ በፊት በልጅ ኃይለማርያም ማሞ የደፈጣ ውጊያ፣ ጫጫ ሱኬ ሲራቤ በምትባለው ቀበሌ ሲጀመር ነው። በዚሁ ቀን ጣሊያን ዱብ ዕዳ የሆነ መከራ ገጥሟት፣ አምስት ካሚዮኖች ተሰባብረው፣ አንድ መቶ አርባ ወታደሮችን ገድለው፣ ሰባቱን ማርከውበት ነበር። እኚህ የመጀመሪያው አርበኛ ቤታቸው ስላሴ ለመውረድ ሲነሱ፣ ሙጠ ገላ ላይ ዘራፊዎች ተገዳድረዋቸው ነበር። ሰውየው ግን ንክች አላሉም፣ ይልቅስ ከባለቤታቸው ወይዘሮ ወሰንየለሽ ጋር ሁሉን ጥለው ወደ ሰላሌ ገቡ። ከዚያም ግንቦት 19 ቀን 1928 ዓ.ም ፊታወራሪ ዘውዱን ለማግኘት ደብረሊባኖስ ሄዱ። በመቀጠል ለደጃዝማች አበራ ሽንኩርት ነገሩን ሁሉ አማከሯቸው።
በኋላም በርካታ የኢትዮጵያ አርበኞች በአንድ ሆነው የጠላትን ሀይል ለመምታት በአንድነት መከሩ፤ የምክራቸውም ዐላማ አዲስ አበባ ላይ የከተመውን የጣሊያን ጦር መምታት ነበር።
በምክክሩም ላይ ፊታውራሪ ዘውዱ አባኮራን ተሳታፊ ሲሆኑ፣ የተለያዩ አርበኞች በተለያዩ ግንባሮች ጦሩን ለመምራት ዕቅድ አውጥተው ነበር። በዚህም መሰረት ባላምባራስ አበበ አረጋይ (በኋላ ራስ የሆኑና በሚኒስትርነት ተሾሙ) የጅሩን ጦር ይዘው በኢየሱስ በኩል ወርደው፣ እላይኛው ግቢ በሰፈረው ጠላት  ላይ አደጋ እንዲጥሉ፣ ሻለቃ መስፍን ስለሺ (በኋላ ራስ) የሙሎና ያዳበርጋ ጦር፣ ክብር ዘበኞችን ጨምሮ ይዘው ከደጃዝማች አበራ ጋር በራጉኤል በኩል፡፡ አሳዛኙ ነገር የነዚህ ጀግኖች አርበኞች ፍልሚያ ከጠላት ጋር ብቻ ሳይሆን በጥቅም ሀገራቸውን አሳልፈው ከሚሸጡ፣ ቅጥረኛ ባንዳዎችም ጋር ነበር።
ከነዚህ አርበኞች አንዱ የሆኑት ፊታውራሪ አጎናፍር ባዩም ከጠላት ጋር በሚደረገው እልህ አስጨራሽ ውጊያ፣ አንጀታቸው ተቃጥሎ ብድር ለመመለስ፣ የመቶ አለቅነት ማዕረግ ያለውን አንድ የጠላት ወታደር ገድለው ለመቀጣጫ አንገቱን ከዛፍ ላይ ሰቅለውት ነበር። ነገሩ ለትምህርት እንጂ የጭካኔ ጥግ ሆኖ አልነበረም።…
ባንዳዎቹ በዚህ ዘመን የራሳቸው ግጥም ነበራቸው።
እንሂድ እንሂድ፣ ሄደን እናምሰው፣
ምን ይመክተናል ደጀን የሌለው ሰው!
እያሉ ይዘፍኑ ነበር።
“ደጀን ሌለው” ማለት፣ አርበኞች ከጀርባቸው መንግስት የለም፣ ስንቅ የላቸውም ለማለት ነው። ያላወቁት ግን ሀቀኛው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ደጀናቸው መሆኑን ነው። ደግነቱ አርበኞቹም መልስ ይሰጡ ነበር። (ፊታውራሪ አጎናፍር ባዩ)
እናንተም መጣችሁ እኛም አየናችሁ፣
እንጋጠማለን ዛሬ እስከ ጌታችሁ፣
እንዳትመለሱ፣ አጣነው ብላችሁ።
ፋሽስት መትረየስህን ለዶሮ ለውጠው፣
መጣሁ አጎናፍር የማልደነግጠው፣
እንሂድ አርበኞች ሄደን እናምሰው፣
ምን ይመክተናል ማተብ የሌለው ሰው፣
እንዴት ይሰድበናል አገር የካደ ሰው፣
ለባንዳና ለጃርት ይበቃል አንድ ሰው።
በአርበኝነቱ ዘመን ነፍሳቸውን ለሀገራቸው አሳልፈው ከሰጡት መካከል፤ ግራዝማች ዕንቁሥላሴ ይገኙበታል። በዶክተር አማረ ተግባሩ በተጻፈው የፀሐዩ እንቁ ሥላሴ መጽሐፍ ላይ እንደሰፈረው ሀሳብ፡-
ደጃዝማች ዕንቁሥላሴ፣ የማይጨው ዘመቻ ሲታወጅ፣ 1000 ዲሞትፎር ያዥ ወታደሮችን አስከትለው፣ ደሴ ላይ የነበሩትን ልዑል አልጋወራሽ አስፋ ወሰንን እንዲጠብቁ በንጉሠ ነገሥቱ ታዝዘው ሄደው ነበር። በጦርነቱ ድል ስላልተገኘ ዕንቁሥላሴ በአርበኝነት በሰሜን ሸዋ ውስጥ ተሰማሩ። ከግንቦት 1928 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 1929 ዓ.ም ድረስ በሸዋ ቆላማ ሥፍራዎች እየተዘዋወሩ የሽምቅ ውጊያ ሲያደርጉ ቆዩ። ሚያዚያ ወር 1929 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ከሽምቅ ውጊያ ከፍ ያለ የፊት ለፊት ውጊያ አድርገው በጠላት ጥቃት ስለደረሰባቸው ወደ መርሃቤቴ ተሻገሩ። በግንቦት ወር 1929 ዓ.ም ላይ እነዋሪ ላይ ሶስት ቀን የፈጀ ጦርነት አደረጉ። በዚህ ጦርነት የተወሰኑ የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችን ማረኩ። ይሁንና መስከረም 12 ቀን 1920 ዓ.ም ጃርሶ ላይ በተደረገ ከፍተኛ ውጊያ፣ በመድፍ ጥይት ተመትተው መስዋዕት ሆኑ።
ሊጋቡ ልጅ ኃይለማርያም ማሞ፣ የያያ ሐሮን፣ የወረጃርሶንና የያያ ጉለሌን ጦር ደጀን ሆነው ሊያዘምቱ፣ ልጅ ኃይለማርያም ገዝሙ (በኋላ ቀኝ አዝማች ኃይለማርያም ገዝሙ፣በማይጨው ዘመቻ የስንቅና ትጥቅ ሹም የነበሩ) የጉረዛኔን  ጦር ይዘው የፋሺስትን ጦር ለማጥቃት ተማምለው ነበር፡፡
ከነዚህ መካከል ደጃዝማች አበራ ደብረሊባኖስ ወርደው ካህናቱንና ፅላቱን ሳይቀር አስከትለው ሾገሌ ሱቅ ድረስ በመዝለቅ ጠላትን ሲመቱ፣ አቡነ ጴጥሮስ በጠላት እጅ ወድቀዋል፡፡ እንዳሳቡት ሁሉም አዲስ አበባ ላይ ጥቃት ባያደርሱም፣ በየግንባሩ ጠላትን መግቢያ መውጫ አሳጥተዋል፡፡
በዚህ የአርበኝነት ንቅናቄ ጊዜ ሌ/ኮሎኑል ነጋ ኃይለስላሴ፣ ሙሉጌታ ቡሌ፣ መንግስቱ ንዋይ፣ ኢሳያስ ገብረሥላሴ፣ አበበ ተፈሪ፣ አክሊሉ ዓዲን፣ መኮንን መንገሻ፣ አብርሃ፣ ዮሴፍ ገብረ  አይን፣ ኃይሌ ወልደጊዮርጊስ እና ሌሎችም ከደጃዝማች አበራ ጋር ነበሩ፡፡
እነዚህ ጀግኖች በጊዜው ከተመቻቸ ሕይወትና ከከተማ ኑሮ፣ የሀገር ክብር በልጦባቸው፣ በዘር ሳይቧደኑ፤ አማራው፣ኦሮሞው፣ ትግራዩ ሌሎቹም በአንድ ሆነው የጠላትን ሀይል አርበድብደዋል፡፡
ያባት ሀገር ዱሬ
የእናት ሀገር ዱሬ
 እገባብሃለሁ የትም ዞሬ ዞሬ!
እያሉ በየዱሩ ገደሉ የተንከራተቱት፣ የዛሬዋን ነፃነቷን ያረጋገጠች፣ ግዛቷን ያስከበረች ኢትዮጵያ ለማትረፍ ሲሉ  ነበር። አርበኞች በዘር የተከፋፈሉ አልነበሩም፡፡ ኢትዮጵያን ያነጻትን፣ ኢትዮጵያን ያቆማትን ለማየት ምሳሌ የሚሆነን የአድዋ ድል ብቻ አይደለም፤ እዩት!... ኃይለማርያም ማሞ፣ኃይለማርያም ገዝሙ፣ አበበ አረጋይ፣ ፈይሳ ቡሊ፤ ዘውዴ አባፈርዳ፣ ሁንዴ ጋሪ፤ ኃይለሚካኤል አይኔ ወይም ገብሩ አድጎይ፣ አብርሃ፣ መንግስቱ አድጎይ፣ -- ለጎሳቸው አልተዋጉም፡፡ ጦርነቱ የአንድ ብሔር፣ ነፃነቱም ተጋድሎውም የመላው ሕዝብ ነበር፡፡
ልጅ ኃይለማርያም ማሞ፣የሰላሴ ሰው ናቸው፤ ግን የተዋጉትም የተዋደቁትም ለአማራ ወይም ለኦሮሞ ነፃነት አይደለም፤ ለአንዲት ኢትዮጵያ ክብር ነው፡፡
ጅሩ ወረዳ የተወለዱት ራስ አበበ አረጋይ፣እናታቸው አስካለ ጎበና፣ የጀግናው ጎበና ዳጬ ልጅ ናቸው፡፡ እኒህ አርበኛ የክብር ዘበኛ  መኮንን ሲሆኑ በኋላ ወደ ፖሊስ ሠራዊት ተዛውረው ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ አምስቱን ዓመታት ቀንና ማታ ሳይሉ ከጠላት ጋር በመተናነቅ፣ጠላትን ፋታ ነስተዋል፡፡ በተለይ በጅሩ፣ በመንዝ፣ በሰላሌ ካቢ፣ዋዩ፣ በላሎ ምድር፣ ደንገዜ፣ ይል፣ ቡልጋ፣ ስቃ ዋጩና ሌሎችም ግንባሮች ላይ  ታላላቅ ጀብዶችን ፈጽመው ለሀገራቸው ውድ ዋጋ ከፍለዋል፡፡
አቶ ሞሶሎኒ ምን አቅበጠበጠው?
አልነገረውም ወይ ካድዋ የተመለሰው?
--የተባለው አርበኞች መፈናፈኛ ስላሰጡት ነበር፡፡
የሰሜኑ አርበኛ በላይ ዘለቀ
ይህ ስመጥር ጀግና አያሌ ከያኒያን ያቀነቀኑለት፣በርካታ ገጣሚያን የብዕር ቀለም የደፉለት፣ የብሔራዊ መዝሙር ያህል የሚታይ የጀግነንት ምስላችን ነው፡፡…. ምንም እንኳ ለሀገሩ የዋለው ውለታ “ዐመድ አፋሽ; ሆኖ መራራ ፅዋ ቢያስጎነጨውም፣ በሕዝብ ልብ ውስጥ ያለው ቦታ ግን እጅግ ታላቅ ነው፡፡
ለዚህም ትንታግነቱ ያገሬው ሰው፡-
ያባ ኮስትር እናት እንዴት ፊቷ ይውዛ
ዘጠኝ ወር በሙሉ ረመጥ አርግዛ
በሚል ስንኝ፣ የማይጨበጥ ፍም መሆኑ መስክሮለታል፡፡
አርበኛው በላይ ዘለቀ “እምቢ ለጠላት!” ብሎ ወራሪን ሲፋለም በዕድሜ ወጣት፣ በአእምሮው ግን የበሰለ ስለነበር፣ በታላላቆቹ ሳይቀር መሪ እንዲሆን የተመረጠ ወጣት ነበር፡፡
በላይ ዘለቀ ፍልሚያው ከጠላት ጦር ጋር ብቻ ሳይሆን፣ከሀገር ውስጥ ባንዳዎችም ጋር ነበር፡፡ በጎጃም ውስጥ ጠላት ከሸዋ ወጥቶ አርበኞች ሊያጠቃ ከመጣ በኋላ፣ አርበኛውንና ተከታዮቹን ለማግባባት የመጡትን ባንዳዎች  ተቆጥቶ በሞት እንዲቀጡ ያደረገ፣ በሀገሩ ጉዳይ መራራ ሰው ነበር፡፡ ለአምስት ዓመታት ያህል በምስራቅ ጎጃም፣ በወሎ ቦረና አካባቢ በጀግንነት ተጋድሎ ያለፈው በላይ ዘለቀ፣ በኋላ ደጃዝማች ተብሎ ተሹሟል፡፡
ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ በግለ ታሪካዊ መፅሐፋቸው ካሰፈሩት ያንድ ቀን የተጋድሎ ኹነት ጥቂት እንደማሳያ እጠቅሳለሁ፡-
“--ጫቃታ በምዕራብ ወሎ፣ ካስማ አምባ ባሻገር በስተምስራቅ ያለች፣ ዓባይ ሸለቆ ደረት ላይ የምትገኝ፣ በላይ ዘለቀ የተወለደባት አካባቢ ስትሆን፤ እዚህች አካባቢ ውስጥ ጣሊያን ብዙ የጦር መሳሪያና ስንቅ የተከማቸበት አንድ የተጠናከረ ምሽግ ነበረው፡፡ በክረምት ዓባይ ጢም ብሎ ሞልቶ ሲፈስ፣ በላይ ዘለቀ ዓባይን መሻገር ስለማይቻል፣ አይመጣም ብሎ በመገመት፣ በ1931 ዓ.ም (ክረምት) የምሽጉ ብዙ ጠባቂዎች ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ በዚህ ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዋናተኞች ተፈልገው፣ አንድ ቀን  ሊነጋጋ ሲል በላይ ዘለቀ በራሱ የሚመራ ተወርዋሪ ጦር ከነመሳሪያው ዓባይን በዋና አሻገሩ፡፡
እንዲሁም የጦር መሳሪያው ውሃ እንዳይነካው ተደርጎ በጥንቃቄ ተሻገረ፤ የበላይ ዘለቀ ጦር ሳይታሰብና በጠዋት ምሽጉ ዘንድ ደርሶ የሚችለውን ማርኮ፣ ስንቅ ዘርፎ፣ የማይችለውን አቃጥሎ፣ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የባንዳውን ጦር አጠቃው፡፡--;
ከላይ እንዳየነው፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ ጠላቶቿ ብዙ ቢሆንም፣በቁጥር እጅግ በርካታ ጀግኖችን የወለደች ታሪካዊ ሀገር ናት፡፡ በየጊዜው አበባዎቿን ከብበው የሚበቅሉ ጠማማ እሾሆች ቢኖሩም ሁሉን አሸንፋ፤ በጠነከረ ተጋድሎና በጸና ባህል ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡ ለዚህም የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪ የሆነውን አምላክ ተስፋ አድርጋለች!... ዛሬም በሌላው  የአርበኞች ተጋድሎ ትውስታ ጊዜ፤ ታሪኳም ተስፋዋም አልተቀየረም፡፡ ኢትዮጵያ በሁሉም ሕዝቧ ተጋድሎና ጥንካሬ እዚህ ደርሳለች፤ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡


Read 1336 times