Saturday, 26 March 2022 11:00

አቤል ተስፋዬና አዴል በሙዚቃ ሽያጭ ቀዳሚ ሆነዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  በ2021 የአለማችን ሙዚቃ 26 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል


            ትውልደ ኢትዮጵያዊው የአለማችን የሙዚቃ ኮከብ አቤል ተስፋዬ (ዘ ዊክንድ) በአመቱ የአለማችን የድረገጽ የነጠላ ዜማ ሽያጭ 1ኛ ደረጃን ሲይዝ፣ እንግሊዛዊቷ ድምጻዊት አዴል በበኩሏ፤ ከፍተኛ የሙዚቃ አልበም ሽያጭ በማስመዝገብ ቀዳሚነቱን ይዛለች፡፡
አቤል ተስፋዬ በቅርቡ ያወጣው ሴቭ ዩር ቲርስ የተሰኘ ነጠላ ዜማ በድረገጾች አማካይነት በአለማቀፍ ደረጃ 2.15 ቢሊዮን ጊዜ በመታየት የ1ኛ ደረጃን ሲይዝ፣ ዘ ኪድ ላሮል እና ጀስቲን ቢበር በጋራ የለቀቁት ስቴይ በ2.07 ቢሊዮን እይታ ሁለተኛ፣ የዱዋ ሊፓ ሊቪቴቲንግ ደግሞ በ1.88 ቢሊዮን ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
አዴል በበኩሏ 30 የተሰኘው አራተኛ አልበሟ በወጣ በ2 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ 5 ሚሊዮን ኮፒ እንደተሸጠላትና በአልበም ሽያጭ 1ኛ ደረጃን መያዟን የዘገበው ብሉምበርግ፣ የኦሊቪያ ሮድሪጎ ነጠላ ዜማ ሶር 2ኛ፣ የጀስቲን ቢበር ጀስቲስ ደግሞ 3ኛ ደረጃን መያዛቸውን አመልክቷል፡፡
አለማቀፉ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2021 ያስመዘገበው ገቢ በ18.5 በመቶ በማደግ፣ 26 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንና የገቢ እድገቱ ሙዚቃ እየተቀረጸ በአልበም መልክ መሸጥ ከጀመረበት እ.ኤ.አ 1990ዎቹ ወዲህ ከፍተኛው መሆኑ ተነግሯል፡፡
ለገቢው በከፍተኛ መጠን መጨመር በምክንያትነት የተጠቀሰው በድረገጾች አማካይነት ሙዚቃዎችን እየገዙ የሚያዳምጡ ሰዎች መበራከታቸው ነው ያለው የብሉምበርግ ዘገባ፣ የድረገጽ ደንበኞች ቁጥር 523 ሚሊዮን መድረሱንም አመልክቷል፡፡
የሙዚቃ ኢንዱስትሪውን ገቢ 65 በመቶ ድርሻ የያዘው በድረገጾች አማካይነት የሚከናወን የቀጥታ ሽያጭ ሲሆን፣ በሲዲና በካሴት እየታተሙ የሚሸጡ የሙዚቃ ስራዎችም 19 በመቶ እና 4 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ተነግሯል፡፡

Read 1390 times