Sunday, 27 March 2022 00:00

ግራ ገብቷቸው ግራ የሚያጋቡ ፖለቲከኞች!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(3 votes)

 “ድርድርም - ውይይትም - ምርጫም - እርቅም - የሽግግር መንግስትም” ይፈልጋሉ!
                          
                 ወዳጆቼ፤ የዚህ ፖለቲካዊ ወግ ዓላማ ፖለቲከኞችንም ሆነ ፓርቲዎችን ያለስማቸው ስም መስጠት ወይም ማሳጣት አሊያም መወንጀል ወይም ደግሞ ማውገዝ አይደለም። (በፍጹም!) እውነት እውነቱን - ሃቅ ሃቁን እያፈረጡ ብቻ ማውጋት ነው። ሃሳብ ማንሸራሸር፡፡ ለምን ቢሉ? ፖለቲካ በአብዛኛው ከሃቅ የራቀ- ከእውነት የተፋታ ነውና። (በተለይ የጦቢያ ፖለቲካ!) በምሬትና በጥላቻ ግን አይደለም። በፍቅርና በፈገግታ ነው- ፖለቲካን በፈገግታ እንዲሉ። በዚሁ መንፈስ ወጋችንን እንቀጥላለን፡፡
እንደምታስታውሱት… በአንጋፋው የፖለቲካ ልሂቅ ፕ/ር መረራ ጉዲና የሚመራው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ ከ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ራሱን ያገለለው “ተገፍቼአለሁ” በሚል ነበር። ትርጉም፡- "አመራሮቼና አባላቶቼ ታስረው እንዲሁም ከ200 በላይ ጽ/ቤቶቼ ተዘግተውብኝ በምርጫው መሳተፍ አልችልም" (አመራሮቻቸው ታስረውባቸው በምርጫው የተሳተፉ ግን ነበሩ!) ራስን ከምርጫው ከማግለል ይልቅ ጉዳያቸውን ወደ ፍ/ቤት ወስደው ምርጫ ቦርድን የረቱም ፓርቲዎች አልጠፉም (በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ!)። ለአብነትም "ባልደራስ" እና "ኦነግ" ይጠቀሳሉ።
በነገራችን ላይ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ኦፌኮ በምርጫው ይሳተፍ ዘንድ ያልፈነቀሉት ድንጋይ እንደሌለ ምንጮች ይናገራሉ (ሽምግልናም ሳይቀር!)። የፕሮፌሰሩ ፓርቲ ግን አሻፈረኝ አለ (አመራሮቼ ከእስር ካልተፈቱ ሞቼ እገኛለሁ በማለት!)። የፓርቲውን  ከምርጫ ራሱን ማግለል ተከትሎ፣ ራሳቸውን ከኦፌኮ አባልነት ያገለሉ አንድ የህግ ባለሙያና አንጋፋ ፖለቲከኛ፤ “እኔ ለዓመታት የታገልኩለት ፓርቲ (ኦፌኮ) ይሄ አይደለም” ሲሉ አስተያየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኦፌኮ አመራር በዳያስፖራ ፅንፈኛ ፖለቲከኞች ተፅዕኖ ሥር ወድቋል የሚሉት የቀድሞው አባል፤ የፓርቲው ራሱን ከምርጫው ማግለል የውጭ ተፅዕኖ ውጤት ነው ሲሉ ተችተዋል።
አንድ የኦፌኮ ከፍተኛ ሃላፊ በቅርቡ ለሚዲያ በሰጡት አስተያየት ደግሞ፤ በምርጫው ማግስት የፓርቲው ሊቀመንበር ከኦነግ አመራር ጋር ሆነው "የኦሮሚያ የሽግግር መንግስት አቋቁመናል" በሚል የሰጡትን መግለጫ የኦፌኮ ሥራ አስፈጻሚ እንደማያውቀው ተናግረዋል፡፡ ሃላፊው አክለውም፤ "ፓርቲውን እንዳሻቸው የሚዘውሩት ሊቀ መንበሩ ናቸው፤ እሳቸው በተናገሩት ሁሉም ይስማማል" ሲሉ እውነታውን አፍርጠዋል፡፡ (ኦፌኮ ሳይረፍድ ራሱን ይገምግም!)
ወደ ጀመርነው አጀንዳ ስንመለስ፣ምንም እንኳን ኦፌኮ ራሱን ከምርጫው ቢያገልም፣ 6ኛው አገራዊ ምርጫ መካሄዱ ግን አልቀረም። ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንጻራዊነት ሰላማዊና  ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄዷንም ብዙዎች መስክረዋል- የምዕራቡን ዓለም ጨምሮ!!
"ምርጫው ከተካሄደ በአገሪቱ ቀውስ ይፈጠራል፤አሁን ጊዜው አይደለም" የሚሉ ድምጾች ከውስጥም ከውጭም፤ ከሚያገባቸውም ከማያገባቸውም ተስተጋብቶ ነበር፡፡ (ደግነቱ ሟርቱ አልሰራም!)
ምርጫው በተካሄደ ማግስት ታዲያ የፕሮፌሰሩ “ኦፌኮ” እና “ኦነግ” ዱብዕዳ የሆነ መግለጫ አውጥተው ነበር - “የኦሮሚያ የሽግግር መንግስት ተቋቁሟል" የሚል (ደግነቱ “ፕራንክ” ነው ተባለ!)
ብዙም ሳይቆይ ደግሞ ኦፌኮ ለብቻው ሌላ ዱብዕዳ የሆነ መግለጫ አወጣ - #በ6 ወር ጊዜ ውስጥ በብሔራዊ ምክክር የታጀበ ብሔራዊ ምርጫ እንዲካሄድ እፈልጋለሁ; የሚል፡፡ ("የባሰ አታምጣ" ነው!)
ወዳጆቼ፤ በምርጫው አልሳተፍም ብለው ሲያበቁ፣ ምርጫው ከተካሄደ ገና 6 ወር እንኳን ሳይሞላው "አዲስ  ምርጫ ማወጅ" ግራ መጋባት ካልተባለ፣ ምን ሊባል ይችላል?!
ልብ በሉ! ኦፌኮ ራሱን ከ6ኛው አገራዊ ምርጫ ያገለለው፣ አባላቱና አመራሩ በእስር ላይ ስለነበሩና ጽ/ቤቶቹ ስለተዘጉበት እንደነበር ነግሮናል። ታዲያ ምን ተገኝቶ ነው በ6 ወር ውስጥ ሌላ ምርጫ እንዲካሄድ የፈለገው? (አመራሩና ፓርቲው ብቻ ነው የሚያውቁት!) እኛ ግን ዛሬም ድረስ  ግራ እንደተጋባን ቀጥለናል። ("ግራ ተጋብተው ግራ የሚያጋቡ ፖለቲከኞች” ያልነው በምክንያት ነው!)
በሌላ በኩል፤ ኦፌኮ ከምንም በፊት የብሔራዊ ምክክርና መግባባት መድረክ እንዲፈጠር ለዓመታት ሲወተውትና ሲጎተጉት የከረመ ፓርቲ እንደሆነ ይታወቃል። ነገር ግን ሁሉን አካታች አገራዊ ምክክር (National dialogue) ለማድረግ መንግስት በዝግጅት ላይ መሆኑን ሲገልጽ፣ ፓርቲው “ስለቴ ሰመረ” ብሎ አልጨፈረም፡፡ ሻምፓኝም አልከፈተም። ይልቁንም በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑም ሆነ በኮሚሽነሮቹ ላይ እምነት እንደሌለው በመግለፅ፤ ራሱን ከሂደቱ ሊያገል እንደሚችል ፍንጭ ሰጠ፡፡
ፓርቲው በምክክሩ ለመሳተፍ ቅድመ ሁኔታዎችም አስቀምጦ ነበር፡፡ ከቅድመ ሁኔታዎቹ አንዱ ደግሞ፡- “በፓርላማ በሽብርተኝነት የተፈረጁት “ህውሓት” እና “ሸኔ” በውይይቱ የግድ  መሳተፍ አለባቸው” የሚል ነው። ("ሁለቱ ካልተሳተፉ ግን ሂደቱ አካታች አይሆንም - ዘላቂ ሰላምም አያመጣም" ባይ ነው ፓርቲው!!) ከቡድኖቹ ጋር የሚነሳውን የህግና የሞራል ጥያቄዎች ወደ ጎን ትተን፣ ሁለቱ ቡድኖች በመድረኩ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ባይሆኑ፣ ኦፌኮ ምን ይውጠዋል? (ያሳምናቸው ይሆን?!)
በነገራችን ላይ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በምርጫው እንዳደረጉት ሁሉ፣ አሁንም በአገራዊ ምክክሩ ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰበብ ሳይደረድሩ በመሳተፍ፣ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
በአገራዊ ምክክሩ ቅድመ ዝግጅት ላይ መነታረክ አያስፈልግም የሚሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በህዝብ ጥቆማና በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የተመረጡት 11ዱ ኮሚሽነሮች፣ የውይይት መድረክ ከማመቻቸትና አጀንዳ ከመቅረጽ ውጭ ምንም ውሳኔ የመስጠት ስልጣን የላቸውም” ሲሉም አስረድተዋል።
“በተመረጡ የተለያዩ አወዛጋቢ አጀንዳዎች ላይ ተወያይተንና ተፋጭተን ከተግባባን እሰየው፤ መግባባት ላይ ካልደረስን ግን አጀንዳውን ለሪፈረንደም እናቀርብና የኢትዮጵያ ህዝብ ይወስንበታል” ሲሉም የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪው ብልፅግና ወይም ሌላ ፓርቲ ሳይሆን ራሱ የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑን በማያወላዳ ቋንቋ አስረግጠው ተናግረዋል- ጠ/ሚኒስትሩ።
ወዳጆቼ፤ በአገራዊ የምክክር መድረኩ ላይ ይቀርባሉ ተብለው ከሚጠበቁት አወዛጋቢ የመወያያ  አጀንዳዎች መካከል አብዛኞቹ የተፈጠሩት በፖለቲካ ልሂቃኑ ነው፡፡ (ህዝብማ እርስ በርስ የሚጠፋፋበትን እሳት አይፈጥርም!) ምሳሌ እንጥቀስ፡- የባንዲራ ንትርክ፣ የበዳይ-ተበዳይ ትርክት፣ ልዩነትን የማጉላት ፖለቲካ፣ ጥላቻን ማቀንቀን፣ ወዘተ-- ሁሉም የፖለቲከኞች የእጅ ሥራ ነው፡፡ (ትኩረት ለማግኘትና ስሜት ለመኮርኮር የሚፈጥሩት!) እናም ጣጣ ሳያበዙ በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ተሳትፈው ራሳቸው ለፈጠሯቸው አወዛጋቢ አጀንዳዎች፣ መፍትሄ በማበጀት ይተባበሩን። (ያለውዝግብ መኖር የማይችሉ ምን በጃቸው?!)
***
ወዳጆቼ፤ ባለፈው ሳምንት የህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ከፋና ቴሌቪዥን ጋር ያደረጉትን አስገራሚ ቃለ-ምልልስ አይታችሁልኛል? እውነት ለመናገር ቃለ-ምልልሱ ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድረስ በተቃርኖና በግራ መጋባት የተሞላ ነው።  ይታያችሁ… ራሳቸውና ፓርቲያቸው የተሳተፉበት 6ኛው አገራዊ ምርጫ በተካሄደ በዓመቱ "በአስቸኳይ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም" እየጠየቁ ነው፡፡ (ከምርጫ ወደ ሽግግር መንግስት!)
በእርግጥ በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ኢንጂነሩ አልቀናቸውም፤ በዝረራ ነው የተሸነፉት፡፡ አንድም ድምጽ እንኳ ሳያገኙ። ግን እንደተለመደው "ተጭበርብሯል; ምናምን ብለው ለማለቃቀስ አልሞከሩም፡፡ ይልቁንም ደጋፊዎቻቸው ስላልመረጧቸው አመሰግነዋል (ከአንጀታቸው ይሁን ከአንገታቸው ባይታወቅም!)፡፡ ያኔም ታዲያ ደጋፊዎቻቸው ሳይመርጧቸው በመቅረቱ ለምን እንዳመሰገኗቸው ሲጠየቁ፤ "ቀድሞውኑም የሚያስፈልገው ምርጫ ሳይሆን የሽግግር መንግስት እንደሆነ ስንገልጽ ቆይተናል" አሉና አረፉት፡፡ (ለምን በማያምኑበት ምርጫ እንደተወዳደሩ አናውቅም!)
ፖለቲከኛው፤ አገራዊ ውይይት (National dialogue) ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር መፍትሄ ነው ብለው እንደሚያምኑ ለፋና ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ነግረውታል። ችግሩ ግን በኮሚሽኑም በኮሚሽነሮቹም እምነት የላቸውም፡፡ የእሳቸውን ትንሽ የከፋ የሚያደርገው ግን በኢትዮጵያ ውስጥ አገራዊ ምክክሩን ለመምራት የሚያምኑት አንድም ግለሰብ፣ አንድም ምሁር፣ አንድም ሽማግሌ፣ አንድም የሃይማኖት መሪ፣ አንድም ተቋም… አለመኖሩ ነው። ስለዚህም የውጭ አገር መንግስት በውስጥ ጉዳያችን ገብቶ እንዲፈተፍት ይፈልጋሉ፡፡ “እኛ ካልቻልን አሜሪካ ታደራድረን” ነው ያሉት - ቃል በቃል!
እዚህ ላይ የፋናው ጋዜጠኛ ዝም አላላቸውም። “የውጭ አገር መንግስታት በአደራዳሪነት ገብተው ሰላም ያመጡበት ሁለት አገሮችን ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ? ሲል ጠየቃቸው። ከየት ያምጡት! (የለማ!)  ቢቸግረው ጋዜጠኛው ራሱ መለሰላቸው። “እኔ ግን በውጭ መንግስት አደራዳሪነት የባሰ ቀውስ ውስጥ የተዘፈቁ አገራትን ልጥቀስልዎ” አላቸው። እናም ሁለት አገሮችን ጠቀሰላቸው - ሊቢያና ሱዳንን! (ፖለቲከኛው አልተከራከሩም!)
ወዳጆቼ፤ መጀመሪያ ላይ እንደነገርኳችሁ የዚህ ፖለቲካዊ ወግ ዓላማ፤ ሃቅ ሃቁን- እያፈነዱ-እውነት እውነቱን ማውጋት ነው። በምሬትና በጥላቻ ስሜት ግን አይደለም፡፡ በፍቅርና በፈገግታ ነው- ፖለቲካን በፈገግታ እንዲሉ።
የዛሬውን ወግ ከመቋጨታችን በፊት ታዲያ፣ ለጦቢያ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች ጥቂት ፈታኝ ጥያቄዎችን ለማቅረብ እንወዳለን- የፖለቲከኞች ቻሌንጅ ዓይነት።
የፖለቲከኞች ቻሌንጅ
1. በጦቢያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንጻራዊነት ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በተካሄደ ማግስት ዳግም ምርጫ እንዲካሄድ ወይም “አስቸኳይ የሽግግር መንግስት” እንዲቋቋም የሚወተውቱ ፓርቲዎች ወይም ፖለቲከኞች ፍላጎታቸው ምንድን ነው? (እኛን ግራ ከማጋባት ውጭ ማለቴ ነው!)
2. ፖለቲከኞች “ብሔራዊ መግባባት”፣ “አገራዊ ውይይት”፣ “እርቅና ድርድር”፣ ወዘተ… ሲሉ በትክክል ምን እያሉ ነው? (ከእነ ትርጉሙ ይንገሩና!)
3. ፖለቲከኞቻችን በአፋርና አማራ ክልሎች ጦርነቱ ያደረሰውን ጥፋትና ውድመት በተመለከተ ምን አደረጉ? በጦርነቱ የተጎዱና የተፈናቀሉ ዜጎችን ጎብኝተዋል? አጽናንተዋል? ድጋፍ አድርገዋል? ሌላው ቢቀር በየጊዜው በሚያወጧቸው መግለጫዎች ጠቅሰዋቸዋል? (ለዚህ መቼም መንግስት መሆን አያስፈልም!)
4. በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በየጊዜው ታጣቂ ሃይሎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጽሙትን አሰቃቂ ግድያና ማፈናቀል ለማስቆምና ህዝቡን ያለስጋት በሰላም እንዲኖር ለመታደግ ፖለቲከኞች ምን የመፍትሄ ሃሳብ አላቸው? (በመንግስት ላይ ጣት ከመቀሰር ውጭ ማለቴ ነው!)
ወዳጆቼ፤ በመጨረሻ ኳስ በመሬት እንደሚባለው፣ እኛም ፖለቲካ በጠረጴዛ ዙሪያ ብቻ እንላለን!! የነገ ሰው ይበለን!!


Read 2255 times