Saturday, 26 March 2022 11:11

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

      ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ በእንባ ተሞልታ ያቀረበችው ተማፅኖ


            “...የሀገራችን ጉዳይ ያመናል ሁላችንንም። ... ሁላችንም የትግራይ እናቶች አባቶች፤ እናቶቻችን አባቶቻችን ናቸው። በእርግጠኝነት ደግሞ ነገ ሌላ ቀን ነው፤ ኢትዮጵያ ታርቃ አንድ ሆና ትቆምና የኢትዮጵያን ባንዲራ ታውለበልባለች። ስለዚህ አይክፋችሁ ክብር ይገባችኋል። በብዙ ፈተናዎች አልፋችሁ፣ በብዙ ተፅእኖ አልፋችሁ፣ የኢትዮጵያን ባንዲራ ከፍ ስላደረጋችሁ በጣም እናመሰግናለን።
ትግራይ ትላንትም ብትሆን ኢትዮጵያ ናት፤ ዛሬም ኢትዮጵያ ናት፤ ነገም ኢትዮጵያ ነች፤ ስለዚህ እባካችሁ መሪዎቻችን እባካችሁ ... እባካችሁ ... እባካችሁ ተጠቅማችሁ አይደለም፤ ተጎድታችሁ ኢትዮጵያን አንድ አድርጓት እባካችሁ!!! ከእግዚአብሔር ጋር ትችላላችሁ። ስለዚህ መሪዎቻችን ተጎድታችሁ ለኢትዮጵያ ብላችሁ፣ ለህዝብ ብላችሁ፣ እናንተ አንድ ካደረጋችሁ፣ ኢትዮጵያ አንድ ትሆናለች።
...ስፖርት ወንድማማችነት፣ ፍቅር፣ ሰላም ነው!! ለሰላም፣ ለፍቅር ቆመው፣ እነዚህ ልጆች ምንም ሳይበግራቸው ለዚህ ውጤት በቅተዋልና፣ አሁንም ቢሆን ክብር ይገባቸዋል። እናከብራችኋለን። በእርግጠኝነት ቤተሰቦቻችሁ የት እንዳሉ ታውቃላችሁ፤ ግድ የላችሁም እንወዳችኋለን እናከብራችኋለን፤ እንደ ልጆቻችን ነው አሁንም የምናያችሁ፤ ስለሆነም ትግራይ ዛሬ ብቻዋን አይደለችም፤ ከኢትዮጵያ ጋር ነች፤ ነገም ከኢትዮጵያ ጋር ትሆናለች።
አሜሪካ ትግራይን ለመጥቀም አይደለም፤ ኢትዮጵያንም ለመጥቀም አይደለም ለመበተን ነው፤ H.R. 6600 የሚባለው አሁን ሊፀድቅ በመንገድ ላይ ያለው፤ መሪዎቻችን ስለ ህዝባችን ብለው፣ ስለ ወደፊት ኢትዮጵያ ብለው ከተስማሙ፣ H.R. 6600 የሚፀድቅበት ምክንያት የለውም።
ህዝባችን  ከመንግስቶቻችን ጎን ቆሞ ሁላችንም የትግራይ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ እኔ- የትግራይ ህዝብና የኢትዮጵያ ህዝብ ስል ምቾት አይሰማኝም፤ እንደ ኢትዮጵያ ነው ሁላችሁንም የምናየው፤ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦቻችን ኢትዮጵያ ናቸው፤ ትላንትም ተባብረው ነውና ኢትዮጵያን ለዚህ ያበቋት፤ ነገም ዛሬም እንተባበር፤ ኢትዮጵያን አንድ እናድርጋት።
እኛ ልጆቻችሁ ከኦሮሞ የመጣ፣ ከአማራ የመጣ፣ ከትግሬ የመጣ፣ ከጉራጌ፣ ከየትም የመጣው ለዚህ ነው አንዷን ባንዲራ ከፍ ያደረግነው፤ ስለሆነም ብሔር ሳንለይ፣ ሃይማኖት ሳንለይ፣ ፆታ ሳንለይ፤ ባንዲራችንን ያነሳነው ስለተባበርን ነው፤ በፅናት ስለቆምን ነው። ለእናንተም አያቅትም፤ የትግራይ ክልላዊ መንግስትም የኢትዮጵያ መንግስትም እባካችሁ፤ ...ስለ ነገዋ ኢትዮጵያ አንድነት፣ ስለ ብልፅግናዋ፣ ስለ እድገቷ፣ ስለ ሰላሟ፣ እባካችሁ አያቅታችሁም፤ እኛም ከጎናችሁ አለን፤ ስፖርት ሰላም ነው፤ ስፖርት ፍቅር ነው ብለናል፤ ተያይዘን ኢትዮጵያን አንድ እናድርጋት። እግዚአብሔር ደግሞ አንድ ያድርግልን። “


Read 743 times