Saturday, 02 April 2022 11:38

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ብልጽግና እውነታውን መጋፈጥ ይኖርበታል!
                                  ጌታሁን ሔራሞ


           ከእንግዲህ የብልፅግና ፓርቲ “illusionist” መሆኑን አቁሞ እውነታውን ፊት ለፊት መጋፈጥ ይጠበቅበታል!
ሰሞኑን የብልፅግና ፓርቲ ካካሄዳቸው ሕዝባዊ ስብሰባዎች ወትሮም ብዙዎቻችን አስቀድመን ስንጮህ የነበረውን አንድ ቁም ነገር ፓርቲው ሊገነዘብ ይችላል ብዬ አስባለሁ...ፓርቲው ራሱን በቅዥት ዓለም ውስጥ (illusionist) ሆኖ በመቀጠል ከእውነታው ጋር ለመላተም እስካልፈለገ ድረስ ማለቴ ነው።
Just to say that the PP party has drastically lost the political trust from the public...ማለትም የፓርቲው ፖለቲካዊ ትምምን በእጅጉ ተሸርሽሯል፤ ከዚህም የተነሳ ሕዝቡ የጥበቃ ቀውስ (Expectation crisis) ውስጥ ተዘፍቋል።
የብልፅግና ፓርቲ ፖለቲካዊ ትምምኑን ለማጣቱ የሞጆው ስብሰባ አንዱም ማሳያ ነው። በዚህ ስብሰባ መድረኩ ላይ ሶስት የብልፅግና ተወካዮች ነበሩ፦ ብዙዎቻችን ከተለቀቀው ቪዲዮ እንደተከታተልነው አንዱ የስብሰባ ተሳታፊ፣ “ምናልባትም ከሶስታችሁ ሁለታችሁ ሸኔ ልትሆኑ ትችላላችሁ” ማለቱ የብልፅግና ፓርቲ “political trust” የቱን ያህል መቀመቅ እንደወረደ አመልካች ነው። “Political trust” የሌለው ፓርቲ ደግሞ በቁም እንደሞተ ይቆጠራል። እናም “PP”ዎች ከኢሊዩዥን ዓለም ወጥታችሁ ወደ እውነታው ዓለም እንድትመጡ አንድዬ ያግዛችሁ። ሕዝብም ሆነ ሌሎች በመዋቅራችሁ ውስጥ ያልታቀፉ ምራቅ የዋጡ የፖለቲካና የአስተዳደር ምሁራን የሚሰጡዋችሁን ምክር የሚሰማ ጆሮ ይኑራችሁ። እዚያቹ እርስ በእርስ መሞጋገሱ በዘለቄታዊነት የሚያመጣው ውጤት የለም። ሕዝብ ከተቆጣ ደግሞ ጊዜም ይከዳል፤ በአፍሪካ ደረጃ እንኳን የሚገዳደረን ኃይል የለም ብለው በታንካቸውና በባንካቸው የተመኩ ሕወሓቶች፤ ጊዜ ሲከዳቸው ከቤተ መንግስት ተፈንግለው፣ ከ30 እና 40 ዓመታት በፊት ወደ ነበሩበት ደደቢት በረሃና ዋሻ ውስጥ ገብተው እንደተሸሸጉና አንዳንዶቹም ትግላቸውን በጀመሩበት በረሃ፣ ፍፃሜአቸውም እዚያው እንደሆነ ባለ ሾርት ሚሞሪ ሰለባ ካልሆንን በቀር ከቶ እንዴት ይረሳል?
በተለይ “ጊዜው የእኛ ነው” በሚል እብሪት የሕወሓትን ስህተት መድገም ውድቀቱን ለመድገም እንደመዘጋጀት ይቆጠራል። ካወቃችሁበት በመከባበር ላይ የተመሠረተ አንድነትን በማስረፅ በኢትዮጵያ ዝንተ ዓለም የሚዘከርላችሁን ሥራ ለመስራት ዕድሉን አግኝታችኋልና በሚገባ ተጠቀሙበት። በመጨረሻም ሁለት ገጠመኞቼን ላካፍላችሁ፦
1. በግምት በ1990ዎቹ መባቻ በመለስ ዜናዊ የአገዛዝ ዘመን ነው። ታክሲ ተሳፍሬ ወደ አቃቂ ስሄድ በሾፌሩና በሁለት ወጣት ተሳፊሪዎች መካከል ንትርክ ተፈጠረ። ወጣቶቹ ታክሲው ጉዞውን ከጀመረ በኋላ በትግርኛ አክሰንት “የሠራዊቱ አባል ስለሆንን በታሪፉ መሠረት አንከፍልህም” ማለታቸው ነበር የግጭቱ መንስኤው። የሠራዊቱ አባል ነን ያሉ እነዚህ ወጣቶች በየመኸሉ የወቅቱ ገዥ ብሔር አባል መሆናቸውን ለማሳወቅ “ቧዋ” የምትለውን ቃል በተለመደ ቅላፄ ያስተጋቡ ነበር። ሾፌሩ እንደምንም ታግሶ በወቅቱ የፍተሻ ጣቢያ ወደነበረበት ቃሊቲ እንደደረሰ መኪናውን አቁሞ ለፈታሽ ፖሊሶች ችግሩን ለማስረዳት ወረደ (ፈታሾቹ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ነበሩ)። ከጀርባዬ የነበሩ ሁለቱም ወጣቶች “ቧዋ...ጉቦ ሊሰጣቸው ነው” እያሉ እነርሱም ወረዱ። መውረድ ብቻ ሳይሆን ለፖሊሶቹም ማንነታቸውን systemic በሆነ መልኩ ለማሳወቅ “ቧዋ...ዋይ...የሠራዊቱ አባል ነን” በማለት ለማስፈራራት ሞከሩ። ታዲያ ፖሊሶቹ ምን ቢሏቸው ጥሩ ነው?” ‘ቧዋ’ኣችሁን ቀቅላችሁ ብሉት፤ እንዲያውም ሕዝብን በማወክ ትጠየቃላችሁ፤ የሠራዊቱ አባል መሆናችሁም ተጣርቶ አስፈላጊው እርምጃ ይወሰድባችኋል” በማለት ሾፌሩ ተሳፋሪዎቹን አቃቂ እንዲያደርሳቸው ነግረውት፣ ወጣቶቹን ከነ”ቧዋ”ኣቸው እዚያው አስቀሯቸው...እኛም ተሳፋሪዎች የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በወቅቱ ሰፍኖ በነበረው “ቧዋ እና ዋይ” ፍርሃት ሳይበገሩ እርምጃውን በመውሰዳቸው ድጋፋችንን በጭብጨባ አረጋገጥንላቸው።
2. ይኼኛው ደግሞ ከሁለት ቀናት በፊት ያጋጠመኝ ነው፦ እዚሁ አዲስ አበባ በጧቱ ወደ አንድ የፌዴራል መስሪያ ቤት ተቋም አምርቼ መኪናዬን ሳቆም አንድ የጥበቃ አባል የሆነ ወጣት ቀረብ ብሎ በኦሮምኛ ቋንቋ አናገረኝ። እኔም ኦሮምኛ ቋንቋ እንደማልችልና እንድፈፅምለት የሚፈልገውን ትዕዛዝ በሚገባኝ ቋንቋ እንዲነግረኝ በትህትና ሳስረዳው በአማርኛ “ለምንድነው ያልቻልከው?” በማለት በኦሮምኛ መናገሩን ቀጠለበት፤ በዚሁ መኸል ከላይ ያካፈልኳችሁ ዘመነ “ዋ” እና ዘመነ “ቧዋ” ትዝ አለኝ። እኔም #የምትለው ስላልገባኝ ትዕዛዝህን መፈፀም አልቻልኩምና እባክህ በአዲስ አበባ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ በሆነው በአማርኛ አስረዳኝ; አልኩት። ንትርካችንን ያስተዋሉ ሌሎች ሶስት የጥበቃ አባላትም ወደ እኛ በመምጣታቸው ስለ ተፈጠረው ውዝግብ አስረዳኋቸው። ከሶስቱ አንዱ ኦሮምኛ ተናጋሪ ስለነበረ የሥራ ባልደረባውን ፍላጎት ምን እንደሆነ በእኔው ፊት በአማርኛ በማናገር ጠየቀው። ጓደኛው በኦሮምኛ መለሰለት። የሚገርመው ኦሮምኛ ተናጋሪው ጥበቃ “እዚህ ግቢ ውስጥ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ስለሆነ አሁን ለኔ የተናገርከውን ለባለጉዳይ በአማርኛ አስረዳው” ብሎ አስገደደውና በኋላም መኪናዬን ፓርክ ለማድረግ የሞከርኩበት ቦታ ለድርጅቱ ሠራተኞች ብቻ የተፈቀደ መሆኑን በአማርኛ አስረድቶኝ፣ ለተፈጠረውም ሁኔታ ይቅርታ ተጠይቄ ተለያየን። በዚሁ አጋጣሚ ከጅምላ ፍረጃ መጠንቀቅ እንዳለብኝ ለራሴም ትምህርት ወስጄ፣ ያስታረቀንንም ኦሮምኛ ተናጋሪ የጥበቃ አባሉን አመስግኜው ወደ ቢሮዬ ተመለስኩ።
አሁንም ደግሜ እላለሁ፤ “ጊዜው የኛ ነው” በሚል ቁንፅል ዕይታ ሕወሓት የፈፀመውን ስህተት በመድገም ውድቀቱንም እንዳትደግሙት፣ እባካችሁ መላ የኢትዮጵያ ብሔሮችን በእኩልነት አስተናግዱ። በሚሊተሪው የምንተማመን ከሆነ እንደ ሕወሓት ባደራጀው የመከላከያ ኃይሉ የሚተማመን አልነበረም፤ በደህንነትና ስለላ መረቡም የምትመኩ ከሆነ፣ ወያኔ ምናልባትም የአሁኑን በብዙ እጥፍ የሚበልጥ የደህንነትና ስለላ መረብ ነበራት፤ ፅዋው ሲሞላ ይህ ሁሉ ዋስትናዋ አልሆነላትም፤ እነ ደፂ ወደ በረሃ በተመለሱበት ቅፅበት አንድ የከምባታ “ኮሜዲያን” የገጠመው እንደዚህ በማለት ነበር፦
ደብረ ፂዮን ሀኑታ ኣጎ?
ደብረ ፂዮን ሀኑታ ኣጎ?
ጨሪች ፉሎጋ ጨራን ኣጎ
ሲተረጎም፦
ደብረፂዮን ወዴት ገባ?
ደብረፂዮን ወዴት ገባ?
ከዱር እንደተነሳ ወደ ዱር ገባ(ተመለሰ)!
እንደማለት ነው።
ሰናይ ሰንበት!____________________________________
                       ጥቆማ
                           በእውቀቱ ስዩም


             ራይድ ለመዲናይቱ አሪፍ ጸጋ ነው፤ ለብዙ ሰው ስራ ፈጥሮ የብዙ መንገደኞችን ኑሮ አቅልሏል፥ ራይድ ከሚሰሩ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እንደኔ የክፍለሀገር ልጆች መሆናቸውን መርሳት አይገባም። ባለፈው አንዱ ባለ ቢትስ መጣልኝ፥ ጢንጥዬ መኪና ናት፤ አራት ጎማ ያላት የዲዮጋን ቀፎ በላት፤ (አሁን በመንሽ እግሩ ያዲሳባን አቧራ ሲቀዝፍ የሚውል እንደ እኔ ያለ ዘመን አይሽሬ እግረኛ ሰው፣ መኪና ላይ ሙድ መያዝ ነበረበት? ሰው ምን ይለኛል አይባልም? ሆ!)
“ጋቢና ትገባለህ ወይስ ከሁዋላ?” ሲል አማረጠኝ፥
የመኪናይቱን በር እንደ መርቲ ጣሳ ክዳን ከፍቼ፤ እንደ ሰርከስ ባለሙያ ተጣጥፌ ከሁዋላ ገባሁ፥ እንደ እውነቱ ከሆነ የመኪናይቱ መላ አካል ለሁለት የተከፈለ ጋቢና ቢባል ያስኬዳል፤ መኪናዋ ከመጥበቧ የተነሳ ከሾፌሩ ጋራ አንድ ቀበቶ ለሁለት አስረን መሄድ ጀመርን፤
“የት ነው መዳረሻህ ?”
“ቀበና ፥ሳንፎርድ ‘
“የት ጋ ነው እሱ ደሞ? ”
“እኔም እንግዳ ነኝ፤ ባካባቢው ህብረተሰብ ርብርብ ልናገኘው እንችላለን”
ሹፌሩ በሰፈር መሀል እየነዳ የሆነ ቅያስ ላይ ሲደርስ፣ አንድ ሽማግሌ አስቆመና አድራሻ ጠየቃቸው፥
“በዚህ ቀጥ ብለህ ሂድና ወደ ግራ ስትዞር ያፈንጉስ ነሲቡን ድልድይ ትሻገራለህ” ብለው ጀመሩ፤
“አሀ” አለ ሹፌሩ፥
“ድልድይ ማለት፤ ከገደል ገደል የተዘረጋ ጥፍጥፍ ብረት፤ ጣውላ፥ አለት፥ ወይም ግንድ ሊሆን ይችላል”
“ገባኝ”
“አፈንጉስ ነሲቡ ማለት ደግሞ ባጤ ምኒልክ ዘመን የታፈሩና የተከበሩ ዳኛ ናቸው; ቀጠሉ፤ አረጋዊው፤
“ሰውየው በሙስናም የታወቁ ነበሩ” የሚል ጨመርኩ፤
(በታሪክ ዙርያ የመከራከር ስር የሰደደ ሱስ አለብኝ)
“የተጨበጠ ማስረጃ አለህ ወይስ ከኪስህ እያወጣህ ነው እምትናገረው?!” አሉኝ ሰውየው ደማቸው ፈልቶ፤
እኔና ጠቋሚው ሰውዬ በታሪክ ዙርያ ስንጨቃጨቅ ሾፌሩ ትግስቱ አልቆበት ከጎረቤት ሹፌር ተበደረ፤
“ያፈንጉስ ነሲቡን ድልድይ ካለፍን በኋላስ?” አለ፥ ሹፌሩ በመጨረሻ፥
"ያፈንጉስ ነሲቡን ድልድይ ካለፋችሁ በሁዋላ ያፈንጉስ ነሲቡን አደባባይ ትዞሩታላችሁ”
“ከዞርን በሁዋላስ?”
“ደርቡት!”
በመጨረሻ፥ ሳንፎርድ አካባቢ ደረስኩ፤ ትንሽ ተራምጄ አንዱን ሎተሪ አዟሪ አስቁሜ፤
“ዠለስ እዚህ አካባቢ፤ ንግድ ባንክ አለ?”
“ልታስገባ ነው ልታስወጣ?”
______________________________________________

                        "ከመቼ ወዲህ ነው ጨለምተኛ የሆንከው?;"
                             አንዷለም ቡኬቶ ገዳ

                 አልጄሪያ ለስራ አጥ ዜጎቿ ወርሃዊ ዳረጎት ልትቆርጥ ነው።
ኢትዮጵያ ስራ አጥ ዜጎቿ መቼም የማያገኙትን ስራ ሲፈልጉ ውለው ሲደክማቸው አረፍ የሚሉበትን አደባባይና ፓርክ በመስራት ተጠምዳለች! የሁለቱም አካሄድ አስቂኝ ነው!
የስራ እድል መመናመን፣ የኑሮ ውድነትና የመሰረታዊ ሸቀጦች ከገበያ መጥፋት ቀጣዩ የመንግስት ፈተና ይመስለኛል! በቀደም እለት ካንድ የበለጸገ ወዳጄ ጋር (የበለጸገ ስል የፓርቲ አባል የሆነ ማለቴ ነበር ..ግን ደግሞ አባል ከሆነም መበልጸጉም አይቀርም”) በአጋጣሚ ነዳጅ ለመሙላት የተወሰነች አንድ የሶስት ወረፋ የምትሆን የማትንቀሳቀስ ሰልፍ ላይ ተገናኝተን፣ ከመኪናችን ውጪ ቆመን ስንወያይ ስለ ኑሮ ውድነቱ አነሳሁበት!
ወዳጄ በምንም ጉዳይ ቢሆን መንግስት ላይ የሚያማርር ሰው አይወድም!
‘እኔ የምልህ!’ አልኩት ‘እኔ ምልህ ስጋ እንደ ቀልድ አንድ ሺ ብር ገባ አይደል?!’
‘ምን ችግር አለው፤ ሁዳዴ አይደል እንዴ!!’ አለኝ።
ያው እንደ አለቆቹ አብዛኛው መፍትሄዎቹ ባለ አጭር ርቀት ናቸው!
‘ይሄንንስ ሰልፍ ምን ትለዋለህ?!’ አልኩት እንደ አባይ ወንዝ ተጠማዝዞ፣ የትናየት የደረሰውን ወረፋ እየጠቆምኩ።
(ሰልፉ ከመርዘሙ የተነሳ የመጀመሪያዎቹና የመጨረሻዎቹ ተሰላፊዎች መሃል፣ የ2 ብር የታክሲ መንገድ አለ! ተራ አስከባሪዎቹ እራሱ ተሰላፊውን ‘የታችኛውና የላይኛው ተፋሰስ’ ተሰላፊዎች ብለው ነው የሚጠሩን!)
ወዳጄ ምንም አልመሰለውም ..
‘ጨለምተኛ አትሁን!’ አለኝ ትከሻውን እየሰበቀ።
‘ጨለምተኛ አትሁን አንዲ! በዚህ ሰልፍ እራሱ እንደምታየው ከ15 በላይ ለሚሆኑ ተራ አስከባሪ ወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሯል!!’ አለኝ።
የምለው አጣሁ!
‘ግን ከሰሞኑ በተደረገ ጥናት አዲስ አበባ ከአፍሪካ በኑሮ ውድነት አንደኛ እንደተባለች ሰምተሃል?!’ አልኩት፡፡
አይኑን በልጥጦ በመገረም አየኝ!
‘አንዲ ከመቼ ወዲህ ነው እንዲህ ጨለምተኛና ያልተጣራ መረጃ አሰራጭ የሆንከው !?’ አለኝ
‘ምኑ ነው ያልተጣራ መረጃ ?!’ አልኩት በንዴት ስልኬን ለማስረጃነት እያወጣሁ!
‘የቢዝነስ ኢንሳይደርን ኢንዴክስ ተመልክተኸዋል !? ወሬ ብቻ እንጂ አታዩማ!!!’
አለኝና በረዥሙ ተንፍሶ ሲያበቃ ..
‘ለማንኛውም አንተ እንደምታናፍሰው ያልተጨበጠ በሬ ወለደ እና አሸባሪ ወሬ ሳይሆን፣ አዲስ አበባችን በዚህ ወር በኑሮ ውድነት ከአፍሪካ 2ኛ ነች!!’ ብሎኝ ወደ መኪናው ገባ!
ደህና ዋሉ!
_____________________________________________

                      ስለ ኤችአር 6600 ያለኝ ሀሳብ
                            መኮንን ከተማ


            ኤችአር 6600 የ"nomore" ደጋፊዎችና የለም ጣልቃ መግባት አለባቸው ብለው ከሚያምኑት ጋር ያለውን ትንቅንቅ በትልቁ መድረክ እያሳየን ነው። "nomore"ተብሎ በየከተሞቹ ሰልፍ ሲወጣ የነበረው፣ በሀገራችን ጉዳይ ጣልቃ አትግቡ ለማለት ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ጣልቃ ግቡ የሚሉ አሉ። የትኛው ይሻላል ብለን ስንጠይቅ፣ ብዙ መልሶች እናገኛለን። የእኔ መልስ ይሄ ነው።
ጣልቃ ግቡ ተብሎ የተጀመረው ዛሬ አይደለም። ደርግ ስልጣን ላይ በነበረ ጊዜ በትንሹ ተጀምሮ ነበር። ከዛም በፊት ነበር የሚሉ አሉ። በደርግ ጊዜ ወጣት ስለነበርኩ ብዙም አላውቅም ነበር። የማውቀው በደርግ መንግስት ብዙ ሰው እየተገደለና እንደተሰቃየ ስለነበር ጣልቃ ገብነትን እደግፍ ነበር። ልጅ ነበርኩኝ። ደርግን ተክቶ ኢህአዴግ ሲመጣም ውጭ ሀገር ብዙ ሰልፎች ነበሩ። ማዕቀብ እንዲደረግ የሚፈልጉም ብዙዎች ነበሩ።
በዚህን ጊዜ እድሜ ጨምሬ ብዙ ማወቅ ችዬ ነበር። ታድያ በዛን ሰዓት ሶስት ነገሮች ገብተውኝ ነበር፡፡ አንደኛው፤ ለውጥ በምንም ተዓምር ከውጭ መምጣት እንደማይችል ነው፡፡ ሁለተኛው፤ ማዕቀብ ምንም አድርገው አሳምረው ቢያቀርቡትም፣ ህዝብንም እንደሚጎዳ ገብቶኝ ነበር። ሶስተኛው ደግሞ ጣልቃ ግቡ ብሎ ማለት ለዘላለም የማይዘጋ በር መክፈት መሆኑን ነው፡፡ ፈረንጆች setting a precedent የሚሉት ነው። ያንን በር ከከፈትን በኋላ የምንደግፈው መንግስት ከመጣ በዛው በተከፈተው በር ጣልቃ ገቦቹ መልሰው መግባታቸው አይቀርም።
ኤችአር 6600ን በዚህ መልኩ ነው ማየው። ደጋፊዎቹ ባደረጉት ሊደሰቱ ይችላሉ፤ ግን መንግስት ብዙም አይጨንቀውም። መንግስትን ጎዳን ሊሉ ይችላሉ፤ ግን ህዝብንም እንደሚጎዱ መረዳት አለባቸው።  ለምሳሌ ኤችአር 6600 የአለም ባንክና አለም አቀፍ የገንዘብ ፈንድ ያሉ አለምአቀፍ ኤጀንሲዎች ለኢትዮጵያ የሚሰጧትን ብድር አሜሪካ እንዲያቆሙ ታስገድዳቸዋለች። ያንንም የጣልቃ ገቦች በር ከፍተን፣ ነገ ተመልሰን "nomore"ብንል የሚሰማም ጆሮ አይኖርም።
የትኛው ይሻላል ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ መልሴ፤ #nomore ይሁንልኝ።

____________________________________

                        የአሜሪካ መንግስት የሚመሰርትልን "ቅምጥ መንግስት" መፍትሄ አይሆንም
                                   ሙሼ ሰሙ


             አሁን የት እንደገቡ ባላውቅም “ጣሊያን ቅኝ ገዝታን” ቢሆን ኖሮ፣ ችግሮቻችን ሁሉ ጠፍተው ሀገራችን ትለማ ነበር ብለው ከልባቸው የሚያምኑ፣ የአባቶቻችን እምቢኝ አሻፈረኝ አልገዛም ባይነት ለዛሬ ምቾታቸው አለመሳካትና ተንደላቆ ላለመኖራቸው እንደ ደንቃራ የሚወስዱ “ዜጎች” እንደነበሩን አስታውሳለሁ፡፡
ዛሬ ደግሞ "የሕዝቤን መብትና ጥቅም ለማስከበር ተደራጅቼና አደራጅቼ አማራጭ ያልኩትን የትግል ስልት ተጠቅሜ እታገላለሁ፤ ታስሬ፣ ተሰድጄና ተሰውቼ የሕዝቤን መከራና ስቃይ እካፈላለሁ፤ ነጻነቱንም አረጋግጣለሁ" ከሚል ሕዝባዊ ጽናትና ቁርጠኛነት ይልቅ የልዕለ ሃያላን አውዳሚ ማዕቀብ እንዲሰብረን መማጸን የሚያኮራ ተግባር ሆኗል።
ሉዐላዊነት ትርጉም ከማጣቱ የተነሳ አማራጫችን ሁሉ አንድ ጊዜ የቻይና መንግስት ይድረስልን፣ ሌላ ጊዜ የራሽያ መንግስት ከጉድ ያውጣን አሊያም የአሜሪካ ሴኔት መንግስታችንን ያንበርክክልን የሚል ነው። ማዕቀብ መንግስትን ከማንበርከኩ በፊት ሀገርና ሕዝብን እንደሚያንበረክክ ከኢራቅ፣ ከሶርያና ከየመን መማር አልፈለግንም።
በዚህ ላይ አሳዛኙ ጉዳይ መርህ አልባነቱ ነው። ትናንት አሜሪካ እጅግ የለዘበ ሪዞልዮሽን ልታጸድቅ ስታቅድ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ መግባት ነው ሲሉ የነበሩ ሁላ፣ ዛሬ መለስ ብለው አሜሪካ አውዳሚ ሪዞሉሽን በማጽደቅ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ትግባልን እያሉ ሲማጸኑ ማየት እኛን አይደለም አሜሪካኖቹም ቢሆኑ “መርህ” የሚባለው ቃል በመዝገበ ቃላታችን ውስጥ መኖሩን እንዲጠራጠሩ የሚያደርግ ነው፡፡
መንግስት ላይስማማን ይችላል። እንዲለወጥ መታገል የዜግነት መብትና የውዴታ ግዴታችን ነው። ዘለቄታ ያለው መንገድ ከታሰበም፤ ውድ ዋጋ ቢያስከፍልም ብቸኛው መንገድ በሕዝብ መፍትሔ ሰጭነት ላይ መተማመን ብቻ ነው።
ፈተናና ችግር ባጋጠመን ቁጥር የአሜሪካ መንግስት ማዕቀብ ጥሎ ሕዝብ አዋርዶ፣ ሀገር አዳክሞ፣ መንግስት ገልብጦ የሚመሰርትልን ቅምጥ መንግስት፣ መፍትሔ ከመሰለን ፍጹም ተሳስተናል። ይህ መንገድ ከውድቀት ባሻገር ማቆምያ ወደ ሌለው የግጭት አዙሪት ይወስደን እንደሁ እንጂ የታሪካችን አኩሪ ምዕራፍ ሊሆን አይችልም።

_____________________________________________

                             የተፋለሰ ነገርማ አለ?
                                    Pace Negaa

              መጀመሪያ ብላ፣ ጠጣ፣ ነፍስ ዝራ፣ በህይወት ኑር፣ ተጫወት።
እየተጫወትክ ሌሎችን ተመልከት፣ አስተውል፣ ተማር።
ከሌሎች ተማር፣ ተማር፣ ተማር - እግራቸው ሥር ቁጭ ብለህ ተማር።
ከዚያ ተነስና ቁም - መጀመሪያ ተደግፈህ፣ ከዚያ ተስተካክለህ በራስህ እግር ቁም።
ከዚያ መራመድ ልመድ። እንዴትም ይሁን ወዴት .... ብቻ ተራመድ።
ከዚያ አቅጣጫ ምረጥ። በመረጥከው አቅጣጫ ወደፊት ተራመድ፤ አልፎ አልፎም ዱብ ዱብ፣ እመር ማለት ልመድ።
ከዚያ ብረር! ብርርርር ብለህ ብረር።
የህይወትህ ፀሃይ ማዘቅዘቅ ስትጀምር ሌሎችን አስተምር፤ ልምድህን አካፍል። ከልምድህ የተረዳኸውን የተሻለውን መንገድ ጠቁም። ለመሆኑ ከህይወት ልምድህ ምን ተረድተሃል? የምትሠራውን ሥራ፣ ከድሮው አንተ ስትጀምር ከነበረው በምን የተሻለ አድርገሃል? ነው አሁንም ገና እየተማርክ ነው? እውነት ነው ትምህርት አያልቅም። ግን ሁሌ መማር በራሱ ትርፍ የለውም። መማር ብቻውን በራሱ ግብም አይደለም - ጉዞ እንጂ! በእርግጥ የሚያስደስት ጉዞ ነው። አንዳንዴ ሲበዛ ግን እንደ ስካር ያለ ነው - የሚያስደስት ግን ቁም-ነገርና ፍሬ የሌለው።
ጃምቦ :- ማንም ሰው አንተ ስለተማርከው ትምህርት፣ ስላገኘኸው ነጥብና ሜዳልያ፣ ስላካበትከው ሀብትና ስለሠራኸው ቤት ግድ የለውም። ይህንን ልብ በል።
ታሪክ ቁም-ነገሬ ብሎ የሚከትብህ፣ ለሌሎች የሚተርፍ ሥራ ካለህ ብቻ ነው።
ለመሆኑ የአጼ ምኒልክ ሚኒስትሮች እነማን ነበሩ? የደርግ ሚኒስትሮችስ? የደርግ የመብራት ኃይል ኃላፊ ማን ነበሩ? የመለስ የኢንዱስትሪ ሚኒስትርስ ማን ነበሩ? የአሁኑስ? ምን ሠሩ? በምን ይታወሳሉ?
ማን አለማን? ማን አጠፋን? ለምን ሁነኛ ሰው አጣን? እስኪ እንጠይቅ።
መኮንን ሀብተወልድ፣ ሙሉጌታ ቡሊ፣ አበበ አረጋይ፣ ዑመር ሰመተር፣ ገርማሜ ነዋይ፣ መስፍን ስለሺ፣ ስንዱ ገብሩ፣ መንገሻ ስዩም፣ መኮንን ሙላት፣ ሰናይ ልኬ፣ በዓሉ ግርማ፣ አፈወርቅ ተክሌ፣ ተሰማ አባደራሽ፣ ተስፋዬ ዲንቃ፣ አስራት ወልደየስ፣ አበበች ጎበና፣ ይድነቃቸው ተሰማ፣ ንጉሤ ሮባ፣ አበበ ቢቂላ፣ ወልደመስቀል ኮስትሬ፣ ሳህሌ ደጋጎ፣ ኤልያስ መልካ፣ ... ምን ዓይነት ሰዎች ነበሩ? ምን ሠሩ? በምን ትዝ ይሉሃል?
ከድር ኤባ፣ ማሞ ካቻ፣ ተካ ኤገኖ፣ በቀለ ሞላ፣ ፊታውራሪ አመዴ፣ ሞላ ማሩ፣ መኮንን ነጋሽ፣ ዱጉማ ሁንዴ፣ ... እነማን ነበሩ? ከየት ተነስተው የት ደረሱ?
ጃምቦ:- የሠራኸው ነገር ከሌለ ስልጣን ኖሮህም፣ ሀብትና ጥሩ ቤት ኖሮህም፣ ሃርቫርድ ተምረህም ያለ ማርክ፣ ያለ አሻራ ታልፋለህ። ለነገሩ ዋናው ቁም-ነገር፣ አሻራ ማስቀመጥ ቢያቅት፣ ህይወትን ካለ ጠባሳ ማሳለፍን ማወቅ ላይ ነው።
የህይወትህ ጉዞ እንዴት ነው? መጀመሪያ ፊሪሃ-እግዚአብሔር፣ ከዚያ እውቀት፣ ከዚያ ሥራ፣ ከዚያ ስልጣን ከዚያ ሀብት የሚል ነበር፤ የተለመደው የጉዞ መስመር።
አሁን ደግሞ መጀመሪያ ስልጣን፣ ከዚያ ሥራ፣ ከዚያ ሀብት፣ ከዚያ እውቀት፣ ከዚያ ንስሃ የሆነ ይመስላል።
እናም ያለ እውቀት ሥራ በርክቷል፤ ነገሩ ተዛብቷል።
የሆነ የተፋለሰ ነገርማ አለ!
በሉ ፋልሶው እንዲስተካከል ንስሃ እንግባ።
አይሻልም?Read 732 times