Saturday, 02 April 2022 11:25

ከትግራይ ወደ ቆቦና አላማጣ ከተሞች የሚገቡ ተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

 ከትግራይ ክልል ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል ቆቦና አላማጣ ከተሞች የሚገቡ የትግራይ ክልል ተፈናቃይ ወገኖች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው ተባለ። የተፈናቃዮቹ ቁጥር ከሁለቱ ከተሞች አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በየዕለቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ወደ ሁለቱ ከተሞቹ የሚገቡ ሲሆን ተፈናቃዮቹ በየእምነት ተቋማት፣በሰው መኖሪያ ቤት ግቢ ውስጥ በንግድ ቤቶች በረንዳ ላይ፣ በስቴዲየም  በጋራዦችና በየጎዳናው ሰፍረው እንደሚገኙም ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡
 የቆቦና አላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ቀደም ሲል የትግራይ ታጣቂ ሃይሎች ከተሞቹን ተቆጣጥረው በቆዩባቸውም ጊዜያት ከፍተኛ ጉዳት አድርሰው የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ከትግራይ ተፈናቅለው ወደ ከተሞቹ ለመጡት ወገኖቻቸው የሚያሳዩት ሰብአዊ ተግባር በእጅጉ የሚያስመሰግን መሆኑን ከስፍራው የሚገኙ አስተያየት ሰጪዎች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ከስምንት ቀናት በፊት ከመቀሌ ቆቦ ከተማ የገባው ወጣት ሳምሶን ግደይ እንደሚናገረው፤ የቆቦ ከተማ ህዝብ ለተፈናቃዩ የትግራይ ክልል ህዝብ እያደረገ ያለው ሰብአዊ ተግባር ከአእምሮ በላይ ነው። ከመቀሌ ወጥተን ወደ አማራ ክልል ስንገባ ለመሞት ተዘጋጅተንና ቆርጠን ነበር። በረሀብ ከመሞት በጥይት መሞት ይሻለናል ብለን ቆርጠን ነበር የመጣነው ስንመጣ  ከሌለው ላይ ቆርሶ የሚያካፍል፣ የወገኖቹን መራብ እንደራሱ  የሚቆጠር ወገን ነው ያገኘነው በዚህም በጣም ተገርመናል” ብሏል፡፡
እንደ ሳምሶን ሁሉ ከትግራይ ክልል ሁቅሮ ከተማ ተፈናቅሎ ቆቦ የገባው ብሩክ ተስፋ፣ ባገኙት አማራጭና መንገድሁሉ ከትግራይ ለመውጣት ጥረት የሚያደርጉ በርካታ ወገኖች መኖራቸውን ጠቆሞ፤  በመንገድ ላይ በተለያዩ ሁኔታዎች ህይወታቸው የሚያጡ ስደተኞች መኖራቸውንም አልሸሸገም፡፡ ከ3 የአካባቢው ወጣቶች ጋር ከውቅሮ ተነስተው ሁለቱ ብቻ ቆቦ ከተማ መድረሳቸውን የሚገልፀው ብሩክ፣ አንደኛው ወጣት በመንገድ ላይ ባጋጠመው ድንገተኛ ህመም መሞቱን ተናግሯል፡፡
በስፍራው ከትግራይ  ክልል ተፈናቅለው በቆቦና አላማጣ ከተሞች ውስጥ በተለያዩ ስፍራዎች ተጠልለው ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖችና በትግራይ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ነዋሪዎችም የሃዋላ አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎችም ተበራክተዋል ተብሏል፡፡
በዚሁ የሃዋላ ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ወገኖች ገንዘብ አላማጣ አሊያም ቆቦ ከተማ ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ለማድረስ ከ35-40 በመቶ ክፍያ የሚጠይቁ ሲሆን መቀሌ ከተማ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ገንዘቡን ለማስተላለፍ  ከ50-60 በመቶ ክፍያ እየጠየቁ ነው ተብሏል፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለቤተሰቦቻቸው ገንዘብ ለማድረስ የሚፈልጉ ሰዎች ለእነዚህ የሃዋላ አስተላለፊዎች ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ፡፡ የከፋው ገንዘቡን ለተቀባዩ ሳያደርሱ ስልካቸውን አጥፍተው የሚጠፉ አዘዋዋሪዎች መኖራቸው ነው ተብሏል፡፡
የትግራይ ክልል አጎራባች የሆኑት የቆቦና አላማጣ ከተሞች ከዕለትወደ  ዕለት ቁጥራቸው  እየጨመረ  የመጣውን  የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች ለመቀበል  ከማይቻሉበት  ደረጃ ላይ እንየደረሱ መሆኑና ሁኔታው ከአቅማቸው በላይ እየሆነ መምጣቱን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡


Read 11916 times