Saturday, 26 March 2022 11:15

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  የዕድሜ ግ-ሽበት
                             በእውቀቱ ስዩም

          አዲሳባ እየሰፋች ነው፤ ከጥቂት አመታት በሁዋላ “በአዲስ አበባ አስተዳደር በአንኮበር ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ በእውቀቱ“ የሚል ነገር መስማታችን  አይቀርም፥ አያት ወደሚባለው ሰፈር ብቅ ካሉ የፈረስ ጋሪ፥ ባጃጅና ዘመናዊ መኪና ትከሻ ለትከሻ እየተጋፉ ሲያልፉ ያያሉ፥ ባንድ ከተማ ውስጥ ሶስት ክፍለዘመኖች፥ ጎን ለጎን ይራመዳሉ፥
ሀብታሞች በሀብት ላይ ሀብት ጭነዋል፥ ድሆች የባሰ ድሀ ሆነዋል፥ የዛሬ ሶስት አመት ያንድ ሆቴል ባለቤት የነበረው ሰውዬ፤ ዛሬ ሶስት ቅርንጫፎች ከፍቷል! የዛሬ ሶስት አመት መጽሐፍ እሚያዞረው ልጅ ዛሬም መጽሐፍ አዟሪ ነው፥
ከትናንት ወዲያ። በከተማው ዘናጭ ከተባሉት ሬስቶራንቶች ወደ አንዱ ጎራ አልኩ፥ አዲስ ዩኒፎርም የተሰፋለት ዘበኛ፥ ከሸራ ጫማዬ እስከ ጋሜዬ ድረስ ገምግሞኝ ሲያበቃ፥
“ወዴት ነው?” አለኝ፥
“ወደ ምሳ;
ዘቡሌው ያለምንም እፍረት እንዲህ ሲል ጠየቀኝ፥
“መኪናህስ?”
“ትናንት ከዱባይ ተጭኗል፥አየሩ ጥሩ ከሆነ ነገ ጅቡቲ ይደርሳል”
ገባሁ፤
ምግብ ቤቱ ጠረጴዛ ላይ እንደ ሪፖርተር ጋዜጣ ዳጎስ ያለ ገጽ ያለ ሜኑ ተከምሯል፥ ይህንን ሲገልጥ ማን ይውላል?
“አስተናጋጅ”
“አቤት”
“ግማሽ ሽሮ ግማሽ ቲማቲም፥ ከስንግ ቃርያ ጋር፥ ስንት ሺ ብር ነው?”
በማግስቱ፥ ካስፓልት ዳር ያለች፥ በቆርቆሮ የተከበበች መናኛ ምግብ ቤት ሄድኩ፥ ድንች ጥብስ በሚጥሚጣ ተበላ! የጀበና ቡናም ደርሶናል፥ ጥቂት ሰዎች በሰማያዊ ፕላስቲክ በርጩማ ላይ ተደርድረዋል፤ ካጠገቤ የተቀመጠ ሰውዬ በወሬ ጠመደኝ። ንግግሩ ሳይሆን በካቲካላ የተመረዘ ትንፋሹ እጄን ባፌ አስጫነኝ!
“ስራህ ምንድነው?” አለኝ፥
“ጸሀፊ ነኝ”
“የመዝገብ ቤት ነው?”
ገላመጥሁት፥
“ስንት ልጆች አሉህ?” ሲል ቀጠለ፥
“አልወለድሁም”
“ያልወለድክበት ምክንያት ምንድነው?”
“ከግብረስጋ ታቅቤ ስለምኖር ነው”
“ቡና ጠጣ”
“አሁን ጠጣሁ”
"ግዴለህም ጠጣ”
“አልጠጣም”
“የይርጋ ጨፌ ቡና ነው”
“ለምን የይርጋ ዱባለ አይሆንም፥ አልጠጣም ካልሁ አልጠጣም”
በምልልሳችን መካከል ተንቃሳቃሽ ነጋዴዎች ጣልቃ ገቡ፥
- "ነጭ ሽንኩርት! ነጭ ሽንኩርት!
- ሸንኮራ ያስፈልጋል ፍሬንድ?
ጭራሽ የሆነ ሰውየማ ደርዘን ከዘራ ይዞ ቀረበኝ፥
“በዚህ ዘመን ከዘራ ገዝቼ ምን አደርገዋለሁ ዠለስ! ጨዋታው በስናይፐርና በዲሽቃ ነው" አልኩት፥
“እንድትፋለምበት ሳይሆን እንድትመረኮዝበት ብዬ ነው፤" ሲለኝ፥
ስለ ኢኮኖሚ ግሽበት ማሰብ አቁሜ፣ ስለ እድሜዬ ግሽበት ማሰብ ጀመርኩኝ፡፡


Read 1697 times