Saturday, 26 March 2022 11:26

ራሷ ጋግራው አልበሰለም፤ ራሷ ወልዳው አልመሰለም

Written by 
Rate this item
(5 votes)


           ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዋቂና አንድ አላዋቂ ሰው መንገድ ሲሄዱ ይገናኛሉ።
አዋቂ፡-
“እንደምን ውለሃል ወዳጄ?” ሲል በሰላምታ ጀመረ፡፡
አላዋቂ፡-
“ደህና እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ ወዴት እየሄድክ ነው?”
አዋቂ ፡-
“ወደ ገበያ”
አላዋቂ፡-
“ጎሽ ብቻዬን ከምጓዝ የሚያካሂደኝ አገኘሁ፡፡ እኔም ወደዚያው ስለሆንኩ አብረን እንጓዛለን”
በዚሁ ተስማምተው እየተጨዋወቱ ሲጓዙ ድንገት አንድ አጥር ላይ የተቀመጠ አውራ ዶሮ ያያሉ፡፡
አላዋቂ፡-
“አሁን ይህ አውራ ዶሮ እዚህ ሲጮህ ሰማይ ቤትም ይህንኑ የሚመስል አውራ ዶሮ ይጮኻል” አለ፡፡
አዋቂው፡-
“አይ አይመስለኝም”
አላዋቂው፡-
“ለምን?”
አዋቂው፡-
“መንግስተ ሰማይ’ኮ የንፁሃን ቦታ ነው፡፡ እንደ ዶሮ ያለ ኩሳም ነገር እዚያ አይገባም፡፡”
አላዋቂውም፤
“አይ፤ አውራ ዶሮው ቂጡን ወደ ገሃነም አፉን ወደ ገነት አድርጎ ነው የሚጮኸው”
አዋቂው፤
“አይምሰልህ ሲዖል’ኮ እንኳን የዶሮ ላባ አይነት ደረቅ ነገር አግኝቶ የሰውንም እርጥብ ገላ የሚያነድ ነው፡፡”
አላዋቂ፤
“ዎዎ! እኔ ምን ቸገረኝ፤ ያባቴ ዶሮ አይደለ ቢያንቦገቡገው!” አለው ይባላል።
*  *  *
አገራችን በእንደዚህ ዓይነት የአዋቂና የአላዋቂ አተካሮ ውስጥ መግባት ከጀመረች ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ በከንቱ ሙግት የሚጠፋው ጊዜ በርካታ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ክርክሩ ለአገርና  ለህዝብ ሁነኛ ጥቅም ሲባል በሆነ እሰየው ነበር። ሆኖም እንዲያው ለአፍ ወግና ውግ ብቻ እንዳፈተተ የሚነገርና የሚሰነዘረው ይበዛል። ከሁሉ የሚከፋው ደግሞ በከፍተኛ ስልጣን ቦታ የተቀመጡ ሹማምንት፣ ምንም ሳይሉ ለሰዓታት የቴሌቪዥንና የሬዲዮ አየር ሰዓት ሲያባክኑ ማየት ነው፡፡ በተሰብሳቢው ፊት ቆሞ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ፍሬ-ነገር የሌለው ውትወታና ሀተታ ለማንም አይበጅም! በአፍ ይጠፉ በለፈለፉም ነው፡፡
የአገራችን እጅግ ሥር የሰደደ ችግር ዛሬም ትክክለኛው ሰው በትክክለኛው ቦታ አለመቀመጡ ነው፡፡ (THE RIGHT MAN AT THE RIGHT PLACE እንዲሉ) የተማረና ባለሙያ ሰው አለመኖሩ ሳይሆን፣ እያለ ሁነኛ ቦታ አለመመደቡ ነው፡፡ እንደገና መበወዝ የሚያሻቸውን ወንበሮች ቦታ የማለዋወጥ ነገር ከታሰበበት ይቻላል። ሆኖም ከታሰበበት ነው! አለበለዛ ወርውረውት ራስን መልሶ እንደሚወጋው ቀስት (boomerang) ይሆናል፡፡ አገር ለመምራትና ለማሳደግ ለዋናው ወንበር ቀረቤታ ያላቸውን ባለስልጣናት መመልመልና መሾም ሳይሆን፤ ከዝምድናና ከቦናፓርቲዝም በፀዳ መልኩ ካቢኔን ማዋቀር ብልህነት ነው፡፡ ምንጊዜም ቢሆን የቅራኔ አፈራረጅና አፈታት በጥበብ የተሞላ ሊሆን ይገባዋል። ከሙስና የነጻ ይሆንም ዘንድ ጥበብ ያስፈልጋል፡፡ “አህያን ስጋ ጭነህ፣ ጅብን ንዳ ብለህ፤ አይሆንም” ይላሉ አበው፡፡
የለውጥና እንቅስቃሴ መስተጋብራችን ምንጊዜም ወርቅና ሰም፤ ፈትልና ቀሰም ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይሄውም በአያሌው ከተጠያቂነት ጋር  በአግባቡ የተሰናሰለ ተደርጎ ከተበጀ ነው፡፡ አለበለዚያ ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮህ የሚባለውን ተረት መድገም ይሆናል። ራሳችን መመሪያ አውጥተን፣ ራሳችን መመሪያ ጥሰን አይሆንም - A LAW MAKER IS A LAW BREAKER - ይሆንብናልና! “ራሷ ጋግራው አልበሰለም፤ ራሷ ወልዳው አልመሰለም” ማለት ይሄው ነው! የጀመርነውን መጨረስ፣ የጨረስነውን መገምገም፣ ስህተት ካለ መቀበል የስራ መርሃችን ሊሆን ይገባዋል፡፡Read 11944 times