Saturday, 26 March 2022 10:36

ማራኪ አንቀፅ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  ሁለተኛው ጎጆ በማይታወቀው ቤተሰብ መካከል


              ፀሐይ የተወለደችበትንና ያደገችበትን ቤትና ቤተሰብ የሚያስረሱ በጣም ብዙ ጉዳዮች ቀልቧን ወስደውታል። የእናት የአባቷን ጎጆ፣ የወተት የእንቁላሉን፣ የላምና በጉን ፍቅር ረስታ አዳዲስ የህይወት ልምምዶች ማርኳታል።
የልጅነት ህልሟ እውን ሊሆን መንገዱም የተጠረገ፣ እንቅፋቱ የተነጠለ መሰላት። በዚህ በሁለተኛው የወላጆች ቤት የጎደለባት ነገር ቢኖር የላሞቹ ጠረን፣ የበጎቹ ጩኸት ብቻ ነው። በዚህ ቤት ከቁጥር በላይ የጎኑ መጫወቻዎች አሉ። ብዙ ስዕሎች፣ ብዙ አይነት ምግቦች፣ ብዙ የፈረንጅ መጠጦችና ቸኮሌቶች ይገኛሉ።
ከአንድ ቅያሬ ልብስና ጫማ በላይም አሏት። ኑሮ በነጮቹ ቤት ደስተኛ አድርጓታል። እነ ሊሊን በፈለገችው ሰዓት ቀስቅሳ ለጨዋታ ትጋብዛቸዋለች። ያለ ማንም ከልካይ በግቢው ውስጥ እየተሯሯጡ በመስኩ ላይ እየቦረቁ ይጫወታሉ። ቤተሰቦቿ በሚናፍቋት ጊዜ ነጮቹን ይዛ በመሄድ ሲጫወቱ ውለው ሲመሽ ይመለሳሉ።
ፀሐይ አሁን ላይ በቆዳዋ ቀለም ካልሆነ በአለባበስና በአኗኗር ዘይቤዋ ከነጮቹ የሚለያት ነገር የለም። አንዳንድ ወፍ በረር ቋንቋዎችን እሷ ከእነሱ፣ ነጮቹም ከሷ እየለቃቀሙና እየገጣጠሙ ለመግባቢያነት እያዋሏቸው ነው።
በተለይ በምልክት የፈጠሯቸው የመግባቢያ ቋንቋዎች ከምንም በላይ እርስበርስ እንዲደማመጡ አድርጓቸዋል።
ከዓመት በኋላ ፀሐይን አዲሶቹ ቤተሰቦች ፒያሳ አፍንጮበር አካባቢ የሚገኘው “ብርሃን ኢትዮጵያ” ከሚባለው ት/ቤት አስገቧት። የፈረንጆቹ ልጆች ቀደም ሲል ጀርመን ት/ቤት (6 ኪሎ) አካባቢ ገብተው እየተማሩ ነበር። ፀሐይም ወላጆቿን ቤት በመተው ሙሉ በሙሉ ከአቶ ዴቪድ መኖሪያ ቤት ጓዟን ጠቅልላ ገባች። አቶ ዴቪድ ልጆቻቸውን በሚወስዱበት ሰዓት ፀሐይንም ከብርሃን ኢትዮጵያ ት/ቤት በመኪና ያመላልሷት ነበር።
ስድስት ኪሎ፣ አራት ኪሎ፣ ፒያሳ እና አምስት ኪሎ የቤተመንግስቱን አጥር የሚጋሩ፣ የንጉሡን የዙፋን በሮች በቅርብ ርቀት የሚቃኙ፣ የሀገሪቱ ፖለቲካ የሚጠነሰስበት፣ የሚጠመቅበት አካባቢ ነው።
ይህ የመንግስት ዋና ዋና መስሪያቤቶች መነሃሪያ የሆነው ቦታ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ረብሻና ብጥብጥ የማያጣ ነውጠኛ ሰፍራ ሲሆን በየጊዜውና በየዘመኑ የፖለቲካው ድፍድፍ የሚጣልበት በመሆኑ ጤንነት የማይሰማው መንደር ነው።
አንድ ቀን ይኸው ነውጠኛ ሰፈር አገረሸበትና “ንጉሡ ይውረዱልን፣ ሕዝባዊ መንግሥት ይመስረትልን” በሚሉ ሃይሎች ጩኸትና መዝሙር ተናወጠ። ከሁሉም ት/ቤቶችና መ/ቤቶች የሚገኙ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች ሰልፉንና ነውጡን ተቀላቀሉ። ስድስት ኪሎን፣ አራት ኪሎን፣ ፒያሳንና አምስት ኪሎን አመለኛ በሬ የዋለበት ሜዳ አስመሰሉት። የመኪና መስታዎት የቤትና የቢሮ በሮች ከየአቅጣጫው የሚወረወሩ ድንጋዮች ስብርብራቸው ወጣ። በመንገድ የሚያልፉ ሰዎች እየተመቱ በየቦታው ወደቁ።
ት/ቤቶች ተማሪዎች ተረጋግተው መማር አልቻሉም በሚል እንዲዘጉ ታዘዙ። በራቸውን ባልዘጉ ት/ቤቶች ላይም የድናጋይ ናዳ ይወርድባቸው ጀመር።
ፀሐይ የምትማርበት ብርሃን ኢትዮጵያ፣ የዚሁ የረብሻው ቀጠና አካል በመሆኑ፣ የድንጋይ በትር ከቀመሱ ት/ቤቶች መካከል አንዱ ነበር። ት/ቤቱ ተማሪዎችን ወደቤታቸው እንዲሄዱ በለቀቀበት ወቅት ታዲያ የተወረወረ ነውጠኛ ድንጋይ በፀሐይ ግራ እጅ ላይ አረፈ።
ምንም እንኳን ጉዳቱ መካከለኛ ጉዳት ቢሆንም፣ የረብሻ ቀጠና ከሆነው ከዚያ አካባቢ አውጥተው ወደ ሌላ ቦታ ቢያስገቧት አዲሶቹ ወላጆቿ መከሩበት።
“ይሄ የግል ት/ቤት ቢቀርባት ይሻላል” አሉ አቶ ዴቪድ።
“አዎ! ለዛሬ ቢሰውራትም ድጋሚ ይመቱብኛል ት/ቤቱ ይቀየር” አሉ ወ/ሮማርያ።
“ከነ ሊሊ ጋር ትማር ከልጆቹ ጋር ብትሆን ይሻላል፤ ለማምጣትም አልቸገርም” አሉ አቶ ዴቪድ።
“ለቋንቋውም ቢሆን ከእነሱ ጋር ብትማር ነው የሚሻለው፤ ሀበሻ ብቻ ከሚማርበት ት/ቤት አንድ አይነት ቋንቋ ብቻ ተናጋሪዎች ስለሆኑ ሌላ ቋንቋ ለመልመድ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው” አሉ ወ/ሮ ማርያ።
ፀሐይ በአዲሶቹ ወላጆቿ አማካኝነት ፒያሳ ከሚገኘው ብርሃን ኢትዮጵያ ት/ቤት ወጥታ፣ የፈረንጆች ልጆች ከሚማሩበት ከስድስት ኪሎ ወደ ፈረንሳይ ኤምባሲ በሚወስደው መንገድ፣ ከጃንሜዳ ጀርባ ከሚገኘው ጀርመን ት/ቤት ገብታ መማር ጀመረች።
መስከረም ወር በ1963 ዓ.ም (በፈረንጆች) ፀሐይ የ10 ዓመት ልጅ እያለች፣ ሙሉ ለሙሉ ተጠቃላ ከፈረንጆቹ ቤት ገባች። አይኖቿን ለማየት የሚጓጉት እናቷና ወላጅ አባቷ፤ መልኳ እስኪጠፋባቸው ድረስ ለረዥም ጊዜ ወደ ቤቷ ሳትመለስ ትምህርቷን እየተማረች ከነጮች ፊት ገብታ ቀረች።
ፈረንጆቹ ቤተሰቦቿ ይናፍቋታል ብለው እንድትሄድ ሲጠይቋት፣ ብዙም የናፍቆትና የመጓጓት ባህሪ ስለማይታይባት ውትወታውን ትተው፣ እሷን እንደልጃቸው አድርገው መንከባከብና ማሳደጉን ገፉበት።
ፈረንጆቹ እየሰባበሩ በሚያወሯት አንዳንዴ ወደ ጀርመንኛው በተጠጋ አማርኛ ሲያናግሯት፣ ፀሐይም አስቂኝ በሆነው ጀርመንኛ ቋንቋ እየመለሰችና እያወራቻቸው በመካከላቸው የሚፈጠረው በቋንቋ ግራ የመጋባት ችግር እየተቀረፈ መጥቷል። በተለይ በተለይ ጀርመን ት/ቤት ከገባች ጊዜ ጀምሮ የሚከብዳትን በማስጠናትና የቤት ስራ በማሰራት ወ/ሮ ማርያ ከፍተኛ እገዛ ስለሚያደርጉላት፣ የመግባባት ችሎታዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
አቶ ዴቪድ በመካኒካል ኢንጅነሪንግና በኮንትራት ከሚያስተምሩበት አምስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ፣ በመግቢያና በመውጪያ ሰዓት አምስቱንም ታዳጊዎች በማመላለስ አስፈላጊ የሆነውን የትምህርት አጋዥ መጸሐፍት በመግዛትና ወደተለያዩ ቦታዎች በዕረፍት ሰዓት ወስዶ በማዝናናት እንዲሁም በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ ያደርጉላቸዋል።
ወ/ሮ ማርያ በበኩላቸው፤ ከልጆቻቸው ጋር የቤተሰቡ አምስተኛ አካል የሆነችውን አዲሲቷ ልጃቸውን ፀሐይን ከወለዷቸው ልጆቻቸው አስበልጠው ይንከባከቧታል። የቋንቋ ችግር ስላለባትና በፍጥነት እንዲገባት ረዥሙን ሰዓታቸውን እሷን የቋንቋው ባለቤት ለማድረግ ሲጥሩ ይውላሉ።
የፀሐይ ቤተሰቦች ልጃቸውን የሚያዩት በዓመት በዓል ጊዜ በ3 ወር አለዚያም በ6 ወር አንድ ጊዜ ብቻ ቢሆን ነው። ዓመት በዓል ሲመጣ በፋሲካ እንቁጣጣሽና ገና ወቅት ግን መላውን ቤተሰቡን ስለሚጠሯቸው ፀሐይና አዲሶቹ ቤተሰቦቿ ወደ ወላጆቿ ቤት በመሄድ በዓሉን ያከብራሉ። በዚህም የፀሐይ ወላጆች ልጃቸውን ለረዥም ሰዓት የሚያዩበትና ናፍቆታቸውን የሚወጡበት ጊዜ ነው።
በበዓሉ ቀን ዶሮ ተሰርቶ፣ ቅርጫ ገብቶና በግ ተገዝቶ ይታረዳል። ጠላ ይጠመቃል። የሐበሻ አረቄም ተገዝቶ ይመጣና ለፈረንጆቹ ይቀርባል።
ፈረንጆቹ በበኩላቸው፤ ወደ ፀሐይ ቤተሰብ ከመሄዳቸው በፊት ለበዓሉ ያስልጋቸዋል የሚሉትን ጤፍ፣ የቅርጫ ስጋ መግዣና መጠነኛ ብር ለወ/ሮ አበባ ይልኩላቸዋል። ለልጆቻቸው ደግሞ ልብስና ጫማ ገዝተው ለበዓሉ ዋዜማ ይልኩላቸዋል።
(በወሰን ደበበ ማንደፍሮ ከተፃፈው “የደመና ሥር ፀሐይ” የተሰኘ መፅሐፍ የተቀነጨበ)

Read 1509 times