Monday, 28 March 2022 00:00

በእጆቿ ላይ የሚገኝን ርህራሄ የምታካፍል እናት (የደመና ሥር ፀሐይ!)

Written by  ወንድወሰን ተሾመ መኩሪያ (አልታ ካውንስሊንግ)
Rate this item
(1 Vote)

በመፅሐፍ መደርደሪያዬ ላይ አንድ እጅግ የምሳሳለት መፅሐፍ አለኝ፡፡ በ786 ገጾች የተሰነደው Our lives & Times From the turn of the last century to the war on Terrorism- An illustrated History የተሰኘው ይህ መፅሐፍ፤ የአንድ መቶ አመታትን ወሳኝና ታሪካዊ እውነታዎችን በውስጡ አስፍሯል፡፡ በምድሪቱ ላይ ታሪክ የሰሩ ሰዎችን ውልደት፣ ሥራና የፈጠሩትን ተፅእኖ ለትውልድ አጋርቷል፡፡ በዚህ ትልቅ መፅሐፍ ውስጥ ከተጠቀሱት በርካታ ተፅእኖ ፈጣሪዎች መካከል ማዘር ቴሬዛ ይገኙበታል። መፅሐፉ በገፅ 83 ላይ ማዘር ቴሪዛ እ.ኤአ. በ1910 ዓ.ም እንደተወለዱ ያበስረናል፡፡ ሲገልፃቸውም፤ “የአልባኒያዋ የሮማን ካቶሊክ መነኩሴ” በማለት ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በ1979 ዓ.ም የኖቤል ኮሚቴ ማዘር ቴሬዛን “የኖቤል የሠላም ሽልማትን” ሲሸልም፤  “ለሰው ልጆች ባላት  አክብሮት ላይ የተመሠረተ በጣም ብቸኞች፣ በጣም ምስኪኖችና በሞት አፋፍ ላይ  ያሉ ሰዎች በእጆቿ ላይ የሚገኝን  ርህራሄ ተቀበሉ” በማለት ማዘር ቴሬዛ የሰሩትን ሥራ በመጥቀስ  አወድሷቸዋል፡፡ እኛም ኢትዮጵያኖች ማዘር ቴሬዛዎች አሉን፤ እኛም ደጋግ ሰዎች አሉን፤ እኛም እጆቻቸው ላይ የሚገኝን ርህራሄ ለብቸኞች፣ ለምስኪኖችና በሞት አፋፍ ላይ ለሚገኙ የሚያካፍሉ እናቶች አሉን፡፡
ወ/ሮ ፀሐይ ሮሽሊ የሠላም ህፃናት መንደር መሥራች ናቸው፡፡ ወ/ሮ ፀሐይ ገና በልጅነታቸው ነበር እናትና አባታቸውን በሞት የተነጠቁት፡፡ የስድስት ልጆች እናትና አባት ድንገት ተከታትለው ሲሞቱ፣ ለወ/ሮ ፀሐይና ለእህት ወንድሞቿ እጅግ አስደንጋጭና ስጋት ላይ የሚጥል ነበር፡፡ በወቅቱ የወደቁትን የሚያነሳ የርህራሄ እጅ የነበራቸው ሚስተር ዴቪድ ሮሽሊ እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ማሪያ ሮሽሊ የተባሉ የስዊዝ ዜጎች፤ ፀሐይንና አምስቱን እህትና ወንድሞቿን ከዘመድ አዝማድ ፈቃድ አግኝተው በጉዲፈቻ ሊያሳድጓቸው ወደ ራሳቸው ቤት ወሰዷቸው፡፡ ስድሰት ልጆችን ከወለዷቸው ልጆች ጋር ጨምረው ለማሳደግ የወሰኑትን የሚስተር ዴቪድ ሮሽሊን ቤተሰብ ሳስብ እጅግ እደነቃለሁ። ስድስት ልጆችን በጉዲፈቻ  የማሳደግ ትልቅ ሃላፊነትን መውሰድ በእግዚአብሔር በተሰጠ ፀጋ ከሚገኝ ድፍረት ካልሆነ በስተቀር እንዴት ይቻላል? ብዬም አስባለሁ፡፡
ወሮ ፀሐይ ሮሽሊ ከአሳዳጊ ወላጆቿ ጋር ስዊዘርላንድ ከሄደች በኋላ ለአስር ዓመታት ያህል ስለ አገሯ ምንም ዜና ሰምታ አታውቅም ነበር፡፡ አንድ ቀን ግን ድንገት ቴሌቪዥኗን ስትከፍት ስለ ኢትዮጵያ ድርቅና ረሃብ ሰማች፡፡ በቴሌቪዥን መስኮት ያየቻቸው በረሃብ የተጎሳቆሉ ሰዎች ምስል እጅግ የሚረብሽ ነበር፡፡  ያቺ ሌሊት ያለ እንቅልፍ  በለቅሶና ስለ አገሯ አብዝታ እያሰበች ያሳለፈቻት ሌሊት ነበረች፡፡ ያቺ ሌሊት ርዕይ (Vision) የመቀበያ ሌሊት ነበረች፤ ያቺ ሌሊት የህይወትን አቅጣጫ ቀያሪ ሌሊት ነበረች፤ ያቺ ሌሊት የመኖሪያ ሥፍራን የምትቀይር ሌሊት ነበረች፤ ያቺ ሌሊት ብዙ ትውልዶችን ከፊቷ ያየች ሌሊት ነበረች፣ ያቺ ሌሊት ድሆችን የምትታደግ  እናት በውስጧ የፈጠረች ሌሊት ነበረች። ያቺ ሌሊት ሠላም የህፃናት መንደርን የምትፈጥር ሌሊት ነበረች!
ማዘር ቴሬዛ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የጂኦግራፊ መምህርት ነበሩ። ከቤታቸው ወደ ትምህርት ቤታቸው ሲመላለሱ በካልካታ ጎዳናዎች ላይ በጠራራ ፀሐይ የተመለከቷቸው የታረዙ፣ የተራቡና በብዙ ጉስቁልና ውስጥ የሚገኙ ዜጎች የህይወታቸውን አቅጣጫ ፈፅሞ ቀየሩት፤ ሰዎችን የመርዳት ርዕይ የተቀበሉት ማዘር ቴሬዛ፣ እነዚህን ሰዎች ሊረዷቸው፣ ከወደቁበት ሊያነሷቸው ተነሱ፡፡ ሰዎች በጠራራ ፀሐይም በሌሊትም ርዕይን እንደሚቀበሉ ወ/ሮ ፀሐይ ሮሽሊና ማዘር ቴሬዛ አስተማሪዎቻችን ናቸው፡፡ ሰው ርዕይን ችግር በማየትና በመስማት ሊቀበል እንደሚችል እነዚህ ሁለት እናቶች ምስክሮች ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ እርስዎ (አንባቢ) ርዕይን እንዴት ተቀበሉ? ትክክለኛ ርዕይ ድርጊትን ይፈጥራል፤ እንቅስቃሴ ውስጥ ያስገባል፤ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን አልፎ ይሄዳል፣ ችግር አያቆመውም! ትክክለኛ ርዕይ ገና ያልደረሱበትን መዳረሻ እየጎመጁና እየናፈቁ  በደስታ  እንዲኖሩ ያደርጋል፡፡ ርዕይ አለዎት? በአንድ ወቅት እነ ዶክተር ወሮታው በዛብህ በሚያዘጋጁት “የብልፅግና ቁልፍ” በሚባል ተከታታይ መፅሐፍ ላይ “ራዕዬን ከየት ላግኘው?” የሚል ፅሑፍ ፅፌ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ከርዕይ ምንጮች ሁለቱ ማየትና መስማት ናቸው፡፡ “ይሄ ለምን ሆነ? ይሄስ ለምን አልሆነም? እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ?” የሚሉ ጥያቄዎች ራዕይን የመፍጠር አቅም አላቸው ብዬ ፅፌ ነበር፡፡
ወ/ሮ ፀሐይ ሮሽሌ በስዊዘርላንድ አገር ሆና በትውልድ አገሯ ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ረሃብ በቴሌቪዥን ካየች በኋላ የመረጠችው በሁኔታው እያለቀሰች መቀጠልን ሳይሆን፤ ችግሩን እንዴት መቅረፍ እንዳለባት በማሰብ ወደ እንቅስቃሴ መግባት ነው፡፡ “የደመና ሥር ፀሐይ” መፅሐፍ ገፅ 96  ስለ ወ/ሮ ፀሐይ የሚከተለውን አስፍሯል፤ “በ1977 ዓ.ም ከጓደኞቿና ከቤተሰቦቿ የሰበሰበችውንና አጠራቅማ ያስቀመጠችውን ገንዘብ ይዛ በታህሳስ አጋማሽ ላይ በኢትዮጵያ አየር መንገድ  አዲስ አበባ ገባች፡፡  ከአስር ዓመት ቆይታ በኋላ የአገሯን ምድር ስትረግጥ ይበልጥ ሆድ ባሳት፡፡”  
በመቀጠልም ኢትዮጵያ ውስጥ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተፈጠረውን ረሃብ በአካል በመገኘት ከተመለከተችና ወደ ስዊዘርላንድ ከተመለሰች በኋላ ለሶስት ቀናት በመፀለይና በማሰላሰል በግሏ ጊዜ ወሰደች፡፡ “ለወገኖቼ እንዴት ነው የምደርሰው? --- እነዚህን ሜዳ ላይ የተጣሉ፣ ባዶ ድንኳን ውስጥ የወደቁ፣ ደረቅ ጡት ታቅፈው የሞት እንቅልፍ የሚያንጎላጃቸውን ሕፃናት እንዴት አድርጌ ነው የማድናቸው? እያለች [ፈጣሪዋን] በእንባ ጠየቀች” ይለናል፤ ወሰን ደበበ በመፅሐፉ ገፅ 114 ላይ፡፡
ጥቂት ስለ ሰላም የህፃናት መንደር
ሰላም የሕፃናት መንደር የተመሰረተው በ1978 ዓ.ም የዛሬ 35 ዓመት ነው፡፡ በወቅቱ በሃገራችን ተከስቶ የነበረውን ድርቅና ረሃብ ተከትሎ ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ህፃናትን ህይወት ለመታደግ በሚል ድርጅቱን የመሰረቱት ባለ ራዕይና የብዙዎች እናት የሆኑት ወ/ሮ ፀሐይ ሮሽሊ ናቸው፡፡
ሰላም የሕፃናት መንደር ሥራውን የጀመረው በወቅቱ በነበረው የከፋ ድርቅ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ 28 ህፃናትን ተቀብሎ በማሳደግ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና እያደገ፤ የሚሰጣቸውንም አገልግሎቶች እየጨመረ መጥቶ ለበርካታ ህፃናትና ለችግር ለተጋለጡ የማህበረሰብ ክፍሎች አለኝታ መሆን ችሏል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ሰላም የሕፃናት መንደር፤ ሁለት የህፃናት ማሳደጊያ ግቢዎች አሉት። በሁለቱም ግቢዎች በተለያየ ምክኒያት ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን ሲያሳድግ ቆይቷል፤ በማሳደግም ላይ ይገኛል፡፡ ህፃናቱ ጤነኛ፣ የተሟላ ሰብዕና ያላቸው፣ በእውቀትና በህይወት ልምድ የዳበሩ ሆነው እንዲያድጉና ራሳቸውን የቻሉ ብቁ ዜጎች እንዲሆኑ የሚያስችሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን ያገኛሉ፡፡
ከመሰረታዊ ፍላጎቶች ማለትም መጠለያ፣ ምግብና ልብስ ጨምሮ የጤና፤ የትምህርትና ስልጠና እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊና ስነልቦናዊ (ሳይኮሶሻል) አገልግሎቶች እያገኙ እንዲያድጉ ከመደረጉም በላይ በተማሩበት የትምህርትና ስልጠና መስክ ስራ እንዲይዙና ራሳቸውን እንዲችሉ የተጠናከረ ድጋፍና እገዛ ይደረግላቸዋል። ከ20 እስከ 24 ዓመት የሚወስደውን  የድርጅቱን ቆይታ አጠናቀው የወጡ ወጣቶች በግል፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ተቀጥረው በተለያዩ ሞያዎችና የስራ ሃላፊነቶች በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም የራሳቸውን የግል ድርጅት አቋቁመው ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ለሌሎች  የስራ እድል ፈጥረው እየሰሩ ያሉም ቁጥራቸው በርካታ ነው፡፡
ሰላም በመንደሩ ውስጥ ከሚያሳድጋቸው ህፃናት በተጨማሪ በአካባቢው ለሚኖሩና በተለያዩ ምክንያቶች  ወላጆቻቸውን ላጡ ወይም ለችግር ለተጋለጡ ህፃናት ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከሶስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ከማህበረሰቡ ሊሚመጡ ህጻናት፣ የነፃ የትምህርት እድል ይሰጣል፤ የትምህርት መሳሪያዎችና የዩኒፎርም ድጋፍ፤ እንዲሁም የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎትና የንፅህና መጠበቂ ድጋፍ ለልጃገረድ ተማሪዎች ይሰጣል፡፡
በሌላ በኩል፤ ድርጅቱ በአካባቢው ለሚገኙ በኢኮኖሚ ድሃ ለሆኑ እናቶች ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ ለማስቻል የህፃናት ማቆያ አገልግሎት አቋቁሞ ለ150 ህፃናት  ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል፡፡ እነዚህ እናቶች የእለት ጉርስ ለማግኘት የተለያዩ የጉልበት ስራዎችን ተዘዋውረው የሚሰሩ በመሆኑ ህጻናት ልጆቻቸውን የሚጠብቅላቸው በማጣት በከፍተኛ ችግር ላይ የነበሩ ናቸው፡፡ በዚሁ ችግር ሳቢያ ልጆቻቸውን በመያዝ ምጽዋት ፍለጋ ለመውጣት ይገደዱ ነበር፡፡ በሰላም የህጻናት ማቆያ አገልግሎት በማግኘታቸው የቀን ስራቸውን በተረጋጋ መንፈስ ሰርተው በሚያገኙት ገቢ ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን ማስተዳደር በመቻላቸው ለተፈጠረላቸው እድል ያመሰግናሉ፡፡ ጠዋት ልጆቻቸውን ወደ ማቆያው ያመጣሉ፤ ማታ ልጆቻቸውን ወደ ቤታቸው ይወስዳሉ፡፡
ሌላው ሰላም ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራበት የአገልግሎት ዘርፍ የጤናው ዘርፍ ነው። ለዚህም አገልግሎት አንድ በመካከለኛ ደረጃ የሚገኝ ክሊኒክ አቋቁሟል፡፡ በመሆኑም ድርጅቱ የሚያሳድጋቸውን ህፃናት ጨምሮ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች የነፃ ህክምና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የመክፈል አቅም ላላቸው ደግሞ በዝቅተኛ ክፍያ አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡
የመደበኛ ትምህርት አገልግሎት ሌላው ሰላም የህፃናት መንደር ከሚሰጣቸው ዋና ዋና አገልግሎቶች አንዱ ነው፡፡ ትምህርትን ለህፃናት ተደራሽ ለማድረግ ሰላም በህፃናት መንደሩ አቅራቢያ አንድ መዋዕለ ህፃናት፣ ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶችና አንድ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አቋቁሞ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ በእነዚህ ት/ቤቶች ድርጅቱ የሚያሳድጋቸው ህፃናትና የአካባቢው ማህበረሰብ ልጆች ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል፡፡
ሰላም ከመደበኛ ትምህርት ባለፈ ለወጣቶች የሙያ ስልጠናና የስራ እድል በማመቻቸት ህይወታቸውን መምራት እንዲችሉ የማድረግ ስራ ይሰራል፡፡ ይህን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል በኮሌጅ ደረጃ የሚገኝ አንድ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም በማቋቋም በርካታ ወጣቶች የሙያ ስልጠናና የሥራ ዕድል እንዲያገኙና ህይወታቸውን እንዲለውጡ የሚያስችል የተቀናጀ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፤ እየሰጠም ይገኛል፡፡ በነገራችን ላይ ሰላም የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ፣ አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ አስር ምርጥ ኮሌጆች አንዱ ሲሆን በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት የኮሌጁ ተሞክሮ በአፍሪካ ህብረት ዌብ ሳይት በኩል ለሌሎች እንዲደርስ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በቅርቡም በአዲስ አበባ ከሚገኙ ከ107 የመንግስትና የግል ኮሌጆች ጋር ተወዳድሮ አንደኛ በመውጣት በአዲስ አበባ ትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ተገምግሞ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
የማሰልጠኛ ተቋሙ ከመደበኛ የስልጠና ፕሮግራሙ በተጨማሪ በተለይ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች የተነሳ የትምህርትና የስልጠና እድል ላላገኙ ወጣቶች እንዲሁም ከስደት ተመላሽ ለሆኑ ወጣቶች የአጭር ጊዜ ስልጠና ፕሮግራም አዘጋጅቶ እንዲሰለጥኑና በተለያዩ ኢንደስትሪዎችና ኩባንያዎች ተቀጥረው ወይም የግል ስራ አቋቁመው እንዲሰሩ በማመቻቸት በርካታ ወጣቶች ራሳቸውን እንዲችሉና ህይወታቸውን እንዲለውጡ አስችሏል፡፡
እንግዲህ ሰላም የህፃናት መንደር ከምስረታው ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ፕሮግራሞችን በመክፈት በተለያዩ ዘርፎች ለበርካታ ዜጎች አገልግሎቱን በመስጠት የተሻለ ህይወት እንዲመሩ እያስቻለ የሚገኝ ደርጅት ነው። ሰላም ከውጭ በሚገኝ የእርዳታ ገንዘብ ላይ ብቻ ጥገኛ ላለመሆን የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎችንም ጎን ለጎን እንዲሰራ የሚያስችለውን ሮፋም የማኑፋክቸሪንግና አገልግሎት የተሰኘ ገቢ ማስገኛ ተቋምም በቅርቡ መፍጠር ችሏል፡፡
ሰላም በዚህ መልክ በሚያካሂዳቸው ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች በርካታ የበጎ አድራጎት ስራዎች የሰራ ሲሆን አሁንም የድርጅቱን እገዛ ፈልገው የሚመጡ ሰዎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ድርጅቱን ለመርዳት የሚፈልጉ ሰዎች ኮተቤ ወደ ወሰን በሚወስደው መንገድ፣ ሂል ሳይድ ትምህርት ቤት አጠገብ በሚገኘው ቢሮ በመሄድ ማገዝ ይችላሉ ወይም በድርጅቱ ዌብ ሳይት በሚገኝ አድራሻ የሚመለከተውን አካል ማናገር ይችላሉ፡፡
ዛሬ ቅዳሜ መጋቢት 17 ቀን 2014 ዓ.ም. የሠላም ህፃናት መንደር መሥራች የሆኑት  የወ/ሮ ፀሐይ ሮሽሊን ግለ ታሪክ የያዘ መፅሐፍ “የደመና ሥር ፀሐይ” በሚል ርዕስ በሠላም ህፃናት መንደር ሃሳብ አመንጪነት፣ ድጋፍና ክትትል፣ በወሰን ደበበ ማንደፍሮ በግሩም ሁኔታ ተፅፎ፣ የሠላም ወዳጆች በተገኙበት  በደማቅ ሥነስርዓት ይመረቃል፡፡ ከመፅሐፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ሙሉ ለሙሉ ለበጎ አድራጎቱ እገዛ እንደሚውል ተረጋግጧል፡፡  ሰላም ህፃናት መንደርን ለማገዝ  አሻራቸውን ላስቀመጡ ሰዎች ሁሉ ምስጋና ይድረሳቸው እያልኩ እንደ ወ/ሮ ፀሐይ ሮሽሊ በእጃቸው ላይ የሚገኝን ርህራሄ ለሌሎች የሚያካፍሉ ዜጎች እንዲበዙልን እመኛለሁ፡፡ ቸር እንሰንብት!

Read 2480 times